Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ልጓም አልባ ተረክ!

ልጓም አልባ ተረክ!
መልእክቱ ስለጣፈጣቸው ብቻ ጠንካራ መሰረት የሌላቸውን ቂሳዎች ያለምንም ጥንቃቄ የሚያራግቡ ተራኪዎች የበዙበት ዘመን ላይ ነን፡፡ የአድማጫቸውን አፍ እስከከፈተላቸው ድረስ ያለ ምንም ጥንቃቄ የሰሙትን ሁሉ ያግበሰብሳሉ፡፡ በዚህ ረገድ በሰፊው ከሚራገቡ ቂሳዎች ውስጥ አንዱ የሚከተለው ነው፡-
አንድ ሰው ሚስቱ በቁጣ እየጮኸችበት ቢቸገር ተቆጥቶ ለዑመር ኢብኑል ኸጣብ ሊወቅስ ይሄዳል፡፡ ደርሶ በር ሊያንኳኳ ሲል የዑመር ሚስት በዑመር ላይ ስትጮኽ ይሰማል፡፡ ዑመር ግን አይመልሱም፡፡ ሰውየው “የሙእሚኖች መሪ የሆነው ዑመር ሁኔታ እንዲህ ከሆነ እኔ ማን ነኝ?” ብሎ ሲመለስ ዑመር ወጥተው አዩትና ጠሩት፡፡ “ምን ነበር ጉዳይህ?” ሲሉት “የአማኞች መሪ ሆይ! የሚስቴን ክፉ ስነ-ምግባር እና ምላሷን ማስረዘም አቤት ለማለት ነበር አመጣጤ፡፡ ያንተም ሚስት እንዲሁ ስትሆን ስሰማ ተመለስኩኝ…” አለ፡፡ ዑመርም እንዲህ አሉት፡- “የታገስኳት በኔ ላይ የሷ ሐቆች ስላሉብኝ ነው፡፡ እሷ ምግቤን ታበስላለች፡፡ ልብሶቼን ታጥባለች፡፡ ልጆቼን ታጠባለች፡፡ ይህ ሁሉ ግን በሷ ላይ ግዴታ አይደለም፡፡ በሷ ላይ ነፍሴ ከሐራም ተብቃቅታ ትረካለች፡፡ ስለዚህ ለዚህ ስል ነው የምታገሳት፡፡” ሰውየው በዚህን ጊዜ “የሙእሚኖች መሪ ሆይ! የኔም ሚስት እንዲሁ ናት” አለ፡፡ “ታገሳት ጥቂት ጊዜ ናት” አሉት፡፡
ታሪኩ ከሞላ ጎደል ይሄው ነው፡፡
የአንድን ትውፊት ደረጃ ለማጥናት የቅብብሎሽ ሰንሰለት ወይም ሰነድ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ሰነድ ከሌለው ጉዳዩ ለአቅመ- ምርመራም አልደረሰም ማለት ነው፡፡ ይህ ታሪክም ወደምርመራ ክፍል ለመግባት የሚያስችል ቅድመ-ሁኔታን እንኳን አያሟላም፡፡ ከነጭራሹ ሰነድ የለውም፡፡ በዚያ ላይ ታሪኩን የዘገቡት በሙሉ ደካማነቱን በሚጠቁም መልኩ ነው ያሰፈሩት፡፡ ለምሳሌ አቡ አልለይሥ አስሰመርቀንዲ [ተንቢሁል ጋፊሊን፡ 517]፣ ሱለይማን ኢብኑ ሙሐመድ አልቡጀይሪሚ [ሓሺያህ ዐላ ሸርሒል ሚንሃጅ፡ 3/441-442]፣ ኢብኑ ሐጀር አልሀይተሚ [አዝዘዋጂር፡ 2/80] ከነዚህ ውስጥ አንዳቸው እንኳን ሰነድ አልጠቀሱም፡፡ ሁሉም ለደካማነቱ ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ ነው ያሰፈሩት፡፡
ታሪኩ ደካማ እንደሆነ የሚጠቁሙ ዳሰሳዎችን በቀላሉ ማገኘት ስለሚቻል የፈለገ ማሰስ ይቻላል::