Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የዒድ ሶላት ሁክም ምንድን ነው? አሰጋገዱስ እንዴት ነው


ጥያቄ፡- የኢድ ሶላት ሁክም ምንድን ነው?
መልስ፡- በእኔ አመለካከት የኢድ ሶላት በያንዳንዱ ሰው ላይ ግዴታ (ፈርዱ ዐይን) ነው፡፡ ወንዶች መተው አይፈቀድላቸውም፡፡ ነብዩ  አዘውበታልና፡፡ እንዲያውም ከቤት የማይወጡ  ልጃገረዶችም ሳይቀሩ ለኢድ ሶላት እንዲወጡ አዘዋል፡፡ የወር አበባ ያለባቸውንም ሴቶች ወደ ኢድ ሶላት እንዲሄዱ አዘዋል፡፡ ነገርግን ከመስገጃው ቦታ ገለል ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ጉዳዩ ጠንከር ያለ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አቋም ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ከመሆኑም በላይ የሸይኹል ኢስላም ኢብን ተይሚያም አቋም ነው፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ጁምዓ ሶላት ሁሉ ካመለጠ ቀዷ አይወጣም፡፡ ቀዷ ማውጣት ግዴታ እንደሚሆን የሚያሳይ ማስረጃ የለምና፡፡ በምትኩም ሌላ ሶላትም አይሰገድም፡፡
ሙስሊም ወንድሞቼን የምመክራቸው አላህን እንዲፈሩና ይህንን መልካም ስራ፡- ዱዓን፣ የሰዎች እርስ በርስ መተያየትን፤ መቀራረብን እና መዋደድን ያካተተ ሶላት እንዳይተውት ነው፡፡ ሰዎች የማይጠቅም ወይም ጨወታ ብቻ ለሆነ ስብሰባ ቢጠሩ እየተቻኮሉ ይሄዳሉ፡፡ ታዲያ ይህንን ከአላህ ምንዳ ወደ ሚያገኙበት እና ነብዩ  ወደ ጠሯቸው የሶላት ግብዣ ይበልጥ ተቿክለው መሄድ አልነበረባቸውምን!?
ሴቶች ግን ለዒድ ሶላት ከወጡ ወንዶች ካሉበት ቦታ ራቅ ብለው መቀመጥ አለባቸው፡፡ ለዚህ ሶላት ሲወጡም ተውበውና ሽቶ ተቀብተው ወይመም ተገላልጠው መውጣት የለባቸውም፡፡ ነብዩ ሴቶች ለኢድ ሶላት እንዲወጡ ሲያዟቸው ሴቶቹ ነብዩን ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አንዳዶቻችል ጅልባብ አናገኝም›› ብለው ሲጠይቋቸው ነብዩም ‹‹እህቷ ከጅልባቧ ታልብሳት›› ብለው መሉሱላቸው፡፡[1]  ጅልባብ አባያ የሚመስል ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን ልብስ ነው፡፡ ሴት ጅልባብ ለብሳ መውጣት ግዴታዋ እንደሆነ ይህ ሀዲስ ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም ነብዩ- ጅልባብ የሌላት ሴት ምን ማድረግ እንዳለባት ሲጠየቁ ያላትን ነገር ለብሳ ትውጣ አላሉም፤ ‹‹እህቷ ከጅልባቧ ታልብሳት፡፡›› ነው ያሉት፡፡ ይህም ካሏት ጅልባቦች አንዱን ትስጣት (ታውሰዋት) ማለት ነው፡፡
ኢማሙ ኹጥባ ሲያደርግ ሴቶች የማይሰማቸው ከሆነ ለነሱም ለብቻቸው ኹጥባ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ የሚሰሙ ከሆነ ግን መድገም አያስፈልግም፡፡ ይሁን እንጂ በኹጥባው መጨረሻ ሴቶችን የሚመለከት መልዕክት በማካተት ሴቶችን መገሰጽ፣ መምከርና ማስታወስ የተወደደ ነው፡፡ ነቢዩ - ለወንዶች በኢድ ሶላት ላይ ኹጥባ ካደረጉ በኋላ ወደ ሴቶች በመሄድ ይገስጹና ይመክሩ ነበርና፡፡
ጥያቄ፡- የሁለቱ ኢድ ሶላቶች አሰጋገድ እንዴት ነው?
መልስ- የኢድ ሶላቶች አሰጋገድ ኢማሙ ተገኝቶ ሁለት ረከዓ ያሰግዳል፡፡ መጀመሪያ ለኢህራም ተክቢራ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ስድስት ጊዜ ተክቢራ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ፋቲሃ ቀጥሎም የሱረቱለረ ቃፍ ምዕራፍ ይቀራል፡፡ ይህ መጀመሪያ ረከዓ ላይ ነው፡፡ ለሁለተኛው ረከዓ ሲነሳ ተክቢራ አድርጎ ይቆማል፡፡ ከቆመ በኋላ አመምስት ጊዜ ተክቢራ ያደርጋል፡፡ ከዚያም ፋቲሃን ቀጥሎም ሱረቱል ቀመርን ይቀራል፡፡ እነዚህን ሁለቱን ሱራዎች-ቃፍና አልቀመርንነብዩ- በኢድ ሶላቶች ይቀሯቻ ነበር፡፡[2] ከፈለገም በአንደኛው ረከዐ ላይ ‹‹ሰቢህ ኢስመ-ረቢከል አዕላ››ን በሁለተኛው ረከዓ ላይ ደግሞ ‹‹ሀል-አታከ ሀዲሱል ጋሺያ››ን መቅራት ይችላል፡፡[3] የጁምዓና የኢድ ሶላቶች ሁለት ሱራዎችን ይጋራሉ፡፡ በሁለት ሱራዎች ደግሞ ይለያያሉ፡፡ የሚጋሯቸው ሁለቱ ‹‹ሰቢህ›› እና ‹‹አል-ጋሺያህ›› ናቸው፡፡ የሚለያዩባቸው ሁለቱ ደግሞ ‹‹ቃፍ›› እና ‹‹አል-ቀመር›› ለኢድ ብቻ ሲሆኑ ሱረቱል ‹‹ጁምዓ›› እና ‹‹አል-ሙናፊቁን›› ለጁምዓ ሶላት ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ ኢማሙ እነዚህን ሱራዎች በመቅራት ሱናውን መተግበርና ሰዎችንም ማስለመድ ይጠበቅበታል፡፡ ከሶላት በኋላ ኹጥባ ያደርጋል፡፡ ኢማሙ ነብዩ - እንዳደረጉት በኹትባው ውስጥ ሴቶች ብቻ የሚመለከት በመጨመር መፈጸም ያለባቸውን ትዕዛዛት እንዲፈጽሙ እና መከልከል ካለባቸው ነገሮች እንዲከለከሉ ሊመክራቸው ይገባል፡፡



[1] ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል፡፡
[2] ሙስሊም ዘግቦታል፡፡
[3] ሙስሊም ዘግቦታል፡፡