Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መውሊድን ማክበር ይፈቀዳል የሚሉ ሰዎች የሚያቀርቧቸው 10 ማደናገሪያዎችና ምላሾቻቸው!



መውሊድን ማክበር ይፈቀዳል የሚሉ 10 ማደናገሪያዎችና ምላሾቻቸው!


الحمد لله رب العالمين ، والصلاة والسلام على خاتم الأنبياء والمرسلين ، المبعوث رحمة للعالمين، محمد وعلى آله وصحبه أجمعين . أما بعد
እውነተኛ የነብዩ صلى الله عليه وسلم ወዳጆች ለሱናቸው እጅ ይሰጣሉ፤ ፈለጋቸዉን ይከተላ፣ እውነተኛ ወዳጅ አያምፅም ያልታዘዘውን አይሰራም ከታዘዘው ነገርም ወደኋላ አያፈገፍግምና፡፡ መዉሊድን አስመልክቶ ብዙ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች በየአመቱ ይሰማሉ። አብዛኞቹን በመረጃነት የሚቀርቡ ነገሮች በአትኩሮት ማንበብ ብቻ ተቀባይነትን ያሳጣቸዋል። ይሁንና አንዳንዶችን ሊያሳስቱ ስለሚችሉ በዚህ ጽሁፍ 10 ማደናገሪያዎችን እና ምላሾቻቸውን ለማየት እንሞክራለን። በአላህ እንታገዛለን! በመቀጠል፤


  1. የነብዩን صلى الله صلى الله عليه وسلمليه وسلم መውሊድ ማክበር አለም ተስማምቶበታል ብዙ ሰዎችም ያከብሩታል የአረብ መንግስታትም ያፀድቁታል ለምንድ ነው የምትከለክሉን?




ለዚህም መልሳልችን… ማስረጃ ከቁርአንና ከሀዲስ እንጅ ከሰው ተግባር ማምጣት አይቻልም፡፡ ከነብያችን صلى الله عليه وسلم የተወረሰው ከቢድዓ ማስጠንቀቃቸውና መከልከላቸው ነው፡፡ የሰው ስራና ተግባር የተግባሪው መብዛትና መበራከት ማስረጃ አለመሆኑን አላህ በሱረቱል አንዓም አብራርቷል፦

وإِن تُطِعْ أَكْثَرَ مَن فِي الْأَرْضِ يُضِلُّوكَ عَن سَبِيلِ اللَّهِ ۚ إِن يَتَّبِعُونَ إِلَّا الظَّنَّ وَإِنْ هُمْ إِلَّا يَخْرُصُونَ

“በምድርም ካሉት ሰዎች አብዛኞቹን ብትከተል ከአላህ መንገድ ያሳስቱሃል ጥርጣሬን እንጅ ሌላን አይከተሉም እነርሱም የሚዋሹ እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡” አል አንዓም 116

ምስጋና ለአለማት ጌታ አላህ ይገባውና ዑለሞች የመውሊድን ቢድዓነት ከማስተማር አልተወገዱም በየዘመናቱ የተለያዩ መፅሐፎችን ከመፃፍ አልቦዘኑም ሐቅ ካወቁ በኃላ መውሊድን ለመብላትና ለመጠጣት ብሎ የሚያከብርን ሰው ተከትሎ መጃጃል ተገቢ አይደለም፡፡


 2. ነብዩ صلى الله عليه وسلم ሰኞን ይፆሙ ነበር:: ሲጠየቁም “ይህ የተወለድኩበት ቁርአንም በእኔ ላይ የተወረደበት ቀን ነው” ብለዋል ይህ ደግሞ ነብዩ صلى الله عليه وسلم የተወለዱበትን ቀን እያከበሩ መሆኑን ይገልፃል ይላሉ፡፡



ነብያችን የተወለዱት ሰኞ ቀን መሆኑ የታወቀ ነው ነብያችን ሰኞ መፆማቸው ቀኑን ለማክበር አይደለም በብዙ ሀዲሶች ላይ "ሰኞና ሐሙስ ለምን ይፆማሉ ተብለው ሲጠየቁ " እነዚህ ሁለት ቀናት ስራዎች ወደ አላህ የሚቀርቡባቸው ቀናት ናቸው እኔም ፆምኛ ሆኜ ስራዬ እንዲቀርብልኝ እወዳለሁ" በማለት መልሰዋል፡፡

የሰኞና ሐሙስ ፆሞች የተያያዙና አላማቸው አንድ የሆኑ ፆሞች ናቸዉ ነብዩ صلى الله عليه وسلم የአኼራ ጥቅሞችንና ደረጃቸው ከፍ እንዲል የፆሟቸው እንጅ ወደ ዱንያ የመጡበትን ቀን ለማክበር ፈልገው እንዳልሆነ ራሳቸው ገልፀውታል፡፡ ነብያችን صلى الله عليه وسلم የተወለዱት በነብይነት የተላኩበትና ያረፉበት ቀን ሰኞ ሲሆን አላህ ሙስሊሞችን ያበሰረው በላካቸው እንጅ በመወለዳቸው አይደለም፡፡
ነብያችን صلى الله عليه وسلم የፆሙት ሰኞን ቀን እንጅ ረቢዓል አወል ወር 12ኛ ቀን አይደለም፡፡ ረቢዓል አወል ወር 12ኛው ቀን ተወለዱ የሚለውን ዘገባ ብዙ ሰዎች ቢደግፉትም ቢያውቁትም የታሪክ ምሁራን ትክክለኛ ማስረጃ በመጥቀስ የሚያፀድቁት ግን 9ኛውን ቀን ነው፡፡ አሁን የተወለዱበትን የአመት በአል ቀን ለማክበር የፈለገ ሰው ዘጠነኛውን ቀን ነው የሚያከብረው ወይስ አስራ ሁለተኛውን? ሌላው ደግሞ ረቢዓል አወል 12ኛው ቀን ሰኞ ላይሆን ይችላል፡፡ ሰኞን ከያዝን ረቢዓል አወል 12ኛ ቀን የሚለውን እናፈርሳለን ረቢዓል አወል 12ኛ ቀን የሚለውን ከያዝን ሰኞ ቀን የሚለውን እናጣለን የትኛውን እንያዝ?
ነብያችን صلى الله عليه وسلم ሰኞንና ሐሙስን በፆም ሲያሳልፉ ለምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ ከመለሱት መልስ ውስጥ ሰኞ ቀን የተወለድኩበት ነው፡፡ ሰኞና ሐሙስ የሰው ልጆች ስራ ወደ አላህ ስለሚቀርብ ፆመኛ ሆኜ ስራዬ ወደ አላህ ሊቀርብ እፈልጋለው ብለዋል፡፡ ነብዩ ፆመኛ ሁነው የሚያሳልፉትን ሰኞን ቀን እሳቸው የተወለዱበት ቀን ብሎ ሲበሉና ሲጠጡ መዋል ምን ይባላል?
ሰኞን ቀን መፆም ሱና ነው የሚከለክል ሰው የለም ቢድዓ ነው ያለም አይገኝም፡፡ ረቢዓል አወል ወር 12ኛውን ቀን ግን ለመፀም ወይም ለማክበር ማስረጃ የለም የሰኞ ቀን መፆማቸው ረቢዓል በአል አድርጐ ለመያዝ አያገለግልም ምክንያቱመ ፆምና በአል ተቃራኒ የሆኑ ተግባሮች ስለሆኑ፡፡ ነብያችን صلى الله عليه وسلم “የኢዳችሁን ቀን ፆም አድርጋችሁ አትያዙ” ሐኪምና አህመድ ዘግበውታል
እውነተኛ የነብዩ صلى الله عليه وسلم ወዳጆች ከሆን ለሀዲሳቸው እጅ እንስጥ በሳቸው ላይ አናምፅ እውነተኛ ወዳጅ አያምፅም ያልታዘዘውን አይሰራም ከታዘዘው ነገር ወደኋላ አያፈገፍግም፡፡ በአመት አንዴ ተሰብስቦ በመብላት በመጠጣት ዉዴታን ገለፅኩ ማለት አይቻልም፡፡
የነብዩ መወለድ ታላቅ ክስተት ቢሆንም፤ አላህ ሱ.ወ ህዝቦችን በቁርአን ላይ ያበሰረው በነብዩ መወለድ ሳይሆን በነብዩ صلى الله عليه وسلم መላክ ነው፡፡ ይህንንም ቅን እናክብርን??
لَقَدْ مَنَّ اللَّهُ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ إِذْ بَعَثَ فِيهِمْ رَسُولًا مِنْ أَنْفُسِهِمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِهِ وَيُزَكِّيهِمْ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَوَالْحِكْمَةَ وَإِنْ كَانُوا مِنْ قَبْلُ لَفِي ضَلَالٍ مُبِينٍ
“አላህ በምእመናን ላይ ከጐሳቸው የኾነን በነርሱ ላይ አያቶችን የሚያነብ የሚያጠራቸውም መፅሐፍንና ጥበብን የሚያስተምራቸውም የሆነን መልዕክተኛ በውስጣቸው በላከ ጊዜ በእርግጥ ለገሳቸው እነርሱም ከዚህ በፊት በግልፅ ስህተት ውስጥ ነበሩ፡፡” አል ዒምራን 164
هُوَ الَّذِي بَعَثَ فِي الْأُمِّيِّينَ رَسُولًا مِنْهُمْ يَتْلُو عَلَيْهِمْ آيَاتِهِ وَيُزَكِّيهِمْ وَيُعَلِّمُهُمُ الْكِتَابَ وَالْحِكْمَةَ وَإِنْ كَانُوا مِنْ قَبْلُ لَفِي ضَلَالٍ مُبِينٍ
“እርሱ ያ (አላህ) በመሀይሞቹ ውስጥ መልዕክተኛ (ሙሐመድን) ከነሱ ውስጥ የላከ ነው፡፡” አል ጁምዓህ 2
لَقَدْ جَاءَكُمْ رَسُولٌ مِنْ أَنْفُسِكُمْ عَزِيزٌ عَلَيْهِ مَا عَنِتُّمْ حَرِيصٌ عَلَيْكُمْ بِالْمُؤْمِنِينَ رَءُوفٌ رَحِيمٌ
“ከጎሳችሁ የኾነ ችግራችሁ በርሱ ላይ ጥኑ የኾኑ በናንተ (እምነት) ላይ የሚጓጓ በምእመናን ሩህሩህ አዛኝ የኾነ መልዕክተኛ በእርግጥ መጣላችሁ” አል ተውባ 128


3. አንዳንድ መውሊድ አክባሪዎች መውሊድ የሚያከብሩበትን ምክንያት ሲናገሩ “ክርስቲያኖች የነብዩ ዒሳን ዐ.ሰ የውልደት ቀን ያከብራሉ እኛስ ከእነሱ በምን እናንሳለን” ይላሉ::


እነዚህ ሰዎች ከክርስቲያኖች በምን እናንሳለን በሚል ምክኒያት መውሊድ ማክበራቸው ከእነርሱ ጋር መመሳሰል ነው፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ደገሞ ከክርስቲያኖች ጋር መመሳሰል ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ ነብያችን صلى الله عليه وسلم “በህዝቦች የተመሳሰለ እሱ ከእነሱ ጋር ነው” ብለዋል ኢመማሙ አህመድና አቡዳውድ ዘግበውታል ኢብኑ ተይሚያና ስውጢይም ሰሂህ ብለውታል
ቲርሚዚይ በዘገቡት ሰሂህ ሀዲሳቸውም “ከእኛ ውጭ ባለ የተመሳሰለ ለእኛ አይደለም በአይሁዳና በክርስቲያኖች አትመሳሰሉ” ብለዋል
“ሙሽሪኮችን ተፃረሯቸው” የሚለውንም ንግግራቸው ኢማሙ ሙስሊም በሀዲስ ቁጥር 259 ዘግበውታል

መውሊድ ማክበር ቢድዓ ከመሆኑና ከክርስቲያኖች ጋር ከመመሳሰል (ሁለቱም የተከለከሉ ናቸው) በተጨማሪም ነብዩን صلى الله عليه وسلم ሲያወድሱና ሲያሞግሱ ድነበር ለማለፍ መንገድ ይጠርጋል፡፡ ከአላህ ውጭ ያለን ነገር እርዳታና እገዛ ለመጠየቅ በር ይከፍታል መውሊድ የሚያከብሩት በደንብ ያውቁታል፡፡ ነብያችንን ከአላህ ውጭ ለመጣራት ከሳቸውም እርዳታና እገዛ ለመለመን ሽርክ ያለባቸውን ሀድራዎችና መንዙማዎች ለማዳመጥ ሰፋ ያለ ድርሻ መያዙ ይታወቃል፡፡

لَا تُطْرُونِي كَمَا أَطْرَتِ النَّصَارَى عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ ، فَإِنَّمَا أَنَا عَبْدُ اللَّهِ وَرَسُولُهُ - مُتَفَقٌّ عَلَيهِ

ቡኻሪ በዘገቡት ሀዲስ ነብያችን “ክርስቲያኖች የመሬምን ልጅ ዒሳን ሲያወድሱ ድንበር እንዳለፉት እናንተም እኔን ስታወድሱኝ ድንበር አትለፉ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ የአላህ ባሪያ የአላህ መልዕክተኛ በሉኝ” ብለዋል፡፡
ክርስቲያኖች የመሬምን ልጅ ዒሳን ሲያወድሱና ሲያልቁ ድንበር ማለፋቸው ድንበር አልፎባቸው ዒሳን ዐ.ሰ ከአላህ ጋር እኩል እስከመገዛት እንደደረሱ አላህ በቁርአኑ ላይ ያብራራልናል፡፡

يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لَا تَغْلُوا فِي دِينِكُمْ وَلَا تَقُولُوا عَلَى اللَّهِ إِلَّا الْحَقَّ ۚ إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللَّهِ وَكَلِمَتُهُ أَلْقَاهَا إِلَىٰ مَرْيَمَ وَرُوحٌ مِنْهُ ۖ فَآمِنُوا بِاللَّهِ وَرُسُلِهِ ۖ

“እናንተ የመጽሐፍ ሰዎች ሆይ በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ የመሬም ልጅ አል መሲህ ዒሳ የአላህ መልዕክተኛ ወደ መርየም የጣላት (የኩን) ቃሉም ከርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነው፡ በአላህ እና በመልዕክተኛዉም እመኑ...፡” አል ኒሳእ 171

ነብያችንም صلى الله عليه وسلم ክርስቲያኖች ወሰን በማለፋቸው ምክንያት የደረሰባቸውና ያጋጠማቸው እኛን እንዳይደርስብንና እንዳያጋጥመን በመፍራት ወሰን ከማለፍ በጥብቅ ያስጠነቅቁናል፡፡ ነሳኢ በዘገቡትና አልባኒ ሰሂህነቱን ባረጋገጡት ሀዲስ ነብያችን “ወየውላችሁ ድንበር ማለፍን ከናንተ በፊት (ያሉትን ህዝቦች) ያጠፋቸው ድንበር ማለፍ ነው” ብለዋል፡፡

4. እነዚህ ሰዎች ‹‹ሁሉም ቢድዓ ጥመት ነው!!›› ከሚለዉ ነብያዊ መርሆ በመውጣት ‹‹ቢድዓ ሁለት ዓይነት ነው፤ጥሩና መጠፎ›› ይላሉ!! መውሊድ ጥሩ ቢድዓ (ቢድዐቱል ሀሰናህ) ነው፡፡ የተከለከለው ደግሞ መጥፎ ቢድዓ ነው፡፡

ለዚህም ሁለት ማደናገያዎችን በመጥቀስ ቢድዓ ሀሰናህ የሚለዉን ሃሳብ ለማጠናከር ሽንጣቸውን ገትረው ይሞግታሉ፡፡
አንደኛ፡- መልዕክተኛው እንዲህ ብለዋል ‹‹በኢስላም ውስጥ የጥሩ ፈለግ(ሱና) ፈር የቀደደ ለእርሱ የዚህ ስራ ምንዳ እና ይህንን ፈለጉን ተከትሎ የሚሰራ ሰውን ሁሉ ምንዳ አለው፡፡ ይህም ከእርሱ ምንዳ ምንም ሳይቀነስ ነው›› ሙስሊም በቁጥር 1017 ከጀሪር ኢብኑ አብዲላህ አል-በጀሊይ ዘግበውታል፡፡

የመጀመሪያዉ ማደናገሪያ ምላሽ እንደሚከተለው ይሆናል፡-

1ኛ፡- ነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) ይህንን ሀዲስ የተናገሩበትን ምክንያት በዚሁ ሀዲስ ላይ ስናነብ ሀሳቡን በትክክል እንረዳዋለን፡፡ነገር ግን ቢድዓቱል ሀሰናህ አለ የሚሉ ሰዎች የሀዲሱን ሙሉ ሀሳብ ማስቀመጥ ስለማያዋጣቸዉ አይጠቅሱትም፡፡ ጀሪር በዚሁ ሀዲስ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ረሱል ዘንድ ተቀምጠን እያለ ከሙደር ጎሳ የሆኑ ሰዎች መጡ፡፡ ረሱልም በሰዎቹ ላይ ባዩት እንግልትና ችግር ስሜታቸዉ ተነክቶ ፊታቸዉ ተቀያየረ…›› ከዛም ሰሃቦችን ሰደቃ አንዲሰጡ ሲያነሳሷቸው አንድ ከአንሳር የሆነ ሰሃብይ ሊሸከመዉ የከበደዉን ምግብ ከሁሉም ቀድሞ በመስጠት መዋጮዉን ጀመረዉና ለሌሎቹ አርዓያ ሆነ፡፡ ሁሉም በሰደቃ ተሽቀዳደሙ፡፡ ጀሪር ‹‹የረሱል ፊት ልክ እንደወርቅ ሲያብረቀርቅ አየሁ›› አሉ፡፡ ከዛም ከላይ የቀረበዉን ንግግራቸዉን ተናገሩ…፡፡ቢድዓ የሚባለዉ በዲን ዉስጥ አዲስ የተጨመረ ነገር ነዉ፡፡ ሰደቃ ደግሞ በሸሪዓ አስቀድሞ የተደነገገ ተግባር እንጂ አዲስ ፈጠራ አይደለም! ስለዚህ ይህ በዲኑ ውስጥ ለሚጨምሩ ሰዎች በፍፁም መረጃ ሊሆን አይችልም።

2ኛ- ነቢዩ በዚህ ሀዲስ ላይ ‹‹በኢስላም ውስጥ›› እና ‹‹ (ሰነ ሱነተን ሀሰናህ) የጥሩ ፈለግ (ሱና) ፈር የቀደደ ›› ማለታቸውን እናስተዉል፡፡

3ኛ- ይህ ሀዲስ ሰዎች የረሱትንና የዘነጉትን ሱና ህያው ማድረግን ይመለከታል፡፡ ይህንን ሀዲስ በሚገባ የሚያብራራዉ ለመነገሩ ሰበብ የሆነዉ ክስተት ቢሆንም ሀሳቡን የሚያጠናክርና ምን እንደተፈለገበት የሚያሳይ መልዕክት ያለዉ ሀዲስም አለ፡፡ቢላል ኢብኑልሀሪስ ረሱል እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ይላሉ ‹‹ከኔ በኋላ (የሞተን) የተረሳን ሱና ህያዉ ያደረገ (እርሱን ተከትለዉ) ይህንን ሱና በሰሩበት ሰዎች ሁሉ ከእነርሱ ምንዳ ምንም ሳይቀነስ ምንዳ ያገኛል፡፡

ሁለተኛ፡- (ሰዎች የተራዊህን ሰላት ተለያይተው በሚሰግዱ ጊዜ ኸሊፋው ዑመር ተሰባስበው እንዲሰግዱ ካደረጓቸው በኋላ ‹‹ምንኛ ያማረች ፈጠራ (ቢድዓ) ናት!›› አሉ) ቡኻሪ በቁጥር 2012 ዘግበውታል

1ኛ፡-የተራዊህ ሰላት ሱና እንጂ ቢድዓ አይደለም! ነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) የተወሰኑ ቀናትን ሰርተው አቁመውታል፤ ምክንያታቸውንም ተናግረዋል፡-ዋጂብ (ግዴታ) እንዳይሆንብን ፈርተው ነው ግን ከአላህ የሚተላለፈዉ ወህይ ከነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) እልፋት በኋላ ስለማይመጣ በዑመር ጊዜ ዋጂብ እንዳይሆንብን የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረም፤ ስለሆነም ነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) የጀመሩትን ሥራ ዑመር ቀጠሉት፣ ይህን ይበልጥ የሚያብራራው የሚቀጥለው ነጥብ ይሆናል፡፡

2ኛ፡-በዲናችን የተከለከለዉ ቢድዓን መስራት ነዉ እንጂ ቢድዓ የሚለውን ቃል መጠቀም አይደለም። ቢድዓ እንደሌሎች አንዳንድ ቃላት ሸሪአዊና ቋንቋዊ ትርጉም ያለው ቃል ነው።ተቋርጦ እንደ አዲስ በመጀመሩ፤ ዑመር የፈለጉት ቋንቋዊ ትርጉሙን ነው። የሰሩትም ሥራ ሱናና መሰረት ያለው እንጂ አዲስ ፈጠራ አይደለም።

3ኛ፡-ዑመር የሠሩት ሥራ በሰሀቦች ሁሉ ስምምነት የፀደቀ የኹለፋዎች ፈለግ በመሆኑ በሸሪዓ ቢድዓ አይባልም!
እንደዚሁም ከላይ በተጠቀሱት ማስረጃዎች የተኮነነው ቢድዓ በዲን ውስጥ የሚተገበረውን የቢድዓ ዓይነት እንጂ አንዳንድ ሰዎች ‹አዲስ ፈጠራ ማምጣት ይቻላል!› ብለዉ ለመሞገት ሲፈልጉ የሚጠቅሷቸውን የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች አይደሉም።ነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) በዋነኝነት ለማስተማር የተላኩት እነዚህን ዝርዝር የዱንያ ጉዳዮች አይደለም፤ ለመዲና ገበሬዎችም ይህንን ምላሽ ሰጥተዋል፡-
“ስለ ዱንያ ጉዳያችሁ እናንተ ይበልጥ ታውቃላችሁ!” ስለዚህ ቁርዓንን በአንድ ጥራዝ ማስቀመጥ፣
የእስር ቤቶችን ማዘጋጀት፣ ስፒከርን (የድምፅ ማጉያ) መጠቀም የመሳሰሉት በመልእክተኛው ዘመን ባይከሰቱም ወጥ የዒባዳ ተግባራት ሳይሆኑ ወደ ኢባዳ የሚያዳርሱ አጋዥ መዳረሻዎች ስለሆኑ ነው።እነዚህ ደግሞ (መሳሊህ ሙርሰላ) ይባላሉ፣ ከቢድዓ ጋር በፍፁም አይገናኙም፡፡

5. አላህ በቁርዓኑ ላይ ነብዩን እንድናከብርና እንድናልቃቸው አዞናል፡፡ ስለዚህ ለእሳቸው ያለንን ክብር ልደታቸውን በማክበር እንገልጻለን ይላሉ፡፡

ለዚህ ምላሽ አላህ ነብዩን صلى الله عليه وسلم ያከበሩትን ከጎኑ የቆሙትን ሲያወድስ አያይዞ አብሮ ከእሳቸው ጋር የወረደውን ኑር (ቁርአን) የተከተሉትን ያወድሳል (አልአዕራፍ157) ‹‹የተከተሉ›› የሚለው በራሳቸው ፈጠራ ውዴታን የገለፁ ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ እውነት ተከታይ የሆነ ሰው ከሚያዝዘው አካል ትዕዛዝ ውጭ በፍፁም አይዛነፍም

  • ሶሃባዎች በዚህ አንቀፅ የተወደሱት አምነው በመከተላቸው እንጂ መውሊድን በማክበራቸው አይደለም፡፡ ይህንን አስበውትም አያውቁም ለነብዩም (صلى الله عليه وسلم) ይህንን ጥያቄ አላነሱም፡፡ የሚል ካለ ግልፅ ጥመት መሆኑን አይዘንጋ፡፡
  • ነቢዩን ማክበርና ማላቅ የሚረጋገጠው ትዕዛዛቸውን በማክበር፤ፈለጋቸውን በመከተልና በመሳሰሉት እንጂ በዓመት አንድ ጊዜ እየተሰባሰቡ መውሊድን በማክበር አይደለም ፡፡ በጥቅሉ በዚህ ዙሪያ እንደ መረጃ የሚጠቀሱት አንቀፆች በሙሉ በተዘዋዋሪ የሚጠቀሙት ተቃራኒውን ነው፡፡


6. ‹‹ነብዩ (ሰዐወ) የተለያዩ ክስተቶችን በማስታወስ ድሆችን ያበላሉ፤ይመፀውታሉ፡፡” በዚህ መልኩ የነብዩን ውልደት በማስታወስ ድሆችን ብናበላ ምንም ችግር የለውም

ለዚህ ምላሽ፡- ነገሩ እንዲህ ነው ላስተዋለው ሰው “ለመውሊድ ተብሎ ብር ሲዋጣ በወለድ (በአራጣ) የሚተዳደሩት በሀራም የሚነግዱ ሌሎችም ተቀላቅለው ያዋጣሉ በሀላልም በሀራምም የተገኘ ብር ተደባልቆ ተሰብስቦ ይቀርባል፡፡ ለሀብታምና ለባለስልጣን ስጋ ታድሎ ለድሃና ለሚስኪን አጥንት ይጣላል፡፡ ነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) ክስተቶችን በማስታወስ ያረዱበትና ያበሉበት አንዳችም አጋጣሚ የለም፡፡ በነቢዩ (صلى الله عليه وسلم) የህይወት ዘመን በርካታ ጥሩ ክስተቶች አልፈዋል፡፡
ለምሳሌ፡- ኢስራእ፣ሚዕራጅ፣የበድር ዘመቻ፣ የመካ መከፈት፣ የቁርአን መውረድ እና የመሳሰሉት ታላላቅ ክስተቶችን ተጨማሪ ክስተቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህን ክስተቶች በማስታወስ የሚያከብሩት ዓመታዊ በዓል አልነበራቸውም፡፡ ለዚህም መረጃ ለማምጣት እንሞክራለን ካሉ ይሞክሩት፡፡ የኑህን ዕድሜ ቢሰጣቸውም መረጃ አያገኙለትም፡፡

7. ነብዩ صلى الله عليه وسلم ሰዎችን አቂቃ እንዲያወጡ ካዘዙ በኋላ ለራሳቸው አወጡ አያታቸው አብዱል ሙጠሊብ ግን በልጅነታቸው አቂቃ አውጥተውላቸዋል ስለዚህ ሁለተኛ ያወጡት ለአቂቃ ሳይሆን ልደታቸውን ለማክበር ነው ምክንያቱም በኢስላም ሁለት አቂቃ የለም አንዱ ልደት መሆን አለበት ይላሉ፡፡

የዚህ ምላሽ:- 


  1. አያታቸው አብዱል ሙጠሊብ አቂቃ ማውጣቸው በትክክለኛ ሀዲስ ተዘግቦ አልተገኘም የተገኘው በጣም ደኢፍ በሆነ ሀዲስ ነው /ኢስትአይብ የኢብኑ ዐብዱልበርን ሃሺየተል ኢሷባን እና ሱብለል ሁዳ ወረሻድን ይመልከቱ/ ስለዚህ ደኢፍ የሆነ ማስረጃ መቁጠራቸው ተገቢም ትክክልም አይደለም፡፡
  2. አቂቃን ለምን የልጅ ልደት ብላችሁ ትተረጉሙታላችሁ ይህንንስ ተፍሲር ያገኛችሁት ከየት ነው? አቂቃና የልጅ ልደት ፍፁም የተለያዩ ናቸው፡፡ አቂቃ የልጅ ልደት ነው ብላችኋል ልደት በየዓመቱ ማክበር ይቻላል ካላችሁ አቂቃ ለምን ሁለቴ አይደረግም የሚገርመው ነገር አቂቃ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲወጣ ስለተደነገገ ሁለት ጊዜ አይደረግም ካላችሁ በኋላ በጭራሽ አንድም ጊዜ ያልተሰራውን መውሊድን በየዓመቱ ሲላችሁም ለወራት ደጋግማችሁ ማክበራችሁ ነው አስተውሉ!
  3. ነብዩ صلى الله عليه وسلم ለራሳቸው አቂቃ አወጡ ተብሎ የተገለፀው ሐዲስ በእርግጥ ሐዲሱ ውዝግብ አለበት፡፡ በርካታ ዑለማዎች ሰነዱ ደካማ እንደሆነ ይገልፃሉ/ ለመረጃነት አይበቃም እንደምትሉትም የሁለተኛው አቂቃ ”መውሊድ ” ቢሆን ኖሮ ለምን ረሱል صلى الله عليه وسلم በየአመቱ አልደጋገሙትም፡፡


8. ሌላው ጠንካራ ማስረጃችን ብለው ከቁርዓን የሚጠቅሱት

قُلْ بِفَضْلِ اللَّهِ وَبِرَحْمَتِهِ فَبِذَٰلِكَ فَلْيَفْرَحُوا هُوَ خَيْرٌ مِّمَّا يَجْمَعُونَ

/ የመልእክቱ ትርጉም/ “በአላህ ችሮታና በእዝነቱ በዚህም ምክንያት ይደሰቱ እርሱ ከሚሰበስቡት /ሃብት/ በላጭ ነው በላቸው፡፡ ” “ራሕማ” (በእዝነቱ) ብሎ አላህ በዚህ አንቀፅ ላይ የጠራቸው ነቢዩን صلى الله عليه وسلم ነው ነቢዩን ራህማ ብሎ ጠርቷቸዋል፡፡ ስለዚህ በራህማ (በነቢዩ) እንደሰታለን ይላሉ፡፡
የዚህ ምላሽ፤-

  1. በሙፍሲሮች ዘንድ በዚህ አንቀፅ "ራሕማ " የተባለው ከዚህ በፊት ባለው አንቀፅ መሠረት "ቁርዓን " ነው አንዳንዶቹ "ኢስላም" ብለው ነው የፈሰሩት፡፡ "ራሕማ " የነቢዩ صلى الله عليه وسلم መልእከተኛ ሆነው መላክ ነው ብለው የፈሰሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ በነቢዩ መደሰት አስፈላጊ ነው፡ ሰሃቦች ከማንኛችንም የበለጠ በረሱል ይደሰቱ ነበር። ነገር ግን ይህንን ደስታቸውን መውሊድን በማክበር አልገለፁትም መደሰት የሚገልፀው በአመት አንዴ / በረቢዕ 12/ በመፈንጠዝ አይደለም፡፡
  2. አላህ /ሱብሃነሁ ወተዓላ/ በቁርዓኑ ውስጥ ለነብዩ صلى الله عليه وسلم የዋለላቸውን ውለታና ያጎናፀፋቸውን የተለይዩ ፀጋዎች አውስቷል፡፡ ኢስራዕ እንዳስደረጋቸው ለሙእሚኖች ነቢይ አድርጎ እንደላካቸው እና ሌሎችንም በርካታ ፀጋዎችን ያወሳል፡፡ ውልደታቸውም ቢሆን በዚህ መልኩ ባይጠቀስም ታላቅ ፀጋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ውልደታቸው ፀጋ አይደለም ለማለት ሳይሆን እነዚህን አላህ /ሱብሃነሁ ወተዓላ/ የተመፃደቀባቸውን ታላላቅ ክስተቶች በየዓመቱ እንዲከበሩ ሳይደነገግ መውሊድን ማክበር እንዴት የተደነገገ ይሆናል?


መውሊድ ምን አጠፋ? ብዙ ሰለዋት እንድናደርግ ይገፋፉናል የነቢዩን صلى الله عليه وسلم ታሪክ ለማስተማር እድል ይከፍታል ሰደቃ እንድናበላ ያደርጋል ስለዚህ የጥሩ ነገር በር ከፋች ስለሆነ አትዋጉት፡፡ ይላሉ

የዚህ ምላሽ፦
1 ሰለዎት ሰደቃ ዚክር እና የመሳሰሉት ኢባዳዎች አመቱን በሙሉ ያለገደብ እንዲፈፀሙ በነቢዩ صلى الله عليه وسلم የተደነገጉ ናቸው፡፡ ረሱልም صلى الله عليه وسلم ለእነዚህ ብዙ መንገዶችንና እድሎችን አመቻችተውልናል ለምሳሌ ያህል ”በጅምአ ቀን ሰለዋት በእኔ ላይ አብዙ የናንተ ሰለዋት እኔ ፊት ትቀርባለች ሌላም አዛን በምትሉ ጊዜ ሙአዚኑ እንደሚለው በሉ እኔም ላይ ሰለዋት አብዙ በእኔ ላይ አንድ ጊዜ ሰለዋት ያወረደ አላህ በርሱ ላይ ሰለዋት ያወርድበታል፡፡”
እነዚህንና የመሳሰሉ እድሎችን ከተጠቀምን ትልቅ ነገር ነው፡፡ “በአመት አንድ ጊዜ” ብቻ መገደቡ ለምን አስፈለገ ?

9. መውሊድ ብናከብር ምን አለበት? ለምስጋና ብለን ነው የምናከብረው ይላሉ፡፡

ለዚህ ምላሽ፦ አንድ ሰው ኢማሙ ማሊክ ዘንድ መጥቶ “ከየት ነው ኢሕራም የማድርገው?” ሲላቸው “ረሱል ከሰሩበት ከዙል ሁለይፍ” አሉት፡፡ “እኔ የምፈልገው ከቀብራቸው መሀረም ነው ” አላቸው እሳቸውም “አታድርግ ፈተና እፈራልሀለሁ” አሉት፡፡ “ይህ ምን ፈተና አለበት? ” ሲል ጠየቃቸው በመቀጠልም ”ጥቂት ርቀት እኮ ነው የጨመርኩት” አላቸው “ረሱል ያልደረሱበትን መልካም ስራ በመስራት ቀዳሚ መሆንህን ከማሰብ የበለጠ ምን ፈተና አለ? ” አሉና የሱረቱ ኑርን አንቀፅ 63 ጠቀሱለት፡፡ “ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ፡፡”

10. ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ መውሊድን ማክበር አጅር /ምንዳ/ ያስገኛል ብለዋል፡፡

ለዚህ ምላሽ
1. ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ ለንግግራቸው ከቁርአንና ከሱና መረጃ ይፈለግላቸዋል እንጂ ንግግራቸው ብቻ በራሱ መረጃ ተደርጎ አይወሰድም፡፡
2. ሸይኹል ኢስላም የተናገሩት እንዲህ በማለት ነው፡፡ “አንዳንድ ሰዎች መውሊድን ያልቃሉ እንደ በዓልም ያከብሩታል ይህንን የሚያደርጉት ከመልካም ኒያና ረሱልን ከማላቅ የተነሳ ነው በዚህም ኒያቸው ታላቅ ምንዳ ያገኙበትል፡፡ * ኢቅቲዷኡ ሲራጥ አል-መስተቂም ገፅ 297
ንግግራቸውን ስናጤነው -ስለ ተግባራቸው ሳይሆን ስለ መልካም ኒያቸው ነው ምንዳው፡፡
3. እኚህ ታላቅ አሊም ንግግራቸውን በዚህ መፅሐፍ ላይ ግልፅ አድርገውታል፡፡

“እንደዚሁ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖችን በኢሳ ልደት በመፎካከር ወይም ለነቢዩ صلى الله عليه وسلم ካላቸው ውዴታ በመነሳት የሚፈጥሩትን /ቢድዓ/ በተመለከተ አላህ ስለ ውዴታቸውና ጥረታቸው ሊመነዳቸው ይችላል፡፡ በቢድዓው ግን አይመነዳቸውም፡፡”
ኢቅቲዲኡ ሲራጥ አል-ሙስተቋም ገፅ 294

4. ለክርክርም ሆነ ለንትርክ ምንም በር በማይከፍት መልኩ ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ በመፅሐፎቻቸው በተለያዩ ቦታዎች ላይ መውሊድ ማክበር እንደማይፈቀድ ተናግረዋል፡፡ ይኸውም፡- “የበዓል ወቅት ተደርጎ ያልተደነገገን በዓል አድርጎ መውሰድ ለምሣሌ በረቢዑል አወል የመውሊድ ሌሊት ተብሎ እንደሚከበረው ዓይነት ሁሉም የዚህ ኡማህ አበው ትውልዶች መልካም አድርገው ያላዩትና ያልሰሩት የቢድዓ ተግባር ነው፡፡ ” አል-ፈታዋ 25/298


አላህ እዉነተኛ የነብዩ ወዳጆች ያድርገን!
ፍንትው ያለዉን ፈለጋቸዉን መገንዘብን እና መከተልን ይለግሰን!
ከመደናገር እና ቢድዓ ዉስጥ ከመዘፈቅ ይጠብቀን!!
አሚን!!

www.nesiha.com

Post a Comment

0 Comments