Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እህቶቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ተዛዘኑ፤ ተከባበሩ፤ ተናነሱ . .


እህቶቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ ተዛዘኑ፤ ተከባበሩ፤ ተናነሱ . . በተውሒድና በሱና ገመድ መተሳሰር የስኬት ሁሉ ቁንጮ ነው። ሸይጧን እናንተ መካከል ቁርሾ ለመፍጠር፤ ለማጣላት፤ ለማነቋቆር የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም! ለምን ምኞቱን ታሳኩለታላችሁ?
እርስ በርስ በነገር አትወጋጉ!
ከምንም በላህ አላህን ፍሩ!
«እከሊት'ኮ እከሊትኮ. .» እያላችሁ አትተማሙ!
በዘር፥ በሃብት በሌላም አንዳችሁ ሌላኛዋን እህት ዝቅ አትድርጉ!
በዱኒያ ጉዳይ ስትጣሉ ወደ ዲንና መንሃጅ አስጠግታችሁ አትዘላለፉ!
ለከት የሌለው ቀልድና መነቋቆር ይቅርባችሁ!
እርስ በርሳችሁ ያላችሁን ግንኙነት አጠናክሩ!
የዲን ትምህርቶችን ተማማሩ!
ቅንነትና ግልጽነት ይኑራችሁ!
አንዷ እህት ብታጠፋ ወይንም ብታስከፋችሁ ለሌላኛዋ እህት ሄዳችሁ «እንዲህ አደረገችንኝ. .» ከምትሉ ለራሷ ቀርባችሁ ወይንም ደውላችሁ «እንዲህ እንዲህ በማድረግሽ ቅር ተሰኝቼብሻለሁ. .» ብላችሁ በግልጽ አሳውቁ።
በመካከላችሁ ያሻከራችሁ ጉዳይ ካለም በግልጽ ተወያዩበት። ይቅርታም ለመጠየቅ ነፍሲያ አትያዛችሁ። አጥፍታችሁ እንኳን ባይሆን የአላህን አጅር ፈልጋችሁበት ይቅርታ ለመጠየቅ አትፈሩ። «ይቅር በይኝ» ስትባሉ ክንፋችሁን ዝቅ አድርጋችሁ ይቅር በሉ።
አንዲት እህት ጠፍታባችሁ ወይንም ካያችኋት ከቆየባችሁ ደውላችሁ አሊያም በአካል ሄዳችሁ «ምን ሆነሽ ነው እህቴ የጠፋሽው?» ብላችሁ ተጠያየቁ።
አንዳችሁ የአንዳችሁን ችግር ተካፈሉ። ያስጨነቃችሁ ጉዳይ ካለ ለብቻችሁ እያብላላችሁ ከምትሰቃዩ ለእህቶቻችሁ በግል አማክሩ ተመካከሩ።
ማንኛችሁም በማንኛችሁም ላይ አትቀናኑ። ሸይጧን በዱኒያ ጉዳይ በእህታችሁ ላይ የቅናት መንፈስ ካመጣባችሁ እንዲያውም እጃችሁን ወደ ላይ ዘርግታችሁ « አላህ ሆይ ለእከሊት እህቴ የሰጠሃትን ጸጋ ባርክላት!» ብላችሁ ዱዐ አድርጉና ሸይጧንን አቃጥሉት ነፍሲያችሁንም ለውስዋስ ቦታ የለሽም በሏት።
ወሬ አታናፍሱ። ሓያእ ተላበሱ። ራሳችሁን በዒልም ላይ ቢዚ አድርጉ። ባለትዳር ከሆናችሁ የባሎቻችሁን ሐቅ ተወጡ። ባለትዳር ካልሆናችሁም አላህ መልካሙን ትዳር እንዲሰጣችሁ ዱዐ አድርጉ። ሆኖም መልካምን ትዳር ስትመኙ እኔ መልካም ነኝ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ራሳችሁን ጠይቁ።
ራሳችሁን በዒባዳ ጥመዱ። ማላሶቻችሁን ክፉ እንዳይናገሩ ጠብቁ።
ለእናንተ ጠቃሚ ሆኖ ያገኛችሁትን እውቀት ለሌሎች እህቶቻችሁ በተቻላችሁ አጋጣሚ አስተላልፉ።
በእህታችሁ ላይ አላስፈላጊ ነገር ብትመለከቱ በግል ምክር ለግሱ። ስትመከሩም ሐቅ እስከሆነ ድረስ ያለምንም ማንገራገር ተቀበሉ።
የባሎቻችሁን አይብ፤ የቤተሰቦቻችሁን ጉድለት አታውሩ። አላህ ያስተካክላቸው ዘንድ ዱዐ አድርጉ።
ሙያ ተማሩ። ንጽህናችሁን ጠብቁ። ራሳችሁን ከፍ ከፍ ከማድረግ ግን ተቆጠቡ። ለቤተሰቦቻችሁ ታዛዥ ሁኑ። ጭቅጭቅ አታዘውትሩ። ስራችሁን በአግባቡ ስሩ። አርቃችሁ አስቡ። ንቁ ሁኑ። የበታችነት ስሜት ፍጹም አይሰማችሁ። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስህተት ብትፈጽሙ ራሳችሁን ከመውቀስ ይልቅ ነገሩን ለማስተካከል ጥረት አድርጉ። እሱ ካልሆነም የአላህ ውሳኔ ተቀብላችሁ ራሳችሁን አረጋጉ። አትጨናነቁ። ራሳችሁን በጭንቀት ስትወጥሩ ለሸይጧን በር እየከፈታችሁ እንደሆነ አስታውሱ።
አንድን ነገር ከማድረጋችሁ ወይንም አንድን ንግግር ከመናገራችሁ በፊት መልካም ጎኑን እና መጥፎ ጎኑን አመዛዝኑ። እንኳን ለሙስሊሟ እህታችሁ ለካፊሯ እንስት ተምሳሌት ሁኑ። አንብቡ። ራሳችሁን በእውቀት ገንቡ።

Abu Aisha