Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

መሀላን የሚመለከቱ ሸሪዐዊ ህጎች!


መሀላን የሚመለከቱ ሸሪዐዊ ህጎች!
መግቢያ፡- 
መሀላ በህይወታችን በስፋት የሚያጋጥመን ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው ህዝባችን ተያያዥ ነጥቦችን በውል ካለመለየቱ የተነሳ ብዙ ግድፈቶችን ይፈፅማል፡፡ በዚህ ረገድ ጠቃሚ እርምቶችን ይሰጣሉ ያልኳቸውን ነጥቦች ሰብስቤ አስፍሬያለሁ፡፡ ፅሑፉ የማንበብ ልማዳቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች ረጅም ሊባል ይችላል፡፡ ቢሆንም እንደምንም ጥርሳችሁን ነክሳችሁ እንድታነቡት አደራ እላለሁ፡፡ መቼም እኔ ለመፃፍ የፈጀብኝን የሚያክል ጊዜ አይወስድባችሁም፡፡ መልካም ንባብ፡፡
#ክፍል_አንድ ምንነቱ፡- 
መሀላ ማለት አንድን ጉዳይ ለማጠናከር ሲባል በተለየ መልኩ የአላህን ስም ወይም መገለጫ /ሲፋ/ ማውሳት ማለት ነው፡፡ “ወላሂ!”፣ “ተላሂ!”፣ “ቢላሂ”፣ “ወረቢል ከዕባ”፣ ወዘተ በሚሉት መማል ይቻላል፡፡ ታዲያ አንድ ሰው በቀጥታ የአላህን ስም ከምላሱ ባያወጣም “ይህን ላደርግ” ወይም “ላላደርግ ምያለሁ” ወይም “መሀላ አለብኝ” ካለ እንደ መሀላ ነው የሚቆጠረው፡፡ ለማሳጠር ያክል ማስረጃ አልጠቀስኩም፡፡ የፈለገ ሱረቱል ሙናፊቁን ከአንቀፅ 1 – 2፣ ቡኻሪ ሐዲሥ ቁ. 7046 እና ሙስሊም ቁ. 2269 ያሉትን ማስረጃዎች ረጋ ብሎ ያስተውል፡፡
#ክፍል_ሁለት የመሀላ ብይኖች
መሀላ በአምስቱ የሸሪዐ ህግጋት ስር ሊያርፍ ይችላል፡፡
1. አስገዳጅ ሁኔታ ሲያጋጥም መማል ግዴታ ነው፡፡
2. ፋይዳ ኖሮት ሲገኝ መማል የሚወደድ ነው፡፡
3. በተፈቀደ ጉዳይ ላይ እውነት እስከሆነ ድረስ ወይም እውነት ነው የሚለው ግምቱ ካደላ መማል የሚፈቀድ ነው፡፡ ማብዛቱ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አላህ “መሀላዎቻችሁን ጠብቁ” ብሏልና። [አልማኢዳህ፡ 89] የመሀላ መብዛት ለውሸት ያጋልጣል፡፡ የኢማን መሳሳትም ነው፡፡
4. በሸሪዐው በሚጠላ ነገር ላይ መማል የተጠላ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ መጓዙ በሸሪዐው የተጠላ ነው፡፡ ይህን ሊያደርግ ቢምል መሀላው የተጠላ ይሆናል፡፡ በግብይት ላይ መማልም እንዲሁ የተጠላ ነው፡፡
5. እውነትን ለማፍረስ ወይም ሀሰትን ለማንገስ የሚማል ከሆነ መማሉ ሐራም ነው፡፡
ማሳሰቢያ፡- የአእምሮ በሽተኛ፣ እራሱን የሳተ ሰው፣ ህፃን፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ ውስጥ የገባ ሰው፣ ሰካራም፣ ሳያስበው መሀላ ከምላሱ ያመለጠው ሰው፣ የረሳ ሰው እና የተገደደ ሰው መሀላቸው ከቁብም አይገባም፡፡ እንደ መሀላም አይቆጠርም፡፡
#ክፍል_ሶስት የመሀላ አይነቶች፡-
1. የዛዛታ መሀላ፡- ታስቦበት ሳይሆን በወሬ መሀል ሳይሰተዋል የሚወጣ መሀላ ነው፡፡ ይሄ የመሀላ አይነት እንደመሀላ አይቆጠርም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
لَا يُؤَاخِذُكُمُ اللَّهُ بِاللَّغْوِ فِي أَيْمَانِكُمْ
“አላህ በመሀላዎቻችሁ በውድቁ አይዛችሁም፡፡” [አልማኢዳህ፡ 89]
2. በውል የተቋጠረ መሀላ፡- ታስቦበት የሚወጣ የመሀላ አይነት ነው፡፡ “ወላሂ! ይህን ላደርግ፣ ወይም ላላደርግ” በሚል መልኩ፣ ባለፈ ሳይሆን ወደ ፊት ባለ ነገር ላይ፣ በማይታሰብ ሳይሆን መሆን በሚችል ጉዳይ ላይ ታስቦ የወጣ መሀላ ሲሆን ሰውየው መሀላውን ካልጠበቀ ማካካሻ (ከፋራ) ይጠብቀዋል፡፡
3. የሀሰት መሀላ፡- የሰዎችን ሐቅ ለመብላት ወይም ለማታለልና ለማጭበርበር ወይም ለሌላም አላማ ቢሆን ሆን ተብሎ በውሸት ላይ የሚፈፀም መሀላ ነው፡፡ ይሄ ዛሬ በንግዱ እና በሌሎችም ማህበራዊ ህይወቶች ውስጥ የተንሰራፋ ጥፋት ነው፡፡ ሆን ብሎ በሀሰት እየማለ የሚሸጥ የሚለውጠው ዛሬ ቀላል አይደለም፡፡ ጌታችን አላህ በዚህ ላይ ምን አይነት ከባድ መልእክት እንዳስተላለፈ እንመልከት፡-
إِنَّ الَّذِينَ يَشْتَرُونَ بِعَهْدِ اللَّهِ وَأَيْمَانِهِمْ ثَمَنًا قَلِيلًا أُولَئِكَ لَا خَلَاقَ لَهُمْ فِي الْآخِرَةِ وَلَا يُكَلِّمُهُمُ اللَّهُ وَلَا يَنْظُرُ إِلَيْهِمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ وَلَا يُزَكِّيهِمْ وَلَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ
“እነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን እና በመሀላዎቻቸው ጥቂትን ጥቅምን የሚለውጡ በመጨረሻይቱ አለም ምንም እጣ የላቸውም፡፡ በቂያማ ቀንም አላህ አያነጋግራቸውም፤ ወደነሱም አይመለከትም፤ አያጠራቸውም፡፡ ለነሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡” [አሊ ዒምራን፡ 77]
ጥፋቱ ከከባኢር ማለትም ከትልልቅ ወንጀሎች ውስጥ የሚመደብ እንደሆነ ሲገልፁ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “በአላህ ማጋራት፣ ወላጆችን ሐቃቸውን መጣስ፣ ነፍስን ማጥፋት እና የቅጥፈት መሀላ ታላላቅ ወንጀሎች ናቸው፡፡” [ቡኻሪ]
የሀሰት መሀላ ከባድ ወንጀል ከመሆኑ የተነሳ ማካካሻ አልተደረገለትም፡፡ ይሄ የብዙሃን ዑለማእ እይታ ነው፡፡ ይህን የፈፀመ ሰው ያለው ምርጫ የወሰደው ሐቅ ካለ መልሶ፣ የፈፀመው በደል ካለ አስተካክሎ ትክክለኛ ተውበት ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ፡- “አምስት ጥፋቶች ማካካሻ የላቸውም፡፡ በአላህ ማጋራት፤ ያለ አግባብ ነፍስን ማጥፋት ሙእሚንን መዝረፍ፣ በጂሃድ ላይ በፍጥጫ ሰዓት መሸሽ እና ያለ አግባብ ገንዘብ የሚበላበት ሀሰተኛ መሀላ!!” [አልኢርዋእ፡ 2564] ኢማሙ ማሊክ ረሒመሁላህ “ሆን ተብሎ የሚፈፀም የሀሰት መሀላ ማካካሻ ቅጣቶች ከሚያብሱት በላይ ነው” ብለዋል፡፡ [አልሙደወናህ፡ 1/577]
#ክፍል_አራት የመሀላ ማካካሻ /ከፋራህ/
አንድ ሰው የሆነን ጉዳይ ሊፈፅም ከማለ በኋላ ቃሉን ቢያፈርስ ወንጀለኛ እንዳይሆን የሚያመልጥበትን ቀዳዳ አላህ አመቻችቶለታል፡፡ ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ፡- “በአንድ ጉዳይ ላይ የማለ ሰው ከማለበት ጉዳይ የተሻለ ነገር ከታየው ይፈፅመው፡፡ ከዚያም መሀላውን ያካክስ፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም] ማካካሻውን አስመልክቶ አላህ እንዲህ ይላል፡-
فَكَفَّارَتُهُ إِطْعَامُ عَشَرَةِ مَسَاكِينَ مِنْ أَوْسَطِ مَا تُطْعِمُونَ أَهْلِيكُمْ أَوْ كِسْوَتُهُمْ أَوْ تَحْرِيرُ رَقَبَةٍ فَمَنْ لَمْ يَجِدْ فَصِيَامُ ثَلَاثَةِ أَيَّامٍ ذَلِكَ كَفَّارَةُ أَيْمَانِكُمْ إِذَا حَلَفْتُمْ
“ማበሻውም ቤተሰቦቻችሁን ከምትመግቡት ከመካከለኛው (ምግብ) አስር ምስኪኖችን ማብላት ወይም እነሱነ ማልበስ ወይም ጫንቃን (ባሪያን) ነፃ ማውጣት ነው፡፡ (እነዚህን) ያላገኘም ሰው ሶስት ቀናትን መፆም ነው፡፡ ይህ በማላችሁ ጊዜ የመሀላችሁ ማካካሻ ነው፡፡” [አልማኢዳህ፡ 89]
ስለዚህ ማካካሻዎቹ፡-
1ኛ፡- አስር ምስኪኖችን ቤተሰቡን ከሚመግበው መካከለኛ የምግብ አይነት የአንድ ወቅት ምግብ ማብላት፣
2ኛ፡- አስር ምስኪኖችን ሶላት የሚያሰግድ ልብስ ማልበስ፣
3ኛ፡- ሙእሚን ባሪያ ነፃ ማውጣት
ከነዚህ ማካካሻዎች ውስጥ ቅደም ተከተል ሳይጠብቅ የቀለለውን መርጦ መፈፀም ይችላል፡፡ እነዚህን ካልቻለ ግን፡-
4ኛ፡- ሶስት ቀን መፆም አለበት፡፡ ከ 1 – 3 ካሉት ውስጥ መፈፀም የሚችል ሰው ዘሎ ወደ ፆም መግባት አይችልም፡፡
ማሳሰቢያ 1፡- የመጀመሪያዎቹን ምርጫዎች ባለመቻሉ ፆም የመረጠ ሰው አከታትሎ የመፆም ግዴታ የለበትም፡፡
ማሳሰቢያ 2፡- ከፋራ ወይም ማካካሻ የሚመለከተው መሀላ፡-
1. ወደ ፊት ባለና ሊሆን በሚችል ጉዳይ ላይ ከተማለ ነው፡፡ ባለፈ ወይም ፈፅሞ ሊሆን በማይታሰብ ጉዳይ ላይ የማለ ሰው ከፋራ አይመለከተውም፡፡
2. መሀላው በአላህ ወይም በስሞቹ ወይም በሲፋዎቹ ከሆነ ነው፡፡ በፍጡር የተማለ መሀላ ወንጀል ስለሆነ ማካካሻ ሳይሆን ተውበት ነው የሚያስፈልገው፡፡
3. ተገዶ ሳይሆን በምርጫው የማለው መሀላ ከሆነ ነው፡፡
4. በቃሉ ሳይገኝ መሀላውን ካፈረሰ ነው፡፡
ማሳሰቢያ 3፡- አንድ ሰው በሚምል ሰዓት “ኢንሻአላህ” የሚል ቃል አብሮ ካወጣ መሀላውን ቢያፈርስም ማካካሻ መፈፀም አይጠበቅበትም፡፡ [ሶሒሑ አትቲርሚዚ፡ 1237]
ማሳሰቢያ 4፡- አንድ ሰው ሌላውን “ወላሂ እንዲህ ልታደርግ” ብሎ ቢምልና ያኛው ሰውየ ሳያደርግ ከቀረ የማለውን ሰው ከፋራ ይመለከተዋል፡፡ ነገር ግን ሰውየውን ለማስገደድ ሳይሆን ለማክበር ብሎ ከሆነ ያደረገው ከፋራ ግዴታ አይሆንበትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን አቡበክር ረዲየላሁ ዐንሁ ዘንድ ሁለት እንግዶች መጥተው ምግብ ሲያቀርቡላቸው “አንተም ብላ” አሉ ለአቡበክር፡፡ “ወላሂ እኔ አልበላም” አሉ እሳቸው፡፡ እንግዶቹም “ወላሂ እኛም አንበላም” አሉ፡፡ ሁሉም ሲምሉ ጊዜ አቡበክር “ይሄ ከሸይጧን ነው” በማለት በሉ፡፡ እንግዶቹም በሉ፡፡ ነብዩ ﷺ ሲነገራቸው አቡበክርን “አንተ ከሁሉም መልካም የሰራና በላጭ ነህ” በማለት ከማሞገስ ውጭ ከፋራ እንደሚመለከታቸው አልነገሯቸውም፡፡ [ሙስሊም፡ 2057]
ማሳሰቢያ 5፡- አንድ ሰው ሌላውን “ወላሂ እንዲህ ልታደርግ ወይም ላታደርግ” ብሎ ቢምል ከሰውየው ጋር እልህ ከመጋባት ይልቅ በመሀላው እንዳይጠየቅ ብንተባበር መልካም ነው፡፡
ማሳሰቢያ 6፡- መሀላን ማፍረስ የተለያየ ብይን አለው፡፡
1. ዋጂብ የሆነ ማፍረስ፡- ወንጀል ሊፈፅም የማለ ሰው መሀላውን ማፍረሱ ግዴታው ነው፡፡
2. ሐራም የሆነ ማፍረስ፡- የማለው ያለበትን ግዴታ ለመፈፀም ወይም ከሐራም ለመራቅ ከሆነ ቃሉን ማፍረሱ ሐራም ነው፡፡
3. ምርጫ ያለው ማፍረስ፡- በሸሪዐው የተፈቀደን ወይም ግዴታ ያልሆነን ነገር ለመስራት ወይም ለመተው ቢምል ፍላጎቱ ከሆነ መሀላውን የማፍረስ ምርጫ አለው፡፡
በሶስቱም ሁኔታዎች መሀላውን ያፈረሰ ሰው ማካካሻ ወይም ከፋራ መፈፀም ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እያወቀ፣ በምርጫው እና እያስታወሰ መሀላውን ካፈረሰ ነው፡፡ እንጂ ባለማወቅ ወይም ተገዶ ወይም ረስቶ መሀላውን የሚፃረር ነገር ቢፈፅም ማካካሻ የመፈፀም ግዴታ የለበትም፡፡
ማሳሰቢያ 7፡- አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ ለምሳሌ “ወላሂ ይህን ላልሰራ” እያለ ደጋግሞ ቢምል የሚመለከተው ከፋራ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
#ክፍል_አምስት በምንድን ነው የሚማለው?
ሰዎች እንደ እምነታቸው በፈጣሪ፣ በደጋጎች፣ በወላጆች፣ በነብያት፣ በመላእክት፣ በመቃብር፣ ወዘተ ሲምሉ ያጋጥማሉ፡፡ በሃይማኖታችን ግን ከአላህ ውጭ ባሉ አካላት መማል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “በአባቶቻችሁ፤ በእናቶቻችሁና ያለአግባብ ሰዎች ለአላህ ብጤዎች ወይም አቻዎች አድርገው በሚይዟቸው ነገሮች አትማሉ። በአላህ እንጂ አትማሉ። እውነተኞች ሆናችሁ እንጂ አትማሉ፡፡” “ከአላህ ሌላ ባለ ነገር የሚማል መሀላ ሁሉ ሺርክ ነው፡፡” “ከአላህ ሌላ ባለ የማለ በርግጥም ክዷል ወይም አጋርቷል፡፡” “አንዳችሁ በመሲሕ (በዒሳ) ቢምል አደጋ ላይ ወድቋል። መሲሕ ግን ከአባቶቻችሁ የበለጠ ነው፡፡” [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 7249] [አስሶሒሐህ፡ 2042] [ኢርዋእ፡ 2561] [ሙሶነፍ ኢብን አቢ ሸይባህ፡ 12278]
ዐብዱላህ ኢብን መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ይላሉ፡- “እውነት ተናግሬ ከአላህ ሌላ ባለ ከምምል ውሸት ተናግሬ በአላህ ብምል እመርጣለሁ” ይላሉ። [ኢርዋእ፡ 2562] ይህ አነጋገር በፍጡር መማል ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
ማሳሰቢያ፡- አንዳንዴ “እንዲህ ካደረግኩኝ እኔ ክርስቲያን ነኝ!” ወይም “ሙስሊም አይደለሁም” እያለ የሚምል ሰው ያጋጥማል። ይሄ እጅግ አደገኛ የሆነ ጥፋት ነው፡፡ ነብዩ ﷺ “ከኢስላም ውጭ ባለ ሃይማኖት መሀላ የማለ ሰው እንዳለው ሆኗል (ከኢስላም ወጥቷል)!” ብለዋል። [ቡኻሪ፡ 1363፣ ሙስሊም፡ 315]
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 01/2010

Post a Comment

0 Comments