Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ውሸት በኢስላምና ትንሽ ስለ ‹ April the fool ›

ውሸት በኢስላምና ትንሽ ስለ ‹ April the fool ›


الكذب في الاسلام ومقال عن ما يسمى ' بكذبة أبريل '


ምስጋና ለአሏህ ይገባው፤ እናመሰግነዋለን በእርሱም እንታገዛለን፤ ምህረትንም እንለምነዋለን፡፡ ከነፍሶቻችን እኩይ ከስራዎቻችንም ክፋት በአሏህ እንጠበቃለን፡፡ አሏህ ያቀናውን ሰው ለእርሱ ምንም አጥማሚ የለውም፤ እርሱ ያጠመመውንም ለእርሱ ቅኑን የሚመራው የለም፤ የአሏህ ሰላትና ሰላም በመልእክተኛው በሙሀመድ ላይ ይስፈን፤

በመቀጠል፡-
ውሸት ከመጥፎ ባህሪዎች ስለመመደቡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከእርሱ ለማስጠንቀቅም ሀይማኖታዊ ድንጋጌዎች መጥተዋል፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮም በዚሁ ላይ ተስማምቷል፤ በዚህም ንጹህ አዕምሮ ያላቸው ሰዎችና በማህበረሰቡ ያሉ መልካም እሴቶችን የሚያከብሩ ሰዎች ሁሉ ይሰብካሉ፡፡
እውነት ለዚህ አለም መኖር አንዱ ማእዘን ነው፤ እጅግ ምስጉን ናቸው ከሚባሉ ባህሪያት ግንባር ቀደሙ ሲሆን፤ የነብያት መለያ፤ የተቅዋ (አሏህ የመፍራት) ፍሬ ነው፡፡ እውነት ባይኖር የሸሪዓ ህግጋት ውድቅ በሆኑ ነበር፡፡ በውሸተኝነት ወይም በሀሰት ባህሪ መገለፅ ከሰብዓዊነት መውጣት ነው፡፡

ቀጥተኛ የሆነው እምነታችን በቁርዓንና በሱና ውሸትን በማስጠንቀቅ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እናገኛለን፡፡ እርምና ክልክል በመሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለውሸታም ሰው በዚህች ቅርቢቱ አለምም ይሁን በመጨረሻው አለም ምስጉን ያልሆነ ፍጻሜ እንዳለው ሁሉም ሰው መገንዘብ ይኖርበታል፡፡

በሸሪዓችን ውሸት የተፈቀደ መሆኑን የሚያመላክቱ ውስን ሁኔታዎች የመጣ ሲሆን እነርሱም በውሸቱ ምክንያት የሰውን መብት (ሀቅ) መብላትን የማያስከትል፣ ደምን ለማፍሰስ ምክንያት የማይሆንና እንዲሁም ክብርን የማያጎድፉ ለሆኑና መሰል ጉዳዮች ነው፡፡ ሆኖም እነዚህም የተፈቀዱ ቦታዎች ነፍስን ለማዳን፣ በሁለት ሰዎች መካከል ያለን ጸብ ወይም አለመግባባት ለማስተካከል እና በባልና ሚስት መካከል ፍቅርን ለማስፈን ሊሆን ይገባል፡፡

በሸሪዓ በምንም መልኩ አንድ ሰው እንደፈለገ የፈለገውን በውሸት ማውራት ይችላል የሚል ድንጋጌ የለም፡፡ ይህ ሆኖ እያለ በዘመናችን በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ በስፋት ከተሰራጩ አስነዋሪ ባህል ወይም ተግባር ውስጥ ‹ April the fool › በመባል የሚታወቅና ይህም በፈረንጆቹ የሚያዚያ ወር (4ኛ ወር) የመጀመሪያው ዕለት ያለምንም ገደብ መዋሸት ይቻላል ተብሎ የሚነገረው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እጅግ ብዙ የሆኑ የሸሪዓን ህግ መተላለፍና ማህበረሰባዊ ቀውሶችን ሲያስከትል ተመልክተናል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቱን ለመጥቀስ ያክል፡-

1- ውሸት እርም(የተከለከለ) ተግባር ነው
አሏህ (ሱ.ወ.) እንዲህ ይላል፡- 

(إِنَّمَا يَفْتَرِي الْكَذِبَ الَّذِينَ لَا يُؤْمِنُونَ بِآيَاتِ اللَّهِ ۖ وَأُولَٰئِكَ هُمُ الْكَاذِبُونَ)

[Surat An-Nahl 105]
" ውሸትን የሚቀጣጥፉት እነዚያ በአላህ አንቀጾች የማያምኑት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚያም ውሸታሞቹ እነሱ ብቻ ናቸው፡፡" ሱረቱ አልነህል-105

ኢብኑ ከሲር አላህ ይዘንለትና እንዲህ ይላል፡- ‹ ከዚያም አላህ ጥራት የተገባ መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ውሸታምም ቀጣፊም አለመሆናቸውን ተናገረ፤ ምክንያቱም በአሏህና በመልክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉት እነዚያ እኩይ ሰዎች እነርሱም በአሏህ አንቀጾችና ታአምራቶች የማያምኑት ከሀዲዎችና ከሰዎች ዘንድ በእብለት የሚታወቁት ጠማማዎች ናቸው፡፡ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሰዎች እውነተኛው፤ በጎ ሰሪያቸው፤ ከእውቀት፣ ከተግባር፤ ከእምነትና ከየቂን (እርግጠኛ ጥርጥር የሌለበት እምነት) በኩል ምሉዕ ናቸው፡፡ማንም ሊጠራጠረው በማይችለው መልኩ በእውነተኝነት የታወቁና መጠሪያቸውም ‹‹ ታማኙ ሙሐመድ›› የሚል ነበር፡፡

ለዚህም ነበር ሂረቅል -የሮማ ንጉስ- አባ ሱፍያንን (አላህ ስራውን ይውደድለት) ስለ መልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ባህሪ በሚጠይቅበት ጊዜ ከጥያቄዎቹ መካከል ፡- “ይህንን ነገር (ነብይ ነኝ ብሎ) ከመናገሩ በፊት በውሸት ትጠረጥሩት ነበርን?” የሚል ነበር፤ አባ ሱፍያንም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፡- ‹በፍፁም› ሂረቅልም እንዲህ ሲል ቀጠለ፡- “በሰዎች መካከል ውሸትን ተከልክሎ በፍጹም በአሏህ ላይ የሚዋሽ ሊሆን አይችልም፡፡” ተፍሲር ኢብኑ ከሲር

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ قَالَ: ((آيَةُ الْمُنَافِقِ ثَلاَثٌ إِذَا حَدَّثَ كَذَبَ وَإِذَا وَعَدَ أَخْلَفَ وَإِذَا ائْتُمِنَ خَانَ)). بخاري ومسلم

ከአባ ሁረይራ (አላህ ስራን ይውደድለት) ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ይዞ በተላለፈ ሀዲስ እነዲህ አሉ፡- “የሙናፊቅ መለያዎች ሦስት ናቸው፡- ሲናገር ይዋሻል፤ ቃል ሲገባ ያፈርሳል፤ ሲታመን ይከዳል” ቡኻሪና ሙስሊም

2- ከውሸትም የከፋው - በአሏህና በመልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ መዋሸት፡
ይህም ከውሸቶች ሁሉ የከፋውና ይህንን ድርጊት የሚፈጽምም ለትልቅ ዛቻ የተዳረገ ነው፡፡ አሏህ አዘ ወጀል እንዲህ ይላል፡-

(وَلَا تَقُولُوا لِمَا تَصِفُ أَلْسِنَتُكُمُ الْكَذِبَ هَٰذَا حَلَالٌ وَهَٰذَا حَرَامٌ لِتَفْتَرُوا عَلَى اللَّهِ الْكَذِبَ ۚ إِنَّ الَّذِينَ يَفْتَرُونَ عَلَى اللَّهِ الْكَذِبَ لَا يُفْلِحُونَ)
[Surat An-Nahl 116]

"በአላህም ላይ ውሸትን ልትቀጣጥፉ ምላሶቻችሁ በሚመጥኑት ውሸት «ይህ የተፈቀደ ነው፤ ይህም እርም ነው» አትበሉ፡፡ እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ አይድኑም፡፡"[Surat An-Nahl 116]

سَمِعْتُ عَلِيًّا يَقُولُ: قَالَ النَّبِيُّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ((لاَ تَكْذِبُوا عَلَيَّ، فَإِنَّهُ مَنْ كَذَبَ عَلَيَّ فَلْيَلِجِ النَّارَ)). بخاري

ከአልይ (አሏህ ስራውን ይውደድለት) በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ ይላል፡- “በእኔ ላይ አትዋሹ፤ እነሆ በእኔ ላይ የሚዋሽ ሰው እሳት ይግባ” ቡኻሪ ዘግቦታል

عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ((مَنْ كَذَبَ عَلَيَّ مُتَعَمِّدًا فَلْيَتَبَوَّأْ مَقْعَدَهُ مِنَ النَّارِ)). مسلم

ከአቢ ሁረይራ (አላህ ስራን ይውደድለት) በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ይላሉ፡- “በእኔ ላይ የዋሸ ሰው መቀመጫውን ከእሳት ያዘጋጅ” ሙስሊም 

3- እንዲሁም በፍጡራን ላይ ከሚፈጸሙ ውሸቶች መካከል፡-
- በግብይት ግዜ የሚፈጸም ውሸት:- ለዚህም 

عَنْ أَبِي ذَرٍّ عَنِ النَّبِيِّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ قَالَ: ((ثَلاَثَةٌ لاَ يُكَلِّمُهُمُ اللَّهُ يَوْمَ الْقِيَامَةِ وَلاَ يَنْظُرُ إِلَيْهِمْ وَلاَ يُزَكِّيهِمْ وَلَهُمْ عَذَابٌ أَلِيمٌ)) قَالَ فَقَرَأَهَا رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ثَلاَثَ مِرَارٍ. قَالَ أَبُو ذَرٍّ خَابُوا وَخَسِرُوا مَنْ هُمْ يَا رَسُولَ اللَّهِ قَالَ: ((الْمُسْبِلُ وَالْمَنَّانُ وَالْمُنَفِّقُ سِلْعَتَهُ بِالْحَلِفِ الْكَاذِبِ)). مسلم

ከአባ ዘር (አላህ ስራውን ይውደድለት) በተወራ ሀዲስ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ይላሉ፡- “ሦስት ሰዎችን በትንሳዔ ቀን አሏህ አያናግራቸውም፤ ወደ እነርሱም አይመለከትም፤ ከወንጀልም አያጠራቸውም፤ እንዲሁም ለእነርሱ አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡ አቡዘር እንዲህ አለ የአሏህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሶስት ግዜ ደጋግመው አነበቧት፤ ከዚያም አቡዘር ፡- ‹አፈሩ፣ ከሰሩ፤ አንቱ የአላህ መልእክተኛ እነማን ናቸው ግለጹልን› አለ፡፡ ነብዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ፡ ‹ልበሱን የሚያስረዝም፣ (በምጽዋት) የሚመጻደቅ እና ሸቀጡን በውሸት እየማለ የሚዋድድ› አሉ” ሙስሊም ዘግቦታል 

- በህልምና መናም ስም የሚዋሽ ውሸት:- 
- ማንኛውንም የሚሰማውን ነገር ማውራት:- 

عَنْ حَفْصِ بْنِ عَاصِمٍ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ((كَفَى بِالْمَرْءِ كَذِبًا أَنْ يُحَدِّثَ بِكُلِّ مَا سَمِعَ)). مسلم

ከሀፍስ ኢበኑ አሲም በተወራ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፡- “ለአንድ ሰው ከውሸት (ውሸታም ለመባል) በቂው ነው የሚሰማውን ሁሉ ማውራቱ” ሙስሊም ዘግቦታል

- ለቀልድ ብሎ መዋሸት:- ይህንን በተመለከተ ከኢብኑ ኡመር (አሏህ ስራቸውን ይውደድላቸው) በተወራ የአሏህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ይላሉ፡- “እኔ እቀልዳለሁ፤ እውነትን እንጅ አልናገርም” ጦበራኒ ዘግቦታል፣ ሸይኽ አልባኒ አላህ ይዘንላቸው በሶሂህ አልጃሚእ ሶሂህ ብለውታል

- ህጻናትን ለማጫወት በሚል መዋሸት:- ከአቢ ሁረይራ በተወራ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ይላሉ፡- “ለህጻን ልጅ ና ልስጥህ ብሎ ከዚያም ያልሰጠው እርሷ ውሸት ናት” አቡ ዳውድ ዘግቦታል፣ ሀዲሱን ሸይኽ አልባኒ አላህ ይዘንላቸው በሶሂህ አልጃሚእ ሶሂህ ብለውታል

- ለማሳቅ በሎ መዋሸት:- ከሙአውያህ ኢብኑ ሀይዳህ በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ ይላል፡- “በሆነ ወሬ ሰዎችን ለማሳቅ ብሎ በውሸት የሚያወራ ሰው ወዮለት፣ ለእርሱ ወይል (የጀሀነም ሸለቆ ነው ተብሏል) አለው፣ ለእርሱ ወይል አለለት” ቱርሚዚ ዘግቦታል፤ ሀዲሱንም ሀሰን ብሎታል፣ 

4- የውሸት ፍጻሜ
ውሸታም ሰው በዱንያ አጥፊ የሆነ ፍጻሜ ሲኖረው በመጨረሻው አለምም አሳፋሪ አዋራጅ ፍጻሜ አለው፡፡ ከእነዚህም ለአብነት ለመጥቀስ ያክል፡-
- በልብ ላይ ንፍቅናን መላበስ:- አላህ ሱብሀነሁ ወተአላ እንዲህ ይላል፡-

(فَأَعْقَبَهُمْ نِفَاقًا فِي قُلُوبِهِمْ إِلَىٰ يَوْمِ يَلْقَوْنَهُ بِمَا أَخْلَفُوا اللَّهَ مَا وَعَدُوهُ وَبِمَا كَانُوا يَكْذِبُونَ)
[Surat At-Tawbah 77]

" አላህንም ቃል የገቡለትን በማፍረሳቸውና ይዋሹትም በነበሩት ምክንያት እስከሚገናኙት ቀን ድረስ ንፍቅናን አስከተላቸው፡፡ " [Surat At-Tawbah 77]

- ወደ አመጽ ብሎም ወደ እሳት ይመራዋል:-

عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ مَسْعُودٍ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ((إِنَّ الصِّدْقَ بِرٌّ وَإِنَّ الْبِرَّ يَهْدِي إِلَى الْجَنَّةِ وَإِنَّ الْعَبْدَ لَيَتَحَرَّى الصِّدْقَ حَتَّى يُكْتَبَ عِنْدَ اللَّهِ صِدِّيقًا وَإِنَّ الْكَذِبَ فُجُورٌ وَإِنَّ الْفُجُورَ يَهْدِي إِلَى النَّارِ وَإِنَّ الْعَبْدَ لَيَتَحَرَّى الْكَذِبَ حَتَّى يُكْتَبَ كَذَّابًا)). مسلم

ከአብደላህ ኢብኑ መስኡድ (አላህ ስራውን ይውደድለት) በተላለፈ ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ፡- “እውነት በጎ መልካም ተግባር ነው፤ መልካም ተግባር ወደ ጀነት ይመረራል፤ አንድ ባሪያ እውነትን ይጠብቃል (ያዘወትራል) ከአላህ ዘንድ እውነተኛ ተብሎ እስኪጻፍ፤ ውሸት ደግሞ አመጽ እኩይ ተግባር ነው፤ አመጽ በእርግጥ ወደ ጀሀነም ይመራል፤ አንድ ባሪያ ውሸትን ያዘወትራል ከአላህ ዘንድ ውሸታም ተብሎ እስኪጻፍ” ሙስሊም

- ምስክርነቱ ውድቅ ይደረጋል:- ኢብኑል አልቀይም በ‹አዕላም አልሙወቂእን› መጽሀፉ እንዲህ ይላል፡- “ምስክርነትን፣ ፈታዋን እና የሀዲስ ዘገባን ከሚመልሱ (ከሚከለክሉ) በጣም የበረታው ውሸት ነው፡፡..……… ዋሾ የሆነች ምላስ ምንም ጥቅም እንደሌለው የአካል ክፍል ነች፤ አንዲያም ከዚያ የባሰች እንጅ፤ በሰው ልጅ ላይ ካለ መጥፎ ነገር ዋሾ ምላስ ዋናዋ ነች” አእላም አልሙወቂኢን
በዱንያም በአኼራም ፊትን ያጠቁራል፤ አላህ ሱብሀነሁ ወተአላ እንዲህ ይላል፡- 

(وَيَوْمَ الْقِيَامَةِ تَرَى الَّذِينَ كَذَبُوا عَلَى اللَّهِ وُجُوهُهُمْ مُسْوَدَّةٌ ۚ أَلَيْسَ فِي جَهَنَّمَ مَثْوًى لِلْمُتَكَبِّرِينَ) [Surat Az-Zumar 60]

" በትንሣኤ ቀንም እነዚያን በአላህ ላይ የዋሹትን ፊቶቻቸው የጠቆሩ ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ በገሀነም ውስጥ ለትዕቢተኞች መኖሪያ የለምን? "[Surat Az-Zumar 60]

- ውሸትን በሚመለከት የሰለፎች ንግግር:-
* አብደላህ ኢብኑ መስኡድ እንዲህ ይላል፡- “አንድ ሰው እውነትን ይናገራል፤ እውነትን ያዘወትራል፤ በልቡ ውስጥ የመርፌ ማስቀመጫ ቦታ እስከማይኖረው ድረስ፤ እንዲሁም አንድ ሰው ውሸትን ይናገራል፤ ውሸትን ያዘወትራል በልቡ ውስጥ የመርፌ ማስቀመጫ ቦታ እስከማይኖረው ድረስ” አንዲሁም በሌላ ንግግሩ “ ውሸት በምርም ይሁን በቀልድ ተገቢ አይደለም” ከዚያም የሚከተለውን የአላህን ቃል አነበበ ፡- 

(يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَكُونُوا مَعَ الصَّادِقِينَ) [Surat At-Tawbah 119]

"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ፡፡ " [Surat At-Tawbah 119]
* አቡ በክር አሲዲቅ እንዲህ ይላል፡- “አደራችሁን ውሸትን ተጠንቀቁ፤ እነሆ እርሱ ከእምነት ያርቃልና”
* ኡመርም (አላህ ስራን ይውደድለት) እንዲህ ይላል ፡- “የእምነት(ኢማን) እርግጧን አትደርስም ውሸትን ለቀልድም ቢሆን እስካልተውክ ድረስ”
ሙሰነፍ ኢብኑ አቢ ሸይባህ (5/235፣236) 

5- የተፈቀደ የሆነ ውሸት
ስለውሸት ክልክልነት በጥቅሉ ከላይ ለምሳሌ ያክል ከጠቃቀስኩ፣ ከዚህ በተለየ መልኩ በሸሪአው ሊፈቀዱ የሚችሉባቸው ምክንያቶችና ሁኔታዎች በአጭሩ በሶስት ሁኔታዎች ብቻ ይሆናል፡፡ እነርሱም፡- በጦርነት ጊዜ፣ በሁለት ጠላቶች መካከል ለማስማማት እና ባል ለሚስቱ ላይ ወይም በተቃራኒው ጸብ ላለመፍጠርና ሰላም ለማስፈን ወይም አስታራቂዎች ለማስማማት የሚሉት ናቸው፡፡ 
ከአስማእ ቢንት የዚድ (አላህ ስራዋን ይውደድላት) የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ አሉ ትላለች፡- “ውሸት በሶስት ቦታዎች እንጅ አይፈቀድም፡- አንድ ሰው ሚስቱን ለማስደሰት ብሎ ቢናገር፤ በጦርነት መዋሸት እና በሰዎች መካከል ለማስማማት መዋሸት” ቱርሚዚ ዘግቦታል፤ ሸይኽ አልባኒ ሀሰን ብሎታል።

6- ዋናውና ነጥባችን የሆነውና የ “April the fool” ውሸት
ይህንን 'የውሸት እለት' በሚመለከት ምንም ትክክለኛ መነሻ መሰረቱን ማግኘት የሚከብድና የተለያዩ የአመለካከት ልዩነቶች መኖራቸውን ማስረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ሆኖም ምንም የተለያዩ አመለካከቶች ስለአመጣጡ ቢተርኩም ለእኛ በጉዳዩ ላይ የሸሪዓዊ ድንጋጌ እይታ ወይም ብይን የሚያሳስበንን ያክል ታሪካዊ አመጣጡ አንገብጋቢ አይሆንም፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ግን በመጀመሪያው ምርጥ የኢስላም ዘመን የሌለና ምንጩ ከኢስላም ያልሆነ ብሎም ከጠላቶች የመጣና ይልቁንም እስልምና እውነትን ለማንገስና ውሸትን ለመጣል የመጣ እምነት መሆኑን ነው፡፡
በዚህ “April the fool” ውሸት ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ: – ስንትና ስንት አለ የልጁን፣ ወይ የሚስቱን አሊያም የሚወደውን ሰው መሞት ተነገሮት ድንጋጤን መቋቋም አቅቶት ለህልፈት የተዳረገ፤ አንዲሁም ስንቱ ነው ከስራ ተባረሀል፣ እሳት አደጋ ተከስቷል፣ ወይም ቤተሰቦችህ ላይ የመኪና አደጋ ደርሷል ተብሎ በውሸት በድንጋጤ ሽባ፣ ስትሮክ ወይም መሰል ከባባድ በሽታዎች ላይ የወደቀው፡፡
አንዳንዱ ሚስትህ ወንድ ጋር ታየች በሚል ውሸት ስንቷ ሚስኪን ለፍች ወይም ለግድያ ተዳርጋለች፡፡
እነዚህንና ይህን መሰል ማለቂያ የሌላቸው መቅሰፍቶች፣ አደጋዎች ደርሰዋል፤ ይህም የሚሆነው ሀይማኖትም ሆነ ንፁህ አዕምሮ በሚከለክለውና በሚቃወመው ውሸት ምክንያት መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝናል፡፡
በእርግጥ እስልምናችን እንዴት ውሸትን ለቀልድም ቢሆን እርም እንዳደረገው ከላይ አይተናል፡፡ አዎ እምነታችን ውሸትን ሰዎች በተለይ ሙስሊሞች በምርም ይሁን በቀልድ በንግግርም ይሁን በተግባር ውሸትን ሊርቁትና ሊጸየፉት እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡
ምክንያቱም ይህ የአሏህ (ጥራት የተገባው) ህግ ነው፤ በእርሱም ውስጥ ሰዎችን ወደ መልካም የሚመራና ለሰዎች መስተካከል ትኩረት የሚሰጡ ጥበቦችን በውስጡ ያዘለ በመሆኑ ነው፡፡
አላህ ባወቅነው የምንሰራ ያድርገን ከማንኛውም አስነዋሪ ባህሪ ይጠብቀን፤ በእያንዳንዱ የህይወታችን እንቅስቃሴ የእርሱን ትእዛዝ የምንፈፅም ያድርገን፤ ከሀሰትና እርሱ ከሚያመጣው መዘዝ አላህ ይጠብቀን። 


(يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَكُونُوا مَعَ الصَّادِقِينَ) [Surat At-Tawbah 119]

"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ፡፡ " [Surat At-Tawbah 119]

አሏህ ሆይ! በንግግራቸውም በተግባራቸውም እውነትን ከሚያዘወትሩት እውነተኞች አድርገን፤ ሰላም በመልእክተኞች ላይ ይሁን ምስጋናም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ይሁን፡፡ 

Indris abu mus'ab

© ተንቢሀት - ሙስሊም ሴቶችን የተመለከቱ ህግጋት Tenbihat - Rulings Pertaining to Muslim Women