Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ትኩረትና እንክብካቤ ለእህቶቻችን!

ትኩረትና እንክብካቤ ለእህቶቻችን!
ዘመናችን ሙስሊሞች ላይ ባጠቃላይ የሚደርሰው ፈተና እጅግ የጨመረበት ጊዜ ነው፡፡ እልቂት፣ ስቃይ፣ እንግልት፣ ከቤት ከቀየ መፈናቀል፣ የሀገር የንብረት መውደም፣ ወዘተ፡፡ ሙስሊሞች ላይ በሚደርሱት በነዚህ ፈተናዎች እንቆጫለን፣ እናዝናለን፣ እናለቅሳለን፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ፈተናዎች ይልቅ የከፋው ፈተና በሀይማኖታቸው ላይ የሚፈፀመው ደባ ነው፡፡ የእምነት ተቋሞቻቸውን ከመሬት የሚያፈርሱባቸው ጠላቶቻቸው ኢስላማቸውን ደግሞ ከልባቸው ላይ ለማፍረስ ሌት ከቀን ያሴራሉ፡፡ ለዚሁ ሲሉም ቢሊዮኖችን ያፈሳሉ፡፡ ሚሊዮኖችን ያሰማራሉ፡፡ ዘመን ተሻጋሪ መርዛማ ሴራዎችን ያቅዳሉ፡፡ የሴራቸውን ግዝፈት ባይመጥንም ከእምነታቸው የሚያርቋቸው ሰዎች ግን በተጨባጭ አሉ፡፡ ስለሚፈርሰው እምነታቸው ያላለቀስንላቸው ስንት ወገኖቻችን ባክነዋል?! ስለሚጠፋው ዘላለማዊ ህይወታቸው ያላነባንላቸው ስንት ወገኖቻችን ከስረዋል?!! ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንደተናገሩት አላህ ዘንድ አንድን ሙስሊም ከመግደል ይልቅ ዱንያ እንዳለ ብትጠፋ የተሻለ ነው፡፡ [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 5077] ይሄ የሙስሊም ህይወት ምን ያክል የከበረ እንደሆነ ግልፅ አመላካች ነው፡፡ ግና እምነት ደግሞ ከነፍስም በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ለዚያም ነው አማኞች ለእምነታቸው ሲሉ ህይወታቸውን አሳልፈው የሚሰጡት፡፡ ስለሆነም ሙስሊሞች ላይ ከሚደርሱ የነፍስና የቁስ ጥቃቶች ሁሉ የሚልቀው በእምነታቸው ላይ የሚፈፀመው ግፍና ሴራ ነው፡፡ አሁን ስለዚህ ብዙ ማለት ስላልፈለግኩ እንደመሸጋገሪያ ያክል ካነሳሁት ይበቃል፡፡
በዘመናችን ኢስላምና ሙስሊሞች ላይ ከተከፈቱ መጠነ ሰፊ ዘመቻዎች ውስጥ አንዱ የሴቶች ጉዳይ ነው፡፡ በሀሰት ወይም ጭብጡን ባልተረዱት ሐቅ፣ ወይም ደግሞ ሆን ብለው በሚጠመዝዙት እውነታ “ኢስላም ሴቶችን ይጮቁናል” ሲሉ ሰፊ ዘመቻ ይከፍታሉ፡፡ የሚደንቀው ይሄ ዘመቻ ሴት ልጅን እንደ እቃ ከሚቆጥር እምነት ተከታዮች ዘንድ መምጣቱ ነው፡፡ ብቻ የእህቶቻችን ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ይበልጥ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚሻ እንደሆነ ብዙ የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ ዛሬ እህቶቻችን፡-
- በስርኣት እንድንይዛቸው የሚያዘንን ዲን በመዘንጋታችን በኛው ይገፋሉ፡፡ ይሄ በየቤቱ ያለ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ የተራውስ ህዝብ ይሁን እንበል፡፡ በትዳር ውስጥ ወይም በትዳር ስም ሴቶችን ደም እንባ የሚያስለቅሱ ስንት ዱዓቶችና ሰባኪዎች አሉ?! ከሚሰጣቸው ግምት ከሚጠበቁበት ቦታ ባለመገኘታቸው ጦሳቸው ከነሱ አልፎ ለዲን ሲተርፍ አስቡት፡፡
- በተለያዩ አሳሪ ልማዶች ምክንያት ለዘላለማዊ ህይወታቸው መሰረት የሆነውን ዲናቸውን እንዳይረዱ ይደረጋሉ፡፡ በዚህም ላይ ከወንዱ ይልቅ ቀዳሚ ሰለባዎች እንደሆኑ አይሰወርም፡፡
- ከጊዜ ጊዜ ከሃይማኖትም ከሞራልም ይበልጥ እያፈነገጡ ባሉ ወንዶች የጥቃትና ትንኮሳ ኢላማ ይሆናሉ፡፡ እዚህም ሴቶች ላይ የሚደርሰው ወንዶች ላይ ከሚደርሰው ጋር ለንፅፅር የሚቀርብም አይደለም፡፡
- ለኢስላምና ሙስሊሞች ጥላቻ ያረገዙ አካላትም ይበልጥ ጥላቻቸውን ለማራገፍ የሚቀሏቸው ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ናቸው፡፡ በየትምህርት ተቋማቱ፣ በየአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ በየትራንስፖርቱ፣ በየሰፈሩ፣ የሚደርስባቸውን አስቡት፡፡ ያለ ጥርጥር ወንዱ ላይ ከሚደርሰው በአይነትም በብዛትም የከፋ ነው፡፡
- ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ ዘመናዊ የሴቶች “መብት” ለፋፊዎች በ“እኩልነት” ስም ሙስሊም ሴቶችን ከእምነታቸው ለማራራቅ የሚያደርጉት ዘመቻ ነው፡፡ ከቤቷ፣ ከቤተሰቧ፣ ከማህበረሰቧ፣… እየተገፋች ያለችዋ ሙስሊሟ ሴት በኢስላም ስም በሚደሰኩሩ ግልብ ሰባኪዎች ዳግም የምትገፋ ከሆነ በ“መብት” ስም ወደ ኩፍር ለሚጠሯት ሰባኪዎች ስብከት ጆሮ ብትሰጥ ብዙም አይደንቅም፡፡ የዚህ ከንቱ ድስኩር ሰለባ ሆነው ባላወቁት መልኩ ወደጥፋት የሚያኮበኩቡት ቀላል አይደሉም፡፡ ለይቶላቸው ይፋ ባይወጡትም ውስጣቸው የተቦረቦሩትም ብዙ ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየው እህቶቻችን ከመቼውም ጊዜ በላቀ መልኩ ይበልጥ ትኩረትና እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ ግና ይህን ሁሉ ጫና ተቋቁመው፣ በስንት አቅጣጫ የሚሰነዘርን የጥቃት ፍላፃ ችለው ለኢስላማዊ ትምህርት ልባቸውን የሚከፍቱ፣ ጊዜያቸውን የሚሰጡ እህቶች ላይ ያልተገራ ምላሱ ያመጣለትን በመልቀቅ ይበልጥ ከኢስላማዊ አስተምህሮት የሚያስበረግግ “አስተማሪ” መኖሩ ገርሞ ገርሞ የሚገርም ነው፡፡ ብቻ ስናስተምር የምናተኩርበት ማህበረሰብ ያለበት ወግና ባህል፣ የግንዛቤ ደረጃ፣ በዙሪያው ያሉ ተግዳሮቶች ከግንዛቤ እያስገባን ሊሆን ይገባል፡፡ ያለበለዚያ በአንድ በኩል የምንገነባውን በሌላ በኩል እናፈርሰዋለን፡፡ “እየፈጩ ጥሬ” አይነት ነገር፡፡ ምናልባትም በኛ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድ ከዲን የምናርቃቸው ሰዎች ከኖሩ ያለጥርጥር “እናተርፍበታለን” ባልነው ደዕዋ ከአላህ ፊት እንጠየቅበታለን፡፡ ሲጠቃለል እህቶቻችን በያቅጣጫው የተከፈተውን ጥቃት መቋቋም ይችሉ ዘንድ ከወትሮው በተለየ ኢስላማዊ ግንዛቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አስተማሪዎች ታዲያ ሴቶችን በተለየ ኢላማ ያደረጉ ብዙ ዘመቻዎች እንዳሉ ከግምት በማስገባት የተከፈቱባቸውን ሴራዎች ለማክሸፍ የሚያስችላቸው የእውቀት ትጥቅ ማስታጠቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በአካሄዳቸውም ላይ ይበልጥ ጥንቁቅና አስተዋይ ሊሆኑ ይገባል ብየ አስባለሁ፡፡ አላሁ አዕለም፡፡ አላህ ማስተዋሉን ያድለን፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ነሐሴ 26/2008)