Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የፌስቡክ ዉሏችንን እንገምግም... አላሁል ሙስተዓን!

የፌስቡክ ዉሏችንን እንገምግም... አላሁል ሙስተዓን!
ፌስቡክ ከማህበራዊ ድረገፆች ሁሉ ሰዎች በብዛት ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉበት እሙን ነው። ፌስቡክም ይሁን መሰል የማህበራዊ ድረገፆች ብዙ ጥቅም እንዳላቸው የማይካድ ቢሆንም ጥፋታቸውም ከባድ ነው። ባለፉት አመታት በሀገራችን የታዩ ኢስላማዊ መነቃቃቶችን ተከትሎ ፌስቡክ አብዛኛው ህዝበ ሙስሊም ዘንድ እንደብቸኛ የዜና እና የዳእዋ ምንጭ በመታየቱ ተቆጥሮ የማይዘለቅ ህዝብ ፌስቡክን ተቀላቅሏል። ያውም ጥሩ ዲነኛ የሚባለው የማህበረሰብ ክፍል። ታዲያ በአብዛኛው በጥሩ ኒያ የተጀመረው የፌስቡክ ህይወት ግን ሁሉንም አልጠቀመም። የማንበብ ልምድ መዳበር እና ግንዛቤን ማሳደግ እንዳለ ሆኖ ለአንዳንዶች ግን ፌስቡክ ከግል ቻት እና ከሰዎች ከተገለለ የሚስጥር ግንኙነት ያልዘለለ ትርጉም ብቻ ነው ያለው። ያነባሉ ይጠቀማሉ በማይባልበት ደረጃ የጊዜ መግደያ ብቸ ያደረጉት ብዙ ናቸው።
ኢብኑ መስኡድ እንዳስተላለፉት የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፤
لا تزول قدم ابن آدم يوم القيامة من عند ربه حتى يسأل عن خمس : عن عمره فيم أفناه ، وعن شبابه فيم أبلاه ، وماله من أين اكتسبه وفيم أنفقه ، وماذا عمل فيما علم
«በትንሳኤ እለት የአደም ልጅ አምስት ነገሮችን ሳይጠየቅ እግሮቹ ከጌታው ዘንድ አይራመዱም።
እድሜውን በምን እንደፈጀው፣ ወጣትነቱን በምን እንዳሳለፈው፣ ገንዘቡን ከየት እንዳመጣውና በምን ላይ እንዳዋለው፣ ባወቀው ምን እንደሰራበት» ቲርሚዚ ዘግበውታል
በእውነቱ ብዙዎች ማንነታቸውን አጥተውበታል። የሀቅ ተፃራሪ መሆኑን በይፋ ለሚለፍፍ ሁሉ ጊዜና ልባቸውን በመስጠታቸው የእምነትና የስነምግባር መላሸቅ ውስጥ ገብተዋል። የኢማንና የአላማ ፅናትን ማጣት፣ ወንጀል በሚያወርሰው የስነልቦና ቀውስ መጠቃት የብዙዎች እጣፈንታ ከሆነ ሰነባብቷል። የነበሩበትን የእምነትና የኢባዳ ጥንካሬ ተነጥቀዋል። በየመስጂዱ ዲን ሲማር የነበረና የኢልም ጥማት የነበረው ብዙ ወጣት ኪታቦችንም ይሁን የኢልም መድረኮችን ከራቀ ሰነባብቷል።
የተቃራኒ ፆታ ፈተናም ብዙዎችን አጭዷል። ፀረ አኽላቅ እና ፀረ ሀያእ የሆኑ ዋልጌዎች ሁሉ ሰው ጋር የሚደርሱበት ድልድይ ተዘርግቶላቸዋል። በተለይ ለሙእሚናት ፈተናው በእጅጉ ከባድ ነው!! በፌስቡክ ምክኒያት የፈረሱ ትዳሮች እጅግ ብዙ ናቸው። በቅርቡ በምእራቡ አለም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ፌስቡክ ከፍቺ ምክኒያቶች ሁሉ ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። በአንዳንድ ማህበረሰቦች 60% ለሚሆኑት ፍቺዎች መከሰት ዋነኛ ምክኒያት ማህበራዊ ድረገፆች መሆናቸውን ይናገራሉ። በአኼራ ስለ ሁሉም ነገር ከመመርመራችን በፊት ዛሬ የፌስቡክ አጠቃቀማችንን ማጤን፤ በግልም ይሁን በገሀድ ጣቶቻችን የሚፅፉትን ሁሉ መገምገምና አራስን ማረም ወሳኝ ነው።
ይህንን አውሎ ጥፋት በዝምታ መመልከትም ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና ሁላችንም መመካከርን መተዋወስን መዘንጋት የለብንም። ኸሊፋው ኡመር ኢብኑልኸጣብ እንዲህ መክረዋል፤
(حاسبوا أنفسكم قبل أن تحاسبوا، وزنوها قبل أن توزنوا، فإن أهون عليكم في الحساب غداً أن تحاسبوا أنفسكم اليوم).
«ከመመርመራችሁ በፊት እራሳችሁን ተሳሰቡ። ከመገምገማችሁ በፊትም ስራችሁን ገምግሙ። የዛሬ እራስን መመርመርና መተሳሰብ ከነገው ምርመራ ለናንተ የቀለለ ነው። »
ጊዜው አልረፈደምና አሁኑኑ እራሳችንን እንገምግም።
ለዱንያም ይሁን ለዲናችን የማይበጀን ከሆነም ባፋጣኝ መፍትሄ እንፈልግ። አላህን በማውሳት ልቦች ይረጋጋሉ። የፌስቡክ ምርኮኛ ከመሆን አላህ ይጠብቀን!
© ተንቢሀት