Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በረጅም ግዜ የወለድ ክፍያ የኮንኮሚኒየም ቤት መግዛት በሸሪዓ እይታ ከተያያዥ ጥቆማዎች ጋር በሸይኽ ኢልያስ አሕመድ


ረጅም ግዜ የወለድ ክፍያ የኮንኮሚኒየም ቤት መግዛት በሸሪዓ እይታ

== ከተያያዥ ጥቆማዎች ጋር ==

----------------------------------------
ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግዢ አፈፃፀም የሚሰጠውን ኢስላማዊ ብይን የተመለከቱ ብዙ ጥያቄዎች መነሳታቸው የተለመደ ነው። እንደሚታወቀው ስለአንድ ነገር የሚኖረን ድምዳሜ ስለ ምንነቱ ያለን ምልከታ ላይ የሚገነባ በመሆኑ ይዘቱን መገንዘብ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ይኖርበታል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የ 40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራምን አስመልክቶ በ2005 አመተ ልደት ያወጣውን የቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ፣ እንዲሁም የኮንዶሚኒየም አፓርትመንት ከአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ "በግዢ ከተላለፈላቸው ግለሰቦች ጋር" የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርገውን "የብድር ውል ስምምነት" ናሙና ማንበብ በብዙዎች የሚፈፀመውን ክፍያ ተጨባጭ ይዘት (التكييف الفقهي) ለመረዳት የሚያግዙ በርካታ ጭብጦችን ያስገኛል። ሸሪዓዊው ብይን የሚወሰንባቸውን ጥቂቱን እንመልከት፦
1- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ከባንክ ተበድሮ ለሚገነባው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሽያጭ ባንኩ ኢንተርፕራይዙን ወክሎ ደንበኛዎችን ይመዘግባል፤ የሽያጩ ውልና ርክክብንም ያደርጋል። ሆኖም ቤቶቹን በባለቤትነት ለደንበኞች የሚሸጠው ኢንተርፕራይዙ/ኤጀንሲው እንጂ ባንኩ አይደለም።
በምዝገባ አፈጻጸም መመሪያው ክፍል 4 አንቀፅ 15 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ "ግንባታው ሲጠናቀቅ ባንኩ በውሉ መሰረት ቤቶችን ይረከባል፣ ኢንተርፕራይዙም ያስረክባል" የሚለው በመስሪያ ቤቶቹ መካከል የሚኖረውን የሃላፊነት ድርሻን ለመለየት የተነገረ እንደሆነ ለማሳየት በክፍል 5 የተዘረዘሩትን አንቅፆች በተለይ አንቀፅ 19 ንዑስ አንቀፅ 9 እና 10 ላይ የሰፈረው ግልፅ ማብራሪያ ሆኖ መቅረብ ይችላል።
2- በአንድ ጊዜ መክፈል ላልቻሉ ደንበኞች ባንኩ ቀሪውን (60% ወይም 80% ወይም 90%) ይከፍልላቸዋል።
በዚህም መሰረት ባንኩ ቤት ገዢዎችን እያበደረ እንጂ እየሸጠላቸው አይደለም፤ ምክንያቱም መኖሪያ ቤቱ በባንኩ የባለቤትነት ይዞታ ስር ያልገባ ነውና።
በተጨማሪም በደንበኛውና በባንኩ መካከል ያለው ውል የብድር ውል ስለመሆኑ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤት ፈላጊዎች የምዝገባ አፈጻጸም መመሪያ ክፍል 1 አንቀፅ 7፣ እንዲሁም ክፍል 5 አንቀፅ 14 ላይ በግልፅ ሰፍሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አፓርትመንቱ "በግዢ ከተላለፈላቸው ግለሰቦች ጋር" የሚያደርገውን የውል ሰነድም "የብድር ውል ስምምነት" ሲል ይጠራዋል። ብሎም በክፍል አንድ አንቀፅ 1 ላይ እንዲህ ይላል፦ "ባንኩ ተበዳሪው ያቀረቡትን የብድር ጥያቄ መሰረት በማድረግ ብር ........... ያበደረ ሲሆን ባንኩ እንደተበዳሪው ሆኖ የብድሩን ገንዘብ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ ይከፍላል።"
ስለሆነም ባንኩ ለኤጀንሲው የሚከፈለውን ሙሉ የቤት ዋጋ ለገዢው ያበድራል ማለት ነው።
3- ከዚያም ባንኩ ብድሩ ላይ የተለመደውን የወለድ ፐርሰንት ጨምሮ በማስላት ደንበኛውን በረጅም ጊዜ ክፍያ ያስከፍላል። ክፍያው እስኪጠናቀቅም የቤቱን ካርታ እንደዋስትና ይዞ ይቆያል።
--------
ከዚህ እንደምንገነዘበው ደንበኛው በአንድ ጊዜ ክፍያም ይሁን በረጅም ጊዜ ክፍያ ዋጋውን ለመክፈል ቢስማማ ከከተማው አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር የሚፈፀመው የሽያጭ ውል በአንድ ጊዜ ተፈፅሞ የሚጠናቀቅና የተገደበ ዋጋ ያለው ነው፤ ሆኖም በአንድ ጊዜ መክፈል ላልቻሉ ደንበኞች ቅድሚያ በቁጠባ ሂሳብ ካጠራቀሙት ውጭ ያለውን ቀሪ ክፍያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር መልኩ ለኤጀንሲው ይከፍልላቸውና ብድሩን በረጅም ጊዜ ከነወለዱ ያስከፍላቸዋል።
👉 ስለሆነም "በረጅም ጊዜ ክፍያ" የመግዛት እውነተኛ ገፅታ ከባንክ በወለድ ተበድሮ መክፈል እንጂ ሌላ አይደለም። ይህ በበርካታ አገራት የተመደ አሰራር ነው።
------
== ሸሪዓዊ ፍርዱ ==
👉 የተወሰነ መጠን ንብረትን (አይነቱ ምንም ቢሆን) በብድር ለሌሎች የሚያስተላልፍ አካል አምሳያውን መጠን ብቻ በመቀበል ፈንታ ማንኛውንም አይነት ጭማሪ ለማስከፈል በግልፅም ይሁን በውስጠ ታዋቂነት መስማማቱ በቁርኣን በጥብቅ የተኮነነው የጃሂሊያው አራጣ ውስጥ እንደሚገባ ምንም አይነት ውዝግብ የለም። [1]
ወለድ የተከለከለ መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን መዘርዘር የዚህ አጭር ፅሑፍ አላማ አይደለም። ሆኖም በሸሪዓችን ለጉዳዩ የተሰጠው አፅእኖት እጅግ ከባድ ከመሆኑ አንፃር የተለያዩ ቁርኣናዊና ሐዲሣዊ አስረጆች ወለድን ከአጥፊ ሃጢያቶች መቁጠራቸው፤ ሌሎች ወንጀሎች ላይ ያለተጠቀሱ አስፈሪ ዛቻዎችን መግለፃቸው፤ ወለድን ብቻ ሳይሆን ወደርሱ በተዘዋዋሪ የሚያመሩ መንገዶችን መዝጋታቸው እሙን ነው።
ክልከላው የሚመለከተው ወለድን መብላትን /መውሰድን/ ብቻ ሳይሆን ማብላቱንም /መስጠትንም/ እንደሆነም ሊዘነጋ አይገባም።
عَنْ جَابِرٍ، قَالَ: «لَعَنَ رَسُولُ اللهِ -صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ- آكِلَ الرِّبَا، وَمُؤْكِلَهُ، وَكَاتِبَهُ، وَشَاهِدَيْهِ»، وَقَالَ: «هُمْ سَوَاءٌ» أخرجه مسلم.
ጃቢር እንደሚያስተላልፉት፦ የአላህ መልእክተኛ ወለድ የሚበላን፣ የሚያበላን፣ ውሉን የሚፅፈውንና መስካሪዎቹን ረግመዋል፤ እንዲሁም "ሁሉም እኩል ናቸው" ብለዋል። ሙስሊም ዘግበውታል።[2]
-----------
== ዶሩራ (ضرورة) እና ወለድ ==
በሸሪዓችን አስገዳጅ የችግር ሁኔታ (ضرورة) ሲኖር የተከለከሉ ተግባራት ይፈቀዱ የለ ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።
በርግጥ ይህ በጥቅሉ ትክክለኛ መርሆ ነው። ሆኖም ወለድ እጅግ የገዘፈ ኃጢያት ከመሆኑ አንፃር ሊፈቀድ የሚቻልበት አስገዳጅ የችግር ሁኔታ (ضرورة) ጭራሽ ስለመኖሩ ዑለማዎች ተወዛግበዋል።
አንዳንዶች የመረጡት የሚከተለውን ዝርዝር ነው፦
በወለድ ማበደር የሚፈቀድበት አስገዳጅ ሁኔታ ሊኖር አይችልም፤ ምክንያቱም የሚያበድረውን ገንዘብ ራሱ መጠቀም ይችላልና።
በወለድ መበደር እንደ ማበደር በጥብቅ የተከለከለ ቢሆንም በአንዳንድ አስገዳጅ የችግር ሁኔታዎች ሊፈቀድ ይችላል።[3] ሆኖም አፈፃፀሙ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይሻል። እርምነታቸው የፀና ወንጀሎች የክልከላ ገደባቸው የሚነሳው የተፈቀደ አማራጭ በማይኖርበት የዶሩራ ቅድመ ሁኔታ እንጂ ድርጊቱን መፈፀሙ አስፈላጊ (حاجة) ስለሆነ ብቻ አይደለም።
== የዶሩራ እና የሓጃ ልዩነት ==[4]
ዶሩራ (ضرورة) የሚባለው ክልከላውን ለመፈፀም የሚያስገድድ አጣብቂኝ ሲሆን ገደቡም ይህን ካላደረጉ በእርግጠኝነት ወይም ተጨባጭነት ባለው አመዛኝ ግምት ህይወት የሚጠፋ፣ አካል የሚጎድል፣ አእምሮ የሚነካ ወይም የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ በሽታ አሊያም አግባብ የሌለው የረጅም ጊዜ እስር የሚከተል፣ ክብረ ስብእና በዝሙትና በመሰል አፀያፊ ተግባራት የሚጎድፍ፣ ከፍተኛ ንብረት የሚጠፋ ወይም መሰል ጉዳት የሚከተል መሆኑ ነው።[5]
ሓጃ (حاجة) ግን ተግባሩን ካልፈፀሙት ችግር ውስጥ ሊያስገባ ይችላል፤ ሆኖም ሊሸከሙት የሚችሉት አይነት ችግር ነው እንጂ የዶሩራ እርከን ላይ የደረሰ ጥበት አይደለም።[6]
ለምሳሌ፦ አንድ ሰው በኪራይም ይሁን በጥገኝነት፣ አልያም በራሱ ይዞታ ስር ያለ ማረፊያ/መጠለያ ማግኘቱ በጥቅሉ ዶሩራ ይባላል፤ ሆኖም መኖሪያው ከኪራይና ከሌሎች ተፅእኖዎች የፀዳ ወይም ለስራ ቦታው የቀረበ መሆኑ ሓጃ እንጂ ዶሩራ አይሰኝም።
ታዲያ በአፅእኖት የተከለከሉ ከባባድ ወንጀሎችን መፈፀም የሚፈቀደው ድርጊቱ ከላይ እንደተጠቀሰው በህይወት ላይ የተጋረጠን አደጋ ለማስቀረት ብቸኛ አማራጭ በሚሆንበት ጠባብ የዶሩራ አጋጣሚዎች (ضرورة خاصة) ላይ ብቻ ነው።[7]
ወለድም በዶሩራ ህግ ረገድ ልክ እንደበከተ ስጋ እና መሰል ክልከላዎች ነው፤ በህይወት ላይ የተጋረጠን አደጋ ለማስቀረት እንጂ አይፈቀድም።[8]
*******************************************************************
👉 በዚህ መሰረት በኪራይ ወይም በሌሎች አማራጮች መጠለያ ማግኘት ለሚችል ሰው የቤት ባለቤት የመሆን አስፈላጊነት አስገዳጅ የሆነው የዶሩራ ክልል ውስጥ አይገባም።[9] የኪራዩ ወርሃዊ ወጪ ከኮንዶሚኒየም ውል ወርሃዊ ወጪ የበዛ ቢሆን እንኳ ተቸግሮም ቢሆን በሐላል መከራየት እየቻሉ እርግማን በሚያስከትለው የወለድ ስምምነት ውስጥ እጅን ማስገባት የሚፈቀድ ሊሆን አይችልም።
*******************************************************************
በርግጥ ሙስሊሞች አናሳ በሆኑባቸው የምእራብ አገራት በአንድ ጊዜ ክፍያ ቤት መግዛት የማይችሉ ሙስሊሞች ከኪራይ ጣጣና ከሌሎች ማህበራዊ ተፅእኖዎች ለመውጣት ከባንክ በወለድ ብድር ቤት መግዛታቸውን ከዶሩራ አንፃር ያግራሩ ፈትዋዎች ተገኝተዋል። ሆኖም እነኚህ ፈትዋዎች የተመረኮዙባቸው መሰረቶች ሲገመገሙ ከፊሎቹ በብዙሃኑ ሊቃውንት የተተቹ "መረጃዎችን" እና ባይተዋር ምርጫዎችን ያማከሉ ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ተጨባጩን ሁኔታ የማይገጥሙ የስሁት ኢጅቲሃድ ውጤቶች እንደሆኑ በብዙ ሂሶች ተብራርቷል።[10]
አንዱና ዋነኛ ምርኩዛቸው "ሓጃ በዶሩራ ደረጃ ላይ ይቀመጣል" የሚለው የፊቅህ መርሆ ነው። መርሆው በመሰረቱ ልቅ በሆነ መልኩ ተፈፃሚ ስለመሆኑ ውዝግብ ያለ ከመሆኑ ጋር በዚህ ንዑስ ጉዳይ ላይ ይህን መደገፊያ ማድረግ መስፈርቱን ያላሟላ እይታ ነው። ምክንያቱም የሓጃው (የአስፈላጊነቱ) ደረጃ ሁሉም ላይ ተጋርጦ እንደሪባ ያለን አጥፊ ወንጀል የሚያስፈቅድበት እርከን ላይ የደረሰ ባለመሆኑና በርሱ ውስጥ ከመነከር የሚያብቃቁ አማራጮች በመኖራቸው ነው።[11]
አዎን! ምናልባት በአንዳንድ መሰናክሎች የተነሳ መከራየት የማይችል ወይም አከራይ ያላገኘ ወይም ከአቅሙ በላይ የሆነ ሙስሊም ቢገኝና በረጅም ጊዜ የወለድ ክፍያ ከመግዛት ውጪ ያለው ብቸኛ አማራጭ መጠለያ አጥቶ ወደ ጎዳና መውጣት ወይም ሌሎችን አጥብቆ ማስቸገር ከሆነ ይህ አይነቱ ያለበት አስገዳጅ ሁኔታ እንደ ዶሩራ ሊታይ ይችላል። ሆኖም በትክክል የዶሩራ እርከን ላይ መድረሱን ለማረጋገጥ ታማኝ ዓሊሞችን መጠየቅ ይኖርበታል።[12]
----------
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ይነሳል፦
በወለድ በተበደረው ገንዘብ ቤት ወይም ሌላ ንብረት ገዝቶ ያለ ሰው ጥፋቱን ለማካካስ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
መልሱ፦ የመጀመሪያው እርምጃ መስፈርቱን ያሟላ ተውበት ማድረግ ነው። ታዲያ ተውበቱ ትክክል እንዲሆን በወለድ ብድር የገዛቸው ንብረቶችን ከይዞታው ማውጣት ግዴታ ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ ብዙ ዑለማዎች ያላቸው ምላሽ እንደሚከተለው ነው፦
"የወለድ ብድር" ሲባል ተበዳሪው የተበደረው ገንዘብ ራሱ ወለድ ነው ማለት አይደለም። ወለዱ ለአበዳሪው ወደፊት የሚከፍለው ጭማሪ ነው። ስለሆነም ቤቱ በቀጥታ በወለድ ገንዘብ የተገዛ አይደለም ማለት ነው። አዎን! አንድ አራጣ አበዳሪ በሚያገኘው "ትርፍ" የሚገነባው ቤት ወይም የሚሸምተው እቃ በወለድ ገንዘብ የተሰራ ወይም የተገዛ መሆኑን እንስማማለን። ተበዳሪ የሚገዛው ቤት ግን በራሱ የሐራም ንብረት እንደሆነ አይታሰብምና ቤቱን በመሸጥም ይሁን በሌላ ሂደት መልቀቁ ግዴታ አይሆንም።
እዳውን ከነወለዱ ከፍሎ ያልጨረሰ እንደሆነ የወለዱን ጭማሪ ሳያክል የተበደረውን መጠን ብቻ ለመክፈል አበዳሪውን ማግባባት ከቻለ ይህንን ማድረጉ ግዴታ ይሆናል። አላህ እንዲህ ብሏል፦
((وَإِن تُبۡتُمۡ فَلَكُمۡ رُءُوسُ أَمۡوَٰلِكُمۡ لَا تَظۡلِمُونَ وَلَا تُظۡلَمُونَ))
{በፀፀት ከተመለሳችሁም ለናንተ ዋናው ገንዘባችሁ አልላቸሁ፤ አትበድሉም አትበደሉምም።}
አበዳሪው ክፍያውን ያለወለዱ ለመቀበል የተቀረውን ሙሉ ክፍያ በአንድ ጊዜ እንዲከፍለው ቢጠይቅ ሌላ የሐላል ብድር ተበድሮ አሊያም የተወሰነ ንብረቱን ሽጦም ቢሆን ክፍያውን አጠናቅቆ ከወለድ ጣጣ መውጣት ይገባዋል።
ይህንን ማድረግ ሳይችል ቢቀር ወይም የወለዱን ጭማሪ ባለመክፈሉ ለእስር ወይም ለንብረት መወረስና ለመሰል ችግሮች የሚጋለጥ ከሆነ ያለበትን እዳ ከነጭማሪው እየከፈሉ መቀጠሉ ከላይ ባሳለፍነው የዶሩራ ህግ መሰረት በይቅርታ የሚታለፍ ይሆናል።
والله أعلم بالصواب
-----
== የመፍትሄ ጥቆማ ==
1/ ኤጀንሲው ዋጋውን በጥቂቱ ከፍ አድርጎ ለደንበኞች ያለ አማካይ በተገደበና በማይጨምር የረጅም ጊዜ ክፍያ (التقسيط) ቤቱን መሸጥ ይችላል።
አሊያም ባንኩ ወይም ሌላ ድርጅት ቤቱን በግዢ በይዞታው ስር አስገብቶ ባለቤት ከሆነ በኋላ ለደንበኛው በተገደበና በማይጨምር የረጅም ጊዜ ክፍያ (installment) አትርፎ መሸጥ ይችላል።
እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ማስተዋል የግድ ነው፦
አንደኛ፦ ይህን የረጅም ጊዜ ክፍያን በተገደበው ጊዜ መክፈል ያልቻለ ግለሰብ በምንም መልኩ ("መቀጫ"ም ተባለ ሌላ) የወለድ ጭማሪ ሊጫንበት አይገባም። አለበለዚያ እስካሁን የጋገርነው ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሆነ ማለት ነው!
ሁለተኛ፦ ባንኩ ለክፍያው ማስተማመኛ የሚሆኑ ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። ከነዚህ አንዱ የዋስትና ንብረት (رهن) መያዝ ሲሆን የሚሸጠውን እቃ (ቤቱንም) ራሱ እንደ መያዣ ማድርግን የፈቀዱ ሊቃውንት አሉ። ሆኖም ደንበኛው መክፈል እንዳቃተው ከተረጋገጠ መያዣው ተሽጦ የተቀረው እዳ ከተከፈለ በኋላ ቀሪው ሊመለስለት ይገባል እንጂ ባንኩም ይሁን ሌላ አካል የመያዣውን ሙሉ ዋጋውን የመውሰድ መብት የለውም።
-----
2/ ሽያጩ በሙራበሓ (مرابحة) መልኩም ሊፈፀምም ይችላል። ይህም ማለት ቤት መግዛት የሚፈልግ ግለሰብ ሙሉ ዋጋውን መክፈል ስለማይችል ባንኩ ወይም ድርጅቱ ግለሰቡ የሚፈልገውን ቤት (ወይም ሌላ እቃ) እንዲገዛውና በረጅም ጊዜ ክፍያ አትርፎ እንዲሸጥለት በውል ደረጃ ሳይሆን በቃል ኪዳን ደረጃ ይስማማሉ። የሽያጭ ውሉ ባንኩ ቤቱን (እቃውን) ገዝቶ በይዞታው ስር ካሳደረው በኋላ የሚፈፀም መሆን አለበት፤ በይዞታ ስር ያልገባን ውስን ነገር መሸጥ ክልክል ነውና።
እዚህ ላይ ለመግዛት ቃል የገባን ደንበኛ ቃሉን እንዲያከብር የሚያስገድድ እንደ ቀብድ ያለ መስፈርት ወይም ሂደት መኖር የለበትም።[13] ካልለ ግን ቃል ኪዳኑ እንደ ሽያጭ ውል ፅኑ እንዲሆንና ማፋረስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ስለሚያደርገው ግብይቱ ገና ቤቱ በሻጩ ይዞታ /ባለቤትነት/ ስር ሳይገባ እንደተፈፀመ ያህል ታስቦ የተከለከለ ይሆናል።
ባንኩ /ድርጅቱ/ ቤቱን ከገዛ በኋላ ለመግዛት ቃል የገባው ደንበኛ ቃሉን ቢያፈርስ ለሌላ ደንበኛ መሸጥ ይችላል፤ ወይም ቀድሞውኑ ቤቱን ሲገዛ በተገደበ የጊዜ ወሰን ውስጥ ለሻጩ መመለስ የሚያስችል ምርጫ (خيار الشرط) እንዲኖረው ቅድመ ሁኔታን ማስቀመጥ ይችላል።
------
በመጨረሻም ሙስሊም ባለሃብቶች በሐላል ገደቦች ተወስነው በእንዲህ ያለ መስክ መዋእለ ንዋያቸውን ማዋላቸው ለችግሩ መፍትሄ የሚያበጅ አንድ እርምጃ ከመሆኑ አንፃር እቅዳቸው (ኒያቸው) ካማረ ከአለማዊ ትርፍ ባሻገር ለአኺራቸው ስንቅ የሚሆን ምንዳም እንደሚያተርፉበት አያጠራጥርም።
والله أعلم
====== የግርጌ ማስታወሻዎች ======
[1] الإشراف لابن المنذر (6/142)، والإحماع له ص 55، المحلى لابن حزم (8/77)، الكافي لابن عبد البر ص 318، والاستذكار له (6/ 513 و 516) ، المغني لابن قدامة (6/436) ، تفسير القرطبي (3/241)
[2] صحيح مسلم (1598)
[3] فتوى " مجمع البحوث الإسلامية " بالقاهرة في مؤتمره الثاني المنعقد في شهر محرم 1385 هـ ( مايو 1965م )
[4] ينظر للتوسع في الفرق بينهما: "الحاجة الشرعية حدودها وقواعدها" لـ أحمد كافي ص 36 - 48
[5] " نظرية الضرورة الشرعية" ( ص 67 ، 68 )، " المنثور في القواعد" للزركشي (2/319)
[6] المنثور في القواعد للزركشي (2/319)، والأشباه والنظائر للسيوطي (1/ 213)، وحقيقة الضرورة الشرعية وتطبيقاتها المعاصرة د. محمد الجيزاني ص- 47
[7] "المفصل في القواعد الفقهية" ص 268 – 269، د. يعقوب الباحسين، و"فقه النوازل للأقليات المسلمة" 2/868
[8] مجموع فتاوى ومقالات الشيخ ابن باز (19/301)
[9] ينظر قرار رقم: (52/1/6) لمجلس مجمع الفقه الإسلامي الدولي المنعقد في دورة مؤتمره السادس بجدة من 17-23 شعبان 1410 الموافق 14 – 20 آذار (مارس) 1990م ، بشأن التمويل العقاري لبناء المساكن وشرائها،
مجلة المجمع (العدد الخامس، ج4 ص2773 والعدد السادس ج1 ص81)
[10] انظر كُتيب "وقفات هادئة مع إباحة القروض الربوية لتمويل شراء المساكن في الغرب" د. الصاوي، و"فقه النوازل للأقليات المسلمة" تأصيلا وتطبيقا د. محمد يسري إبراهيم 2/851 - 893
[11] "المفصل في القواعد الفقهية" د. يعقوب الباحسين، ص 268 – 269، و"ضوابط الحاجة التي تنزل منزلة الضرورة" مجلة جامعة دمشق للعلوم الاقتصادية والقانونية – المجلد 26-العدد الأول -2010 ص- 683 – 687، و"فقه النوازل للأقليات المسلمة" 2/868
[12] قرارات وتوصيات المؤتمر الثاني لمجمع فقهاء الشريعة بأمريكا (ص- 100)، و"وثائق النوازل" (فقه النوازل – الإصدار الثاني) د. الجيزاني 4/2361 وثيقة رقم 692
[13] ينظر: قرار مجمع الفقه الإسلامي بجدة، قرار رقم: 40 -41 (2/5 و3/5)، والمعايير الشرعية لهيئة المحاسبة والمراجعة للمؤسسات المالية الإسلامية، رقم 8 ص- 205

🖌 በሸይኽ ኢልያስ አሕመድ
ነሲሓ መፅሄት / ቅፅ 1 | ቁጥር 2

Post a Comment

0 Comments