Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የረመዳን ልዩ መታወቂያዎች


የረመዳን ልዩ መታወቂያዎች

አንድ አመት ከአላህ ዘንድ አስራ ሁለት ወራትን ይዟል፡፡ ጌታችን አላህ በችሎታው በጥበቡ ነብይን ከነብይ፣ ወልይን ከወልይ፣ ቦታን ከቦታ፣ ዘመንን ከዘመን አበላልጧል፡፡ ከነብይ ሁሉ በላጩ ነብዩ ናቸው፡፡ ከሳቸው ህዝብ ሁሉ በላጩ ወልይ አቡበክር አስሲዲቅ ናቸው፡፡ ከቦታዎች ሁሉ በላጭ መስጂዶች ናቸው፡፡ ከመስጂዶች ሁሉ በላጩ መስጂደል ሐራም ነው፡፡ ልክ እንዲሁ ከአላህ ወራትም ውስጥ ረመዳን በብዙ ነገሮች ልዩ ማዕረግ አለው፡፡ ለምሳሌ ያክል፡-

  1. ረመዳን ቁርኣን የወረደበት ወር ነው፡፡ 
  2.  የረመዳን ወር ፆም ከአምስቱ የኢስላም ማእዘናት አንዱ ነው፡፡
  3. ረመዳን ከ 1000 ወራት (83 ዓምት)  የምትበልጠው ለይለተል ቀድር የምትገኝበት ወር ነው፡፡
  4.  ረመዳን በተራዊሕ የደመቀ ወር ነው፡፡
  5.  ረመዳን የጀነት፣ የሰማያትና የእዝነት በሮች የሚከፈቱበት፤ የጀሀነም በሮች የሚዘጉበት፣ ሸይጧኖች የሚጠፈሩበት ወር ነው፡፡
  6. በዚህ ወር የተደረገ ዑምራ ምንዳው ከነብዩ ጋር ሐጅ የማድረግ ያክል የገዘፈበት ወር ነው፡፡
  7.  ረመዳን በዘካተል ፊጥር የታጀበ ወር ነው፡፡
  8.  ረመዳን በአግባቡ ለፆመው ሰው እስከ ቀጣይ ረመዳን ድረስ ወንጀልን የሚያሳብስ ወር ነው፡፡
  9.   ረመዳን የቸርነት ወር ነው፡፡
  10. ረመዳን ከሌሎች ወራት በተለየ “የቁርኣን ወር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ወር ነው፡፡

ረመዳንን ለመፆም የሚያስገድዱ መስፈርቶች፡-

  1.  ሙስሊም መሆን፣
  2. አእምሮ ጤነኛ መሆን፡- በእብድ ላይ ፆም የለበትም፡፡
  3. ኒያ (ለመፆም ቁርጠኛ ውሳኔ መያዝ)
  4. ከወር አበባና ከወሊድ ደም ነፃ መሆን፣
  5. ነዋሪ መሆን፡- ጉዞ ላይ ያለ ሰው የመፆም ግዴታ የለበትም፡፡
  6. ችሎታ
  7. አቅመ አዳም ወይም አቅመ ሄዋን መድረስ (ይህም የብልት አካባቢ ፀጉር የሚላጭ ቀድር ሆኖ መብቀል፣ በህልምም ይሁን በውን በስሜት የዘር ፈሳሽ መርጨት መጀመር፣ የወር አበባ ደም ማየት እና እነዚህ ካልታዩ ደግሞ 15 አመት መሙላት ናቸው፡፡)

የረመዳን ፆም ግዴታዎች፡-

  1.  የረመዳን ጨረቃ መግባቱን ማረጋገጥ፣
  2.  ከእውነተኛው ፈጅር ጀምሮ ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ከሚያስፈጥሩ ነገሮች በሙሉ መቆጠብ፣
  3. በሌሊት የተቋጠረውን ኒያ እስከ ፀሐይ ግባት ድረስ ማዝለቅ፡- በመሀል የማፍረስ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ባይበላ ባይጠጣም ፆሙ ይበላሻል፡፡
  4. ረስቶ እየበላ ወይም እየጠጣ ያለ ሰው ካስታወሰ ወይም ሌሎች ካስታወሱት ባስቸኳይ አፉ ላይ ያለውን ማውጣት፣
  5. ግንኙነት ላይ እንዳይወድቅ ለሚሰጋ ሰው ከሚስቱ መራቅ፣
  6. ከመጥፎ ቃላትና ተግባራት መቆጠብ፣ 
  7.  ፆምን በጥላቻ መንፈስ ሳይሆን እየወደዱ መፆም

ፆም የሚያፈርሱ ነገሮች

  1. አውቆ መብላት፣
  2. አውቆ መጠጣት፣
  3. አውቆ መድሃኒት መዋጥ፣
  4. አውቆ ግንኙነት መፈፀም፣
  5. የዘር ፈሳሽን አውቆ ማፍሰስ፡፡ ከግንኙነት ውጭ ባለ መንገድ ለምሳሌ ብልትን በእጅ እየነካኩ የዘር ፈሳሽን ማፍሰስ ከአራቱ የፊቅህ መዝሀብ አኢማዎችና ብዙሃን ዑለማዎች ዘንድ ፆምን ያበላሻል፡፡
  6. በአፍንጫ የሚወሰድ ጠብታ፡- ነብዩ “ፆመኛ ካልሆንክ በስተቀር በአፍንጫህ በጥልቅ ውሃ ሳብ” ብለዋል፡፡ ይህንን ሐዲሥ መነሻ በማድረግ ኢብኑ ባዝና ኢብኑል ዑሠይሚን ረሒመሁሙላህ በአፍንጫ ጠብታ መውሰድ ጾም እንደሚያበላሽ ተናግረዋል፡፡
  7. አውቆ ማስታወክ (ማስመለስ)፣
  8. ሲጋራና መሰል ነገሮችን ማጨስ፣
  9. የወር አበባ ደም መምጣት፣ 
  10.   የወሊድ ደም መምጣት፣ 
  11.  ዋገምት፡፡ ከባድ ውዝግብ ያለበት ነው፡፡ ስለሆነም መራቁ ተመራጭ ነው፡፡ 
  12.    የምግብ መርፌ መወጋት፣ 
  13.   ደም መቀበል፣ 
  14.   ፆምን ለማቋረጥ በቁርጥ መወሰን፣ (ባይበላም ባይጠጣም ፆሙ ፈርሷል፡፡) 
  15.  ከኢስላም ማፈንገጥ፣
  16. አላህን አስቦ ሳይሆን ለይሉኝታ ብሎ መፆም፣ 
  17.  ከአላህ ውጭ ላለ አካል እርድ፣ ስለት፣ ዱዓእ፣… መፈፀም፡፡ ትልቁ ሺርክ ስለሆነ፡፡ 
  18.  በጠንቋይና በደጋሚ ማመን፡፡ ነብዩ “የወር አበባ ላይ ያለችን ሴት ወይም ደግሞ ሴትን በፊንጢጣዋ በኩል የተገናኘ፣ ወይም ከጠንቋይ ዘንድ ሄዶ በሚናገረው ያመነ ሰው በሙሐመድ ላይ በተወረደው ክዷል” ብለዋል፡፡ አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡ [ሶሒሑ አትተርጊብ ወትተርሂብ፡ 2433]

ለፆመኛ የሚወደዱ ነገሮች፡-

  1. ሰሑር መመገብ፡- ነብዩ “በኛና በመፅሐፉ ሰዎች መካከል ያለው ጾም መበላለጫው የሱሑር ምግብ ነው” ብለዋል፡፡ [ሙስሊም፡ 1096]
  2.  ሰሑርን ተምር ማድረግ፡- ነብዩ “ተምር ምን ያማረ የሙእሚን ሰሑር ነው” ብለዋል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 562] 
  3.  ሰሑርን ማዘግየት፡- ነብዩ “ሶስት ነገሮች ከነብያዊ ተግባራት ናቸው፡፡ ፊጥራን ማፋጠን፣ ሰሑርን ማዘግየት እና በሶላት ላይ ቀኝ እጅን ግራ ላይ ማድረግ ናቸው፡፡” [አልጃሚዑ አስሶጊር፡ 5349] 
  4.  ፊጥራን ማፋጠን፡- ነብዩ “ሰዎች ፊጥራን እስካቻኮሉ ድረስ ከኸይር አይወገዱም” ብለዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
  5. ስሑርና ፊጥራን በልክ ማድረግ፣
  6.  በእሸት ተምሮች ማፍጠር፣ ካልተገኘ በበሰሉ ተምሮች፣ ከሌለ ውሃ መጎንጨት፡- “ነብዩ ከመስገዳቸው በፊት በእሸት ተምሮች ያፈጥሩ ነበር፡፡ እሸቶች ከሌሉ በተምሮች፣ እነሱም ከሌሉ ውሃ ይጎነጩ ነበር፡፡” [አስሶሒሐህ፡ 2056]
  7. ከፊጥራ በኋላ የሚከተለውን ዱዓእ ማድረግ፡- “ዘሀበ’ዝዞመኡ፣ ወብተልለቲል ዑሩቁ፣ ወሰበተል አጅሩ ኢንሻአላህ፡፡” አልባኒ “ሐሰን” ብለውታል፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 4678] ትርጉሙም፡- “ጥሙ ተወገደ፤ ደም ስሮች ረጠቡ፤ በአላህ ፈቃድ ምንዳውም ተረጋገጠ፡፡”
  8. ላስፈጠረህ ዱዓእ ማድረግ፣
  9. ፆመኛ ማስፈጠርን ማብዛት፡- ነብዩ “ፆመኛን ያሰፈጠረ ሰው ልክ የሱን (የፆመኛውን) አምሳያ ምንዳ አለው፡፡ ባይሆን የፆመኛው ምንዳ ምንም አይቀንስም” ብለዋል፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 6415] 
  10.  ተራዊሕን ኢማሙ እስከሚያጠናቅቅ አብሮ መስገድ፣
  11. በመልካም ስራዎች ላይ ከወትሮው በተለየ መበርታት፡- ኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡- “ነብዩ ከማንም በላይ ቸር ነበሩ፡፡ ይበልጥ ቸር የሚሆኑት ደግሞ በረመዳን ነበር፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] ስለዚህ ለቤተሰብ፣ ለዘመድ፣ ለጎረቤት፣ ለችግረኞች ከወትሮው በተለየ ማሰብና መደጎም፡፡ ዚክር፣ ዱዓእ፣ ቁርኣን መቅራት፣ ሱና ሶላቶችን መስገድ፣ በሽተኛን መጠየቅ፣ ቀብር መዘየር፣ ደዕዋ ማድረግ፣ መፋቂያ መጠቀም፣ ሰላምታ፣ ፈገግታ፣ መልካም ንግግር፣… ማብዛት፣ 
  12.   በመጨረሻው አስሩ የወሩ ቀናት በተለይም ሌሊቱ ላይ ይበልጥ ለዒባዳ መነሳሳት፡- “የአላህ መልእክተኛ በመጨረሻዎቹ አስሮች ላይ - በሌሎቹ ከሚበራቱት በተለየ - ይበልጥ ይበራቱ ነበር፡፡” [ሙስሊም፡ 1175]
  13. በሱሑር ሰዓት ኢስቲግፋር ማብዛት፣
  14. ለሚሳደብ ሰው “እኔ ፆመኛ ነኝ” ብሎ መመለስ፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] 
  15. ልጆችን ፆም ማለማመድ፣
  16. ለቻለ ዑምራ ማድረግ፣ 
  17. ኢዕቲካፍ ማድረግ፣…

ለፆመኛ ሰው የሚጠሉ ነገሮች፡-

  1. ስሜትን በማነሳሳት የሚፈታተን ከሆነ ሚስትን መሳም፣ መተሻሸት፣ ስለ ግንኙነት ማሰብ፣ እይታን ማዘውተር፣
  2. በጥልቅ መጉመጥመጥና በአፍንጫ ውሃ መሳብ፣
  3.  ወሬ ማብዛት፣
  4. የአይን ወይም የጆሮ ጠብታ መጠቀም፣
  5. ሰሑርን መተው፣
  6.  ፊጥራን ማዘግየት፣
  7. ስለሴቶች ማውራት፣ ለሴቶች ደግሞ ስለወንዶች ማውራት፣ 
  8.  ጩኸት ማብዛት፣…

ለፆመኛ የሚፈቀዱ ነገሮች

  1.  እራሱን ለሚቆጣጠር ሰው ሚስቱን መሳም፣ ከሚስቱ ጋር መጫወት፣
  2. መታጠብ፣ ሳሙናና ሻምፖ መጠቀም፣
  3. መፋቂያና የጥርስ ሳሙና መጠቀም፣
  4. ሽቶ፣ ዶዶራንት መቀባት፣
  5. ምራቅን መዋጥ፣ ሆን ብሎ መሰብሰብ ሳይኖር፣
  6. አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ምግብን መቅመስ፣ ግን መትፋት ያስፈልጋል፣
  7. የደም ምርመራ ማድረግ፣
  8. የምግብ ያልሆነ መርፌ መወጋት፣
  9. የወር አበባ ለማስቆም ክኒን መውሰድ (በቀኑ ክፍለ ጊዜ አይደለም)፣
  10. ስኳር ህመም ላለባቸው ኢንሱሊን መወጋት፣…

በወርሃ ረመዳን በብዛት የሚያጋጥሙ ስህተቶች

  1.  ከመጠን በላይ መመገብ፡-
           ይሄ ችግር በተለይም ረመዳን ላይ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ያለመጠን መመገብ ለብዙ ሸር መንሰኤ ነው፡፡ ሱፍያን አሥሠውሪ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “አካልህ ጤናማ እንዲሆን፣ እንቅልፍህ እንዲቀል ከፈለግክ ምግብህን አቅልል፡፡” ጌታችን እንዲህ ይላል፡
    وَكُلُواْ وَٱشۡرَبُواْ وَلَا تُسۡرِفُوٓاْۚ [الأعراف: 31]

    “ብሉ ጠጡ፡፡ አታባክኑ፡፡” [አልአዕራፍ፡ 31]
    ታላቁ ዓሊም ኢብኑ ቀይም አልጀውዚያ ረሒመሁላህ ከዚች አንቀፅ ቀጥለው እንዲህ ይላሉ፡- “ባራገፉት ፋንታ ሰውነታቸውን የሚያቆሙበት ምግብና መጠጥ እንዲያስገቡ ባሮቹን ጠቆማቸው፡፡ መጠኑም አይነቱም አካላቸው በሚጠቀምበት መጠን እንዲሆንም አሳሰባቸው፡፡ ይህንን ባለፈ ጊዜ ብክነት ይሆንበታል፡፡ ሁለቱም ጤናን ጎጅ፣ በሽታን ጎታች ነው፡፡ ማለትም አለመብላትና አለመጠጣት እንዲሁም በምግብና በመጠጥ ድንበር ማለፍ፡፡” [አጥጢቡ አንነበዊ፡ 181] 
  2.   በስህተት የበላ ወይም የጠጣ ሰው ፆሙ ተበላሽቷል በሚል መቀጠል፡፡ በስህተት መመገብም ሆነ መጠጣት በምንም መልኩ ፆምን አያበላሽም፡፡ ነብዩ “አንድ ሰው ረስቶ ከበላና ከጠጣ ፆሙን ይቀጥል፡፡ ያበላውና ያጠጣው አላህ ነው” ብለዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]  
  3. የወር አበባ ከመጣ በኋላ ፆምን መቀጠል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ፆም ይዘው ቀኑን ካጋመሱ በኋላ የወር አበባ ሲመጣባቸው ደክሜበታለሁ ብለው ይቀጥላሉ፡፡ ይሄ አጉል ልፋት ነው፡፡ የወር አበባ ላይ ያለች ሴት በኢጅማዕ ፆም አይፈቀድላትም፡፡ ይልቁንም በዚያው ልክ ቀዷ ታወጣለች፡፡
  4. የተምር ፍሬዎችን በየመስጂዱና ካልሆነ ቦታ መጣል፣
  5.   ከእኩለ ቀን በኋላ መፋቂያ መጠቀም እንደማይፈቀድ ማሰብ፡- በርግጥ ይሄ እሳቤ ቀጥተኛ ማስረጃ ባይኖረውም ከአንዳንድ ታላላቅ ዑለማዎች የተወሰደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በተቃራኒ ከብዙ ዑለማዎች ተዘግቧል፡፡ በዚያ ላይ ነብዩ “ከፆመኛ በላጭ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሲዋክ ነው” ብለዋል፡፡ ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል፡፡ ሶሐብዩ ዓሚር ኢብኑ ረቢዐ ረዲየላሁ ዐንሁ “ነብዩን ፆመኛ ሆነው እጅግ ብዙ ጊዜ ሲዋክ ሲጠቀሙ አይቻለሁ” ብለዋል፡፡ ቲርሚዚ ዘግበውታል፡፡
  6.  የወር አበባ እና የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች “ፆም አልያዝንም” ብለው ከመልካም ስራ መዘናጋታቸው፡- የተከለከሉት ፆምና ሶላት ነው፡፡ ስለዚህ ዚያራ፣ ሶደቃ፣ ባጠቃላይ ሌሎች ኸይር ስራዎችን በመስራት በረመዳን በተለየ የሚገኘውን ምንዳ ለማግኘት ሊጥሩ ይገባል፡፡
  7.  አንዳንድ ሴቶች የወር አበባ ስሜት ስለተሰማቸው ብቻ ደም ሳያዩ ፆማቸውን ማፍረሳቸው፡- የወር አበባ በታወቀ ጊዜ የሚመጣ የታወቀ የደም አይነት ነው፡፡ ኢብኑ ጁረይጅ ረሒመሁላህ ዐጣእን “በወር አበባዋ ቀናት ከደሙ ቀደም ብሎ የምታየው ዳለቻ ወይም ውሃ ፈሳሽ የወር አበባ ነውን?” ብየ ጠየቅኳቸው ይላሉ፡፡ እሳቸውም “በጭራሽ! ደሙን እስከምታይ ድረስ ሶላት እንዳትተው፡፡ ከሶላት ሊያግዳት የሚያስብ ሸይጣን እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡” [ሙሶነፍ ዐብዲርዛቅ፡ 1160]
  8.  መስጂድ ውስጥ ረጅም የውስጥ ሱሪ ሳይለብሱ መተኛት፡- ሃፍረተ ገላ ሲጋለጥ ያጋጥማል፡፡ ይሄ በኢዕቲካፍም ጊዜ ሆነ በሌላ ሰዓት መስጂድ ውስጥ ከሚተኙ ሰዎች ዘንድ በብዛት የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ችግር እንዳያጋጥምና ሌሎችም እንዳይቸጋገሩ ጥንቃቄ ሊኖረን ይገባል፡
  9. አንዳንድ የወለዱ ሴቶች ደም ከቆመም በኋላ አርባ ቀን አልሞላንም ብለው አይፆሙም፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ኢማም አትቲርሚዚ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “የነብዩ ሶሐቦች፣ ታቢዕዮችና ከነሱም በኋላ ያሉ ምሁራን የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች ለአርባ ቀናት እንደማይሰግዱ ተስማምተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የጠራች ካልሆነች በስተቀር፤ በዚህን ጊዜ (ከአርባ በፊት ከጠራች) ታጥባ ትሰግዳለች፡፡” [ጃሚዑ አትቲርሚዚ፡ 1/258]

የፆመኛ ስርኣቶች

  1.  ስክነትና መረጋጋትን መላበስ፣
  2. ጥሩ መአዛ ወይም ጠረን መኖር፣
  3.  የፊት ፈገግታ፣
  4. ትእግስትን፣ ይቅር ባይነትን መላበስ፣ 
  5.  ውብ ገፅታን መላበስ፣
  6.  በቤተሰብም፣ ባጠቃላይ በሰዎችም ላይ ርህሩህ መሆን፣
  7.  ረመዳን በመምጣቱ ደስተኛ መሆንል፣

የፆም ፋይዳዎች፡-

  1. ፆም ተቅዋን ያላብሳል፡፡ የተደነገገውም ለዚሁ ነው፡፡ 
  2.  ፆም አካላዊ ጤንነትን ያጎለብታል፡፡
  3. ፆም ዱንያ ላይ ከጥፋት በአኺራ ደግሞ ከእሳት የሚከላከል ጋሻ ነው፡
  4.  ፆም ትእግስትን ያለማምዳል፡፡
  5.  ፆም ነፍስያን ማሸነፍ ነው፡፡
  6.  ፆም ሸይጧንን ማሸነፍ ነው፡፡
  7.  የረመዳን ፆም ለሙስሊሞች የአንድነት አርማ ነው፡፡ 
  8.  ፆም የአላህን ውዴታ ያስገኛል፡፡
  9.  ፆም የዱዓእ ተቀባይነትን ይጨምራል፡፡
  10.  ፆም ለባለቤቱ ያማልዳል፡፡
  11.  ፆም ወንጀልን ያሳብሳል፡፡
  12. ፆም እዝነትን፣ ርህራሄን፣ የወንድማማችነት ስሜትን፣ አለኝታነትን ያዳብራል፡፡
  13. ፆመኞች ብቻ “ረያን” በተባለው በር ወደ ጀነት ይገባሉ፡፡ 
  14. ፆም ለዱንያ መንሰፍሰፍን፣ ስግብግብነትን፣ ጭካኔን፣ ድርቅናን፣ ኩራትን፣ ክፉ ስሜትን ያዳክማል፡፡
  15. ፆም ለአላህ ሲሉ መስዋእትነት መክፈልን ያለማምዳል፡፡ 
  16.  ፆም ከእሳት ነፃ መውጫ ሰበብ ነው፡፡
  17.  ፆም በይፋም በስውርም ከአላህ ጋር ሙራቀባ እንዲኖረን ያግዛል፡፡
  18. ፆም አማና መሸከምን፣ አደራ መወጣትን፣ … ያለማምዳል፡፡
  19.  ፆም ስነ ምግባርን ያንፃል፡፡
  20. ፆም ለባለቤቱ በቀብር ይከላከላል፡፡
ያ አላሁ! ያ ረሕማኑ! በመልካም ስሞችህ፣ በላቁ መገለጫዎችህ ይሁንብህ! ረመዳንን ፆመው ከእሳት ነፃ ከሚወጡት፣ በረመዳን ከሚጠቀሙት አድርገን፡፡ ኣሚን፡፡ [ከአንዳንድ ኪታቦች የተለቀመ]

@ሙሐመድ አሕመድ  ሙነወር(ኢብኑ ሙነወር)





Post a Comment

0 Comments