Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሲራጥና በርሱ ላይ ማለፍ


በሲራጥ ላይ ማለፍ ከቂያማ ክስተቶች አንዱ ነው ። <<ሲራጥ>> በጀሃነም ላይ የተዘረጋ ድልድይ ሲሆን ፥ ሁሉም ሰዎች ያልፉበታል ። ሰዎች በርሱ ላይ በሚያልፉበት ወቅት የሚኖራቸውም ፍጥነት እንደየስራዎቻቸው ይወሰናል ። ከጸጉር የቀጠነ ፣ ከሰይፍ የሰላና ከእሳት ረመጥ የበለጠ የሚያቃጥል ነው ። ሲራጥ እንዲነጥቁት የታዘዙትን ሰው የሚነጥቁ መንጠቆዎች አሉበት ። ሰዎች ፍጥነታቸው እንደየ ስራቸው ሆኖ ፦ በርሱ ላይ ያልፋሉ ። እንደ መብረቅ ብልጭታ በሆነ ፍጥነት የሚያልፉ አሉ ። እንደ ንፋስ ፈጥኖ የሚሻገረውም አለ ። እንደገስጋሽ ፈረስ ፈጥኖ የሚሻገረውም አለ ። እንደ ገስጋሽ የእግር ተጓዥ የሚፈጥንም አለ ። ከእርምጃ ባልበለጠ አካሄድ የሚያልፉትም አሉ ። እየተንገዳገደ የሚሻገረውም አለ ። ተይዞ ጀሃነም ውስጥ የሚቀቀልም አለ ። ከጥፋት ይጠብቀን ዘንድ አላህን እንማፀናለን ።

ሰፋሪኒ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል ፦ <<ሲራጥ መኖሩን ይህ ኡምማ በአንድ ድምፅ ያፀድቃል ። ግና የእውነት ባለቤቶች በዘገባዎች የተላለፈላቸውን መልዕክቶች እንዳለ ይቀበላሉ ። ይኸውም ሲራጥ ከፀጉር የቀጠነና ከሰይፍ የሰላ መሆኑን ያፀድቃሉ ። ይህንን ግልፅ የዘገባዎች መልዕክት የሙዕተዚላ አመለካከት አራማጅ የሆኑት ቃዲ አብድልጀባርና ተከታዮቻቸው አይቀበሉትም ። <<ሲራጥ በዚ ባህሪው በበላዩ ማለፍ ይከብዳል ። ቢቻልም እንኳን የቅጣት አይነት ነው ። ሙእሚኖችና መልካም ሰዎች ደግሞ ሊቀጡ አይገባም >> ይላሉ ። <<ሲራጥ በሚል ማመላከት የተፈለገው በተከታዮች አንቀፆች የተገለፁ የጀንነትና የጀሀነም መንገዶች ናቸው >> ይላሉም ፦

سَيَهْدِيهِمْ وَيُصْلِحُ بَالَهُمْ
በእርግጥ ይመራቸዋል፡፡ ኹኔታቸውንም ሁሉ ያበጃል፡፡ /ሙሐመድ ፥ 5/

مِن دُونِ ٱللَّهِ فَٱهْدُوهُمْ إِلَىٰ صِرَٰطِ ٱلْجَحِيمِ
«ከአላህ ሌላ (የሚገዙዋቸውን ሰብስቧቸው) ወደ እሳት መንገድም ምሩዋቸው፡፡ /አል ሳፍፋት ፥ 23/

<<ሲራጥ ግልፅ መረጃ ፥ የተፈቀደ ተግባር ፥ መጥፎ ሥራ ........ ነው ሰውየው ይጠየቅበታል ። በርሱ ይቀጣበታል>> የሚል ትርጓሜ የሰጡትም አሉ ።

ይህ ሁሉ ትክክለኛ አመለካከት አይደለም ። በዘገባዎች የተገለፀውን እውነታ መቀበል ግዴታ ነው ና ። በሲራጥ ላይ ማለፍ በውሃ ላይ ከመጓዝ ፥ በሰማይ ላይ ከመብረር ወይም ከመቆም የበለጠ የሚያስገርም አይደለም ። ነብዩ (ሰለላሁ አለይሒ ወሰለም) በመጭው ዓለም ካፊሮች በፊቶቻቸው ተደፍተው ስለመነዳታቸው ተጠይቀው ፦ <<የአላህ ችሎታ ይህን የመፈፀም ብቃት አለው>> የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።

ስዩጢ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል ፦ <<ሐውድ ከሃምሳ በላይ ሶሐባዎች ባስተላለፋአቸው ዘገባዎች ውስጥ ተወስቷል ። ከእነኝህ ሶሃቦች መካከል አራቱ ኸሊፋዎች ፥ በርካታ ሐዲስ ያጠኑ ሶሐቦችና ሌሎችም ይገኙበታል በሁሉም ላይ የአላህ ውዴታ ይስፈን ።>>

ቡኻሪና ፣ ሙስሊምና ሌሎችም የሐዲስ አውታሮች አብድላህ ኢብን ዐምር ኢብንል ዐስን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ አለይሒ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል ፦ <<የኔ ሐውድ ለአንድ ወር ያሕል ያስኬዳል ። ውሃው ከወተት የነጣ ነው ። ሽታው ከሚስክ የበለጠ መአዛ አለው ። መጠጫዎቹ እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበራሉ ከርሱ የጠጣ ዘልዓለም የውሃ ጥም አይሰማውም ።>>

ሙስሊም አነስ ኢብን ማሊክን በመጥቀስ እንደዘገቡት የአላህ መልዕክተኛ ትንሽ አሸለቡ ። ከዚያም እየሳቁ ተነሱና <<ምሉዕ ምዕራፍ ተወረደልኝ ።>> በማለት ፦ <<በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ። እኛ በጣም ብዙ ነገሮችን ሰጠንህ >> የሚለውን የቁርአን ምዕራፍ /አል ከውሰርን/ እስከመጨረሻው አነበቡ ። ከዚያም <<ከውሰር / በጣም ብዙ በጎ ነገርን / ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ? >> ሲሉ ጠየቁ ። <<አላህና መልዕክተኛው ያውቃሉ >> ተባሉ ። <<ጌታዬ ጀነት ውስጥ የሰጠኝ ወንዝ ነው ። በጣም ብዙ በጎ ነገሮች አሉት ። በቂያማ ዕለት ተከታዮቼ ከርሱ ይጠጣሉ ። መጠጫዎቹ እንደ ከዋክብት ያበራሉ ። ከርሱ እንዳይጠጣ የሚከለከል ሰው አለ ። <<ጌታዬ ሆይ ! ከተከታዮቼ አንዱ ነው ።>> እላለው ። <<ከአንተ ሕልፈት በሗላ የተከሰተውን አታውቅም >> የሚል ምላሽ ይሰጠኛል ።

ቁርጡቢይ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል ፦ <<ዑለሞቻችን እንደሚሉት ከአላህ ዲን የወጣ ወይም አላህ የማይወደውንና ያልፈቀደውን ነገር ከዚህ ዲን ላይ የጨመረ ከሐውዱ ከሚባረሩ ሰዎች ይሆናል ። ከሁሉም ይበልጥ ለመባረር ተገቢ የሚሆኑት እንደ ኸዋሪጅ ፣ ሙዕተዚላ ፣ ራፊዷ ያሉና መሰል ከሙስሊሙ ኡምማ ያፈነገጡ አንጃዎች ናቸው ። እነኝህ ሁሉ የአላህን ዲን ለውጠዋልና ። የበዛ ግፍ የሚፈፅሙ ፣ ሐቅን ያድበሰበሱና ፣ የእውነት ተከታዮችን ያዋረዱ ከታላላቅ ወንጀሎች ውስጥ የተዘፈቁና ሐጢአትን አቅልለው የሚመለከቱ ፥ እንዲሁም መንገድ የሳቱና የቢድዓ ጀማአዎች ባጠቃላይ ከሐውዱ ይባረራሉ ። የአላህን ዲን የለወጡት በዐቂዳቸው ሳይሆን በተግባራቸው ብቻ የሆኑ ወገኖች ለጊዜው ከተባረሩ በሗላ ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሐውዱ ይቀርባሉ ።

ሙዕተዚላዎች ይህን እውነታ ተቃርነዋል ። ሐውዱ መኖሩ በቁርአንና በሐዲስ ቢገለፅም ሊያወድቁት አልፈቀዱም ። የሐውዱን መኖር ያልተቀበሉ ሁሉ ሙብተዲዕ በመሆናቸው ከማንም ይበልጥ ከሐውዱ ሊርቁ የተገባ ነው ።

ያ አላህ የመልዕክተኛህን ሐውድ ከሚታደሉት ባሮችህ አድርገን ። በዲን ላይ ከሚፈበረኩ አዳዲስ ፈጠራዎች በአንተ እንጠበቃለን ። የመልዕክተኛህን ሱና የሙጥኝ ካሉና በዚያው ላይ ሞተው ከአንተ ጋር ከሚገናኙ እንቁ ባሮች አድርገን ። አሜንን !!!

ምንጭ ፦ አል ኢርሻድ ዶ/ር ሷሊህ ቢን ፈውዛን ቢን ዐብደላህ አል ፈውዛን (ሀፊዘሁላህ)

✍ አቡ ሱመያ ነጋሽ (6 ሙሐረም 1436)

Post a Comment

1 Comments