Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ታጋሾችን አበስራቸው

«ታጋሾችን አበስራቸው›› (2:155)
ትዕግስት የሰው ልጅ ሊኖረው ከሚገቡ ድንቅ ስብዕናዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ በአላህ ያመኑ ሙዕሚኖች ሊሸለሙበት የሚገባ ውድና ድንቅ ጌጥ ነው፡፡ አላህ በተለያዪ የቁርአን አንቀፆች ስለ ትእግስ አውስቷል መልዕክተኛው በሀዲሳቸው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፣ በህይወታቸውም ብዙ ስቃይና መከራዎችን በትእግስት በማለፍ ተግባራዊ ትምህርት ሰጥተው አሳይተዋል፡፡ የሰው ልጅ በህይወቱ አንዴ በችግርና ሰቆቃ እየታሸ ሌላ ጊዜ ድሎትና ምቾት ፈንጠዝያ እየተፈተነ የሚኖር ፍጡር ነው።
አምላካችን አላህ በተከበረ ቃሉ ቁርአን ስለ ሶብር እንዲህ ብሏል፦
‹‹ከፍርሃትና ከረኃብም በጥቂት ነገር፣ ከገንዘቦችና ከነፍሶችም፣ ከፍራፍሬዎች በመቀነስ በእርግጥ እንፈትናችኃለን፡፡ ታጋሾችንም (በጀነት) አበስራቸው››
(አል በቀራህ:155)
‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ ታገሱ››
(አል-ዒምራን፡200)
የኢስላም ሊቃውን አንድ ሰው አላህ መልካም ችሮታውን ውሎለት ቢያመሰግን ይሻለዋል ወይስ ፈተና ገጥሞት በዚያ ላይ ቢታገስ በሚለው ሀሳብ ላይ የተለየዩ ሀሳቦችን ከሰነዘሩ ከባድ ልዩነትን ካንፀባረቁ በኃላ በመጨረሻ የደረሱበት መቋጫ ሀሳብ ግን በችግር ላይ መታገስ ይሻለዋለዋል የሚል ነበር።
ምክንያቱም ታላቁ አምላካችን እንዲህ ብሏልና ነው፦
‹‹ታጋሾቹ ምንዳቸውን የሚሰጡት ያለግምት ነው›› (ዙመር፡10)
ያለ መለኪያ፣ያለ ሚዛን ለሰብረኞች ምንዳቸውን ይሰጣቸዋል፡፡ አላህ ካዘጋጃቸው ምንዳዎች ለታጋሾች ከተዘጋጀው የሚበልጥ ምንደ ያለው የለም፡፡
ምንዳ የሚባለውን ነገር ለምሳሌ እንደ "ፍሬ" አድርገን ብንወስደው አመስጋኞች ከፍሬው ተቆጥሮ ሲሰጣቸው ታጋሾች ግን እየታፈሰ ያለገደብ ይሰጣቸዋል።
ስለዚህም ታገስ ምንዳህን ያለ ሀሳብ ያለ ገደብ እፈስ!
‹‹የታገሰና ምህረት ያደረገም ሰው ይህ ከምርሮቹ (ከተፈላጊዎቹ) ነገሮች ነው፡፡›› (ሹራ፡43)
‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስና በሶላት ተረዳዱ፡፡ አላህ ከታጋሾች ጋር ነውና››(አል በቀራ፡153)
የአኼራን ምንዳን በመፈለግ ነፍስን ከመጥፎ በመከልክል አላህን ከማመፅ በማቀብ ታገዙ፡፡
‹‹ከእናንተም ታጋዮቹንና ታጋሾቹን እስከምናውቅ፣ ወሬዎቻችሁንም እስከምንገልፅ ድረስ በእርግጥ እንሞክራችኃለን›› (ሙሀመድ፡31)
ይህ ማለት እውነተኛው ታጋሽ አማኝ ከውሸተኛው እስከሚለይ ድረስ ላማለት ነው፡፡ ስለዚህ አማኞች ነቃ ብለው ራሳቸውን ሊፈትሹ ይህን ፈተና ለማለፍ ቀን ከሌት ሊጥሩ ይገባል! ለዚህም ትእግስት ያስፈልጋልና ታገሱ!
‹‹ከመልዕክተኞች የቆራጥነት ባለቤቶች የኾኑት እንደ ታገሱ ሁሉ ታገስ፡፡››(አል-አህቃፍ፡35)
የቆራጥነት ባለቤት የሚባሉት (ኑህ ፣ ኢብራሂም ፣ ሙሳ ፣ ዒሳ ፣ ሙሀመድ) (የአላህ ሰላምና እዝነት በእነርሱ ይሁን)
‹‹ለጌታህ ፍርድም ታገስ››(አል-ጡር፡48)
‹‹ታገስም፤ መታገስህም በአላህ (ማስቻል) እንጂ አይደለም››(አል-ነህል፡127)
‹‹ታገሱ፤ አላህ ከትዕግስተኞች ጋር ነውና፡፡››(አል-አንፋል፡46)
‹‹ከበፊትህም መልዕክተኞች በእርግጥ ተስተባበሉ፡፡ በተስተባበሉትም ነገርና በተሰቃዩት ላይ እርዳታችን እስከመጣላቸው ድረስ ታገሱ፡፡››
(አል-አንዓም፡34)
አሁንም ተገስ የኢስላምና የሙስሊሞች ጠላቶች ሊቀጥፉብህ ሊበድሉህ ይችላሉ ይችላሉም አይደለም ይበድሉሀል! በድለውሀልም! በዚህም ላይ ግን ጌታህ ታገስ ብሎሀልና!
ስለዚህም ታገስ!
ሶብር ሶስት ክፍሎች አሉት፡-
1 የአላህ ትዕዛዝን በመፈፀም ላይ ትዕግስት ማድረግ፡፡
2 አላህ ክልክል ባደረጋቸው ነገሮች ላይ (በመራቅ) መታገስ፡፡
3 በአላህ ውሳኔ ላይ ሶብር ማድረግ፡፡ (መጥፎ የተባሉ ነገሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ የአላህ ውሳኔ መሆኑን አውቆ በፀጋ መቀበል)
‹‹በጊዜያቱ እምላለሁ፡፡ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ውስጥ ነው፡፡ እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ በእውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ፡፡>> ››(አል-ዐስር፡1-3)
መልዕክተኛው (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ስለ ሶብር ባማራ አንደ በታቸው እንዲህ ብለዋል፦
ከአቢ ማሊክ ሀሪስ ኢብን ዓሲም አል-አሽዓሪይ አላህ መልካም ስራውን ይውደድለት እንዳለው የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹ትዕግስ አንፀባራቂ ነው››
(ሙስሊም ዘግበውታል)
አማኞች በትእግስት ብርሀን አንፀባርቀው የጠላትን ዓይን ደም ሊያለብሱ ይገባል! እንጂ በሀዘን ፅልመት ተውጠው የጠላቶች ፊት እንዲያበራ ሊያደርጉ አይገባም! ስለዚህ አብሽሩ ታገሱ!
ትዕግሰት ለተስተካከለ ኢማን መገለጫ ነው፡፡ ምክንያቱም ትዕግስት ነፍስን በእጅጉ በመታገል እንጂ የማይገኝ በመሆኑ ነው፡፡
ከአቢ የህያ ሱሀይብ ኢብን ሲናን አላህ መልካም ስራውን ይውደድለትና እንደተወራው የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹የሙእሚን ጉዳይ ያስገርማል! ጉዳዩ በጠቅላላ ለእርሱ ኸይር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሙዕሚን እንጂ ለማንም አይሆንም፡፡ መልካም ነገር ሲገጥመው ያመሰግናል በዚህም መልካም ይሆንለታል፡፡ መጥፍ (ችግር) ሲገጥመው ይታገሳል ለርሱም ኸይር ይሆንለታል፡፡››(ሙስሊም ዘግበውታል)
ምንኛ ያማረ ነገር ነው! ጉዳይህ ሁሉ ኸይር ነው ተብሏል ታዲያ የምን ጭንቅ ነው! ታገስ! አላህ ከሙእሚኖቹ ጎራ ይደብልቀን!
ከዚህ ሀዲስ በመልካም ጊዜ ማመስገንና በችግር ጊዜ መታገስን ያስተምረናል፡፡ ይህን ማድረግ የቻለ የሁለቱንም ሀገር ደስታ ይጎናፀፋል፡፡
ከአነስ ኢብኑ ማሊክ እንደተወራው
‹‹ሰብር በሀዘን የመጀመሪያ ክፍል ነው›› (ቡኻሪ ሙስሊም ዘግበውታል)
ስለዚህ በትኩሱ ጊዜ ታገስ!
በሌላ ሀዲስም፦
‹‹አላህ እንዲህ ብላል ባሪያዬን ሁለቱ ተወዳጆቹን (ዓይኖቹን) በመውሰድ ከፈትኩት በዚያም ከታገሰ በምትካቸው ጀነትን እሰጠዋለሁ›› (ቡኻሪ ዘግበውታል)
ታገሱ! አላህ ከታጋሾች ጋር ነው!
(አቡ ሀማድ ሀምሌ 28/07)

Post a Comment

0 Comments