Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እኛስ ከየትኛው ምድብ ውስጥ ነን?



እኛስ ከየትኛው ምድብ ውስጥ ነን?
ሙሐመድ ኢብኑ ፈድል ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡-
“ኢስላም የሚጠፋው በአራት አይነት ሰዎች ነው፡፡
1. በሚያውቁት በማይሰሩ
2. በማያውቁት በሚሰሩ
3. የማያውቁትን በማይማሩ እና
4. ሰዎችን ከእውቀት በሚከለክሉ፡፡”

አልኢማም አዝዘሀቢ ረሒመሁላህ ከዚህ ስር እንዲህ ይላሉ፡-
“እነዚህ የዐረብና የቱርክ ቁንጮዎች መታወቂያ ባህሪዎች ናቸው፡፡ የተራው መሀይማን ህዝብም እንዲሁ (ባህሪዎች ናቸው፡፡)
1. በሚያውቋት ጥቂት ቢሰሩ ኖሮ በዳኑ ነበር፡፡
2. በቢድዐህ መስራታቸውን ቢያቆሙ ኖሮ በተገጠሙ ነበር፡፡
3. ስለዲናቸው ቢፈትሹ፣ ብልጣብልጦችንና ሴረኞችን ሳይሆን የእውቀት ባለቤቶችን ቢጠይቁ ኖሮ በታደሉ ነበር፡፡
4. ይልቁንም እየዋለሉና እየተዘናጉ መማርን ይተዋሉ፡፡
ከነዚህ ነጥቦች አንዷ ብቻዋን አጥፊ ናት፡፡ ሲሰበሰቡማ እንዴት ሊያደርጉ ነው?! በነዚህ ላይ ኩራት፣ ዋልጌነት፣ አመፀኝነትና አላህን መዳፈር ሲደመርበት ደግሞ ምን የሚሆን ይመስልሃል?!!! ከዚህ ሁሉ እንዲጠብቀን አላህን እንለምነዋለን፡፡” [ሲየሩ አዕላሚ አንኑበላእ፡ 14/525]
ከንፈር መምጠጥ፣ እራስን መነቅነቅና መደነቁ ለአፍታ ከሆነ ምን ፋይዳ አለው? ይልቅ ያለንበትን ሁኔታ እንፈትሽ፡፡ ለዘላቂ ለውጥ እንነሳ፡፡ ቀጠሮ አናራዝም፡፡ ያቅማችንን እንፍጨርጨር፡፡ አላህ እንዲያግዘን ዱዓእ እናድርግ፡፡ የሰለፎቻችንና የዑለማዎቻችንን አስደማሚ የእውቀት ፍለጋ ታሪኮች ከአጉል “እንዲህ ነበርን” ኩፈሳ አውጥተን ለተግባራዊ ጉዟችን እንደ ብርታት ሰጪ መድሃኒት እንጠቀማቸው፡፡ አላህ ለመልካሙ ያድለን፡፡

Ibnu Munewor