Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሰዎች ልክ እንደ ማበጠሪያ ጥርሶች (እኩል) ናቸው” የሚለው “ሐዲሥ” ዶዒፍ ነው


በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስም “ዶዒፍ” ሐዲሦችን የምታሰራጩ ሰዎች ተጠንቀቁ!
“ሰዎች ልክ እንደ ማበጠሪያ ጥርሶች (እኩል) ናቸው” የሚለው “ሐዲሥ” ዶዒፍ ነው- ደካማ፡፡ የዘመናችን ታላቁ የሐዲሥ ምሁር ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ “ሐዲሡ” ደካማ እንደሆነ በጥናታቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ [አድዶዒፋህ፡ 3158] ስለሆነም ይህን ደካማ “ሐዲሥ” ወደ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ማስጠጋት በስማቸው ማውራት አግባብ አይደለም፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በኔ ላይ ሆን ብሎ የዋሸ ሰው መቀመጫውን ከእሳት ያዘጋጅ” ብለዋል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 1383]
ልብ ይበሉ 1
“ሐዲሡ” ደካማ ነው ስንል በሰው ልጆች መካከል የመደብ ልዩነት አለ ለማለት አይደለም፣ ምንም እንኳን እኩልነት በራሱ ጥልቅና ከተለያዩ ተፅእኖዎች ነፃ የሆነ ምዘና የሚፈልግ ቢሆንም፡፡ ባይሆን ሰዎች በኢማን በተቅዋ በደንብ ይበላለጣሉ፡፡ ይህን ሙስሊም ሆኖ የሚዘነጋው የለም፡፡
ልብ ይበሉ 2
በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስም የተወራ ሁሉ በትክክልም የሳቸው ንግግር ነው ማለት አይደለም፡፡ በተለያየ ምክንያት ጠንካራ መሰረት የሌላቸው ወይም ደግሞ ቅጥፈት እንደሆኑ የተደረሰባቸው በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ስም የሚወሩ “ሐዲሦች” ስላሉ ይህን ከግንዛቤ ልናስገባ ከዚህ አንፃርም ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡
ልብ ይበሉ 3
ብዙ ሰዎች አንድ “ሐዲሥ” ደካማ ወይም ዶዒፍ ነው ሲባል ግር ይላቸዋል፡፡ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር ሐዲሥ ከተቀባይነቱ አንፃር ለሁለት ይከፈላል፡፡ እሱም ተቀባይ የሆነ እና ተቀባይነት የሌለው፡፡ ተቀባይ የሆነው ሶሒሕ እና ሐሰን ተብሎ ሲከፈል ተቀባይነት የሌለው ደግሞ ዶዒፍ ይባላል፡፡ ይሄ ደግሞ በተራው አይነቱ ብዙ፣ የደካማነት ደረጃውም የተለያየ ነው፡፡ ታዲያ ለተለያዩ ሐሳቦች ማጠናከሪያ ወይም ማስረጃ አድርገን የምንጠቅሳቸው ሐዲሦች ተቀባይነት ያላቸውና መስፈርት የሚያሟሉ መሆናቸውን ከማሰራጨታችን በፊት እርግጠኞች ልንሆን ወይም ከዘርፉ ባለሙያዎች ማጣቀሻ ልንይዝ ይገባል፡፡ ባለማወቅ ደካማ ማስረጃዎችን ካሰራጨንም ስናውቅ ጊዜ እርማት ልንወስድ ይገባል፡፡
ልብ ይበሉ 4
አንድ አባባል መልእክቱ ስላማረን ወይም ጤነኛ መልእክት ስላዘለ ብቻ የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ይሆናል አይባልም፡፡ እናም አንድ አባባል ሰንሰለቱ ተፈትሾ ብቁ በሆነ ድጋፍ ከነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ዘንድ ከደረሰ ለማስረጃ ብቁ ሲሆን መስፈርት ማሟላት ካልቻለ ግን ከቻልን ወደ ትክክለኛ ተናጋሪው እንጂ ወደ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ልናስጠጋው አይገባም፡፡ ስለሆነም አንድ አባባል ደካማ ነው ወይም ዶዒፍ ነው ስንል በነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሊተላለፍ አይገባውም ለማለት እንጂ በውስጡ ያለው መልእክት ሀሰት ነው ወይም እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡ በውስጡ ያለው መልእክት ልክ መሆን አለመሆኑ ከያዘው እውነታ አንፃር ተፈትሾ ልክ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ታዲያ መልእክቱ እውነት ቢሆን እንኳን በዘርፉ ምሁራን ተፈትሾ በትክክልም የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ንግግር መሆኑ ካልታወቀ በስማቸው ልናወራው አይገባም፡፡
አላህ ሁላችንንም ለመልካሙ ያድለን፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ሃምሌ 21/2007)

Post a Comment

0 Comments