አስፈሪ ነብያዊ ሐዲሥ
ከአቡ ሁረይራህ - ረዲየሏሁ ዐንሁ - ተይዞ የአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ሲሉ ሰምቻለሁ ይላሉ፡-
“ከበኒ ኢስራኢል (ህዝቦች) አንድ ወንጀል የሚያበዛና ሌላ በዒባዳ (በአምልኮ) ላይ የሚታገል ሁለት ጓደኛሞች
ነበሩ፡፡ ዒባዳ ላይ የሚታትረው ያንኛውን ሁሌ ወንጀል ላይ ስለሚመለከተው ‘ተው’ ይለዋል፡፡ የሆነ ቀን ወንጀል ላይ
አገኘውና ‘ተው’ አለው፡፡
(ወንጀለኛው): ‘ተወኝ (እባክህ) በጌታዬና በእኔ መሀል አትግባ! በእኔ ላይ ተቆጣጣሪ ሆነህ ተልከሀል?’ ሲል መለሰለት፡፡ ያንኛው በዚህን ጊዜ፡
‘ወላሂ! አንተን አላህ አይምርህም!! ወይም አላህ አንተን ጀነት አያስገባህም’ አለ፡፡
የሁለቱም ሩሕ ተወሰደ (ሞቱ፡፡) ከአለማቱ ጌታ ዘንድ ተገናኙ፡፡ ለዚያ ታታሪ ሰውም (አላህ) እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-
‘በእኔ ላይ (እንደማልምረው) አዋቂ ነበርክ?! በእጄ ላይ ባለውስ ቻይ ነበርክ?!’
ለወንጀለኛው፡- ‘ሂድ በእዝነቴ ጀነት ግባ’ አለው፡፡ ያንኛውን ደግሞ ‘ወደ እሳት ውሰዱት’ አለ፡፡”
አቡ ሁረይራ - ረዲየሏሁ ዐንሁ ከዚህ ሐዲሥ በመቀጠል እንዲህ አሉ፡- “ነፍሴ በእጁ በሆነችው እምላለሁ! በርግጥም ዱንያ አኺራውን የምታጠፋ ንግግርን ተናገረ፡፡” [ሶሒሕ ኢብኑ ሒባን፡ 5712]
……………………………………………..
ከሐዲሡ የሚወሰዱ ቁም-ነገሮች
በመጀመሪያ የዚህን ሐዲሥ መልእክት ምን ያክል እናውቀዋለን? ምን ያክልስ አደጋው ይታየናል? ምን ያክልስ ጥንቃቄው አለን? ከዚህ ጥፋት ያለንስ ርቀት ምን ያክል ነው?
1. በሐዲሡ እንደተገለፀው
1.1. አንደኛው ሰው ወንጀል የሚያበዛ ነው፡፡ በዚያ ላይ ምክር አልተቀበለም፡፡
1.2. ሁለተኛው ሰው ዒባዳ የሚያበዛ ነው፡፡ በዚያ ላይ ከመጥፎ ለመመለስ የሚመክር አስተማሪ ነው፡፡
2. ውጤቱ ግን አስደንጋጭ ነው፡፡ ወንጀለኛው ወደ ጀነት፣ ዓቢዱና መካሪው ወደ እሳት!!!
3. ምክንያቱ ደግሞ፡-
3.1. የመጀመሪያው ወንጀሉ ከሺርክ በታች እስከሆነ ድረስ ከአላህ መሻት ስር ነው፡፡ “አላህ የሚያጋራበትን
አይምርም፡፡ ከዚያ በታች ያለውን ግን ለፈለገው ይምራል” ማለቱ አይዘንጋ፡፡ ስለዚህ ሰውየው የተማረው ስላላጠፋ
ሳይሆን በአላህ እዝነት ነው፡፡ “ሂድ በእዝነቴ ጀነት ግባ” እንዳለው ይታወስ፡፡
3.2. ሁለተኛው በማያገባው
ገብቶ “ይህን አያደርግም” እያለ በአላህ ላይ እየማለ ነው፡፡ ይህን ወንጀለኛ ይምረዋል ወይስ አይምረውም የሚለውን
የሚያውቀው ባለምህረቱ ብቻ ነው፡፡ ስልጣኑም ችሎታውም የሱው ነውና፡፡ ስለዚህ አቶ ዐቢድና መካሪ የአላህን ሐቅ
ነው እየተጋፋ ያለው፡፡
4. ከሳሽ ማን ነው?!
በቂያማ ቀን ታዲያ የዚህ ሰውየ ከሳሽ የሆነው ያ
ወንጀል የሚያበዛው አካል አይደለም፡፡ እህሳ ከሳሹም ዳኛውም የአለማቱ ጌታ አላህ ነው!! አያስፈራም?! “በእኔ ላይ
(እንደማልምረው) አዋቂ ነበርክ?! በእጄ ላይ ባለውስ ቻይ ነበርክ?!” ሲል አፋጠጠው፡፡
5. ቀይ መብራት!
እንዳቅሚቲ በዲን ላይ የምትታትረው ወንድሜ ሆይ! እንዳቅሚቲ ሸሪዐውን ለመተግበው ተፍ ተፍ የምትይዋ እህቴ ሆይ!
የምናውቃትን ከማስተላለፍ ባለፈ፣ ስለ ሰዎች መፃኢ እድል ከመዳፈር በእጅጉ ልንቆጠብ ይገባል፡፡ ይሄ ሐዲሥ እጅግ
አስፈሪ የሆነ መልእክት ነው የያዘው፡፡ ድንበር ማለፍ በዲን ስም ስለተፈፀመ ከተጠያቂነት አያተርፍም፡፡ አላህ
መጨረሻችንን ያሳምረው፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 16/2009)