Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የራስዎንም ይሁን የልጆችዎን ስሞች ከሸሪዐህ ጋር የማይፃረሩ አለመሆናቸውን አስረግጠዋልን?


የራስዎንም ይሁን የልጆችዎን ስሞች ከሸሪዐህ ጋር የማይፃረሩ አለመሆናቸውን አስረግጠዋልን?

በቤታችን ወይም በአካባቢያችን በተለያዩ ምክንያቶች በእምነታችን የማይፈቅዱ ስሞች በብዛት ያጋጥማሉ፡፡ በብዛት እነዚህ የተሳሳቱ ስሞች የሚወጡት ለጉዳዩ ኢስላም የሚሰጠውን ቦታ ስለማያውቁ በግዴለሽነት፣ ከጎረቤት፣ ከዜና ወይም ከፊልም ላይ ያዩትን እንዳመጣላቸው በመሰየም ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ “አበጀሁ” ብሎ ጥፋት ላይ የሚወድቅ አለ፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እርማት የሚሹ ስሞችን ልናርም ይገባናል፡፡ በተለይ ደግሞ ልጆቻችን ህጋዊ ማስረጃዎቻቸው (ዶክሜንቶቻቸው) ላይ አላስፈላጊ ስም ሰፍሮ ሁሌ ምቾት ከሚነሳቸው በጊዜ ልናርመው ይገባናል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተለያዩ ስሞችን በተለያዩ ምክንያቶች ቀይረዋል፡፡ ለምሳሌ “ዓሲያህ” (በሷድ ፊደል) የሚለውን ስም በጀሚላህ ቀይረዋል፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] “አልዓስ” የሚባለውን “ሙጢዕ” ብለው ሰይመውታል፡፡ [ሙስሊም] እንዲሁም “ዐዚዝ” የሚለውን “ዐብዱርረሕማን” ብለው ቀይረውታል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 904] ሌሎችም አሉ፡፡
ለመሆኑ የማይፈቀዱ ስሞችን መለያ ጥቅል መርህ ይኖራልን? ከተለያዩ ምንጮች ያገኘሁት መረጃ ይህን ይመስላል፡-
1. እያንዳንዱ አስቀያሚ ወይም መጥፎ መልእክት ያዘለ ስም ሁሉ ክልክል ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አልዓሲ” (ወንጀለኛ)፣ “ዐትላህ” (አረመኔ)፣ “ሸይጧን”፣ “ጉራብ” (ቁራ)፣ “ሐርብ” (ጦርነት) እና መሰል ስሞችን ቀይረዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት መጥፎ መልእክት ያላቸው ስሞች እንደማይፈቀዱ ዓሊሞች ይጠቅሳሉ፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አስቀያሚ ስም ሲሰሙ በጥሩ ስም ይቀይሩት ነበር፡፡ [ሶሒሑልጃሚዕ፡ 4743]
2. እንደ “አልቁዱስ”፣ “አርረሕማን”፣ “አልሙሀይሚን”፣ … ያሉ የአላህ ብቻ መጠሪያ የሆኑ ስሞችንም በምንም መልኩ ለፍጡር መጠሪያነት ልናውል አይገባም፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አቡልሐከም” የሚለውን “ኩንያ” “አቡ ሹረይሕ” ሲሉ ቀይረውታል፡፡ [ኢርዋኡልገሊል፡ 2615] “ንጉሰ ነገስት” እና መሰል ስያሜዎችም ከዚሁ ስር ይካተታሉ፡፡
3. ግብረ-ገብነትን የሚፃረሩ፣ ስሜት ቀስቃሽ ስሞችም አይፈቀዱም፡፡ ለምሳሌ፡- ኑሃድ (ጡቷ ወጣ ወጣ ያለች ሴት ለማለት ነው)፣ ጋዳህ (ለስላሳ እና ምቹ የሆነች ሴት ለማለት ነው)፣ ፊትናህ፣ ፋቲን፣ ዐቢር፡፡ በሀገራችንም ተቀራራቢ ወይም የከፋ መልእክት ያላቸው ስሞች አሉ፡፡
4. ለፍጡር ባርነትን ወይም በደጋጎች ላይ ድንበር ማለፍን የሚያመላክቱ ስሞችን ማውጣትም እንዲሁ ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ “ዐብዱርረሱል” (የረሱል ባሪያ)፣ “ዐብዱልከዕባህ”፣ “ዐብዱልሑሰይን”፣ …፡፡ እንዲህ አይነቱ ስም ሐራም በመሆኑ ላይ ኢጅማዕ እንዳለበት ኢብኑ ሐዝም ረሒመሁላህ ጠቅሰዋል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ አይነት ስሞችን ቀይረዋል፡፡
5. ውዳሴና ማጥራራት ያለባቸው ስሞችም እንዲሁ አይፈቀዱም፡፡ ለምሳሌ “ዒዘዲን”፣ “ናሲሩዲን”፣ “ሙሕዩዲን”፣ “ኢማን”፣ “ኢስላም”፣ “ተቅዋ”፣ “ሰይፈልኢስላም”፣ “ኸይረድዲን”፣ “ኑረላህ” እና የመሳሰሉት፡፡ እነዚህ ስያሜዎች ከእውነታ የራቀ ግነት የያዙ ናቸው፡፡ (በተለይ “ኑረላህ” የሚለው አላስፈላጊ መልእክት ሊያስተላልፍ ስለሚችል “ጥሩ አይደለም ሊቀየር ይገባል” ይላሉ ኢብኑ ባዝ ረሒመሁላህ፡፡) ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “በርራህ” የምትባለዋን ሶሐቢያህ “ዘይነብ” ብለው መቀየራቸው ከግምት ይግባ፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] እንዳውም በአንድ ወቅት ስሟን ከቀየሩ በኋላ አንዷ “በርራህ” ብላ ስትጣራ ሰምተው “እራሳችሁን አታጥራሩ!! ከናንተ ጋጠ-ወጧን ከክቡሯ ለይቶ የሚያውቀው አላህ ነው” ብለዋል፡፡ [ሙስሊም] ጁወይሪያም እንዲሁ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ቀይረውት እንጂ “በርራህ” ነበር ስሟ፡፡ [ሙስሊም] ከዑለማዎች በነዚህ ቅፅሎች የሚታወቁ መኖራቸው እንዳይሸውደን፡፡ ለምሳሌ ነወዊ “ሙሕዩድዲን”፣ ኢብኑ ተይሚያም “ተቅይዩድዲን” በሚል ቅፅል ቢታወቁም እነሱ ግን ይጠሉት እንደነበር ተወስቷል፡፡ ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ “ዒዝዘዲን፣ ሙሕዩድዲን፣ ናሲሩድዲን እና መሰል ስሞችን መሰየም አይፈቀድም” ይላሉ፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 216]
6. ካፊሮች የሚታወቁባቸው የሆኑ ስሞችን መጠቀምም አይፈቀድም፡፡ ለምሳሌ ዮሐንስ፣ ቴዎድሮስ፣ ሮናልዶ፣ ሜሲ፣…
7. የጋጠ-ወጦች፣ የዘፋኞች፣ የፊልም ሰዎችን ስያሜ ሆን ብሎ ለልጆች ማውጣት ተገቢ አይደለም፡፡
8. “በቁርኣን ስሞች እና በቁርኣን ምእራፎች መሰየምም እንዲሁ ከሚከለከሉ ስሞች ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ‘ጧሀ’፣ ‘ያሲን’፣ ‘ሐሚም’፣ …፡፡ (ኢማሙ) ማሊክ፡ ‘ያሲን’ ብሎ መሰየም የተጠላ እንደሆነ አስፍረዋል፡፡ ‘ያሲን’ እና ‘ጧሃ’ ከነብዩ ስሞች ነው እያሉ መሀይማን የሚያወሱት ልክ አይደለም፡፡ እነዚህ ፊደሎች ልክ እንደ ‘አሊፍ ላም ሚም’፣ ‘ሓ ሚም’ እና መሰሎቻቸው የሚመደቡ ናቸው፡፡” ይሄ (8ኛው) ነጥብ ሙሉ ለሙሉ ከኢብኑልቀይዪም የተወሰደ ነው፡፡ [ቱሕፈቱልመውዱድ፡ 127]
9. በቃላቱ ውበት ተመርኩዞ በረካ የሚሻትባቸው ወይም “ተፋኡል” የሚታሰብባቸው የሆኑ “ምን ይሄ እንትን ነው? እንትን ነው እንጂ!” እያሉ ሰዎች ገልብጠው መጥፎ ግምት (ተሻኡም) የሚያሳድሩባቸው ስሞችም ክልክል ናቸው፡፡ እናም እንደ “የሳር”፣ “ረባሕ”፣ “ነጂሕ”፣ “አፍለሕ”፣ “በረካህ”፣ “ናፊዕ” እና መሰል ስሞችን እንድንርቅ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አሳስበዋል፡፡ [ሙስሊም፡ 5722-5724]
10. የሚወጣው ስም የኋላ ኋላ የልጁን ስነ-ልቦና የሚጎዳ፣ በእኩዮቹ የሚሾፍበት፣ የሚሳለቁበት ሊሆንም አይገባም፡፡ በየቋንቋው እንዲህ አይነት ስሞች በብዛት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ፡- “ዘገየ”፣ “ሞቅያለው”፣ “እርገጤ” … አማርኛ ውስጥ ከሚገኙ ለሹፈት ከሚያጋልጡ ስሞች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ የዐረብኛ ስሞች በራሳቸው ጥሩ ይሆኑና በአካባቢው ቋንቋ ግን መጥፎ መልእክት ኖሯቸው ለተጠሪው መቸገር ሰበብ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የአካባቢያችንን እውነታ ከግምት ልናስገባ ይገባል፡፡ ሸይኽ ኢብኑልዑሠይሚን ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰው ለልጁ ትልቅ ሲሆን የሚነወርበት፣ የሚንቋሸሽበት ያልሆነን ስም የመምረጥ ግዴታ አለበት፡፡ ምናልባት አባት የሆነ ስም ሊመስጠው ይችላል፡፡ ነገር ግን የኋላ ኋላ ልጁ የሚቸገርበት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ወላጁ ለልጁ መቸገር መንስኤ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ ሙእሚንን ማስቸገር ደግሞ ክልክልነቱ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም ውብ የሆኑ እና አላህ ዘንድ የተወደዱ ስሞችን ሊመርጥ ግድ ይለዋል፡፡” [አሽሸርሑልሙምቲዕ፡ 7/495]
11. ልጆችን “ጂብሪል”፣ “ሚካኢል” … እያሉ በመላእክት ስም መሰየምን በተመለከተ ዑለማዎች የተለያዩ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ኢብኑልዑሠይሚን ረሒመሁላህ ከነዚህ ሀሳቦች ውስጥ “የተጠላ ነው” ወደሚለው በማዘንበል “በነዚህ ስያሜዎች ልንሰይም አይገባም” ይላሉ፡፡ [አሽሸርሑልሙምቲዕ፡ 7/495] ሐቁ ምንም ይሁን ምን ከውዝግብ መራቁ ጥሩ ብልሃት ነው፡፡
12. የሚወጣው ስም ለጆሮ እንግዳ ለምላስ ከባድ ባይሆን ተመራጭ ነው፡፡ ያለበለዚያ በአቅራቢያው ባሉ ሰዎች ዘንድ ተንሻፎ የመጠራቱ እድል ሰፊ ነው፡፡ የሆነ ቦታ “ቁርረተልዐይን” ለማለት ከብዷቸው “ቁራ” እያሉ እንደሚጠሩ ሰምቻለሁ፡፡ ተጠሪው ላይ የሚፈጥረውን ስሜት አስቡት፡፡
13. አንዳንዱ ቃሉ ቁርኣን ላይ ስለሚገኝ ብቻ ምንም ሳያስተውል፣ መልእክቱን በቅጡ ሳይረዳ የሚሰይም አለ፡፡ ሸይኽ ኢብኑልዑሠይሚን ረሒመሁላህ ከዚህ ጋር የሚያያዝ አንድ አስቂኝ አጋጣሚ እንዲህ ይነግሩናል፡- “የሆነ ሰው ልጁን ‘ነክተል’ ብሎ ይሰይመዋል፡፡ ‘ምነው?’ ሲባል ‘አይ ይሄ የዩሱፍ ወንድም ስም ነው’ በማለት (فأرسل معنا أخانا نكتل) ብሎ ማስረጃ ያጣቅሳል፡፡” አንቀፁዋ ውስጥ የተጠቀሰው “ነክተል” የሚለው ቃል መልእክት ግን “ይሰፈርልናል” ማለት ነው፡፡ አስቂኝ!! ይሄ እውነት ተከስቶ ከሆነ ቁርኣን ላይ ስለተገኘ ብቻ መልእክቱን በውል ሳይለዩ መሰየም ሰያሚንም ተሰያሚንም የነቁ እለት የሚያሳፍር ጥራዝ-ነጠቅ አካሄድ ነው፡፡
14. የሚወጣው ስም በቤተዘመዱ ወይም በአቅራቢያው ካሉ ዘንድ ከመብዛቱ የተነሳ እስከሚያምታታ ባይደርስ ጥሩ እንደሆነ ኢብኑልዑሠይሚን ይገልፃሉ፡፡ አንዳንዱ ስም ድግግሞሹ ከመብዛቱ የተነሳ እስከ አራት እስከ አምስተኛ አያት ካልተጠቀሰ አንዱን ከሌላው ለመለየት የሚያስቸግርበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ይሄ “ሐራም ነው” ባይባልም ባይደረግ ይመረጣል፡፡
ባጭሩ የዚህ ፅሁፍ አላማ የተከለከሉ ስሞችን መዘርዘር አይደለም፡፡ ይልቁንም የማይፈቀዱ ስሞችን የምንለይባቸውን መርሆዎች ማሳየት፣ ስንሰይም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መጠቆም፣ የራሳችንም ይሁን “የኛ” የምንለው ሰው ስም ላይ ፍተሻ እንድናደርግ ማስታወስ እና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በጊዜ እርማት እንድናደርግ ማመላከት ነው፡፡ ይስተዋል! የክልከላ ዝርዝሮቹ በዝተው ከታዩን መለስ ብለን እናጢናቸው፡፡ አብዛሃኛዎቹ ገደቦች ለማንም የማይሰወሩ ሲሆኑ ሲያጋጥሙንም “ግን ለምን?” ብለን የምንደነቅባቸው ናቸው፡፡ በዚያ ላይ የሚወደዱና የሚፈቀዱ ስሞች ሞልተው የተትረፈረፉ ናቸው፡፡ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡-
1. ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ይላሉ፡- “አላህ ዐዝዘ ወጀል ዘንድ ከስሞቻችሁ ሁሉ ተወዳጁ ዐብዱላህ እና ዐብዱርረሕማን ነው፡፡” [ሙስሊም]
2. በመቀጠልም ለአላህ ባርያ መሆንን የሚገልፁ ስሞች ተወዳጅ እንደሆኑ ዑለማዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለምሳሌ ‘ዐብዱልመሊክ’፣ ‘ዐብዱልዐዚዝ’፣… በማለት ለአላህ ባርነትን በሚገልፁ ስሞች መጥራት፡፡ ባይሆን ያስጠጋነው በተጨባጭ ወደ አላህ መልካም ስሞች መሆኑን እርግጠኛ ልንሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም ያለ ተጨባጭ ማስረጃ የትኛውንም ስም “የአላህ ስም ነው” ማለት አይፈቀድምና፡፡ ከዚህም በመነሳት አንዳንዶች “ዐብዱ ምናምን” ብለው ነገር ግን ትርጉም ወደሌለው ነገር ወይም የአላህ ስም ለመሆኑ ግልፅ ማስረጃ ወዳልመጣበት ስያሜ የሚያስጠጉ አሉ፡፡ ይሄ ችግር በሀገራችንም ይስተዋላል፡፡ “ዐብዱልካፍ” የሚለውን እንደምሳሌ ውሰዱ፡፡
3. በመቀጠል በታላላቅ የአላህ ነብያት ስሞች መሰየም ተመራጭ ነው፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ዛሬ ሌሊት ልጅ ተወለደልኝ፡፡ በአባቴ ስምም ‘ኢብራሂም’ ብየ ሰየምኩት” ብለዋል፡፡ [ሙስሊም] “ዩሱፍ” ብለው የሰየሙበትም አለ፡፡ [ሶሒሑልአደቢልሙፍረድ፡ 642] “በስሜ ተሰየሙ” ማለታቸውም የሚታወቅ ነው፡፡ [ቡኻሪና ሙስሊም] ቁርኣን ውስጥ የብዙ ነብያት ስሞች እንዳሉ ይታወስ፡፡
4. ከዚያም በደጋጎችና በሙስሊም ዑለማዎች ስሞች መሰየም ይወደዳል፡፡ “እነሱ (ጥንታውያኑ የሁዶች) በነብዮቻቸውና ከነሱ በፊት በነበሩ ደጋጎች ስም ይሰይሙ ነበር” ብለዋል ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ [ሙስሊም] በዚህ ረገድ የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦችና የመልካም ቀደምቶቻችን ስሞች ጥሩ መነሻ ይሆናሉ፡፡ ከልጆችም ልቦና ውስጥ የነዚህን ደጋጎች ታሪክ ለማወቅ፣ አልፎም ፈለጋቸውን ለመከተል መነሳሳትን ከውስጣቸው ይጭራል፡፡
5. ከዚያም ስርኣቱን በጠበቀ መልኩ እውነተኛ እና በተጨባጭ ገላጭ የሆነ ስም ይከተላል፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ከስም ሁሉ እውነተኛው (ተሰያሚውን የሚገልፀው) ‘ሀማም’ እና ‘ሓሪሥ’ ነው” ብለዋል፡፡ [አስሶሒሐህ፡ 1040] “ሀማም” ማለት “ሀሳብ የሚያበዛ” ማለት ሲሆን “ሓሪሥ” ማለት ደግሞ “አራሽ”፣ “ገበሬ” ማለት ነው፡፡ እነዚህ ስሞች ብዙሃኑን ህዝብ በተጨባጭ ይገልፁታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ተጨባጭ መልእክት ያላቸው ስሞችን መጠቀም ይቻላል ማለት ነው፡፡
ስሞቻችን በተቻለ ዐረብኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህን ስል ትንሽ ትልቁን በዘር መነፅር የሚመለከቱ አጉል ፀጉር ሰንጣቂዎችን አስተያየት ከቁብም መቁጠር አያስፈልግም፡፡ እነ እስክንድር፣ እነ ዳንኤል፣ እነ ሄለን፣ እነ ዮሴፍ፣ ዮሐንስ፣ ራሄል፣ ወዘተ ኢትዮጵያዊ መነሻ ያላቸው ስሞች አይደሉም፡፡ በቁም የሚያንቀላፋ ፉዞ ሳያስተውል ቢያስተጋባም አንዳንዶች ዘንድ ዐረብኛ ስሞችን መቃወም አላማው ሌላ ነው፡፡ መቼስ ዐረብኛ ቋንቋ ከእምነታችን ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር ወዳጅ ቀርቶ ጠላት አይዘነጋውም፡፡ ስለዚህ አደፍርስ፣ ተምትሜ፣ አልጋነሽ፣ ጃኖ፣ ፈጌሳ፣ አምዴግባ፣ ቶሎሳ፣ ጫልቱ፣ ኢናሂና፣ ጉደሌ፣ ሸርሞሎ፣ ቢፍቱ፣ … እያልን ልጆቻችንን አንሰይም፡፡ አላህ ያውቃል! ይህን የምለው ለየትኛውም ቋንቋ ጥላቻን አንግቤ አይደለም፡፡ ወሰላም፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ህዳር 2/2008)

Post a Comment

0 Comments