Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ተውሂዱል_አስማኢ_ወሲፋትን የማወቅ አንገብጋቢነት



#ተውሂዱል_አስማኢ_ወሲፋትን የማወቅ አንገብጋቢነት

የዕውቀት አይነቶች ብዙ ናቸው፤ የአስፈላጊነታቸውም ደረጃ እንዲሁ ይለያያል። ታዲያ የአንድ ዘርፈ-ዕውቀት ክብርና ቦታ በዋነኝነት የሚለካው በውስጡ ባካተተው ርዕስ ታላቅነት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በዕውቀት ሊዳሰሱ ከሚችሉ አጀንዳዎች ሁሉ ይበልጥ ክቡርና አሳሳቢ የሆነው የጌታችን ማንነት የሚገለፅባቸውን አምላካዊ ስሞቹንና ባህሪዎቹን የተመለከተው ርዕሰ-ጉዳይ ነው።

- የርዕሱን ታላቅነት ከሚያጎሉት ምክንያቶች አንዱ ከፍጥረተ-ዓለሙ መገኘትና በውስጡ ከሚስተናበሩት ሂደቶች በስተኋላ ካሉት ሚስጥሮች ጋር ያለው ቁርኝት ነው፦

اللَّهُ الَّذِي خَلَقَ سَبْعَ سَمَاوَاتٍ وَمِنَ الْأَرْضِ مِثْلَهُنَّ يَتَنَزَّلُ الْأَمْرُ بَيْنَهُنَّ لِتَعْلَمُوا أَنَّ اللَّهَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ قَدِيرٌ وَأَنَّ اللَّهَ قَدْ أَحَاطَ بِكُلِّ شَيْءٍ عِلْمًا [الطلاق: ١٢]

=«አላህ ያ ሰባት ሰማያትን ከምድርም መሰላቸውን የፈጠረ ነው፣ በመካከላቸው ትዕዛዙ ይወርዳል፦ አላህ በሁሉ ነገር ላይ ቻይ መሆኑንና ሁሉን ነገር በዕውቀቱ እንዳካበበ ታውቁ ዘንድ» [አጥ-ጦላቅ 12]

አዎን! የዚህን ግዙፍ ዓለም ረቂቅ ሂደትና ክንውን የሚቆጣጠረውና የሚያስተናብረው ፈጣሪያችን ችሎታው ያለ ልኬት የመጠቀ፣ ጥበቡ ያለ አምሳያ የረቀቀ፣ ዕውቀቱ ያለ ገደብ የጠለቀ ስለመሆኑ የፍጥረተ-ዓለሙ ትዕይንት ራሱ መስካሪ ነው። ይህን ማወቃችንም ፍጥረታት ከተገኙበት ክቡር ዓላማዎች አንዱ መሆኑን የላይኛው አንቀፅ በግልፅ ያስረዳል።

* እንደሚታወቀው ከኢማን መሰረቶች የመጀመሪያውና ዋነኛው ምሰሶ በአላህ ማመን ነው፤ ይህ ደግሞ ብቸኛ ጌትነቱንና አምላክነቱን ከማረጋገጥ ጋር በመልካም ስሞቹና ባህሪያቱ ማመንን ያጠቃልላል። እንዲያውም አላህ በእነዚህ መገለጫዎቹ ተጋሪ የሌለው ብቸኛ መሆኑን ማፅደቅ ሌሎቹን የተውሒድ ዘርፎች በአግባቡ ለማረጋገጥ ዋነኛ መሠረት ነው! ምክንያቱም፦

* በቁርኣንና በነብዩ (ﷺ) አስተምህሮቶች የተዘረዘሩት መልካም ስሞቹና እንከን - የለሽ ባህሪያቱ ፍፁምነቱንና ምሉዕነቱን በተለያዩ መንገዶች የሚገልፁ ናቸው። እነዚህ የጌትነት መገለጫዎቹ ደግሞ የአምልኮ ብቸኛ ባለቤትና ባለመብት እንደሆነ ስለሚያረጋገጡ ባሮች ጌታቸውን በነዚህ ያማሩ ስሞች እንዲጠሩትና እንዲለምኑት ታዘዋል።

وَلِلَّهِ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَى فَادْعُوهُ بِهَا وَذَرُوا الَّذِينَ يُلْحِدُونَ فِي أَسْمَائِهِ سَيُجْزَوْنَ مَا كَانُوا يَعْمَلُونَ
[الأعراف: ١٨٠]

-> «ለአላህም ከሁሉ የተሻሉ መልካም ስሞች አሉት፤ በነሱም ጥሩት፤ እነዚያ ስሞቹን የሚያጣምሙትንም ተዉዋቸው፤ ይሰሩት የነበረውን (ዋጋ) ይመነዳሉ።» [አል-አዕራፍ 180]

* እንዲሁም ነብያት አላህ ያለ አንድም ተጋሪ ሊመለክ የሚገባው መሆኑን ለህዝቦቻቸው ሲያስተምሩ የዚህ ታላቅ መብት ብቸኛ ባለቤት የሚያደርጉትን ባህሪያቱንና መገለጫዎቹን እያወሱ ነበር! በአንፃሩ ደግሞ ቢያንስ እንደ ማየት፣ መስማትና መናገር ያሉ የምሉዕነት ባህሪያት የሌሉት ማንኛውም አካል ይህ ጉድለቱ ለርሱ የሚውለውን የትኛውንም የአምልኮ ዘርፍ ከመሠረቱ ፉርሽ ከሚያደርጉ አስረጆች እንደሚመደብ በማስረዳት ጥሪያቸውን ያካሂዱ ነበር! ለምሳሌ፦ አላህ በቁርኣኑ ታላቁ ነብይ ኢብራሂም () ለጣዖት አምላኪ አባታቸው የተናገሩትን ሲያስተላልፍልን እንዲህ ይላል፦

إِذْ قَالَ لِأَبِيهِ يَا أَبَتِ لِمَ تَعْبُدُ مَا لَا يَسْمَعُ وَلَا يُبْصِرُ وَلَا يُغْنِي عَنْكَ شَيْئًا
مريم:42
- «ለአባቱ፦ “አባቴ ሆይ! ለምን የማይሰማ፣ የማያይና ምንም የማይጠቅምህን ታመልካለህ?!” ባለ ጊዜ..»[መርየም 42]

እንደዚሁም አላህ የሙሳ () ህዝቦችን ሲነቅፋቸው እንዲህ ይላል፦
وَاتَّخَذَ قَوْمُ مُوسَى مِنْ بَعْدِهِ مِنْ حُلِيِّهِمْ عِجْلًا جَسَدًا لَهُ خُوَارٌ أَلَمْ يَرَوْا أَنَّهُ لَا يُكَلِّمُهُمْ وَلَا يَهْدِيهِمْ سَبِيلًا

- «የሙሳ ህዝቦችም ከርሱ (መሄድ) በኋላ ጩኸት ያለው በድን ጥጃ ከጌጦቻቸው (በመስራት) (አምላክ አድርገው) ያዙ፤ እርሱ እንደማያናግራቸውና መንገድ እንደማይመራቸው አላዩምን?!..»[አል-አዕራፍ 148]

* በደፈናው የፈጣሪን ስሞችና ባህሪያት በተገቢው መልኩ መገንዘብ ወደ ሐሰት የአምልኮ መስኮች የሚያመሩ መንገዶችን ሁሉ ሙሉ ለሙሉ የሚዘጋ ከመሆኑ ባሻገር በዚህች ምድር የመገኘታችን ክቡር ምክንያት የሆነውን የእውነተኛ አምልኮ ግዴታችንን በአግባቡ እንድንወጣው ይረዳናል!

* መቼም የማንኛውም ሰው ልቦና ስለሚገዛው አምላክ ማንነት በጥቅሉም ቢሆን ለማወቅ ይጓጓል! ጭራሽ የማያውቁትን እንዴት ማምለክና መውደድ ይቻላል?!

- ታዲያ አላህን እርሱ ራሱና መልዕክተኞቹ በገለፁት መልኩ ማወቅ ከጥራዝ-ነጠቅ ንትርኮችና ከህሊናዊ ውጥንቅጦች በማሳረፍ የእምነት እርካታን ያወርሰናል። እንዲሁም ለርሱ ያለንን ውዴታና ፍራቻ በልቦናችን ከማሳደግ አልፎ የኢማናችንን አድማስ በየአቅጣጫው ያሰፋልናል፤ በአምልኮ መስክም ላይ ብርታትን ያላብሰናል! ምክንያቱም እያንዳንዱን የአላህ ስም እና ባህሪ በአግባቡ ማወቅ እራሱን የቻለ የአምልኮ ፍሬ አለውና!

ለምሳሌ፦ አላህ ሰሚ፣ ተመልካች እና ሁሉን አዋቂ መሆኑን በፅኑ ያመነ ሰው አንደበቱን እና አካሉን አላህ ከማይወደው ንግግርና ተግባር ለመጠበቅ ሳይታክት ይጥራል! አላህ መልካም ሰሪ አማኞችን እንደሚወድ ያረጋገጠም የርሱን ውዴታ ለመጎናፀፍ ለመትጋት ይነሳሳል፤ በሩህሩህነቱ የሚያምንም እዝነቱን ይለምናል፤ ከቁጣውም ይጠነቀቃል!.. ለዚህ ነው “ከሰዎች አላህን ይበልጥ የሚፈሩት ይበልጥ የሚያውቁት ናቸው” የሚባለው!

ስለሆነም ሀይማኖቱን በትክክለኛ መሠረት ላይ መገንባት የሚሻ ማንኛውም ሙስሊም ይህንን የእምነት መሠረት ከሚበክሉ ወረርሽኞች ራሱን ሊያድን ይገደዳል!

የፌስ ቡክ ገፃችንን ላይክ ያድርጉ

☞ “የአማኞች ጋሻ”
https://www.facebook.com/asmaewesifat

ሼር ማድረግም እንዳይረሱ!