#በእምነት ጉዳዮች ላይ “ውዝግቡ” አንዴት ተጀመረ?!
የመጨረሻው መልዕክተኛ (ﷺ) የቀድሞዎቹን ነብያት ተልዕኮ የሚያረጋግጡና የሚያሟሉ ግልፅ መለኮታዊ መመሪያዎችን ይዘው ብቅ እንዳሉ በዐረቢያ ምድር አጥልቶ የነበረው የመሃይምነት ፅልመት ተገርስሶ የቅናቻ ወጋገን በየአድማሱ ተሰራጨ። የመልዕክተኛው ታታሪ ሰሓቦችም ከጌታቸው ዘንድ ለተላከው ፍፁም መመሪያ በቅን ልቦና ተገዢ መሆናቸውን በንፁህ ተግባራቸው አስመሰከሩ። አዎን! በጥራዝ ነጠቅ ፍልስፍና አእምሯቸው አልተበረዘም፤ በአጉል ፈሊጥም እይታቸው አልተሟሸም፤ የመልዕክተኛው አስተምህሮት ስብእናቸውን በቁርኣናዊ ስርዓት አንፆታልና!
ከእሳቸው (ﷺ) ሕልፈተ-ሕይወት በኋላ በነበሩት ዘመናትም በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የኢስላም ስርጭት ሲቀጥል ሰሓቦችና ቅን ተከታዮቻቸው በጫንቃቸው ላይ የተጣለውን የእምነት ሀላፊነት በመወጣት ረገድ ለተተኪው ትውልድ መልካም አርዓያ ሆኑ። በተለያዩ የእምነት መስኮችም የቀድሞውን ነብያዊ ፋና በመከተል በወንድማማችነት መንፈስ ተዋህደው አንድነታቸውን ጠብቀው ሰነበቱ። ይህንን ድንቅ የኢማን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ አንዳንድ አለመግባባቶች ከተከሰቱ ወደ ቁርኣንና ወደ መልዕክተኛው (ﷺ) ፈለግ በመመለስ መፍትሄን ይሹ ነበር።
ሆኖም ወደሚቀጥሉት ትውልዶች በጥራት እየተላለፈ የነበረውን የእምነት አደራ የሚያደፈርሱ አዳዲስ ፈሊጦች በሙስሊሙ ማህበረሰብ መሐል ማጎጥጎጥ የጀመሩት ገና ከረፋዱ ነበር።
ነገሩ እንዲህ ነው፦
ነገሩ እንዲህ ነው፦
አንዳንዶች በጠባብ “አእምሯዊ” እይታዎች ላይ ተመርኩዘው በመለኮታዊው መመሪያ በተገለፁት እምነታዊ ጉዳዮች ላይ አዳዲስ አመለካከቶችን መሰንዘር ጀመሩ! ይህ አጋጣሚ የደላቸው ከጥንቱ የኩፍር አሻራ ያልተፈወሱ አንዳንድ አሜኬላዎች በማህበረሰቡ መሀል ተሰግስገው መርዛቸውን በማር እያላወሱ በመርጨት እገዛ አደረጉላቸው።
ይህ ሁሉ ሲሆን በዕውቀት የተካኑት የኢስላም ባለአደራ ጀግኖች እጃቸውን አጣምረው አላዩም። የሰሓባዎች ትውልድ ሳይገባደድ በፊት አንዳንድ የፈጠራ ተግባራትና አመለካከቶች ቢስተዋሉም በአብዛኛው በውስን ግለሰቦች ላይ የተገደቡ ስለነበሩ እነርሱ የሚጭሩትን የቢድዓ እሳት የመልዕክተኛው (ﷺ) ምርጥ ወራሾች በዕውቀት ባህራቸው ከመቅፅበት አዳፍነው ያከስሙት ነበር።