Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

በተወሱል ርዕስ የሚነሱ ብዥታዎችና እርምቶቻቸው




በተወሱል ርዕስ የሚነሱ ብዥታዎችና እርምቶቻቸው

ተወሱል በዓረብኛ ቋንቋ ወደ አንድ ነገር መዳረስ ማለት ሲሆን ተወሱል ሸሪዓው የፈቀደውና የከለከለው በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡

☞ ሸሪዓው የተፈቀዳቸው የተወሱል ዓይነቶች፦

ሸሪዓው የፈቀደው ተወሱል በአላህ ስሞች ባህሪዎች፣በሚወዳቸው መልካም ተግባራትና ህያው በሆኑ ደጋግ ባሮች ዱዓ አማካኝነት ወደ አላህ መቃረብ ነው፡፡

ሸሪዓው ከፈቀዳቸው የተወሱል ዓይነቶች መካከል፡-

1ኛ
በአላህ ስሞችና ባህሪዎች ተወሱል ማድረግ፡- ለምሳሌ፦ “يا رحمن ارحمني” (አዛኙ ሆይ! እዘንልኝ) “يا غفار اغفرلي”(መሐሪው ሆይ! ምህረትን ለግሰኝ) “يا شافي اشفيني”(ፈዋሹ ሆይ ፈውሰኝ) በመሳሰሉ የልመና ዓይነቶች የአላህን ስሞችና ባህሪዎችን እያጣቀሱ አላህን መለመን ማለት ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَلِلَّهِ الْأَسْمَاءُ الْحُسْنَى فَادْعُوهُ بِهَا

“ለአላህም መልካም ስሞች አሉት በርሷም ጥሩት” (አል አዕራፍ 180)

2ኛ
አንድ ሰው ራሱ በሰራው መልካም ስራ አማካኝነት ወደ አላህ መቃረብ (ተወሱል) ማድረግ፡፡
ለምሳሌ፦ “ጌታዬ ሆይ! ይህን እለት እገሌን ላንተ ብዬ ከዚያ ጭንቀት ባወጣሁት መልካም ስራዬ ይሁንብህ ዛሬ ከዚህ ጭንቅ አውጣኝ በማለት አላህን መለመን፡፡
ለዚህ ተግባር ከማረጃዎች ውስጥ፡-

الَّذِينَ يَقُولُونَ رَبَّنَا إِنَّنَا آمَنَّا فَاغْفِرْ لَنَا ذُنُوبَنَا وَقِنَا عَذَابَ النَّارِ

“እነዚያ ፦ ጌታችን ሆይ! እኛ አመንን፤ ኃጢአቶቻችንንም ማር፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቀን የሚሉ ናቸው” (አል ዒምራን 16)

رَبَّنَا آمَنَّا بِمَا أَنزَلْتَ وَاتَّبَعْنَا الرَّسُولَ فَاكْتُبْنَا مَعَ الشَّاهِدِينَ

“ጌታችን ሆይ! ባወረድኸው አመንን መልክተኛውንም ተከተልን ፤ ከመስካሪዎችም ጋር መዝግበን (አሉ)” (አል ዒምራን 53)

ነብዩም ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡-
“ከእናንተ በፊት ከነበሩ ህዝቦች ውስጥ ሶስት ሰዎች ሲጓዙ መሸባቸውና ዋሻ ስር ሲገቡ ትልቅ ቋጥኝ ተንከባሎ ዋሻውን ዘጋባቸው፡፡ ከዚያ እንዲህ ተባባሉ ‹‹ ዛሬ ከዚህ ቋጥኝ ሊያወጣችሁ የሚችለው በመልካም ስራዎቻችሁ (ተወሱል በማድረግ) አላህን ስትለምኑ ብቻ ነው፡፡
ከሶስቱ አንዱ እንዲህ አለ “ጌታዬ ሆይ! ያረጁ ወላጆች ነበሩኝ ሁልጊዜ ወተት አልቤ መጥቼ ከቤተሰቦቼና ባሪያዬ በፊት አጠጣቸው ነበርና አንድ ሌሊት እንጨት ስፈልግ አርፍጄ ስመጣ ተኝተው አገኘኋቸው::

ከእንቅልፋቸው መቀስቀም ሆነ ከእነሱ በፊት ቤተሰቦቼን እና ባሪያዬን ማጠጣት ከበደኝና ህፃናቶች እግሬ ስር እየተጯጯሁ እኔ ግን ጎህ ቀዶ እስኪነቁ ድረስ ወተቱ በእጄ ላይ እንዳለ ጠበቅኳቸው፡፡

ጌታዬ ሆይ! ይህን የፈፀምኩት ያንተን ፊት ፈልጌ እንደሆነ ታውቃለህና ካለንበት ጭንቅ አውጣን

ይህን ጊዜ ቋጥኙ ትንሽ ከፈት ቢልም ነገር ግን የሚያስወጣ አልነበረም፡፡
ሌላኛውም፦ “ጌታዬ ሆይ! እኔ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የነበረች የአጎቴ ልጅ ነበረች ነፍሷን አሳልፋ እንድትሰጠኝ ስጠይቄያት እምቢ ብላኝ ቆየችና በረሀብ ጊዜ ስትቸገር ወደኔ መጣች እኔም ክፍት እንድትሆንልኝ 120 ዲናር ሰጠኋትና ተመቻቸችልኝ፡፡ ነገር ግን በቁጥጥሬ ስር ሆና በእግሮቿ መሀል ከገባሁ በኋላ “አላህን ፍራ የታሸገን ያለ ሀቅ አትክፈት” አለችኝ፡፡ ይህን ግዜ እየወደድኳት የሰጠኋትንም ዲናር ትቼላት ተነሳሁ” አለ፡፡

ጌታዬ ሆይ! ይህን የፈፀምኩት ያንተን ፊት ፈልጌ እንደሆነ ታውቃለህና ካለንበት ጭንቅ ገላግለን”

ይህን ጊዜ በድጋሚ ቋጥኙ ትንሽ ከፈት ቢልም ነገር ግን ማስወጣት የሚችል አልነበረም፡፡

ሶስተኛውም፦ “ሰራተኞችን ቀጥሬ ካሰራሁ በኋላ ክፍያቸውን ስሰጥ አንዱ ሳይቀበለኝ ሄደ፡፡ እኔ ግን ገንዘቡን አሳድጌ ብዙ ንብረት አፈራሁበት፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ መጣና ‹‹ አንተ የአላህ ባሪያ ሆይ ደሞዜን ስጠኝ ሲለኝ እነዚህ የምታያቸው ግመሎች ላሞች በጎችና ባሪያዎች ሁሉም ያንተ ገንዘብ ነው አልኩት፡፡ እሱም እባክህን አታሹፍብኝ ሲለኝ በፍፁም እያሾፍኩ አይደለም አልኩት፡፡ ይህን ጊዜ አንድም ሳያስቀርልኝ እየነዳ ወሰዳቸው፡፡
ጌታዬ ሆይ! ይህን የፈፀምኩት ያንተን ፊት ፈልጌ እንደሆነ ታውቃለህና ካለንበት ጭንቅ አውጣን” አለ::

ይህን ጊዜ ቋጥኙ ተከፈተና ወጥተው ተጓዙ”::

3ኛ
ዱዓው ተቀባይነት አለው ተብሎ የሚገመትን ሰው ዱዓ አድርግልኝ በማለት በሱ ተወሱል ማድረግ፡፡
ይህ ድርጊት ሶሃቦች ዝናብ ሲጠፋ አባስን ዱዓ እንዲያደርጉ የሚጠይቋቸው ዓይነት ተግባር ነው፡፡
አነስ ኢብኑ ማሊክ እንደዘገቡት “ኡመር አብኑል ኸጣብ ዝናብ ሲጠፋ ዓባስ ኢብኑ ዓብደል ሙጠሊብን ዱዓ እንዲያደርጉ ይጠይቋቸውና፦ “ጌታችን ሆይ ዝናብ ሲጠፋ በነብያችን አማካኝነት ለምነንህ ታጠጣን ነበርና አሁን በነብያችን አጎት አማካኝነት እንለምንሀለን አጠጣን” ይሉ ነበር::

ይህ ሀዲስ እንደምንመለከተው ህያው የሆነውን የነብዩን አጎት አላህን እንዲለምኑላቸው የሚያደርጉ እንደሆነ ግልፅ ሆኖ ሳለ ነገር ግን አላህ ልቡን ያሳወረው ሰው ከዚህ ሀዲስ አላህን በእገሌ ይሁንብህ ብሎ መለመን እንደሚቻል አድርጎ ይረዳል፡፡

ይህ አረዳድ ስህተት መሆኑ ግልፅ ነው ምክንያቱም የዚህ ሐዲስ ትርጉም በእገሌ ይሁንብህ ማለት እንደሚቻል የሚጠቁም ቢሆን ኖሮ ነብዩን ትተው ወደ ዓባስ ባልዞሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ነብዩ ይኑሩም ይሙቱም በሳቸው ይሁንብህ ማለት ለውጥ አይኖረውም ነበር፡፡ ነገር ግን ዓባስን ዱዓ አድርግልን ማለት ስለሆነ የሞቱትን ነብያችን በዚህ መልኩ ማናገር ስለማይቻል ወደ ዓባስ ዞሩ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በነብዩ ክብር ፣ በእገሌ ሸይኽ ፣ በአባቴ ትልቅነት በመሳሰሉት ይሁንብህ በማለት አላህን መለመን እንደሚፈቀድ አያመለክትም::

☞ ክልክል የሆኑ ተወሱሎች
ክልክል የሆኑ የተወሱል ዓይነቶች ከተፈቀዱት ተወሱሎች ውጭ ያሉ ሁሉ ናቸው፡፡ ይሁንና ሁሉም አንድ ዓይነት ክልክሎች አይደሉም፡፡ ይልቁንስ ትልቁ ሽርክ የሆነና ያልተፈቀደ ቢድዓ የሆነም አለ፡፡

ሽርካዊ ተወሱል
ተወሱል ትልቁ ሽርክ ሆኖ ከእስልምና የሚያስወጣው ከአላህ ውጭ ማምለክ ሲኖረው ነው፡፡ ወደ አላህ ያቃርቡናል በማለት ቀብሮችን ወልዮችንና ሼኾችን ለአላህ የሚገባውን ልመና መለመን፣ ለእርሱ ብቻ የሚገባውን ፍራቻ መፍራት ወይም ማንኛውም ለአላህ የሚገባውን አምልኮ ከርሱ ውጭ ለሆነ ፍጡር የሚያውል በአላህ ላይ አጋርቷል (ሽርክ ፈፅሟል)፡፡
አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ اتَّخَذُوا مِن دُونِهِ أَوْلِيَاءَ مَا نَعْبُدُهُمْ إِلَّا لِيُقَرِّبُونَا إِلَى اللَّهِ زُلْفَى

“እነዚያም ከርሱ ሌላ (ጣዖታትን) ረዳቶች አድርገው የያዙት ወደ አላህ ማቃረብን እንዲያቃርቡን እንጅ ለሌላ አንግገዛቸውም (ይላሉ)” (አዝ ዙመር 3)
ይህ ተግባር ከእስልምና የሚያስወጣ ትልቅ ሽርክ ሲሆን ወደ አላህ ለመቃረብ በማሰብ ቀብር ወይም ቁባ ዘንድ አላህን መገዛት ደግሞ ወደ ትልቁ ሽርክ የሚያደርስ ትንሹ ሽርክ ነው፡፡

☞ ቢድዓዊ ተወሱል
ቢድዓዊ ተወሱል የምንለው አላህ በነብዩ ክብር ወይም በእገሌ ሸይኽ በመሳሰሉት ይሁንብህ ብሎ መለመን ነው፡፡ ይህ ተግባር ነብዩ ያልፈቀዱት እና ሰሐቦችም ያልፈፀሙት በመሆኑ የተጠላ ቢድዓ ነው፡፡

፨ በተወሱል ርዕስ የሚነሱ ብዥታዎችና እርምቶቻቸው፦
ሱና ተከታዮችን የሚፃረሩ አንጃዎች በተወሱል ዙሪያ የተሳሳተ አመለካከታቸውን ለማጠናከርና የያዙትን ሀሰት እምነት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ጥሩ እይታ እንዲኖ ረው ሲሉ የሚያነሷቸው ብዥታዎች አሉ፡፡ ይሁንና የሚያመጧቸው ማጭበርበሪያዎች ከሁለት ነገሮች አይዘልም::

አንደኛ፡- የዘገባ መንገዳቸው የደከመና የተቀጠፉ ሀዲሶችን ለአቋማቸው ማስረጃነት መጠቀም ሲሆን ይህ ግን ትክክል ያልሆኑ ሀዲሶች መሆናቸውን በማወቅ ብቻ ያበቃለታል፡፡

ከሚጠቀሟቸው ትክክለኛ ያልሆኑ ሀዲሶች፡-
1. ‹‹በማዕረጌ አመካኝታችሁ አላህን ለምኑ አላህ ዘንድ ማዕረጌ የላቀ ነውና፡፡›› ‹‹አላህን ስትለምኑ በክብሬ ለምኑት ክበሬ አላሀ ዘንድ ትልቅ ነው፡፡››
ይህ አንድም ዓሊም ያልዘገበውና በየትኛውም የሀዲስ መፅሐፍ ተፅፎ የማይገኝ የተቀጠፈ ወሬ ነው፡፡

2. ‹‹ነገሮች ሲከብዷችሁ በቀብር ሰዎች ታገዙ›› ‹‹የቀብር ሰዎች ከጭንቅ እንዲያወጧችሁ ተማፀኑ››
ይህም በነቢዩ(ሰ.ዐ.ወ) የተቀጠፈ ሀዲስ እንደሆነ ዑለማዎች በሙሉ ተስማምተዋል፡፡

3. ‹‹ለድንጋይ እንኳን ጥሩን ግምት ብታሳድሩ ይጠቅማቹሃል›› ይህ ሀዲስ ውሸት ከመሆኑም በላይ እስልምናን የሚፃረር ሙሽሪኮች የቀጠፉት ነው፡፡

4. ‹‹አደም ሀጢአትን ከተዳፈረ በኋላ እንዲህ አለ “ጌታዬ ሆይ! በሙሀመድ መብት ይሁንብህ እንድትምረኝ እለምንሃለሁ” አላህም “አደም ሆይ! ሙሀመድን ገና ሳልፈጥረው እንዴት አወቅኸው?” ሲለው “ፈጥረኸኝ ነፍስ ስትዘራብኝ ራሴን ከፍ ሳደርግ የዐርሽ እግር ላይ “ላ ኢላሃ ኢለላህ ሙሀመዱ ረሱሉላህ” የሚል ፅሁፍ አነበብኩና ከፍጡራን በጣም የምትወደውን እንጂ ወደአንተ ስም እንደማታስጠጋው ተረዳሁ” ሲል አላህም “በል ምሬሃለው ለሙሀመድም ስል እንጂ አልፈጥርህም ነበር አለው”::

5. ይህም መሠረት የሌለው የሀሰት ወሬ ነው፡፡ “ለአንተ ስል እንጂ ከዋክብትን አልፈጥርም ነበር” የሚለውም ሀዲስ ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህን መሰል የውሸት ሀዲሶችና የተቀጠፉ ዘገባዎችን አንድ ሙስሊም ማስረጃ አድርጐ ሊመረኮዝባቸው ይቅርና ዞር ብሎም ሊያያቸው አይገባም፡፡

ሁለተኛ፡- በትክክለኛ ዘገባ ከነብዩ የተላለፉ ሀዲሶች ቢሆኑም ነገር ግን እንደነዚህ አይነት ሰዎች በትክክል ካለመገንዘብ አልፈው የሚጠቁመውን ትርጉም የሚያዛቧቸው ሀዲሶች ናቸው:: ከነዚህም ውስጥ፡-

1. ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ዝናብ ሲጠፋ በአባስ አማካኝነት እንዲህ በማለት አላህ እንዲያዘንብላቸው ይለምኑ ነበር ‹‹ጌታዬ ሆይ በነብዩ አማካኝነት ዝናብን እንለምንህና ታዘንብልን ነበር አሁን ደግሞ በአጎታቸው ዓባስ አማካኝነት እንለምንሃለን አጠጣን›› ይዘንብላቸዋል፡፡
ይህን ሀዲስ የሚረዱት ዑመር ያደረገው ተወሱል አላህ ዘንድ ባለው የዓባስ ክብር እንደሆነ ነው፡፡ “በአባስ አማካኝነት …………. በነብዩ አማካኝነት…………. ማለት በነሱ አረዳድ አላህ ዘንድ ባላቸው ክብር” ማለት ሲሆን
ይህ ግን መቶ በመቶ የተሳሳተ ግንዛቤና የራቀ ትርጓሜ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰሃቦች ዘንድ በነብዩ አካልም ይሁን ክብር አማካኝነት አላህን መለመን አይታወቅም፡፡ ሲፈፅሙት የነበረው ተወሱል ነብዩ በህይወት እያሉ ዱዓ እንዲያደርጉላቸው መጠየቅ ነበር፡፡ ዑመርም ቢሆን እኛ በነብያችን አጐት አማካኝነት እንለምንሃለን ማለቱ በእርሱና በክብሩ ማለት ሳይሆን በእርሱ ዱዓ አማካኝነት ማለት ነው፡፡
በሰው ወይም በሰው ክብር አላህን መለመን እነርሱ ዘንድ ተፈፃሚ ቢሆን ኖሮ ዑመር ነብዩን ትቶ ወደ ዓባስ ባልመጣ ነበር፡፡ ሰሃቦችም ቢሆኑ እንዴት ታላቁን ፍጡር ነብዩን ትተህ ዓባስን ትመርጣለህ? ሲሉ ይቃወሙ ነበር፡፡ ይህን አለማለታቸውና ነብዩ በህይወት እያሉ የሚያደርጉት በእርሳቸው ዱዓ ምክንያት ተወሱል የሚያደርጉ መሆኑ መታወቁ የተፈቀደው ተወሱል በዱዓ እንጂ በሰውዬው ክብር እንዳልሆነ ግልፅ ይሆናል፡፡
በዚህ መሰረት ሀዲሱ በሰዎች ወይም በክብራቸው አላህን መለመን እንደሚቻል የሚጠቁምበት ምንም አቅጣጫ እንደሌለው ግልፅ ይሆናል፡፡

2. ዑስማን ኢብኑ ሁነይፍ እንዳስተላፉት ‹‹አንድ አይነ ስውር ሰው ወደ ነብዩ በመምጣት አላህ እንዲፈውሰኝ ለምኑልኝ አላቸው፡፡ እሳቸውም “ከፈለግክ ትግስት አድርግ ይህ ለአንተ የሻለ ነው ከፈለግክ ደግሞ አላህን እለምንልሃለው” አሉት፡፡ እሱም “አላህን ለምኑልኝ” አላቸው:: ከዚያም ውዱእ አሳምሮ እንዲያደርግና እንዲህ ብሎ እንዲለምን አዘዙት “ጌታዬ ሆይ! ጉዳዬን እንድታሳካልኝ እየተማፀንኩ በእዝነቱ ነብይ ነብይህ ሙሐመድ ምክንያት ወዳንተ ዞርኩ ጌታዬ ሆይ! ነብዩን በእኔ ጉዳይ አማላጅ አድርጋቸው፡፡››ከዚህም ሀዲስ በነብዩ ክብር ተወሱል ማድረግ እንደሚቻል ግንዛቤ ቢወስዱም ነገር ግን ሀዲሱ ውሰጥ ይህን የሚጠቁም የለም፡፡ ምክንያቱም አይነስውሩ ነብዩ ዱዓ አድርገውለት አላህ አይኑን እንዲመልስለት ሲፈልግ ነብዩ እንዲህ አሉት “ከፈለግህ ትግስት አድርግ ከፈለግህ ደግሞ ዱዓ አድርግልሃለው” እሱም ዱዓ እንዲያደርጉለት መረጠ ይህ የሚያስረዳው በነብዩ ዱዓ ተወሱል እንዳደረገ እንጂ በእርሳቸው አካል ወይም ክብር አላህን እንደለመነ አይደለም፡፡

ዑለማዎች ይህንን ሀዲስ ስለ ነብዩ ተዓምራትና ስለ ዱዓቸው ተቀባይነት የሚተነትን ርዕስ ስር ሲጠቅሱት መስተዋሉም ይህን ይጠቁማል፡፡ ምክንያቱም አይነስውሩ አላህ አይኑን የመለሰለት በነብዩ ዱዓ በረከት ነው፡፡

✘ ነብዩ ከሞቱ በኋላ ግን ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በመሞታቸው ዱዓ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ነብዩም እንዲህ ብለዋል ‹‹አንድ ሰው ሲሞት ከሶስት ነገሮች በቀር ስራዎቹ ሁሉ ይቋረጣሉ ቀጣይነት ያለው ምፅዋት፣ ወይ ሰዎች የሚጠቀሙበት እውቀት ወይም ደግሞ ለእርሱ ዱዓ የሚያደርግለት መልካም ልጅ፡፡›› ዱዓ በመሞት ከሚቋረጡ መልካም ተግባራት ይመደባል፡፡

በጥቅሉ እነዚህ ሰዎች የሚንጠለጠሉት ሁሉ ማስረጃ በሌለው ነገር ነው:: የሚጠቀሙት ዘገባው ትክክል ያልሆ ነን ተራ ወሬ ወይም ከርዕስ ውጭ የሆነን ሀዲስ ነው::

http://www.facebook.com/emnetihintebiq