በወርሃ ረመዳን በብዛት የሚያጋጥሙ ስህተቶች
1. ከመጠን በላይ መመገብ፡-
ይሄ ችግር በተለይም ረመዳን ላይ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ያለመጠን መመገብ ለብዙ ሸር መንሰኤ ነው፡፡ ሱፍያን አሥሠውሪ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “አካልህ ጤናማ እንዲሆን፣ እንቅልፍህ እንዲቀል ከፈለግክ ምግብህን አቅልል፡፡” ጌታችን እንዲህ ይላል፡-
وَكُلُوا وَاشْرَبُوا وَلَا تُسْرِفُوا ۚ إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُسْرِفِينَ
“ብሉ ጠጡ፡፡ አታባክኑ፡፡” [አልአዕራፍ፡ 31]
ታላቁ ዓሊም ኢብኑ ቀይም አልጀውዚያ ረሒመሁላህ ከዚች አንቀፅ ቀጥለው እንዲህ ይላሉ፡- “ባራገፉት ፋንታ ሰውነታቸውን የሚያቆሙበት ምግብና መጠጥ እንዲያስገቡ ባሮቹን ጠቆማቸው፡፡ መጠኑም አይነቱም አካላቸው በሚጠቀምበት መጠን እንዲሆንም አሳሰባቸው፡፡ ይህንን ባለፈ ጊዜ ብክነት ይሆንበታል፡፡ ሁለቱም ጤናን ጎጅ፣ በሽታን ጎታች ነው፡፡ ማለትም አለመብላትና አለመጠጣት እንዲሁም በምግብና በመጠጥ ድንበር ማለፍ፡፡” [አጥጢቡ አንነበዊ፡ 181]
2. በስህተት የበላ ወይም የጠጣ ሰው ፆሙ ተበላሽቷል በሚል መቀጠል፡፡ በስህተት መመገብም ሆነ መጠጣት በምንም መልኩ ፆምን አያበላሽም፡፡ ነብዩ ﷺ “አንድ ሰው ረስቶ ከበላና ከጠጣ ፆሙን ይቀጥል፡፡ ያበላውና ያጠጣው አላህ ነው” ብለዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
3. የወር አበባ ከመጣ በኋላ ፆምን መቀጠል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ፆም ይዘው ቀኑን ካጋመሱ በኋላ የወር አበባ ሲመጣባቸው ደክሜበታለሁ ብለው ይቀጥላሉ፡፡ ይሄ አጉል ልፋት ነው፡፡ የወር አበባ ላይ ያለች ሴት በኢጅማዕ ፆም አይፈቀድላትም፡፡ ይልቁንም በዚያው ልክ ቀዷ ታወጣለች፡፡
4. የተምር ፍሬዎችን በየመስጂዱና ካልሆነ ቦታ መጣል፣
5. ከእኩለ ቀን በኋላ መፋቂያ መጠቀም እንደማይፈቀድ ማሰብ፡- በርግጥ ይሄ እሳቤ ቀጥተኛ ማስረጃ ባይኖረውም ከአንዳንድ ዑለማዎች የተወሰደ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በተቃራኒ ከብዙ ዑለማዎች ተዘግቧል፡፡ በዚያ ላይ ነብዩ ﷺ “ከፆመኛ በላጭ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሲዋክ ነው” ብለዋል፡፡ ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል፡፡ ሶሐብዩ ዓሚር ኢብኑ ረቢዐ ረዲየላሁ ዐንሁ “ነብዩን ﷺ ፆመኛ ሆነው እጅግ ብዙ ጊዜ ሲዋክ ሲጠቀሙ አይቻለሁ” ብለዋል፡፡ ቲርሚዚ ዘግበውታል፡፡
6. የወር አበባ እና የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች “ፆም አልያዝንም” ብለው ከመልካም ስራ መዘናጋታቸው፡- የተከለከሉት ፆምና ሶላት ነው፡፡ ስለዚህ ዚያራ፣ ሶደቃ፣ ባጠቃላይ ሌሎች ኸይር ስራዎችን በመስራት በረመዳን በተለየ የሚገኘውን ምንዳ ለማግኘት ሊጥሩ ይገባል፡፡
7. አንዳንድ ሴቶች የወር አበባ ስሜት ስለተሰማቸው ብቻ ደም ሳያዩ ፆማቸውን ማፍረሳቸው፡- የወር አበባ በታወቀ ጊዜ የሚመጣ የታወቀ የደም አይነት ነው፡፡ ኢብኑ ጁረይጅ ረሒመሁላህ ዐጣእን “በወር አበባዋ ቀናት ከደሙ ቀደም ብሎ የምታየው ዳለቻ ወይም ውሃ ፈሳሽ የወር አበባ ነውን?” ብየ ጠየቅኳቸው ይላሉ፡፡ እሳቸውም “በጭራሽ! ደሙን እስከምታይ ድረስ ሶላት እንዳትተው፡፡ ከሶላት ሊያግዳት የሚያስብ ሸይጣን እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡” [ሙሶነፍ ዐብዲርዛቅ፡ 1160]
8. መስጂድ ውስጥ ረጅም የውስጥ ሱሪ ሳይለብሱ መተኛት፡- ሃፍረተ ገላ ሲጋለጥ ያጋጥማል፡፡ ይሄ በኢዕቲካፍም ጊዜ ሆነ በሌላ ሰዓት መስጂድ ውስጥ ከሚተኙ ሰዎች ዘንድ በብዛት የሚያጋጥም ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ችግር እንዳያጋጥምና ሌሎችም እንዳይቸጋገሩ ጥንቃቄ ሊኖረን ይገባል፡፡
9. አንዳንድ የወለዱ ሴቶች ደም ከቆመም በኋላ አርባ ቀን አልሞላንም ብለው አይፆሙም፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ኢማም አትቲርሚዚ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “የነብዩ ﷺ ሶሐቦች፣ ታቢዕዮችና ከነሱም በኋላ ያሉ ምሁራን የወሊድ ደም ላይ ያሉ ሴቶች ለአርባ ቀናት እንደማይሰግዱ ተስማምተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የጠራች ካልሆነች በስተቀር፤ በዚህን ጊዜ (ከአርባ በፊት ከጠራች) ታጥባ ትሰግዳለች፡፡” [ጃሚዑ አትቲርሚዚ፡ 1/258]
ከተለያዩ ኪታቦች የተሰበሰበ
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 16/2010)
0 Comments