Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የኢስላም እንግዶችን ተዋወቁ!!


የኢስላም እንግዶችን ተዋወቁ!!
መልእክተኛው ወደ መዲና ሂጅራ ካደረጉ በኃላ የምእመናን የአምልኮ አቅጣጫ በይተል መቅዲስ የነበረ ሲሆን፤ አላህ ወደ መካ እንዲዞሩ ሲያዛቸውና ሲቀየር ቀድሞ በቂብላው አቅጣጫ የነበረው ግድግዳ ብቻውን ቀረ። መልእክተኛው ይህን ባዪ ግዜ ጣሪያ እንዲደረግለት አዘዙና ኢስላምን ከጅለው ለተሰደዱና ማረፊያ ለሌላቸው ደሀ አማኞች ማረፊያ አደረጉት። በሌሎች አቅጣጫዎች የሚከልል ግድግዳ ባይኖረውም ከፀሀይ የሚከላከል ጥላ ስላለው ብዙ ችግረኞች አረፉበት። ቦታውም አስ’ሱፋህ الصفة ወይም አዝ’ዙላህ الظلة ተብሎ ይጠራ ጀመር። እነዚህ ችግረኛ የአላህ ባሮችም አህሉስ’ሱፋህ أهل الصفة በመባል ታወቁ።
አልቃዲ ኢያድ እንዲህ ብለዋል፤
الصفة ظلة في مؤخر مسجد رسول الله - صلى الله عليه وسلم - يأوي إليها المساكين، وإليها ينسب أهل الصفة .
«አስ’ሱፋህ በመልእክተኛው መስጂድ የኃላ ክፍል የሚገኝ ጥላ ሲሆን ለችግረኞችም ማረፊያ ነበር። አህሉስ’ሱፋህ ስያሜያቸውን ያገኙትም ከዚሁ ነው።»

አህሉስ’ሱፋህ የኢስላም እንግዶች بأضياف الإسلام ይባሉ ነበር። ታላቁ ሰሀቢይ አቡ ሁረይራ እንዲህ ብሏል፤
..وأهل الصفة أضياف الإسلام، لا يأوون على أهل ولا مال ولا على أحد (البخاري)
አህሉስ’ሱፋህ የኢስላም እንግዶች ነበሩ፤ የሚጠጉበት ቤትም ይሁን ቤተሰብ የላቸውም።
የመጀመሪያዎቹን ስደተኛ መየሀጅሮች በተለይም እስከ በድር ዘመቻ ድረስ አንሳሮች በየቤታቸው ማስተናገድ ችለው ነበር። ኃላ ግን የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ መጠለያ ያጣ ሁሉ ሌላ አማራጭ እስኪያገኝ የሚጠለለው በዚህ ስፍራ ነበር።
ከአህሉስ’ሱፋህ መካከል ታላቁ ሰሀብይ አቡ ሁረይራ ይገኝበታል። መክእክተኛው ለአህሉስ’ሱፋህ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ ነበር። ከሚመጣላቸውን ሰደቃና ስጦታ እነዚህ የአላህ ባሮች ይቋደሱ ነበር። አቡ ሁረይራም በቅርብ የሁሉንም ሁኔታ ስለሚያውቅ መልእክተኛው በሱ በኩል ለከፊሎቹ ጥሪ ያደርጉ ነበር። እነዚህ መሳኪን ባብዛኛው የተሟላ ልብስ ያልነበራቸው እንደነበሩ አቡ ሁረይራ ሲገልፁ « ሰባ የሚሆኑ መሳኪኖች በዚህ ቦታ ተጠልለው ነበር፤ ከነሱ መካከል ሽርጥና ኩታ የሚያገኝ አልነበረም፣ ቁራጭ ጨርቅ ብቻ ጣል ያደርጉ ነበር። »
አህሉስ’ሱፋህ ከነበረባቸው ችግር ጋር በመዲና መስጅድ ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ በብዛት ኢባዳ በማድረግ መስጅዱን ያስጌጡ ድንቅ የኢስላም ልጆች ነበሩ። ከመልእክተኛው ብዙ የመማር እድል እንዳገኙም አቡሁረይራ መልካም ማሳያ ናቸው።
ይህ በፎቶው ላይ የምትመለከቱት በመስጅድ አነበዊ የቀድሞው ይዞታ የሚገኘውና አህሉስ’ሱፋህ
የነበሩበት ክልል ወቅታዊ ይዞታ ነው።
አቡሁረይራ፣ አህሉስ’ሱፋህ እና ሁሉንም ሰሀቦች
አላህ ስራቸውን ይውደድላቸው።
رضي الله عن أبي هريرة ، وعن أهل الصفة، وعن جميع الصحابة أجمعين ..
وصلى الله وسلم على سيدنا محمد وآله وصحبه وسلم
© ተንቢሀት