Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በአጥፊዎች ላይ ስለመጠንከር መጠነኛ ዳሰሳ

በአጥፊዎች ላይ ስለመጠንከር መጠነኛ ዳሰሳ
በመልካም ማዘዝ ከመጥፎ መከልከል የዚህ ኡማ አንድ መገለጫ ነው፡፡ በአጥፊዎች ላይ ምላሽ መስጠት የዚህ እሴት አንድ ንኡስ ክፍል ነው፡፡ ይሄ ንኡስ ክፍል በሸሪዐችን ፅኑ መሰረት ያለው ነው፡፡
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ بْنِ مَسْعُودٍ أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- قَالَ «مَا مِنْ نَبِىٍّ بَعَثَهُ اللَّهُ فِى أُمَّةٍ قَبْلِى إِلاَّ كَانَ لَهُ مِنْ أُمَّتِهِ حَوَارِيُّونَ وَأَصْحَابٌ يَأْخُذُونَ بِسُنَّتِهِ وَيَقْتَدُونَ بِأَمْرِهِ ثُمَّ إِنَّهَا تَخْلُفُ مِنْ بَعْدِهِمْ خُلُوفٌ يَقُولُونَ مَا لاَ يَفْعَلُونَ وَيَفْعَلُونَ مَا لاَ يُؤْمَرُونَ فَمَنْ جاهَدَهُمْ بِيَدِهِ فَهُوَ مُؤْمِنٌ وَمَنْ جاهَدَهُمْ بِلِسَانِهِ فَهُوَ مُؤْمِنٌ وَمَنْ جاهَدَهُمْ بِقَلْبِهِ فَهُوَ مُؤْمِنٌ وَلَيْسَ وَرَاءَ ذَلِكَ مِنَ الإِيمَانِ حَبَّةُ خَرْدَلٍ»
ከዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ ረዲየላሁ ዐንሁ ተይዞ የአላህ መልእክተኛ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- “ከኔ በፊት አላህ የላከው አንድም ነብይ የለም፣ ከህዝቦቹ ሱንናውን የሚይዙ፣ በትእዛዙ የሚጓዙ ሐዋርያትና ባልደረቦች የኖሩት ቢሆን እንጂ፡፡ ከዚያም ከነሱ በኋላ ክፉ ምትኮች ይተካሉ፡፡ የማይሰሩትን ያወራሉ፡፡ ያልታዘዙትን ይፈፅማሉ፡፡ በእጁ የታገላቸው እሱ አማኝ ነው፡፡ በምላሱ የታገላቸውም እሱ አማኝ ነው፡፡ በልቡ የታገላቸውም እሱ አማኝ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የሰና-ፍጭ ፍሬ ታክል ኢማን የለም!!” [ሙስሊም፡ 188]
ታዲያ በመልካም የምናዝበት ወይም ከመጥፎ የምንከለክልበት መንገድ ይበልጥ ፍሬ ሊያፈራ በሚችል መልኩ ወይም የከፋ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ይፈፀም ዘንድ መቃኘቱ ከእያንዳንዱ አስተማሪ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ይህንን ሐቅ በተሟላ መልኩ የያዘው ሸሪዐችን እንደ አስፈላጊነቱ ጠንከርም ለስለስም እያልን እንድናስተምር የሚያዙ ብዙ መረጃዎችን አካቷል፡፡ ሸይኽ ኢብኑ ባዝ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ሸሪዐው በቦታው ላይ እስከሆነ ድረስ በደዕዋ ላይ መጠንከርንም ሆነ መለስለስንም ሰብስቦ ይዟል፡፡ እናም ሲጨመቅ የተሟላ የሆነው ኢስላማዊ ሸሪዐ መለሳለስን ከቦታው መጠንከርንም ከቦታው ይዞ ነው የመጣው፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰው ይህን ችላ ሊል አይገባውም፡፡ ጠንካራ አቀራረብ ከሚያስፈልገው ቦታ ላይ ለስላሳ የሆነ አቀራረብ ሊውል አይገባም፡፡ ጠንካራ አቀራረብም እንዲሁ መለስለስ ከሚገባ ቦታ ሊውል አይገባም፡፡ መለስለስን ብቻ እንዳዘዘ ወደ ሸሪዐው ማስጠጋት አይፈቀድም፡፡ በመጠንከር ብቻ እንዳዘዘም ተደርጎም እንዲሁ ሊቀረብ አይገባም፡፡ ይልቁንም ሸሪዐው ጥበብ የተሞላበት፣ የተሟላና ለሁሉም ጊዜና ቦታ ለሁሉም ህዝብ የሚበጅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁለቱንም ነገሮች (መለስለስንም መጠንከርንም) ያስተማረው፡፡…”
ወደ ነገሬ ስመለስ ሸሪዐውን በሚገባ የሚያውቁት ሰለፎቻችን እዝነትን ያንፀባረቁባቸው ብዙ ክስተቶች ቢኖሩም በቢድዐ ሰዎች ላይ ግን በጣም ብርቱዎች እንደነበሩ እጅግ ብዙ መረጃዎች መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ ያክል ኢብኑ ዐባስና ሌሎችም ሶሐቦች ቀደርያዎች ላይ፣ ሰሙራ ኢብኑ ጁንዱብ ኸዋሪጆች ላይ፣ ሐማድ ኢብኑ ሰለማ በቢድዐ ሰዎች ላይ ብርቱ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ [ሺፋኡል ዐሊል፡ 60] [አልኢሷባ፡ 3/130] [አስሲየር፡ 7/447] ይሄ የአንድ ወይም የሁለት ሰው አቋም እንዳይመስለን፡፡ አቡ ዑሥማን አስሷቡኒ (373 ዓ.ሂ.) ረሒመሁላህ የሰለፎችን መዝሀብ ሲገልፁ እንዲህ ይላሉ፡- “የቢድዐ ሰዎችን በመጫን፣ በማዋረድ፣ በማራቅ፣ ከነሱም እነሱን ከመጎዳኘትም እነሱ ጋር ከመኗኗርም በመራቅ፣ ተስማምተዋል፡፡ እነሱን በመራቅና በማኩረፍ ወደ አላህ ዐዘ ወጀል በመቃረብም እንዲሁ (ተስማምተዋል)፡፡” [ዐቂደቱ ሰለፍ ወአስሓቢል ሐዲሥ፡ 113] ኢብኑል ቀይምም እንዲህ ይላሉ፡- “ቀደምቶችና ታላላቅ ኢማሞች በቢድዐ ላይ ያላቸው ተቃውሞ የከፋ ነበር፡፡ በየአፅናፉ በቢድዐ ሰዎች ላይ ጩኸዋል፡፡ ፈተናቸውንም በከባዱ አስጠንቅቀዋል፡፡ በዚህ ላይ አስቀያሚ ወንጀሎችን፣ በደሎችና ግፎችን ከሚቃወሙት በላይ ጫፍ የደረሰ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የቢድዐ ጉዳት፣ የዲን አፍራሽነቷ እና ተፃራሪነቷ የከፋ ስለሆነ ነው፡፡” [መዳሪጁ ሳሊኪን፡ 1/3378]
ስለዚህ ሺድዳ (ጠንካራ አቀራረብ) ሁሌ የተወገዘ አይደለም፡፡ እንዲያውም በቁርኣን በሐዲሥ መሰረት ያለው ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
(يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ جَاهِدِ الْكُفَّارَ وَالْمُنَافِقِينَ وَاغْلُظْ عَلَيْهِمْ ۚ وَمَأْوَاهُمْ جَهَنَّمُ ۖ وَبِئْسَ الْمَصِيرُ) التوبة: ٧٣
“አንተ ነብዩ ሆይ! ከሃዲዎችንና መናፍቃንን ታገል፡፡ በእነሱም ላይ ጨክን፡፡ መኖሪያቸውም ጀሀነም ናት፡፡ መመለሻይቱም ከፋች፡፡” [አትተውባ፡ 73]
በዚህ ላይ የተሰጡ ተፍሲሮችን ይመልከቱ፡፡ ሸውካኒ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ጭካኔ ማለት የልብ ጥንካሬ፣ አቀራረብን ማሻከር ማለት ነው፡፡ ሙእሚኖች በነዚህ ሁለት ክፍሎች ላይ የሚኖራቸው መስተጋብር በዚህ መልኩ ነው፡፡” [ፈትሑል ቀዲር፡ 2/436] የነብዩ ኢብራሂምን ታሪክ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ቀንጨብ አድርገን እንመለከት፡-
"وَتَاللَّهِ لَأَكِيدَنَّ أَصْنَامَكُمْ بَعْدَ أَنْ تُوَلُّوا مُدْبِرِينَ(٥٧) فَجَعَلَهُمْ جُذَاذًا إِلَّا كَبِيرًا لَهُمْ لَعَلَّهُمْ إِلَيْهِ يَرْجِعُونَ(٥٨) ... قَالَ أَفَتَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ مَا لَا يَنْفَعُكُمْ شَيْئًا وَلَا يَضُرُّكُمْ(٦٦) أُفٍّ لَكُمْ وَلِمَا تَعْبُدُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ ۖ أَفَلَا تَعْقِلُونَ(٦٧)"
(“በአላህም እምላለሁ ዞራችሁ ስትሄዱ ጣዖቶቻችሁን ተንኮል እሠራባቸዋለሁ" (አለ)፡፡ ስብርብሮችም አደረጋቸው፡፡ ለእነሱ የሆነ አንድ ታላቅ (ጣዖት) ብቻ ሲቀር ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ (እርሱን ተወው)፡፡ ... “ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትገዛላችሁን?! ኡፍ! ለእናንተ ከአላህ ሌላ ለምትገዙትም ነገር! አታውቁምን?” አላቸው፡፡) [አንቢያእ: 57-67]
ከነብዩ ﷺ ሐዲሦች ለናሙና ያክል ብቻ እንመለከት
عَنْ عَدِيِّ بْنِ حَاتِمٍ، أَنَّ رَجُلًا خَطَبَ عِنْدَ النَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ، فَقَالَ: مَنْ يُطِع اللهَ وَرَسُولَهُ، فَقَدْ رَشَدَ، وَمَنْ يَعْصِهِمَا، فَقَدْ غَوَى، فَقَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: « بِئْسَ الْخَطِيبُ أَنْتَ (رواه مسلم)
ከዐድይ ኢብኑ ሓቲም ተይዞ የሆነ ሰው ከነብዩ ﷺ ዘንድ እንዲህ ሲል ኹጥባ አደረገ፡ “አላህና መልእክተኛውን የታዘዘ በእርግጥም ተቀና፡፡ ሁለቱን ያመፃቸው ግን በእርግጥም ጠመመ፡፡” የአላህ መልእክተኛ ﷺ በዚህን ጊዜ “ምንኛ ክፉ ደስኳሪ ነህ አንተ!” አሉት፡፡ [ሙስሊም] ይህን ያሉበት ምክንያት በአላህና በሳቸው መካከል የደረጃ ልዩነትን እንዳለ በማያሳይ መልኩ ስለገለፀ ነው፡፡ በሌላ ሐዲሥ አቡ ዘር ረዲየላሁ ዐንሁ የሆነን ሰው በዘሩ በማነወራቸው ምክንያት ነብዩ ﷺ
«يَا أَبَا ذَرٍّ أَعَيَّرْتَهُ بِأُمِّهِ؟ إِنَّكَ امْرُؤٌ فِيكَ جَاهِلِيَّةٌ (البخاري ومسلم)
“አቡ ዘር ሆይ በዘሩ አነወርከው አይደል?! አንተ ጃሂሊያ ያለብህ ሰው ነህ!!” የሚል ጠንካራ ሂስ በታላቁ ሶሐባ ላይ ሰንዝረዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም]
ምናልባት ይሄ የሰለፎች ጠንካራ አቀራረብ እንደ ጀህምያ ባሉ ከባባድ ቢድዓ ላይ በወደቁ ላይ ብቻ እንዳንገድበው፡፡ እንደዚያ ካደረግን ብዙ ግድፈቶችን እንፈፅማለን፡፡
አንደኛ፡- ድምዳሜያችን ለመረጣ ይጋለጣል፡፡ ማለትም በዚህ መልኩ የምናስብ ከሆንን ሌሎች በርካታ መረጃዎችን እንደፈጥጣለን፡፡ ለምሳሌ፡-
أَنَّ عَبْدَ اللَّهِ بْنَ عُمَرَ قَالَ سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- يَقُولُ «لاَ تَمْنَعُوا نِسَاءَكُمُ الْمَسَاجِدَ إِذَا اسْتَأْذَنَّكُمْ إِلَيْهَا». قَالَ فَقَالَ بِلاَلُ بْنُ عَبْدِ اللَّهِ وَاللَّهِ لَنَمْنَعُهُنَّ. قَالَ فَأَقْبَلَ عَلَيْهِ عَبْدُ اللَّهِ فَسَبَّهُ سَبًّا سَيِّئًا مَا سَمِعْتُهُ سَبَّهُ مِثْلَهُ قَطُّ وَقَالَ أُخْبِرُكَ عَنْ رَسُولِ اللَّهِ -صلى الله عليه وسلم- وَتَقُولُ وَاللَّهِ لَنَمْنَعُهُنَّ
በሆነ ወቅት ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር “የአላህ መልእክተኛን ﷺ ሴቶቻችሁን መስጂድ ለመሄድ ካስፈቀዷችሁ አትከልክሏቸው ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ” ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ቢላለ ኢብኑ ዐብዲላህ “ወላሂ እንከለክላቸዋለን!” አለ፡፡ ዐብደላህ ወደሱ በመዞር ጭራሽ እንደዚያ ሲሰድበው ሰምቼው የማላውቀው ከባድ ስድብ ሰደበው፡፡ “ከአላህ መልእክተኛ ﷺ እየነገርኩህ ‘ወላሂ እንከለክላቸዋለን’ ትላለህ?” አሉት፡፡ አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል፡፡ [ጋየቱል መራም፡ 201] የተፈፀመው ጥፋት በግልፅ እንደሚታየው እንደ ጀህምያና ሙዕተዚላ ያለ የኩፍር ጉዳይ አይደለም፡፡ ይበልጥ ግልፅ ይሆን ዘንድ ነብዩ ﷺ የጠነከሩባቸውን ክስተቶች ማስተዋል ጥሩ ነው፡፡ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዐምር ተይዞ እንዲህ ይላሉ፡- ነብዩ ﷺ በኔ ላይ ሁለት ቢጫ ልብሶችን አዩ፡፡ ከዚያም “እናትህ ናት በዚህ ያዘዘችህ?!” አሉኝ፡፡ “ልጠባቸው?” ብየ ስጠይቅ “የለም! አቃጥላቸው” አሉ፡፡ [ሙስሊም] ሌሎችም በርካታ ሐዲሦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል የተሳሳተ ብይን በመስጠታቸው ሳቢያ ሰው ለሞተባቸው አካላት ነብዩ ﷺ “ገደሉት አላህ ይግደላቸውና” ብለዋል፡፡ [ሶሒሕ ኢብኑ ማጃህ፡ 464] ይህን ከባድ ቃል የተጠቀሙበትን ጥፋት ምንነት ያስተውሉ፡፡ ዛሬ ካሉ ጥፋቶች ጋርም ያገነዛቡት፡፡ “አላህ ቢሻ አንተ ብትሻ” ያላቸውን ደግሞ “ለአላህ ባላንጣ አደረግከኝን?” ብለውታል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 139] እነዚህን ክስተቶች ያለበቂ ምርኩዝ ልዩ አጋጣሚ እንጂ ከዚያ ያለፈ መልእክት የሌላቸው አድርገን እንዳናስብ፡፡
ሁለተኛ፡- የሰለፎቹን ጠንካራ ሂስ እንደ ጀህምያ ባሉ አንጃዎች ንፃሬ የምንገድበው ከሆነ ሰዎች ዘንድ “ዛሬ ያሉ ጥፋቶች ቀላል ናቸው” የሚል አንድምታ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይሄ አደገኛ ውጤት ያስከትላል፡፡ የሙግቱን ውድቅነት ለማሳየት ከላይ የተዘረዘሩት በፊቅህ ጉዳዮች ሳይቀር የመጡ ጠንካራ አቀራረቦችን ማስተዋል በቂ ነው፡፡ ደግሞም ሁሉም እንደሚያውቀው ዛሬም እንደ ጥንቱ ሱፍዮች አሉ፡፡ ታዲያ ቀደምቶች በሱፍያዎች ላይ ጠንካራ ሂሶችን አልሰነዘሩምን? ኢማሙ ሻፊዒ “አንድ ሰው ጧት ሱፊ ከሆነ ዙህር ላይ ቂል ሆኖ አንጂ አታገኘውም” አላሉምን?! አቡበክር አጥጦርጡሺ “የሱፍያ መንገድ ቦዘኔነት፣ ድንቁርና እና ጥመት ነው” አላሉምን?! የያኔዎቹ ሱፍዮች እኮ ጥፋታቸው የዛሬዎቹን አልደረሰም፡፡ ይህም ከመሆኑ ጋር በዚህ መልኩ ይኮንኗቸዋል፡፡
ዛሬም እንደ ጥንቱ ኸዋሪጆች አሉ፡፡ ሰለፎች በነሱ ላይ ምን አይነት አቋም ነበር የነበራቸው? ዛሬም እንደ ጥንቱ አዒራዎች አሉ፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባሉ የሱና ዑለማዎች እጅግ ጠንካራ ሂሶችን በነሱ ላይ እናገኛለን፡፡ ኢማሙ ማሊክ “ከይፈ ኢስተዋ” ብሎ የጠየቃቸውን ሰው “ኢስቲዋእ የሚታወቅ ነው፡፡ ከይፍያው አይታወቅም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ መጠየቅ ቢድዐ ነው፡፡ ሙብተዲዕ /ጠማማ/ እንጂ አትመስለኝም” ብለው ከቤታቸው አባረውታል፡፡ ይሄ ጥፋት ዛሬ በሰፊው የነገሰ አይደለምን?! ዛሬም እንደ ጥንቱ ሶሐባን የሚያንቋሽሹ አሉ፡፡ የሰለፎች አቋም በዚህ ላይ በጣም የጠነከረ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኢማሙ አሕመድ “አንድ ሰው ከነብዩ ﷺ ሶሐቦች ውስጥ አንዱንም በክፉ ሲያነሳ ካየኸው እስልምናውን ጠርጥረው” ብለዋል፡፡ [አልቢዳያ ወንኒሃያ፡ 8/142] አቡ ዙርዐም “የነብዩ ﷺ ሶሐቦችን ክብር የሚያጎድፍ ሰው ዚንዲቅ (አፈንጋጭ) ነው” ብለዋል፡፡ [አልኪፋያ ሊልኸጢቢል በግዳዲ፡ 97]
በሶስተኛ ደረጃ፡- የሰለፎቹ ጠንካራ አቀራረብ ከባድ ጥፋት በታየባቸው እንደጀህምያ ባሉ አንጃዎች ንፃሬ ማቅረብ የሚያስከትለው ሌላው ግድፈት ሺድዳና ሊን የጥፋትን ክብደትና ቅለት ብቻ ተከትሎ የሚወሰን ማስመሰሉ ነው፡፡ አላህ ለፊርዐውን “ልዝብን ቃል ተናገሩት” ብሏል፡፡ [ጠሀ፡ 44] ለማንም እንደማይሰወረው ጥፋቱ ከሙዕተዚላዎች ጥፋት ያነሰ አልነበረም፡፡ ነብዩ ﷺ ለመካ አጋሪዎች የለሰለሱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ጥፋታቸው ግን ከኸዋሪጆች ጥፋት የቀለለ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ለከሃዲዎች መለስለስን የሚጠቁሙ መረጃዎች ብዙ ናቸው፡፡ በሙስሊም አጥፊዎች ላይ የተወሰዱ ጠንካራ እርምጃዎችም ብዙ ናቸው፡፡ ከነብዩ ﷺ ሶሐቦች ውስጥ ትልቅ ደረጃ ያለው ሆኖ ሳለ በብርቱ የተነቀፈ ሲኖር ደረጃው በንፅፅር ዝቅ ያለ ሆኖ በልስላሴ የተስተናገደም አለ፡፡ አዋቂዎች ላይ ጠንካራ መሀይማን ላይ ግን ለስላሳ የሆኑባቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ አጥፊዎቹ ከጥፋታቸው የሚመለሱበትን የተሻለ መንገድ መጠቀም፤ ወይም ቢያንስ ሌሎች እንዲገነዙ በማድረግ ላይ የተሻለውን መንገድ ማሳየት፤ መስለሐና መፍሰዳን ከማስላት ጋር ወዘተ የሚያያዝ እንጂ እንዲሁ ወጥ በሆነ መልኩ በአንድ መስፈሪያ የሚሰፈር እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡
ምናልባት ሰለፎች በቢድዐ ሰዎች ላይ ጠንካራ ቃላትን ሲጠቀሙ የነበረው እነሱ ተሰሚነት ስለነበራቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህን ሙግት የሚያፈርሱ ከቁርኣንም፣ ከሐዲሥም፣ ከሰለፎችም፣ ከኋለኛው ዘመን ዑለማዎች አካሄድም እጅግ በርካታ ማስረጃዎችን መቁጠር ይቻላል፡፡ አላህ ካለ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
በዚህ ዘመን ወደ ልስላሴ (ሪፍቅ) አጥብቀው ከተጣሩ ዑለማዎች እራሱ በርካታ ጠንካራ አካሄዶችን ማየት ይቻላል፡፡ ኢብኑ ባዝን እንደምሳሌ ብንወስድ ከውሠሪን፡ “ወንጀለኛው ወንበዴው” ብለውታል፡፡ “ወደ ልዩነትና ውዝግብ፣ መሪዎችንና ዑለማዎችን ወደ መሳደብ የሚጣሩ ቆሻሻ ካሴቶችን ማሰራጨት ያለጥርጥር መጠንቀቅ ከሚሹ ከባባድ ጥፋቶች ውስጥ ናቸው፡፡ ዲናቸውንና አደራቸውን ለሸይጧን የሸጡ ከሆኑት እንደ ሙሐመድ አልሚስዐሪ እና መሰሎቹ ያሉ ቂም ያረገዙ እና መሀይማን ዘንድ ከለንደን የመጣም ይሁን ከሌላ…” እያሉ የሚናገሩበት አለ፡፡ ወላሂ ይህን ከባድ አነጋገር ተመልከቱ፡፡ ሌላም ጊዜ እንዲህ ይላሉ፡- “ኡሳማ ቢን ላደን ምድር ላይ ከሚያጠፉ ሰዎች ነው፡፡ ብልሹ የሆኑ የተንኮል መንገዶችን ሆን ብሎ ይከታተላል፡፡” ስለ ሰይድ ቁጥብ ደግሞ “ተፍሲር ላይ ደካማ የሆነ ምስኪን ነው፡፡” ኪታቦቹንም “መቦጫጨቅ አለባቸው” ያሉበት አለ፡፡ ስለ ዐብዱርረሒም አጥጢሓን ደግሞ “ንግግሩ የእብዶችና የራፊዷዎች ንግግር ነው” ብለዋል፡፡
ከዚህም በላይ በሙብተዲዖች ላይ ጠንካራ የነበሩ እንደ ሐሙድ አቱወይጂሪና ረቢዕ ኢብኑ ሃዲ ያሉ ዑለማዎችን በድንበር አላፊነት እስከመወረፍ ሊደርሱ ቀርቶ ለኪታቦቻቸው መቅድም ፅፈዋል ወይ ደግሞ አወድሰዋቸዋል፡፡ ስለዚህ “ዘመኑ የሪፍቅ ነው” የሚሉት ኢብኑ ባዝ በዚህ መልኩ የተጓዙበትም አለ ማለት ነው፡፡
ባጭሩ ከዚህ ነጥብ የፈለግኩት ሰዎች ላይ የሆነ ጥንካሬ ብናስተውል ይሄ “ድንበር አላፊዎች” /ጉላት/ በሚል ገላጭ እስከመወራረፍ ያደርሳል ወይ? የሚለውን እንድናስብበት ነው፡፡ አንዳንዶቻችንማ ልስላሴያችን ለኢኽዋኖች ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ ይበልጥ ለሚቀርበው አካል ይበልጥ የሚጠነክር ሰው ምንኛ የሚደንቅ ነው?! በቅርቡ ወሰን ያለፉ ወንድሞችን “ሲመክሩ” “እውነት እናንተ ሙስሊም ናችሁ?” እያሉ የሰዎችን ኢስላም ጥያቄ ውስጥ እስከመክተት የደረሱ ተመልክተናል፡፡ ወላሂ “ጣኦት አምላኪዎች” እያለ ባደባባይ የተውሒድ ሰዎችን የሚወነጅል ሁሉ ተመልክተናል፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉ፡፡ አስገራሚ የሆነ መጣረስ!! እነዚህ ሰዎች ከሪፍቅ እና ሊን ስብከት እራሳቸውን ኢስቲሥናእ ያወጡ ይመስላሉ፡፡ ሌሎችን በእዝነትና ልስላሴ እጥረት ምክንያት በጠርዘኝነት የሚወርፍ ሰው ለራሱ በዚህ መልኩ ሲጓዝ ማየት የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
ሳጠቃልል የሪፍቅ ጥሪያችን ፍሬ ያፈራ ዘንድ አካሄዳችንን ከብዙ አቅጣጫ እንመልከተው፡፡
1. የእውነት እራሳችንን በቅድሚያ እንፈትሽ፡፡ የቢድዐ ሰዎች ላይ በወንድሞቻችን የሚሰነዘረው ሂስ አደብ ጥሷል ብለን ካመንን ለምን እኛ “ወሰን ያለፉ ወንድሞችን” የምናርምበት መንገድ ሪፍቅ /ልስላሴ/ ያጥረዋል?! በዚህ መልኩ እየሄድንስ ጤናማ ውጤት ላይ እንደርሳለን? ደግሞስ ለምን የምንለውን አካሄድ በተግባር አናሳይም?! ይህን ብናደርግ የአካሄድ ስህተት ያለበት እንዲመከር ማድረግ ስንችል፣ ስራችንን ከራሱ ለመከላከል፣ ሌሎችን ለማጥቃትና እርስበርስ ለማባላት የሚያውለው አካል እጁን እንዲሰበስብ ማድረግ እንችላለን፡፡ ያለበለዚያ ስራችን “የቆጡን አወርድ ብላ…” አይነት ይሆናል፡፡
2. አንዳንዶች ዘንድ ሺድዳን የሚቃወሙበት ምክንያት ከአቀራረብ ክፍተት ያለፈ እየመሰለ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በኢኽዋን ላይ የተሰጠ የድምፅ ፋይል “ለምን ተለጠፈ?” እያሉ በሻከረ ቃና የሚቃወሙ ሰዎችን መመልከት በእጅጉ አነጋጋሪ ነው፡፡ ይሄ አንድምታው ምንድን ነው?! (ስለፍርድ ስላላወራሁ “አንድምታው ለምን አስፈለገህ?” እንዳይባል፡፡) ስለዚህ አቀራረባችን ብዥታንና ጥርጣሬን የሚገፍ ሊሆን ይገባል፡፡
3. “በቢድዐ ሰዎች ላይ የሚሰነዘረው መልስ ካፊሮችን በሚያስደስት መልኩ መሆን የለበትም” የሚል አባባል እየሰማን ነው፡፡ ይሄ አባባል ከፊል እውነታ ቢኖረውም በአግባቡ እየዋለ አይደለም፡፡ አንደኛ በአህሉ ሱና ላይ የሚሰጠው መልስ እንዴት አህሉል ቢደዕን በሚያስደስት መልኩ ይደረጋል?! ካልሆነ መርሃችንን እራሳችን እየደፈጠጥነው እኮ ነው፡፡ በሌላ በኩል “የቢድዐ ሰዎችን ስንተች ካፊሮችን በሚያስደስት መልኩ መሆን የለበትም” የሚለው አባባል እነሱ ሱናን ቢያጠለሹም፣ ሰው ቢያሳስቱም፣ ዑለማዎችን ቢያብጠለጥሉም፣ ጥፋታቸውን በየመሳጂዱ፣ በየሶሻል ሚዲያው በገፍ ቢያሰራጩም ዝም እንበል የሚል አንድምታ ሊኖረው አይገባም፡፡ ዛሬ ወደዚህ ያሽቆለቆሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡ “ጧት ማታ ኢኽዋን ኢኽዋን እያላችሁ” ብለው እየተቹ ጧት ማታ ክፍተት አለባቸው የሚሏቸውን ወንድሞች መነዝነዝን የመረጡ አሉ፡፡ ዘይገርም ነገር!! ይሄ አቀራረብ እንደ ዐድል (ፍትሃዊነት)፣ መስለሐና መፍሰዳ፣ ሪፍቅ እና መሰል ጩኸቶቻችንን በዜሮ የሚያባዛ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዳዒሾችን (አይሲስ) ምዕራብ ከመስራቅ ተባብሮ ካፊር እየቀጠቀጣቸውም የሙስሊም ዑለማዎች ጥመታቸውን ከማጋለጥ አልቦዘኑም፡፡ የነዚህ ሰዎች ጠማማነት መጋለጡ የህዝብ ድጋፍ የሚያሳጣ፣ ጠላቶቻቸውን የሚጠቅም ከመሆኑ ጋር ጦሳቸው ለሙስሊሙም የተረፈ በመሆኑ ምክንያት እጅግ በርካታ ዑለማዎች በሰፊው አጋልጠዋቸዋል፡፡ ይህም ቢድዐን ማጋለጥ ለኩፍር ማገዝ ማለት እንዳልሆነ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
4. ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው መስለሐና መፍሰዳን የማገናዘብ መርህ በውል ይፈተሽ የሚል ነው፡፡ የቢድዐ ሰዎች የከፋ ጥፋት ይበልጥ እየተራገበ ባለበት ወቅት የቢድዐ ሰዎች በሚጠቀሙበት መልኩ የወንድሞችን “ድክመቶች” ለማረም መዝመት እስኪ ከመስለሐውና ከመፍሰዳው የቱ ያደላል?! እዚህ ላይ ለብዙዎች አይሰወርም ብየ ባስብም እይታችን ቢለያይ አይገርምም፡፡ የግድ ማድረግ ካለብንም ቢያንስ የቢድዐ ሰዎች ሊጠቀሙበት በማይችሉት መልኩ ሊሆን ይገባል፡፡ “ይሄ ሸርጥ ነው ወይ?” “ይህን ማድረግ ግዴታ ነው ወይ?” “ይህን አለማድረግ ከሱና ያስወጣል ወይ?” የመሳሰሉ አፍ ለማዘጋት ያክል ብቻ ምክንያቶችን ከመደርደር መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ያገናዘበ መፍተሔ መምረጥ የተሻለ ነው፡፡
5. እርምታችን ልኩን የጠበቀ መሆኑን እናስተውል፡፡ ኢኸዋን ላይ መናገር እንደ ድንበር ማለፍ ተቆጥሮ ብዙዎች የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው እስከሚደርስ የተሻገረ ምክር ሰዎችን ወደ ሌላ ፅንፍ ነው የሚገፋው፡፡ በተግባርም እያየነው ነው፡፡
(ውድ ወንድሞቼ! አላማየ ቂም መዝራት፣ ወይም መካሰስ፣ ወይም ቁጭትን ማስተንፈስ አይደለምና “ማን እንዲህ አለ? ማን እንደዚያ አለ?” እና መሰል የሐሳብ ሙግት ውስጥ እንድንገባም አልፈልግም፡፡ “ቅድሚያ ለሪፍቅ መስጠት የለብንም ወይ?” “ሰዎች ላይ መናገር ያለበት ማነው?” “በቢድዐ ሰዎችስ ላይ ፍትህ አያስፈልግም ወይ?” “እውነት በመካከላችን ክፍተቶች የሉም ወይ?” “እራሳችንስ መተራረም የለብንም ወይ?” “የተለያቸውን ሁሉ በተልካሻ ምክንያቶች በኢኽዋንነት የሚፈርጁ ጠርዘኞችስ የሉም ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ገሸሽ ያደረግኩ እንዳይመስል፡፡ በአንድ በኩል ፅሑፌ ስለረዘመ በሌላ በኩል ከፊሎቹ ከርእስ ውጭ ስለሆኑ ነው በዚህ ላይ የተገደብኩት፡፡) ልቀጥል እችላለሁ፡፡

Ibnu Munewor