Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በነገራችን ላይ

በነገራችን ላይ

የፖለቲካው ወሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጨምሯል። ውሸቱም በዚያው ልክ ጨምሯል። እንደጉድ እየተዋሸ ነው። እንደጉድ። መንግስቱ ይዋሻል። ተቃዋሚው ይዋሻል። ከሁለቱም በኩል ጭፍን ደጋፊው ይዋሻል። የሚወዱትን እንከን የለሽ ለማድረግ ይዋሻል። የሚጠሉትን ጭራቅ ለማድረግም ይዋሻል። ሁሉም ቀባብቶ ለማቅረብ የተካኑ ናቸው። ብዙ ወገናችን ደግሞ በቀደዱት የሚፈስ ነው። ካደነቀው ጋር ያደንቃል። ካወገዘው ጋር ያወግዛል። ለምን እንዴት የለም።
ጥላቻን የሚዘሩ የሀሰት አካውንቶች በአንድ በኩል፤ "መልአካቸውን" እንድናወድስ የሚፈለፈሉ ሂሳቦች ደግሞ በሌላ በኩል እንደ ኢኮኖሚያችን በ "11 በመቶ" እያደጉ ነው። ትግሬ ሳይሆን በትግሬ ስም አካውንት ከፍቶ ሌላውን ወገን ይሳደባል። የተሰደበው በጅምላ ትግሬን በመስደብ ላይ ይረባረባል። ያኔ ትግሬውም ይነሳና ሌላ ፅንፍ ይረግጣል። የተንኮሉ ጠንሳሽም አላማው ይሄው ነበር። ኦሮሞ ሳይሆን የኦሮሞ ሂሳብ ከፍቶ በኦሮሞ ስም ሌላውን ያወግዛል። ሌሎችም እንዲሁ። ሙስሊም ሳይሆን በሙስሊም ስም በተከፈተ አካውንት ኢስላማዊ ሽፋን ያላቸው ግን ኢስላምን የሚያስጠቁሩ ስራዎችን የሚለቅ አለ።
ፖለቲከኞች በመሀላቸው ፍጥጫው ሲከር የሚጠሉትን አካል ፀረ ኢስላም አድርገው በማቅረብ እራሳቸውን ተቆርቋሪ አድርገው ያቀርባሉ። አላማቸው ቢችሉ ከጎናቸው ሊያሰልፉን ነው። እሱ ካልሆነ ደግሞ ቢያንስ ወደ ጠላታቸው እንዳንሰለፍ ሊያዞሩን ነው። እኛ ግን የዋሆች ነን። የጮኸ ሁሉ ይወዘውዘናል። ፋታ ሲያገኝ በኛ ላይ የማይዞር የለም። ዱላው ወደኛ ሲዞር ተቃራኒዎቹም ውጥረታቸው ይቀንሳል። ፍጥጫቸው ሲጨምር ሁሉም ሊጠቀምብን ይነሳል። የግፍ ታሪካችንን እየተረከልን ያስለቀሰን ቡድን በሁለት እግሩ ሲቆም "የሚበጃችሁ የእስልምና አይነት ይሄ ነው" እስከሚል ጥግ የደረሰ ድፍረት ገብቶ ደዕዋ ሊያደርግልን ሁሉ ይዳዳዋል።
እየጠቀማቸው ያለው ግን የነሱ ችሎታ አይደለም። ይልቁንም የኛ ሞኝነት ነው። "ሙእሚን ከአንድ ጉድጓድ በወጣ እባብ ሁለቴ አይነደፍም" ወርቃማ መርሀችን ነበር። እኛ ግን በተደጋጋሚ እንነደፋለን። ተረጋግቶ ከማስተዋል ይልቅ በጭፍን እንደግፋለን። በጭፍንም እንቃወማለን። ከኛው ውስጥ የነሱን አሰስ ገሰስ የሚያሰራጭላቸው የዋህ መንጋ ነፍ ነው። እርግጠኛ ያልሆንበትን ሁሉ ከማሰራጨት ብንቆጠብ የስንቱ የፊትና ገበያ በቀዘቀዘ ነበር። ከእንቶ ፈንቶ፣ ከትርኪ ምርኪ መራቅ የጥሩ ሙስሊም መታወቂያው ነው።

Ibnu Munewor

Post a Comment

0 Comments