Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሌሎችን በመጥቀም የሚገኝ እርካታ

ሌሎችን በመጥቀም የሚገኝ እርካታ
“የሰዎችን ጉዳዮች በመፈፀም የሚገኝ የሆነ በተግባር የሞከረው እንጂ (ሌላው) የማያውቀው እርካታ አለ!! የፈለገ ብትንቀው መልካምን ነገር ስራ፡፡ የትኛው በጎ ስራ ጀነት እንደሚያስገባህ አታውቅምና!!” ምንጩን ያላወቅኩት ድንቅ አባባል!! (በአልኢማም ኢብኑልቀይዪም ረሒመሁላህ ስም ተሰራጭቶ ባገኘውም በሻሚላም በጎግልም ታግዤ ከራሳቸው ከኢብኑልቀይዪም ኪታቦች ለማረጋገጥ ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካልኝም፡፡)
ከምንም በላይ ግን ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡- “ከሰው ሁሉ በላጩ ለሰዎች ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ነው፡፡” [አስሶሒሐህ፡ 426] በሌላ ዘገባ ደግሞ “ከሰዎች ሁሉ አላህ ዘንድ የተወደደው ለሰዎች ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ነው” ብለዋል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 906] ስለዚህ አላህን ብቻ በማሰብ ለሰዎች የሚጠቅምን ስራ እንስራ፡፡ ለወላጆቻችን፣ ለልጆቻችን፣ ለእህት ወንድሞቻችን፣ ለዘመዶቻችን፣ ለጓደኞቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ በስራ ቦታ፣ በመንገድ ላይ ለሚያጋጥመን፣ በማህበራዊ ድረ-ገፅ፣… አቅማችን በሚችለው ሁሉ መልካምን በመዋል ከአላህ ዘንድ ያለንን ደረጃ ከፍ ለማድረግ፣ ውዴታውንም ለመጎናፀፍ እንትጋ፡፡ ከጥቅም ሁሉ በላጩ ደግሞ ተውሒድን ለሰዎች ማድረስ ነው፣ ከሺርክ ማስጠንቀቅ፡፡ ከቻልን በራሳችን በማስተማር፡፡ ካልቻልን የሚያስተምሩትን በምንችለው ሁሉ በማገዝ፣ የተውሒድ መፃህፍት እና ካሴቶችን በማሰራጨት፣ ስጦታ በማቅረብ፣ ሰዎችን ከጠማማ አንጃዎች በማስጠንቀቅ… ወዘተ፡፡
ባይሆን አደራ የኒያ ነገር እንዳይረሳ፡፡ አላህን ታስቦ ካልተፈፀመ የፈለገ መልካም ቢሰሩ እንደተበተነ ትቢያ ነው የሚሆነው፡፡
ሰዎችን መጥቀም ያልቻለ ቢያንስ ቢያንስ ምላሱንም እጁንም በመሰብሰብ ያሳርፋቸው፡፡ ይህም ሶደቃ ነው፡፡ “ሙስሊም ማለት ሙስሊሞች ከምላሱም ከእጁም (ትንኮሳ) ሰላም ያገኙበት ነው” ይላሉ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡
ልብ በል! ይሄ ማለት ግን ተሻጋሪ የቢድዐህ ጥፋት ያለባቸውን አካላት ለማስጠንቀቅ “ስም አታንሳ” ማለት አይደለም፡፡ ከሙብተዲህ ማስጠንቀቅን የሚደግፉ እጅግ በርካታ ማስረጃዎች አሉ፡፡ አንዳንዱ አጉል ብልጥ ሊሆን ይሞክራል፡፡ ከሚደግፋቸው የቢድዐህ ተጣሪዎች ለመከላከል ሲል የነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሐዲሥ ያለቦታው ይጠቀማል፡፡ እሱ እራሱ ግን በሀሳብ የማይጋሩትን አካላት ለማብጠልጠል የሚያጣቅሰው ሐዲሥ አይገታውም፡፡
አሕባሹ ከዐብደላህ አልሀረሪ ለመከላከል ሲፈልግ “ሙስሊም ማለት ሙስሊሞች ከምላሱም ከእጁም (ትንኮሳ) ሰላም ያገኙበት ነው” የሚለውን ሐዲሥ ያጣቅሳል፡፡ ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲልወሃብን፣ ኢብኑ ተይሚያን ሲያብጠለጥል ግን ይህን ሐዲሥ አያስታውስም ሊያስታውስም አይፈልግም፡፡
ኢኽዋኑ ከነሰይድ ቁጥብ፣ ቀርዷዊ፣… ለመከላከል ሲፈልግ “ሙስሊም ማለት ሙስሊሞች ከምላሱም ከእጁም (ትንኮሳ) ሰላም ያገኙበት ነው” የሚለውንና መሰል ሐዲሦችን ያጣቅሳል፡፡ ሙሐመድ አማን አልጃሚን፣ ረቢዕ አልመድኸሊን፣ ግፋ ሲልም እነ አልባኒን ሲያብጠለጥል ግን ይህን ሐዲሥ አያስታውስም ሊያስታውስም አይፈልግም፡፡

ወደ ነገሬ ስመለስ እስኪ አሁን የራሳችንን ሚና እንታዘብ፡፡ እውነት እኛ ለሰዎች የሚጠቅም ነገር አለን? ካለን እሰየው እናዳብረው፡፡ ከሌለን እራሳችንን ለለውጥ እናዘጋጅ፡፡ ከትላንት ዛሬ እንሻል፡፡ ከዛሬ ደግሞ ላማረ ነገ እንሰንቅ፡፡ ሁሌ ባለበት የሚዘልቀው ለውጥ የማይነካካው በድን የሆነ ግኡዝ ነገር ነው፡፡ “ሸንበቆ አስር አመት ውሃ ውስጥ ቢቆይ አዞ አይሆንም” ይባላል፡፡ ህህ ከዚያ በላይስ ቢቆይ?
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 30/2008)

Post a Comment

0 Comments