Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

3 አንቀፆች ከቁርዓን ላይ ለአእምሮ ባለቤቶች ሽርክንና ባለቤቶቹን በተመለከተ


3 አንቀፆች ከቁርዓን ላይ ለአእምሮ ባለቤቶች ሽርክንና ባለቤቶቹን በተመለከተ፡፡
የአላህ ባርያዎች ሆይ! ብቸኛው አጋር የሌለው ጌታችን ስለራሱ ጌትነትና ተመላኪነት፣ ብሎም በእርሱ ላይ የሚያጋሯቸው ምንም ማድረግ እንደማይችሉ እሱም ብቸኛው ፈጣሪ፣ ህያው አድራጊ፣ ሲሳይን ለጋሽ፣ ሰጪ ነሺ መሆኑን እንዲህ ሲል ይነግረናል፡፡
1ኛ አንቀፅ
ٱللَّهُ ٱلَّذِى خَلَقَكُمْ ثُمَّ رَزَقَكُمْ ثُمَّ يُمِيتُكُمْ ثُمَّ يُحْيِيكُمْ ۖ هَلْ مِن شُرَكَآئِكُم مَّن يَفْعَلُ مِن ذَٰلِكُم مِّن شَىْءٍ ۚ سُبْحَٰنَهُۥ وَتَعَٰلَىٰ عَمَّا يُشْرِكُونَ
አላህ ያ የፈጠራችሁ፣ ከዚያም ሲሳይን የሰጣችሁ፣ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ሕያው የሚያደርጋችሁ ነው፡፡ ከምታጋሯቸው (ጣዖታት) ውስጥ ከዚህ ነገር አንዳችን የሚሠራ አለን? ለአላህ ጥራት ይገባው፡፡ (በእርሱ) ከሚያጋሩትም ሁሉ ላቀ፡፡
እስቲ አለም ላይ ሰዎች በአላህ ላይ ከሚያጋሯቸው ያለ ፍላጎት ከሚመለኩት ጭምር ከላይ ያለውን መስራት የሚችል አለን?
ለምሳሌ
ጂብሪል (አለይሂ ሰላም)፣ ሚካኢል (አለይሂ ሰላም)፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም)፣ ነብየላህ ኢሳ (አለይሂ ሰላም)፣ ነብየላህ ኡዘይር (አለይሂ ሰላም)፣ አልይ፣ ሁሴን፣ ፋጢማ፣ ዘይነብ፣ ነፊሳ፣ ….. (ረድየላሁ አንሁም)፣ ሸይኽ አብድልቃድር ጀይላኔ ረሂመሁላህ፣ በደዊ፣ ዱሱቂ፣ ጂኖች፣ ኑር ሁሴን፣ የቦረናው ሸይኽ፣ አብሬት፣ ቃጥባሬ፣ አልከሶ፣ …… እና የመሳሰሉት እነዚህ ሁሉ ‹‹መፍጠር፣ ሲሳይ መለገስ፣ መግደል፣ ሕያው ማድረግ›› ይችላሉን?
በፍፁም፡፡ ጭራሽ እነሱ ሁሉ ፍጡር ናቸው፡፡ የፈጠራቸው ብቸኛው አላህ ነው፡፡ ይሞታሉ ብቻውን ቀሪ የሆነው የማይሞተው አላህ ይቀሰቅሳቸዋል፡፡
ቀጠለና አላህ እንዲህ ሲል የመከራና የችግር ምክንያት የሆኑት የሰው ልጆች እራሳቸው መሆኑን እንዲህ ሲል ጠቀሰ
2ኛ አንቀፅ
ظَهَرَ ٱلْفَسَادُ فِى ٱلْبَرِّ وَٱلْبَحْرِ بِمَا كَسَبَتْ أَيْدِى ٱلنَّاسِ لِيُذِيقَهُم بَعْضَ ٱلَّذِى عَمِلُوا۟ لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ
የሰዎች እጆች በሠሩት ኃጢኣት ምክንያት የዚያን የሠሩትን ከፊሉን ያቀምሳቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባሕር ተገለጠ፤ (ተሰራጨ)፡፡ እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና፡፡
እስቲ አለምንና ስራችንን እንፈትሽ የአላህ ቤት ተብሎ የሚጠራው መስጂድ ውስጥ ነው አይደለም በአላህ ላይ ማጋራት የሚፈፀመው?
ቢድዐው አላህን ማመፁ በምድር ላይ ተስፋፍቷል ወይንስ አልተስፋፋም?

3ተኛ አንቀፅ
قُلْ سِيرُوا۟ فِى ٱلْأَرْضِ فَٱنظُرُوا۟ كَيْفَ كَانَ عَٰقِبَةُ ٱلَّذِينَ مِن قَبْلُ ۚ كَانَ أَكْثَرُهُم مُّشْرِكِينَ
«በምድር ላይ ኺዱ የእነዚያንም በፊት የነበሩትን ሰዎች መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ» በላቸው፡፡ አብዛኞቻቸው አጋሪዎች ነበሩ፡፡

የአብዛኛዎች መጥፊያ ሽርክ (በአላህ ላይ ማጋራት) እንደነበረ አላህ በግልፅ አስቀመጠ፡፡ እስቲ እራሳችንን፣ ዙርያችንን እንፈትሽ፡፡ ሽርክና ቢድዐ ብዙ ቦታዎች ላይ ነግሰዋል፡፡
ታድያ ይህ የመጥፊያ ሰበብ አይሆነንምን?
አላህ ሆይ! ቃልህን ከሚያነቡት፣ ከሚገሰጡበት፣ በሱም ሰርተው ምስክር ከሚሆንላቸው አድርገን፡፡ ቁርዓን ከሚመሰከርባቸው አታድረገን፡፡


Sadat Kemal Abu Meryem