Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ኺላፍን ለመገንዘብ!


 
“የአማኞች ጋሻ”

#ኺላፍን ለመገንዘብ!

በሸሪዓዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚነሱ ውዝግቦች ሊኖረን የሚገባውን ምልከታ በሁለት ከፍለን ልናይ እንችላለን፦

#1ኛ- በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ሸሪዓዊ ፍርድ በግልጽ ቁርአናዊና ነቢያዊ አስተምህሮቶች የተቋጨና በቀደምት ዑለማዎች ሙሉ ስምምነት የፀደቀ እንደሆነ የትኛውም ዓይነት ውዝግብ የሚስተናገድበት መድረክ አይኖርም፤ ብይኑንም ያለምንም ማንገራገር ተቀብሎ ማስተናገድ የግድ ይሆናል። ይህንን እውነታ ከተረዱ በኋላ በአጀንዳው ላይ ከተመለከተው ሸሪዓዊ አስተምህሮት ጋር የሚጣረስ አቋም ማንፀባረቅ አላህ ከዘረጋልን ቀጥተኛ ጎዳና ማፈንገጥ በመሆኑ ለውግዘት ይዳርጋል!

وَمَن يُشَاقِقِ الرَّسُولَ مِن بَعْدِ مَا تَبَيَّنَ لَهُ الْهُدَىٰ وَيَتَّبِعْ غَيْرَ سَبِيلِ الْمُؤْمِنِينَ نُوَلِّهِ مَا تَوَلَّىٰ وَنُصْلِهِ جَهَنَّمَ ۖ وَسَاءَتْ مَصِيرًا [النساء: ١١٥]

«(የ)ምራቻ (መንገድ) ከተገለጠለት በኋላ መልዕክተኛውን የሚፃረርና ከሙእሚኖች መንገድ ሌላ የሚከተል የመረጠውን (ጥመት) እናሸክመዋለን፤ ጀሀነምም እናስገባዋለን፤ ከመመለሻነቷ (አኳያ)ም የከፋች ሆነች!» [አን-ኒሳእ 115]

ለዚህ ክፍል ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ድንጋጌዎች አሉ፤ ከአላህ በቀር ማንንም (የአምልኮ ጥሪ) አለመጣራት፣ የአላህ ስሞችንና ባህሪያቱን መልዕክታቸውን ሳያዛቡ በተገቢው መልኩ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ኢማን መልካም ንግግርንና ተግባርን እንደሚያካትት ማረጋገጥ፣ በቀደር በአግባቡ ማመን …ወዘተ። እነኚህ ከእምነት ህልውና ጋራ ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸው ጉዳዮች ላይ ምንም አይነት ቦታ የሚሰጠው “ኺላፍ” (ውዝግብ) የለም!

በርግጥ ከመጀመሪያዎቹ ምርጥ ትውልዶች በኋላ ከመጡት የኋለኞቹ ሊቃውንት መካከል አንዳንዶቹ እንደሌሎች ርዕሶች ሁሉ በዚህኛውም ላይ በተለያዩ ምክንያቶችና ተፅዕኖዎች የተነሳ ስህተት ላይ መውደቃቸው ይታወቃል። ይህ አቋማቸው ግን እንደ ስህተት ታይቶ በስርዓቱ ይታረማል እንጂ የቀድሞዎቹን ትውልዶች (ሰለፎች) ስምምነት የሚንድ “ኺላፍ” በፍፁም አይሆንም!

አዎን! እውነትን ፍለጋ ለተሳሳቱ ዓሊሞች የሚሰጠው ማስተካከያ በቢድዓ አራማጅ ጎጠኞች ላይ እንደሚደርሰው ውግዘት አይደለም! ሆኖም ስህተት ማንም ይስራው ማን ሁሌም ስህተት ነው! ስህተት ሁሉ ደግሞ የመደበኛ «ኺላፍ» ሚዛን ላይ አይሰቀልም፤ አጀንዳው በግልጽ ቁርአናዊና ነብያዊ አስተምህሮቶች የተቋጨና በቀደምት ዑለማዎች ሙሉ ስምምነት የተዘጋ የአንድነት ርዕስ እንጂ የኺላፍ ርዕስ አይደለምና! አለበዚያ ማንም በዲን ስም ያሻውን አቋም ያለተቃውሞ እንዲያራምድ ሰፊ በር መክፈት ይሆንብናል!

እናም ይህንን መሰል መሠረታዊ ጉዳይ ከአንዳንዶች እንደምንሰማው “ተራ የኺላፍ ርዕስ” ወይም “ፍሬ-አልባ ውዝግብ” ብሎ መሰየም የቀደምት የኢስላም ምርጥ ትውልዶችንና ተተኪ መሪዎችን የክፍለ-ዘመናት ልፋት፣ ገድልና መስዋትነትን ከንቱና እርባና-ቢስ አድርጎ መቁጠርና አደራቸውንም መብላት መሆኑን ማወቅ ያሻል!(በመሰረቱ ወደ ጥመት የሚጣሩና ስህተትን የሚያሰራጩ ባይኖሩ ኖሮ የሐቅ ባለቤቶች ምላሽ ለመስጠት መድከም ባላስፈለጋቸው ነበር!)

#2ኛ- በርዕሶቹ ላይ የሚጠቀሱት ማስረጃዎች የሚጠቁሙትን መልዕክት በተመለከተ ቀደምት የኢስላም ሊቃውንት በግንዛቤ ልዩነት የተለያየ አቋም ያንጸባረቁ ከሆነና ጉዳዮቹ በዑለማዎች ዘንድ ሸሪዓዊ ምልከታን (“ኢጅቲሃድ”ን) የሚያስተናግዱ መሆናቸው የታወቀ እንደሆነ አንድ ዓሊም ከዚህ በፊት ከነበሩት የዑለማዎች አቋሞች አንዱን ቢመርጥ፣ ብሎም ቢሳሳት ፍርዱ እንደሙሉ ጥፋት ተወስዶ አይኮነንም፤ መልዕክተኛው (ﷺ) እንደዚህ ብለዋል፦

»إِذَا حَكَمَ الْحَاكِمُ فَاجْتَهَدَ ثُمَّ أَصَابَ فَلَهُ أَجْرَانِ، وَإِذَا حَكَمَ فَاجْتَهَدَ ثُمَّ أَخْطَأَ فَلَهُ أَجْرٌ»

«አንድ ፈራጅ ሲፈርድ (እውነታን ለመረዳት) ተጣጥሮ ትክክል ከሆነ ሁለት ምንዳ (አጅር) አለው፤ ሲፈርድ (እውነታን ለመረዳት) ተጣጥሮ ከተሳሳተ ደግሞ አንድ አጅር አለው!» (አል-ቡኻሪይ (7352) ፣ ሙስሊም (1716))
ሆኖም የላይኛው ሐዲሥ እንደሚያስረዳው በዚህኛውም ርዕስ ላይ ቢሆን እውነትን ለማወቅ ሁሉም እንደየአቅሙ መጣር ይጠበቅበታል።

---
“የአማኞች ጋሻ” ከሚለው የሸይኽ ኢልያስ አህመድ መፅሐፍ መግቢያ የተወሰደ!

የፌስ ቡክ ገፃችንን ለማግኘት…
https://www.facebook.com/asmaewesifat
ሼር ማድረግ እንዳይረሱ!