Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሱሑር ምንድን ነው? ፍቺ ፡ የሱሑር ወቅት መቼ ነው?

ሱሑር ምንድን ነው?
ፍቺ ፡
«ሱሑር» ማለት በቋንቋዊ ፍቺው «ከጎህ መቅደድ በፊት» ማለት ሲሆን ሸሪዐዊ ፍቺው ደግሞ «የፆም ወቅት ከመግባቱ በፊት ማለትም ጎህ ከመቅደዱ በፊት የሌሊቱ የመጨረሻ ጊዜ ላይ የሚመገቡት ምግብ» ማለት ነው።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ለፆመኛ ሰው ሱሑርን በመመገብ ላይ ጠንከር አድርገው አዝዘዋል። እርሱን መተውን ደግሞ ኮንነዋል። ሱሑር ምንም እንኳን ግዴታ ባይሆንም፥ ያልተመገበ ሰውም ወንጀል ባይመዘገብበትም መመገቡ ግን አላህ ዘንድ የሚያቃርብ ተወዳጅ ሱንናህ ነው። የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስለ ሱሑር በርካታ ጥቅሞች እና ፋይዳዎችን ዘክረዋል።
1. በረከት
ከታላቁ ሶሓቢ አቡ ሁረይራህ ረዲየላሁ ዐንሁ ተወርቶ በቡኻሪና በሙስሊም እንደተዘገበው መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
«تسحروا، فإن في السحور بركة»
«ሱሑርን ተመገቡ ። በርግጥም በሱሑር ውስጥ በረከት አለ።»
ኢማሙ ነወዊ ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፦
«በሱሑር ውስጥ ያለው በረከት ግልጽ ነው። ፆመኛውን ግለሰብ ብርታት እና ጥንካሬና ይሰጣል። በዚህም ምክንያት ሱሑር ተመጋቢው ለመፆም መነሳሳትን ይጨምርለታል። የሚደርስበትንም የርሃብ ችግር ያቃልለታል።» [ኢማሙ ነወዊ ሸርሕ]
2. ጌታችን ከመላእክቶቹ ጋር ሰላዋት . . .
ከአቡ ሰዒድ አልኹድሪይ ረዲየላሁ ዐንሁ ተወርቶ በኢማም አሕመድ እና ኢብኑ ሒባን እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
« السحور أكله بركة ؛ فلا تدعوه ولو أن يجرع أحدكم جرعة من ماء ؛ فإن الله عز وجل وملائكته يصلون على المتسحّرين »
«ሱሑር ሁሉም ነገሩ በረከት ነው እንዳትተውት። ከውሃም እንኳን አንድ ጉንጭን መጎንጨት ቢሆንም። በርግጥም የላቀው ጌታ እና መላእክቶቹ ሱሑር ተመጋቢው ላይ ውዳሴን ያወርዳሉ።»
[ሸይኹል አልባኒ በሶሒሕ አትተርጚብ ቁ.1070 ላይ ሐሰን ብለውታል።]
3. ክርስቲያኖችና አይሁዶች ሱሑርን አይመገቡትም!
ከዐምር ቢን አልዐስ ረዲየላሁ ዐንሁ ተወርቶ በኢማም ሙስሊም ረሒመሁላህ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አሉ፦
«فصل ما بين صيامنا وصيام أهل الكتاب، أكلة السحر»
«በእኛ ፆም እና በኪታቡ ባልተቤቶች (የሁዳ እና ክርስቲያን) ፆም መካከል ያለው ልዩነት ሱሑርን መመገብ ነው።»
4. ሱሑር ቀላል ነው።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
«تسحروا و لو بجرعة من ماء»
«ሱሑርን ተመገቡ አንዲትን የውሃ መጎንጨት ቢሆንም እንኳን።»
በሌላ ሐዲሥ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፦
«نعم سحورالمؤمن التمر»
«ለአማኝ መልካም ሱሑሩ ቴምር ነው።»

የሱሑር ወቅት መቼ ነው?
የሱሑር ወቅት መቼ እንደሆነ ከመነጋገራችን በፊት ማውሳት ያለብን አንድ ወሳኝ ነጥብ አለ፦
ፈጅር (ጎህ) ሲባል ሁለት አይነት አለ።
1) የመጀመሪያው ፈጅር : «ፈጅሩልካዚብ» ወይንም «ፈጅሩል ኪዝብ» (የሐሰት ጎህ) ተብሎ ይጠራል። ይህ ፈጅር የሱብሒን ሶላትን መስገድ ሐላል አያደርግልንም። ለፆመኛም ደግሞ ሱሑርን ከመመገብ አይገታውም። ይህ ጎህ በስተምስራቅ የሚታይ ቋሚ የብርሃን አይነት መስመር ሲሆን ፀሃይ የመውጣቷን አምሳያ ወጋገን ስለሚያሳይ ሆኖም ግን የውሸት በመሆኑ «የሐሰት ጎህ» በመባል ይታወዋል።
2) ሁለተኛው ፈጅር: «ፈጅሩልሷዲቅ» ወይንም «እውነተኛው ጎህ» በመባል ይታወቃል። ይህ ጎህ በፆመኛ ላይ ምግብን መብላት እርም ያደርጋል። በተጨማሪም የሱብሒን ሶላት ለመስገድ ያብቃቃል። በመጀመሪያው ጎህ ማለትም በሐሰተኛው ጎህ ላይ ግን የተሰገደ የሱብሒ ሶላት ተቀባይነት አይኖረውም። ይህ እውነተኛው ጎህ በስተምስራቅ የሚመጣ አግድም ከሰማዩ ጋር የተቆራኘ ትክክለኛ ቀይ ብርሃን ነው። የሐሰት ጎህ ላይ የሚታየው ብርሃን በቆይታ የሚጠፋ ሲሆን ይህ ግን እየቆየ እየሰፋ ይሄዳል። በሃገራችን ቋንቋ «ጎህ ቀደደ» በመባል ይታወቃል።
በመሆኑም በረሱል ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጊዜ ሁለት የፈጅር አዛን ይደረግ ነበር።
የመጀመሪያው አዛን ከለሊቱ የመጨረሻ ክፍል ላይ ምናልባትም ሐሰተኛውን ጎህ ያጠቃለለ ጊዜ ላይ የሚደረግ የነበረ ሲሆን ይህ አዛን የሚደረገው ለይል ሶላት ለቆመ ሰው የእውነተኛው ፈጅር ጊዜ መድረሱን በማወቅ ሶላቱን ቶሎ ጨርሶ ወደ ሱሑር ገበታ እንዲቀርብ፤ የተኛም ካለ ከእንቅልፉ ተነስቶ ሱሑርን እንዲመገብ የሚያሳስብ አዛን ነው።
ይህ አዛን የለሊቱ የመጨረሻ ክፍል ላይ ስለሚደረግ ይህን አዛን የሚሰማ ሰው በዚያ ሰአት ሱሑር መብላቱ ተወዳጅ ሱና ነው።
የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በሐዲሣቸው ፦
«لا يزال الناس بخير ما عجلوا الفطر وأخروا السحور»
«ሰዎች ሱሑርን እስካዘገዩ እና ፍጡርን እስካቿከሉ ድረስ ከመልካም ነገር አይወገዱም።» ብለዋል። [ቡኻሪና ሙስሊም]
በመልእከተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጊዜ ላይ የመጀመሪያውን አዛን የሚለው ታላቁ ሶሓቢ አባታችን ቢላል ኢብኑ ረባህ የነበረ ሲሆን እርሱ የሌሊቱ የመጨረሻ ክፍለ ጊዜ ላይ አዛን በማለት ሰዎችን የሌሊቱ ክ/ጊዜ እያበቃ መሆኑን ያሳውቅ ነበር።
«إن بلالا يؤذن بليل، فكلوا واشربوا حتى يؤذن أذان ابن أم مكتوم»
መልእከተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦
«ቢላል እኮ አዛን የሚለው በሌሊት ነው። ኢብን ኡሙ መክቱም (ሁለተኛውን) አዛን እስኪል ድረስ ብሉም ጠጡም።»
እኛ ሃገር እና በሌሎችም የመዝሃብ ጭፍን ተከታይነት የሚስተዋልባቸው ሃገራት ላይ ይህ የመጀመሪያው የፈጅር አዛን ሱና "ተሶሐሩ ..." በሚል ጥሪ ተተክቷል። አንዳንድ በሱና ላይ የቆሙ እንደ ሱዑዲ ያሉ ሃገራት ላይ ግን ይህ ሱና እስከዛሬ ተፈፃሚ ነው።
ሁለተኛው አዛን ደግሞ እውነተኛው ንጋት ወይንም ፈጅሩልሷዲቅ ሲገባ የሚባለው አዛን ሲሆን ይህ አዛን ሲሰማ ሁሉም የሚመገበውን ምግብ የማቆም ግዴታ አለበት። የሱብሒ ሶላትም መግባቱን አውቆ ወደ መስጂድ ማምራት አለበት።
የላቀው ጌታችን አላህ ሱብሓነሁ ወተዓላ በተከበረው ቁርኣን እንዲህ ይላል
فكلوا واشربوا حتى يتبين لكم الخيط الأبيض من الخيط الأسود من الفجر
((ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለእናንተ እስከሚገልጽላችሁ ድረስ ብሉ፤ ጠጡም፡፡))
[በቀራህ 187]
አሽሸይኽ ሙሐመድ ቢን ሷሊሕ አልዑሠይሚን (ረሒመሁላህ) እንዲህ ብለዋል፦
والفجر الأوَّل يخرج قبل الثَّاني بنحو ساعة، أو ساعة إلا ربعاً، أو قريباً من ذلك
አንደኛው ጎህ ከሁለተኛው ጎህ በአንድ ሰአት አካባቢ ወይንም እሩብ ጉዳይ በሆነ ሰአት ወይንም ከዚያ በቀረበ ይወጣል።
ይህ ሁለተኛ አዛንን የሰማ ማንኛውም ፆመኛ መመገብ ማቆም በርሱ ላይ ግዴታ ይሆንበታል። ሆኖም በአጁ ውሃን በመጠጫ አቃ ይዞ ወይንም በአፉ ውስጥ ምግብ ይዞ አዛን ቢልበት ከውሃው የሚፈልገውን ያህል እንዲጠቃቀም አፉም ስር ያለውን ብቻም ከመትፋት ይልቅ እንዲውጠው ኢስላም ገር አድርጎልናል። [ፈትዋ ኢብኑልዑሠይሚን፣ ፈታዋ ሸይኽ ሙቅቢል]
መልእከተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፦
«إذا سمع أحدكم النداء والإناء على يده، فلا يضعه حتى يقضي حاجته منه»
«አንዳችሁ ጥሪን (አዛን) ብትሰሙና እጃችሁ ላይ ኩባያው (መጠጫው እቃ) ካለ ከርሱ የሚያሻውን ያህል እስኪጠቃቀም ድረስ አያስቀምጠው።» [አሕመድ፣ አቡ ዳውድ፣ ሓኪም]
አቢ ኡማማህ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዳወራው
«أقيمت الصلاة والإناء في يد عمر، قال: أشربها يا رسول الله؟ قال: نعم، فشربها»
«የፈጅር ሶላት በቆመች ጊዜ (ሁለተኛው አዛን በተባለ ጊዜ) በዑመር እጅ ኩባያ ነበረ። “የአላህ መልእክተኛ (አዛን ሲባል እጃቸው ላይ ኩባያ ኖሮ ከኩባያው ውሃውን) ጠጥተው ነበርን?” ብዬ ስጠይቀው ”አዎን” አለኝና ጠጣ።»
[ተፍሲር ኢብኑ ጀሪር በሐሰን ሰነድ የተዘገበ]
በተረፈ ኢስላም ሱሑርን መመገብ አግራርቶልን ሲያበቃ ፆምን በቸልተኝነት ወይንም ሆን ብሎ ያለምንም አስገዳጅ ሁኔታ መፍታትን አጥብቆ ከልክሏል። ከትላልቅ ወንጀሎችም ይካተታል።
አላህ መጪውን ረመዷን በሰላም አድርሶን የምንተቀምበት ያድርገን
አሚን