Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ልባችን በኢማን እንዲፈካ እይታችንን እንስበር !


ልባችን በኢማን እንዲፈካ እይታችንን እንስበር!

የአላህ መልእክተኛ ባልደረቦቻቸውን እንዲህ በማለት አስጠነቀቁ... {መንገዶች ላይ መቀመጥን ተጠንቀቁ} ሰሃባዎችም፤ መንገድ ላይ አለመቀመጥማ አይሆንልንም።
{እንግዲያውስ መቀመጣችሁን ካልተዋችሁ የመንገዱን ሃቅ ጠብቁ} ሰሃባዎች የመንገድ ሃቁ ምንድን ነው? ብለው ጠየቁ {አይንን መስበር፣ ከተንኮል መቆጠብና ሰላምታን መመለስ} ብለው ነገሯቸው ።
ያልተፈቀደን ነገር ማየት የሚያመጣቸው በርካታ ችግሮች አሉ። በተለይ አሁን ባለንበት ዘመን አደጋው ከባድ ነው።

አል ኢማም ኢብን አልቀይም አል ጀውዚ አድ’ዳእ ወድ’ደዋእ በሚለው መፅሃፋቸው እንዲህ ብለዋል፤ «ያልተፈቀደን ነገር ተረጋግቶ ማየት የዝሙት ቀስቃሽና ፖስተኛ ነው። እይታን መቆጣጠር ዋና የሆነውን ብልታችንን መጠበቅ ነው። አይኑን ልቅ ያደረገ የጥፋትን ጉድጓድ ይዞት ይነጉዳል።»

ኢብን አልቀይም ረሂመሁላህ ሲቀጥሉ «ማየት የክስተቶች ሁሉ መሰረት ናት። ያልተፈቀደን ነገር ማየት አደጋን ይወልዳል። አደጋ ፍላጎትን መውለዱ ነው። ፍላጎት ስሜትን ይወልዳል። ስሜት ፍላጎትን ያበረታል። እየጠነከረ ይመጣና ለመተግበር ቆራጥ አቋም ይያዛል። በዚህ ጊዜ ማንም ከልካይ አይኖረውም። "ኋላ ከሚፈጠሩ ችግሮች ከመታገስ አንድን ነገር ከመነሻው መቆጣጠርና መታገስ ይቀላል" » ይባላል።

ለመሆኑ አይንን መስበር ያለውን ፋይዳ ያውቃሉ??
1) ልባችንን ከፀፀት እንጠብቃለን። አይኑን የለቀቀ ፀፀቱ ይበዛል። በቀልብ ላይ ከሚከሰቱ በሽታዎች ከባዱ የሚመጣው እይታን ልቅ ከማድረግ ነው። አይን እይታውን ባራዘመ ቁጥር ቀልብ የማይገባውን ይመኛል። ይህም ልባችንን ክፉኛ ይጎዳዋል ።

2) አይንን መልቀቅ ጨለማን እንደሚያከናንበን ሁሉ፤ አይንን መስበር ለቀልባችን ብርሃንን ያወርሳል። ይህ ብርሃን አካላችን ሁሉ ያበራል፣ ከሀራምም ለመጠበቅ ውስጣዊ ብርታትን ይለግሳል።

ይህ ሁሉ ተቃራኒ ፆታን ከማየት አንፃር ያለ ነው። ዛሬ ዛሬ ግን የኢንተርኔት ፈተና እይታን ከመገደብ አንፃር ስር የሰደዱ ችግሮችን አስከትሏል። ብዙዎችን ከጨዋ ማንነታቸው ነጥሎ፣ ከኢማን አድማስ አርቆ፣ ከኖሩት ጣፋጭ የኢማን ህይወት ጋርዶ፣ የልብ ሰኪናን አሳጥቶ እራሳቸውን እንዲጠሉ አድርጓቸዋል። ወደ አላህ ለመመለስ ይሞክራሉ፤ ነገር ግን እይታቸውን ገድበው ጥቂት ከቆዩ በኃላ ፈተናውን ማሸነፍ ተስኗቸው ተመልሰው ወደ ጥፋት ህይወት ይዘፈቃሉ። በርግጥም ሁነኛ መፍትሄ ያሻቸዋል።

☞ “ምን ተሻለን ታዲያ?”

መፍትሄ አንድ፦ ማግባትን የሚስተካከል መፍትሄ አይኖርም፤ ማግባት ከሀራም ለመጠበቅ ብርቱ ፍላጎት ከታከለበት ከሀራም ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው። ብሎም በኢማን መሰላል ላይ ሽቅብ ለመውጣት ያስችላል።

መፍትሄ ሁለት፦ ሱና የሆኑ ጾሞችን ማብዛት፣ ዘወትር ወደ አላህ መመለስ፣ ከሌሊቱ ክፍል ጥቂት ግዜ በመውሰድ ለአላህ አቤት ማለት።

ከዚና ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥፋቶች ደጋግመው የሚፈትኑ ናቸው። በመሆኑም እንዳው አላህ ያንሳውና በመደጋገም ብንፈተን እንኳ መላልሰን ወደ አላህ ከመመለስ እንዳንቦዝን፥ እንዳንሰለችም! ፅናትንም እንለማመድ። ፍላጎታችን የፀና ከሆነ አላህ ብርታቱን ይለግሰናል። ይህ ብቻም አይደል፤ በሌሊቱ ክፍል ለቅሶን እናሰማው፤ “ቢያየኝም ምንም አያመጣም’ ብለህ በግዛቱ በፀጋዎቹ እየኖርክ ወንጀል ስትፈጽም ያልቸኮለብህ አምላክ “እያየኝ ነው” ብለህ ከልብ ስንማፀነው አይጨክንም!!

ألا يا عين ويحك أسعديني بغزر الدمع في ظلم الليالي
لعلك في القيامة أن تفوزي بخير الدار في تلك العلالي

መፍትሄ ሶስት፦ ቁርአንን በተመስጦ መቅራት፣ የሙታንን መቃብሮችን መጎብኘት፣ በሽተኞችን መጠየቅ፣ ሞትን ደገሰግሞ ማስታወስ። እንደ ኩባያ የተገለበጠ ልብን ወደ ቦታው ለመመለስ ነገን ማስታወስ ይገባል:: አላህ በቁርአን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች “እኔን ፍሩኝ” እያለ ያስጠነቅቃል:: አንዲት አያ ላይ ግን “እኔን ፍሩኝ” ብሎ ብቻ አላለፈም:: በአንዲት አንቀፅ ሁለት ግዜ “እኔን ፍሩኝ” አለ፤ በመካከላቸውም “ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት” የሚል ከባድ ማሳሰቢያ አኖረ:: ወዳጆች ሆይ! ነገ እኮ ከዛሬ ቀጥሎ ነው። ዛሬ የስሜት ባህር ውስጥ ነው ያለኸው፥ ለነገ የሚያዘጋጅ ትርፈ ግዜ ይኖረን ይሆን?

☞ አይነተኛው መፍትሄ፦ እይታን መገደብ ከማይጨበጥ አለም ለመውጣት አይነተኛ መፍትሄ ይሆናል::
እይታን ለመገደብ ትግል ያስፈልጋል።

ልታገኛት የማትመጥንህን ፋሲቅ ሴት በየመስኮቱ የምታሳደው ወንድሜ ሆይ! “ጌታዬ ሆይ የተሻለችውን ለግሰኝ” ብለህ አንገትህን ብትደፋ ነገ አንገቶች በሚደፉበት ቀን የአንተን አንገት ቀና የሚያደርግ መልካም ስራ ሊሆንህ ይችላል:: የጌታህን አደራ አትዘንጋ!

ﻗُﻞ ﻟِّﻠْﻤُﺆْﻣِﻨِﻴﻦَ ﻳَﻐُﻀُّﻮا ﻣِﻦْ ﺃَﺑْﺼَﺎﺭِﻫِﻢْ ﻭَﻳَﺤْﻔَﻈُﻮا ﻓُﺮُﻭﺟَﻬُﻢْ ۚ ﺫَٰﻟِﻚَ ﺃَﺯْﻛَﻰٰ ﻟَﻬُﻢْ ۗ ﺇِﻥَّ اﻟﻠَّﻪَ ﺧَﺒِﻴﺮٌ ﺑِﻤَﺎ ﻳَﺼْﻨَﻌُﻮﻥَ

«ለምእመናን ንገራቸው፦ ዓይኖቻቸውን (ያልተፈቀደን ከማየት) ይከልክሉ፤ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፤ ይህ ለነሱ የተሻለ ነው፤ አላህ በሚሠሩት ሁሉ ውስጥ ዐዋቂ ነው፡፡

ፕሮፋይል ፎቶዎችን ስትበረብሪ፣ አላፊ አግዳሚውንም
ስታማትሪ የደነዘዘው ህሊናሽ የማይወቅስሽ እህቴ ሆይ!!
ይህች አለም የፈተና አለም ናትና እራስን በማቀብ፣ የሀራም ድንበሮችንም በማክበር መኖር የነገን ሰላም ያመጣል። ልብ በኢማን ብርሀን የሚፈካውም እይታ ሲገደብ ነው።
የአላህን ተግሳፅ ልብ በይ፦

ﻭَﻗُﻞ ﻟِّﻠْﻤُﺆْﻣِﻨَﺎﺕِ ﻳَﻐْﻀُﻀْﻦَ ﻣِﻦْ ﺃَﺑْﺼَﺎﺭِﻫِﻦَّ ﻭَﻳَﺤْﻔَﻈْﻦَ ﻓُﺮُﻭﺟَﻬُﻦَّ ﻭَﻻَ ﻳُﺒْﺪِﻳﻦَ ﺯِﻳﻨَﺘَﻬُﻦَّ ﺇِﻻَّ ﻣَﺎ ﻇَﻬَﺮَ ﻣِﻨْﻬَﺎ ۖ

«ለምእምናትም ንገራቸው፦ ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ፡፡ ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ፡፡ ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከኾነው በስተቀር አይግለጡ...» አኑር 31

ሁላችንም ወደ አላህ እንመለስ!! እይታን በመገደብ ምን ያክል ለአላህን የክልከላ ወሰኖች የማክበር ብቃት ልባችን ላይ ማስረፅ እንደምንችል እናስተውል። አንቀፁም የተቋጨው ወደ ተውበት ጥሪ በማድረግ ነው!!

ﻭَﺗُﻮﺑُﻮا ﺇِﻟَﻰ اﻟﻠَّﻪِ ﺟَﻤِﻴﻌًﺎ ﺃَﻳُّﻪَ اﻟْﻤُﺆْﻣِﻨُﻮﻥَ ﻟَﻌَﻠَّﻜُﻢْ ﺗُﻔْﻠِﺤُﻮﻥَ
ምእመናኖች ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም ወደ አላህ (በመመለስ) ተጸጸቱ፡፡

والحمد لله رب العالمين!

________
🕰ረጀብ 14 1437
21 ኤፕሪል 2016
www.fb.com/tenbihat

©ተንቢሀት