Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የ"ቫላንታይን ቀን" ወይም የ"ፍቅር በዓል" ስለሚባለው ፈጠራዊ ባህል ኢስላማዊ ብይን

 


ـ | حكم الاحتفال بـ'عيد الحب' |
የ"ቫላንታይን ቀን" ወይም የ"ፍቅር በዓል" ስለሚባለው ፈጠራዊ ባህል
ኢስላማዊ ብይን

በቅድሚያ ይህ የ"ፍቅር በዓል" ወይም "የቫለንታይን ቀን" በመባል በክርስቲያኑ ማህበረሰብ በሰፊው የሚዘከረው አመታዊ ባህል መነሻው ባጭሩ ምንድነው?
ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እውነታን በማሳወቅ ከተለያዩ ፀረ ኢስላም ተለምዶዎች እንዲጠነቀቅ ከፍተኛ ተጋድሎ ከሚያደርጉት የዳዕዋና የትምህርት ማእከላት አንዱ የሆነው በሳዑዲ ዓረቢያ ቅድስቲቷ ከተማ የሚገኘው ኡመልቁራ ዩኒቨርሲቲ "ኩሊየቱ-ዳዕዋ ወኡሱሉዲን" የጥናትና ምርምር ማዕከል ስለዚህ ጉዳይ ከምንጩ ለማወቅ ባደረገው ጥናት "ባርት" የሚባል የምዕራቡ አለም ደራሲ ስለ የዓለም በዓላት ሲዘረዝር ስለ "ቫለንታይን" የፃፈውን ወደ አረብኛ ከመለሱት እንደምንረዳው የ "ዒዱል ሁብ" ማለትም "የፍቅር በዓል" ስለሚባለው ባህል ትክክለኛ ምንነት በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ላይ በማንጠልጠል አብራርቷልና እንደሚከተለው ያንብቡት።☞
የ"ቫላንታይን ዴይ" መነሻ መላምት
∞∞∞∞∞=======∞∞∞∞∞
ደራሲው በሚለው መላምት
1ኛ/ ከ1700 አመታት በፊት በሮማ ላይ ጣዖታውያኑ የበላይ በነበሩበት ዘመን "ቫለንታይን" የተባለ ግለሰብ ከጣዖት አምላኪነት ወደ ክርስትና ተቀየረ። ሆኖም ሮማውያኑ ወዲያው ገደሉት። ከግዜ በኋላ ግን አብዛኞቹ ሮማውያን ወደ ክርስትና ሲቀየሩ "በቫለንታይን" ላይ በፈፀሙት ግድያ ተፀፀቱ። ስለዚህም የሞተበትን እለት ለሱ ማስታወሻ በሚል የበዓል ቀን አደረጉት። ይላል።
2ኛ/ ጥንታውያን ሮማውያኑ አንዲት "ዮኖ YoNo" የምትባል አማልክትን ያመልኳት ነበረ። እሷም የአማልክቶቻቸው ሁሉ ንግስት ናት በሚል ፌብሩዋሪ 14ን የሷ መዘከሪያ አደረጉት። እሷንም የሴቶችና የጋብቻ ተምሳሌት ናት በሚል እለቱን የ"ፍቅር ቀን" ኣሉት። ይላል።
3ኛ/ በሮማውያኑ ዘንድ አንዲት ቅድስት ናት በሚል የሚያመልኳት አማልክት ነበረች። ስሟንም "ሊሲየስ Licious" ይሏታል። የሚገርመው ነገር ይህች አማልክት ተኩላ የምትባል እንሰሳ ናት። ተኩላዋን የሚያመልኳት ለምንድነው ከተባለ ጉዳዩ እንዲህ ነው። ይህች "ሊሲየስ" የሮማ ከተማ መስራች የነበሩን ሁለቱን ሰዎች በህፃንነታቸው አጥብታቸው ነበር በሚል አመታዊ ቀንና ቦታ ወስነው የአምልኮ ቦታውንም "ፍቅር" ኣሉት። ይህም ያቺ "ሊሲየስ" የተባለቿ ተኩላ ለእነዚያ ህፃናት ታዝን ነበርና ፍቅር ሰጥታቸዋለች በሚል ይቀድሷታል።
4ኛ/ ከዘመናት በፊት በነበረው የሀገሪቱ መሪ ወንዶችን ለጦርነት ለማሰማራት ማሰባሰብና ማዘጋጀት ሲሳነው ምክንያቱን ሲያጠና ወንዶቹ ከሚስቶቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ላለመለየት ሲሉ ጥሪውን እንዳልተቀበሉና ከሱ ጋር መዝመትን የጠሉ መሆኑን ደረስኩበት ኣለና ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ይሆነው ዘንድ መንግስቱ ከዚህ በኋላ ማንም እንዳይጋባ በማለት አወጀ። በወቅቱ ሰዎች የሚጋቡትም በካቶሊካውያኑ ስርዓት በቀሳውስቱ እጅ በቤተክርስቲያናቱ ነበርና ለቀሳውስቱም ከማጋባት እንዲታቀቡ ትእዛዝ ተላለፈላቸው። ይሁንና "ቄስ ቫለንታይን" የተባለ ሰው ትእዛዙን ባለማክበር ለጋብቻ ወደ ቤተክህነቱ የመጡትን በድብቅ ያጋባ ነበርና ይህንን መንግስቱ ሲደርስበት ያንን ቄስ በፌብሪዋሪ 14/ 269ዓል ገደለው ኣሉ። ስለዚህም ከዚህ ክስተት በኋላ ይህ ቄስ ቫለንታይን ለኛ ፍቅር ሲል ሞተ በሚል ክብር ይገባዋልና አመታዊ መዘከሪያ እናብጅለት ብለው የ"ፍቅር በዓል" ፈጠሩ የሚል ነው።
==∞===∞==
ይህ እንግዲህ ስለ በዓሉ ራሳቸው ፅፈው ያስነበቡት ኣፈታሪካቸው ነው። ይሁንና ከረዥም አመታት በኋላ ቤተክርስቲያኗ የ"ፍቅር ቀን" የሚባለውን በዓሏን "ሊሲየስ" ከምትባለዋ ተኩላ ጋር የሚያያዘውን ታሪክ ትቻለሁ ኣለችና "ቅዱስ" በሚሉት "ቫለንታይን" ላይ ብቻ በማንጠልጠል የ"ቫለንታይንን" ምስሎችና ቅርፃ ቅርፆች በመላው አውሮጳ እና አሜሪካ ከማሰራጨት ጋር በዓሉን አስፋፋች። ሆኖም ለሁለተኛ ግዜ በቅርቡ በእኤአ 1969 የ"ቫለንታይን ቀን" ብላ ታከብር የነበረውንም ትቻለሁ ኣለችና በቤተክርስቲያን ደረጃ ገሸሽ አደረገችው።
በዚህም መሰረት ይህ የ"ቫለንታይን" ቀን የሚባለው በዓል መነሻው ጣሊያን ሮማ ሲሆን ባለታሪኮቹም የሀገሪቱ ቀደምት ነዋሪ የሆኑት ጣዖታውያኑና ሃይማኖት ኣለን የሚሉት ካቶሊካውያን ክርስቲያኖች መሆናቸው ግልፅ ይሆንልናል።
እንደሚታወቀው ሙስሊም ያልሆኑ ህዝቦች ባእድ አምልኮ ላይ የተመሰረቱ በርካታ በአላትን በአመት ውስጥ ያከብራሉ። ከፊሉ በቅዱሳን ስም ሲሆን ከፊሉ ደግሞ ተራ በሆኑ ሰዎች ወይም እንስሳትና ግዑዛን ጭምር ነው። ለዚህማ ማሳያ ይህን የ"ቫለንታይን ቀን" የሚባል በዓል ከተኩላ አምልኮት ጋር ሁሉ የተያያዘ መሆኑን ሙስሊሞቹ ልብ ሊሉት ይገባል። እርግጥ እያመለኩ ያሉት ቅዱስ ሚካኢል ወይም ቅዱስ ጅብሪል ወይም ነቢይን ወይም ሌላ ደጋግ ፍጡራንንም ቢሆን ለአላህ ብቻ የሚገባን አምልኮ ለፍጡር ማዋል በመሆኑ ሁሉም ባእድ አምልኮ ነውና ተቀባይነት የለውም።
እንደሚታወቀው ሮማውያኑ ጣዖታውያን ለፍቅርም፣ ለዝናብም፣ ለአዝርዕትም አምላክ፣ ለብርሃንም፣ ለጭለማም አምላክ፣ ለባህርም፣ ለወንዙም አምላክ እያሉ ለሁሉም ነገር የተለያየ አምላክ እንዳለው አድርገው አማልክትን ያምኑም ያመልኩም ነበረ። ይህንንም ባህላቸውን ወደ ክርስትናው ሲገቡ ክርስቲያናዊ ቃና አላብሰው አስፋፍተውታል።
ሙስሊሞች ከኢስላማዊ ባህልና በዓል ውጪ የሌሎችን ሊከተሉ አይገባም።
∞∞∞∞∞≈≈≈≈∞∞∞∞
አላሁ ሱብሃነሁ ወተዓላ ከከሃዲያን፣ የፈጣሪን ህልውና ከከዱት ጋር በባህላቸው፣ በበዓላቸውም ሆነ በእምነታቸው "ተሸቡህ" መመሳሰልን እርም አድርጎብናል። ይህንንም የአላህ መልእክተኛ صلى الله عليه وسلم
"من تشبه بقوم فهو منهم" رواه أبو داود وصححه الألباني.
"በኒያ ህዝቦች የተመሳሰለ ከነሱው ነው።" በማለት በነሱ መለያ መመሳሰል የነሱን መንገድ መከተልን እንደሚያሳይ በመግለፅ አውግዘዋል።
ስለሆነም ከሙስሊሙ ተለምዶ ውጪ በሆነ መልኩ የከሃዲያኑና የጣዖታውያኑ መሃይማን ማህበረሰብ የሚለዩበትን መገለጫቸው የሆነን ተለምዷዊ በዓላቸውን መጋራት የተከለከለ ነው። ነቢዩ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ከመካ ወደ መዲና ተሰደው በሄዱበት ወቅት የመዲና ነዋሪዎች የሚያከብሯቸው ሁለት የተለያዩ የበዓል ቀናት ነበሯቸውና فَقَالَ : مَا هَذَانِ الْيَوْمَانِ ؟ "እነዚህ ሁለቱ ቀናት ምንድናቸው?" በማለት ጠየቋቸው
قَالُوا كُنَّا نَلْعَبُ فِيهِمَا فِي الْجَاهِلِيَّةِ.
"በጃሂሊያው ዘመን በነዚህ ቀናት [ተሰባስበን] የምንጫወትበት ቀን ነው።" በማለት መለሱላቸው። የአላህ መልእክተኛም صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ( إِنَّ اللَّهَ قَدْ أَبْدَلَكُمْ بِهِمَا خَيْرًا مِنْهُمَا : يَوْمَ الأَضْحَى ، وَيَوْمَ الْفِطْرِ )
صححه الألباني .
"አላህ ከነዚህ ቀናት በተሻሉ በአድሃ (በአረፋ) ቀንና በፊጥር (በረመዳን ፆም ፍቺ) ዕለታት በመቀየር ተክቶላችኋል።» በማለት የሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓል ያልሆነውን ትተው በኢስላም የተደነገገውን ብቻ እንዲይዙ መክረዋል።
በዚህም መሰረት በየትኛውም የአለም ክፍል ያሉ ሙስሊሞች በተመሳሳይ ባህል የዒድ ቀን በማለት በማክበር ደስታቸውን ጌታቸውን በማመስገን፣ በመሰባሰብ፣ አንዱ አንዱን በመዘየር፣ በመገባበዝ፣ በመጫወት እና በመሳሰሉት የበዓል መገለጫዎች ዘና ብለው እንዲያሳልፉ አስገንዝበዋቸዋል።
ይህም ግልፅ በሆነ ቁርኣናዊና ሱንናዊ መረጃ የተገለፀ ነው። የዚህ ማህበረሰብ ሰለፎችም በዚሁ ላይ የጋራ አቋም እንደያዙ አስተላልፈውልናል። ስለሆነም ለሙስሊሙ ክብረ በዓል፣ ወይም የሚዘከር እለት፣ ወይም የሚታሰብ እለት ወይም የሚወደስና ቅዱስ እለት ተብሎ አመታዊ ስነስርኣት የሚፈፀምለት ቀን ቢኖር ዒድ አልፊጥር እና ዒድ አል አድሃ የተባሉት ሁለቱ የዒድ እለታት ብቻ ናቸው።
ከሁለቱ ዒዶቻችን ውጭ በዓላት የሚባሉ በሆነ ክስተት ወይም በሆነ ግለሰብ ሆነ ቡድን ወይም በሆነ ሀገር ታሪክ የተሳበቡ በዓላት ሁሉ አዳዲስ ፈጠራዎች ናቸውና የኛ አይደሉም።
ስለዚህም እነዚህ በዓላት አይመለከቱንምና ሙስሊሞች ሊሳተፉባቸውም፣ በይሁንታ ሊቀበሏቸውም ሆነ የደስታቸው ተካፋይ ሊሆኑላቸው እንዲሁም ስጦታ ሊሰጣጡባቸው፣ ከመገለጫዎቹ አንዱ በሆነው ሻማ እንደማብራት፣ ካርድ እንደመለዋወጥ፣ የጣፋጭም ሆነ የሌሎች ምግብና መጠጥ ዝግጅቶችን በመከወን ከነሱ መተባበር፣ እንኳን ደረሳችሁም ሆነ አደረሰን በማለት መልካም ምኞትን መግለፅ ሁሉ አይፈቀድላቸውም።
ምክንያቱም የኛ ባልሆኑ በዓላት ላይ ትብብር ማድረግ የአላህን ድንጋጌ በመዳፈር ነው የሚቆጠረው። የአላህን ድንበር ከመተላለፍ መጠንቀቅ አለብን ።
وَمَن يَتَعَدَّ حُدُودَ اللَّهِ فَقَدْ ظَلَمَ نَفْسَهُ ۚ
"የአላህን ድንበር (እሱ የደነገገውን) የጣሰ በእርግጥም ራሱን በደለ።" ብሏልና በዚህ ጥፋቱ ሰበብ ለሚደርስበት ቅጣት ማንንም መውቀስ አይችልምና።
በተጨማሪም ከሀዲያኑ በፈጠሩት በዓላት ላይ መሳተፍ ቀላል ጥፋት ሳይሆን ወንጀል ላይ ወንጀልን መደረብ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ከነሱ መመሳሰልና እነሱን መውደድን ያቅፋልና። ሁለቱም ባህሪ ደግሞ በሙስሊሙ ላይ እርም ተደርገዋል።
በዚህም መሰረት ለፍቅር የተሰኘው የ"ቫለንታይን ቀንስ" ምን ይሆን?
====∞∞∞===∞∞∞===
"የፍቅር በዓል" በሚል ለኛ መፋቀር ሲል የተሰዋ የሚሉትን "ቄስ ቫላንታይን" ን ወይም "ፍቅር ሰጪዋ ተኩላ" በማለት የሚያወሩላትን እንሰሳ ለማክበር በየአመቱ የሚፈፀመው ዝግጅት የክርስቲያኖች ባህል የሆነ የጣዖት አምልኮ ተለምዷዊ በዓል በመሆኑ ከላይ ከተጠቀሰው ከማይመለከተን በዓል ኣንዱ ነው።
ይህንንም በዓል ማንኛውም በአላህና በመጨረሻዋ እለት የሚያምን ሙስሊም ሊተገብረው፣ ሊተባበር፣ አግባብ ነው በሚል በይሁንታ ሊቀበለው፣ ደስታውን ሊገልፅበት አይገባም። ይህንን ጌታውን የሚያስቆጣ ተግባር ሊርቀውና ራሱን በማግለል ለጌታውና ለመልእክተኛው [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] መታዘዙን ማንፀባረቅ አለበትና። ይኸም አቋም በዚህ ጉዳይ ላይ የመምለካው በታላላቅ ሊቃውንት የታጀበው የፈትዋ ቋሚ ኮሚቴ "ለጅነቱ ድዳኢማ" ከሰጠው ፈትዋ የተወሰደ ነው።
በተጨማሪም ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያም رحمه الله ከእንደዚህ አይነቱ የእምነታችን ተፃራሪ ጉዳይ ሲያስጠነቅቁን☞
«የኩፋሮች መገለጫ በሆነ በምግብም ሆነ በልብስ፣ በአስተጣጠብም ሆነ እሳትን በማቀጣጠል (ችቦ፣ ሻማና ጧፍ መለኮስን በመሰሉ) በማንኛውም ልዩ ተለምዷቸው በሆነ ነገር ከነሱ መመሳሰል ለአንድ ሙስሊም ሀላል አይሆንምና አይፈቀድም።
የትኛውንም በዓላቸውን በተመለከተ ግብዣ ማሰናዳት፣ ስጦታ መሰጣጣት፣ ለበዓላቸው ማገዣ ሲባል የሆነን ነገር መሸጥ፣ ልጆች በበዓላቸው መገለጫ ቦታ እንዲጫወቱ እንዲዝናኑና የመሳሰሉትን ማመቻቸትና በእለቱ ለበዓሉ ተጋጊጦ መገኘትም አይፈቀድም።
ባጠቃላይ ሙስሊሞች በከሃዲያኑ በዓል የነሱ መገለጫ በሆነ ልዩ ነገር መታየት የለባቸውም። ስለሆነም በነዚያ በዓላት ቀናት ሙስሊሞች ማሳለፍ ያለባቸው እንደማንኛውም ቀን ቆጥረው በተለመደው ሁኔታ መሆን አለበት እንጂ የነሱን መለያ መላበስ የለባቸውም።» በማለት እምነታችንን እንጠብቅ ዘንድ መክረውናል።
"مجموع فتاوى ابن تيمية" (25/329).
በሌላ በኩል ታላቁ ፈቂህ ሸይኽ ሙሀመድ ሷሊህ አልዑሰይሚን رحمه الله ይህንን የ"ፍቅር በዓል" የተሰኘውን የ"ቄስ ቫላንታይን" ወይም ፍቅር ሰጪ ብለው ተኩላዋን በሚያከብሩበት ቀን በተለይ ወጣቶች ቀያይ ልብሶችንና ጫማዎችን መልበሳቸውና ፅጌረዳ አበባ መሰጣጣታቸውን በተመለከተ የሸሪዐን ብይን ተጠይቀው ይህን በዓል ማክበር የማይፈቀድበትን የተለያዩ ምክንያቶች ሲገልፁ☞
«የ"ፍቅር በዓል" የሚባለውን ነገር አስቦ መዋል (ማክበር) በተለያዩ ገፅታዎች አይፈቀድም።
1ኛ: በሸሪዓችን መሰረት የሌለው ቢድዓዊ በዓል በመሆኑ
2ኛ: [ከትዳር ክልል ውጭ ለብልግና ወደሚዳርግ] አደገኛ ወደሆነ አጣብቂኝ ፍቅር የሚገፋፋ በመሆኑ
3ኛ: የደጋግ ቀደምቶቻችንን رضي الله عنهم የሀቅ ጎዳና ወደሚፃረር አስነዋሪ ህይወት እንዲገባ ልቦችን ወደሚያሸፍት ጉዳይ የሚስብ በመሆኑ ይህንን በዓል ማክበር የለበትም።
በመሰረቱ ሙስሊም የሆነ ሰው በዲኑ ሊኮራ እንጂ የእያንዳንዱን ጩኸት በመከተል የሚያስተጋባ ሊሆንም አይገባውም።» በማለት አስጠንቅቀዋል።
مجموع فتاوى ورسائل ابن عثيمين (16/199-200)
----------------
በመጨረሻም ባሳለፍነው መልእክት መሰረት ለእምነታችን ቦታ ልንሰጥና ክብራችንንም ልንጠብቅ ይገባናል። እኛ ለስሜታችን የምንገዛ የልቅ ፍቅር ባሮች ሳንሆን የአላህ አዝዘ ወጀልለ ባሮችና በመመርያው ስር የምንኖር፣ የምንደሰት፣ የምንረካ፣ የምንዋደድ፣ የምንተዛዘንና አብረን የምንጓዝ ህዝቦች ነን።በትዳር ህይወት ውስጥ ቅመም የሆነውን መተዛዘንና መፈቃቀርን ያደረገልን ፈጣሪያችን
وَجَعَلَ بَيْنَكُم مَّوَدَّةً وَرَحْمَةً ۚ
"በመካከላችሁ ፍቅርንና እዝነትን አደረገላችሁ" በማለት ትክክለኛውን የፍቅር ቦታና መግለጪያ በመጠቆም የጋብቻን ፀጋ ስላበሰረንም ምስጋና ይገባዋል። አልሀምዱ ሊላህ።

Abufewzan Ahmed
=========
04/05/1437🕑13/Feb/16
©ተንቢሃት
🎐⁰¹⁹/¹⁶ أحمـــــــــــــــــــabfــــــد



አድራሻዎቻችን ይቀላቀሉ

ፌስቡክ           ቴሌግራም         ዩቲዩብ