Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሃምሳ እና መቶ የት ተገናኝቶ!! አሜሪካ ህዝቦቿን ከአስካሪ መጠጥ ለመገላገል ያደረገችው ዘመቻ ከውጥን እስከ ክሽፈት


“ሃምሳ እና መቶ የት ተገናኝቶ!!”
አሜሪካ ህዝቦቿን ከአስካሪ መጠጥ ለመገላገል ያደረገችው ዘመቻ ከውጥን እስከ ክሽፈት ከ 350 አመታት በላይ የረዘመ ጊዜ ፈጅቶባታል፡፡ ትግሉ ይበልጥ ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ “ደረቁ የመስቀል ጦርነት” ብለው “ቅዱስ” ስምእስከመስጠት የደረሰቡት ጊዜ ነበራቸው፡፡ ሴቶችም በሰካራም ባሎቻቸው የሚደርስባቸውን እንግልት ለማስቀረት በሚል ዘመቻውን የሚደግፍ የክርስቲያን ሴቶች ማህበር አቋቁመው ነበር፡፡ ከዘመናት መታሸትና ማንከባለል በኋላ በ 1919 የአሜሪካን ኮንግረስ አልኮል የሚከለክለውን 18ኛውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ አፀደቀ፡፡ ህጉ የአልኮል መጠጦችን ከማምረት፣ ከማጓጓዝ እና ከመሸጥ የሚከለክል ነበር፡፡ የነበርን ወንዝ ሳይሻገር ቀረ እንጂ፡፡ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዝ ዘንድ እጅግ የተጋነነ የማስታወቂያ ዘመቻ በሀገረ አሜሪካ ተከፈተ፡፡ አስካሪ መጠጥን ለመዋጋት እና ጉዳቱን ገሃድ ለማውጣት ያግዛሉ የተባሉ ዘመኑ ያፈራቸው የመገናኛ ብዙሃኖች እና የማስታወቂያ መንገዶች ሁሉ ተግባር ላይ ዋሉ፡፡ ጋዜጣው፣ መፅሄቱ፣ መፃህፍቱ፣ በራሪ ወረቀቱ፣ ምስሎች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ጉባኤዎች፣ ሌክቸሮች፣ … ምን አለፋችሁ እጃቸው ላይ ያለውን የማስተማሪያ ቁሳቁስ እና የማስተማሪያ ዘዴዎች ሁሉ ተጠቀሙ፡፡ አጥኚዎች አሜሪካ ለዚህ ዘመቻ ለማስታወቂያ ብቻ ያወጣችውን ከ65 ሚሊዮን ዶላር እንደሚልቅ አስፍረዋል፡፡ ለዚህ አገልግሎት በተግባር ላይ የዋሉት መፃህፍትና ወረቀቶች ጠቅላላ የገፅ ብዛት ከ 10 ቢሊዮን እንደሚልቅ ተገልፁዋል!!! ከዚያም እንዲህ አይነት ሰፊ የቅስቀሳ እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ከተሰራ በኋላ ህጉ በ 1920 በተግባር ላይ መዋል ጀመረ፡፡ ግዙፍ የሆኑ መንግስታዊ መዋቅር እና ተቋማት ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ፡፡
1. የአልኮል መጠጦችን ዝውውር በባህር ዳርቻዎች በኩል ለመቆጣጠር የሀገሪቱ ግዙፍ የባህር ኃይል ተሰማራ፡፡
2. የአልኮል መጠጦችን ዝውውር በድንበሮች በኩል ለመቆጣጠር የአየር ኋይሉና ሰራዊቱ ተሰማራ፡፡
3. የአልኮል መጠጦችን ከያሉበት ለማደን እና ለማውደም የሀገሪቱ ፖሊስ ኃይል ተሰማራ፡፡
4. የአልኮል ክልከላውን ተግባራዊነት የሚሰሩ ሃገር አቀፍ ተቋማት ተቋቋሙ፡፡
5. ዘመቻውን በርካታ የተለያዩ የክርስትና ቡድኖች ደግፈውት ነበር፡፡
ከ 1920 እስከ 1933 ድረስ ለ 13 ዓመታት አሜሪካ የአልኮል መጠጥን ለማጥፋት ባደረገቸው ጥረት ከ 100 ሚሊዮን ዶላር የማያንስ ገንዘብ አፈስሳለች፡፡ ልብ ይበሉ ከ80 አመታት በፊት መቶ ሚሊዮን ዶላር ዛሬ ተመሳሳይ ገንዘብ ከሚሰራው እጅግ የላቀ ብዙ ስራ ይሰራል፡፡ በነዚህ 13 አመታት 300 ሰዎች ከአልኮል ህጉ ጋር በተያያዘ ተገድለዋል፣ የሞት ፍርድ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ወደ ወህኒ ተወርውሯል፡፡ አራት ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ከህጉ ጋር ከሚያያዙ ቅጣቶች ተሰብስቧል፡፡ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ንብረቶች ተወርሰዋል፡፡
ይሄ ሁሉ ልፋት፣ ይሄ ሁሉ ጥረት፣ ይሄ ሁሉ የፈሰሰ ገንዘብ ግን አንዳች ቁም ነገር ጠብ ሳያደረግ በከንቱ ቀርቷል፡፡ አሜሪካውያን ፀረ አልኮል ህጉን ሊቀበሉ ቀርቶ መንግስታቸውን እስከማንገዳገድ ደረሱ፡፡ እንዳውም በ 1932 የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እጩው ፍራንክሊን ሩዝቬልት ከተመረጠ የክልከላ ህጉን እንደሚያነሳ ቃል በመግባት ጉዳዩን ለምርጫ ፍጆታ ተጠቀመበት፡፡ ማሸነፉን ተከትሎም በ 1933 ሃያ አንደኛውን የህገ መንግስት ማሻሻያ በማድረግ የጠጪዎችን ጫና መቋቋም ያቃተው መንግስት ፀረ አልኮል መጠጥ ህጉን አነሳ፡፡ ያ ሁሉ ድካም መና ቀረ፡፡ ይህ የታሪክ ዘመን በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ “የክልከላው ዘመን” /Prohibition Era/ በመባል ይታወቃል፡፡ ዘመኑ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስቀያሚው የታሪክ ዘመን እንደሆነ ይታሰባል፡፡ የአሜሪካው የፊልም ኢንደስትሪ ሆሊውድ በዘመኑ የነበረውን መከራ እና ውጣ ውረድ በከፊል ያሳያል በሚል (Lawless) የሚል ፊልም በ 2012 አውጥቷል፡፡
.
.
ሌላ ታሪክ!!
ከ 1430 ምናምን አመታት በፊት ገና ከተመሰረተ የአንድ እጅ ጣቶችን ያክል እድሜ ባላስቆጠረው ኢስላማዊ ሃገር መናገሻ ከተማ መዲና ውስጥ በነብዩ ሙሐመድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ በአስካሪ መጠጥ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ እንዲህ የሚነበቡ ጥቂት አንቀፆች በየተራ ወረዱ፡፡
1. (ስለ አስካሪ መጠጥ እና ስለ ቁማር ይጠይቁሃል፡፡ “በሁለቱም ውስጥ ታላቅ ኃጢአት እንዲሁም ጥቅሞችም አሉባቸው፡፡ ግን ኃጢአታቸው ከጥቅማቸው የበለጠ ነው” በላቸው፡፡) [አልበቀራህ፡ 219]
የመጀመሪያ እርምጃ!! ከጥቅሙ ጉዳቱ ካመዘነ ታዲያ ለምን …? የተጠቃሚዎችን አእምሮ ለቀጣይ እርምጃ የሚያዘጋጅ ደወል ነው፡፡ አስካሪ መጠጥን ጉሮሮውን የሚያንቅ ሌላ እንዲህ የሚል አዋጅ ተከተለ፡፡
2. (እናተ ያመናችሁ ሆይ! እናንተ የሰከራችሁ ሆናችሁ ሳለ ሶላትን አትቅረቡ፡፡ (ስካሩ ለቋችሁ) የምትሉትን እስከምታውቁ ድረስ፡፡) [አንኒሳእ፡ 43]
አስተውሉ! በቀን አምስት የግዴታ ሶላቶች አሉ፡፡ ማለዳ ላይ፣ ቀትር ላይ፣ 10 ሰዐት አካባቢ፣ ፀሀይ ስትጠልቅ እና ማታ ላይ የሚሰገዱ፡፡ እነዚህን ሶላቶች ወቅታቸውን ጠብቆ መስገድ ከእያንዳንዱ አማኝ የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ አስካሪ መጠጥ ያለገደብ የሚጠጣበት ወቅት በእጅጉ ተገደበ ማለት ነው፡፡ አሁን አእምሮ ለቀጣይ እርምጃ ይበልጥ ተመቻችቷል፣ ይበልጥ ተዘጋጅቷል፡፡ ስለሆነም ሌላ አዋጅ ተከተለ፡፡
3. (እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ፣ ቁማርም፣ ጣኦታትም፣ የጥንቆላ ቀስቶችም ከሰይጣን ስራ የሆኑ እርኩስ ናቸው፡፡ (እርኩስ ነገርንም) ራቁት፣ ልትድኑ ይከጀላልና፡፡ ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል፤ አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ነው፡፡ እናስ እናንተ (ከነዚህ እርኩስ ነገሮች) የምትታቀቡ ናችሁን?) [አልማኢዳህ፡ 90-91]
የመጨረሻና የማያዳግም እርምጃ!!! (የምትታቀቡ ናችሁን?) ሲባሉ ያለምንም ማንገራገር “አቁመናል አቁመናል” ነበር መልሳቸው፡፡ [ሶሒሕ አትቱርሚዚ፡ 3255]
ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መለኮታዊውን የክልከላ አዋጅ ለህዝብ የሚያሰማ ሰው አዘዙ፡፡ “አዋጅ! አስካሪ መጠጥ በርግጥ ሐራም (ክልክል) ተደረገ” ሲል አስተጋባ፡፡ በቃ! ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይል፣ የምድር ኃይል፣ ፖሊስ፣… አልተሰማራም፡፡ የማስታወቂያ ጋጋታም አልነበረም፡፡ ማህበራት አልተቋቋሙም፡፡ ብጥብጥ፣ ትርምስ፣ ማህበራዊ ቀውስ፣ የሚባል ነገር አልተከተለም፡፡ ይልቁንም በአንድ አዋጅ የመዲና መንገዶች በአስካሪ መጠጦች ተጥለቀለቁ፡፡ ሰው በየቤቱ ያለውን እንስራ፣ ማሰሮ ይዞ እየወጣ ደፋ!! እቃዎቹንም ጭምር እየሰበረ ጣለ!!! አለቀ! ደቀቀ!! ልብ በሉ! የአሜሪካ ሃብታሞች ግን የክልከላ ህጉ ተግባራዊ ሊሆን ቀኑ ሲቆረጥ በየማከፋፈያውና ችርቻሮ ሱቁ የሚገኙ አስካሪ መጠጦችን በገፍ ገዝተው ለ “ጥና ቀን” ከቤታቸው በማከማቸት ገበያውን ባዶ አድርገውታል፡፡ ምን ይሄ ብቻ? በጊዜው የአሜሪካ ፕሬዚደንት የነበረው ውድሮው ዊልሰን የስልጣን ጊዜውን ሲያጠናቅቅ የአልኮል መጠጦቹን ከነጩ ቤተ መንግስት ወደ መኖሪያ ቤቱ አጓጓዘ፡፡ ዋረን ጂ. ሃርዲን በቦታው ሲተካ ደግሞ የግሉን ግዙፍ የአልኮል ክምችቱን ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ቤተ-መንግስት አዘዋወረ፡፡ እንዳውም ጆርጅ ካሲዳይ በ 1930 በዋሺንግተን ፖስት ላይ እንዳወጣው 80 ፐርሰንቱ አካባቢ የኮንግረሱ እና የሰኔት አባላት ጠጪዎች ነበሩ፡፡ ልዩነቱ ግልፅ ነው አይደል? The difference is visible!!! ለነገሩ የእውነታውን ርቀት ያላስተዋለ እንዲያስተውል እንጂ ቀድሞ ነገር የሚነፃፀሩ ነገሮች አይደሉም፡፡ እውነታውን የሚያውቅ ዘንድ እንዳውም ንፅፅሩን ኢስላምን ዝቅ የሚያደርግ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ አንድ ሰው “ከጉንዳን እና ከዝሆን የየትኛው እግር ይበልጣል?” ብሎ ቢጠይቅ ጥያቄው ዝሆንን እንደመናቅ ዝቅ ካለም አለማወቅ ተደርጎ ነው የሚሳለው፡፡ ለዚህም ነው አንዱ የዐረብ ገጣሚ እንዲህ ያለው
“አታይም እንዴ የሰይፍ ክብሩ እንደሚቀንስ?
‘ሰይፍ ከብትር የሰላ ነው’ ተብሎ ሲወደስ”
አዎ ሰይፍ ስለታም እንደሆነ ብትር ግን ስለት እንደሌለው ለማንም አይዘነጋም፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ “ሰይፍ ከዱላ ስል ነው” ማለት “ግመል ከትንኝ ይበልጣል” አይነት ለዛ የሌለው ወሬ ማውራት ነው፡፡ ልክ እንዲሁ “ኢስላም ከየትኛውም ምድራዊ ስርኣት የተሻለ ነው” ቢባል እውነት ከመሆኑም ጋር ኢስላምን በሚገባ ለሚያውቅ አካል ንፅፅሩ ምቾት አይሰጥም፡፡ “ወትሮስ መለኮታዊ ህግ ከሰው ሰራሽ ህግ ጋር ሊነፃፀር ነውን?” ቢል አይፈረድበትም፡፡ ለማያውቁት ግን ይህ ነው ኢስላማችን! ይህ ነው እምነታችን!!
ዛሬ ሙስሊሙ ከ 1.5 ቢሊዮን በላይ ነው፡፡ ዛሬ ከረጅሙ የኢስላም ታሪክ ውስጥ ብዙሃኑ ሙስሊም እጅግ አስፈሪና አሳዛኝ በሆነ መልኩ ወርዶ ወርዶ፣ የብርታቱ ምንጭ የሆነውን ዐቂዳውን አርዶ በታሪኩ የመጨረሻው አዘቅት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ በቢሊዮን ከሚቆጠር ሙስሊም ህዝብ ውስጥ እጅግ ጥቂት ካልሆነ በስተቀር በሸሪዐህ ህግ ጥላ ስር አይገኝም፡፡ ይህም ሆኖ ግን እኛ እንደ ውርደት እንደ ብክለት የምንቆጥረው ከሙስሊሙ መሀል የሚገኘው የአስካሪ መጠጥ ፍጆታ በከሃዲው አለም ዘንድ ካለው ጋር ሲነፃፀር ኢምንት መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬም ተአምሩ አለ፡፡ አልሐምዱ ሊላህ ዐላ ኒዕመቲል ኢስላም!! ሙስሊሞች ያደረግከን ጌታ ጥልቅ የሆነ ምስጋና ይድረስህ፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 18/2008)

ፅሁፉን ለመፃፍ ያነሳሳኝ በአንድ ቱኒዚያዊ ወንድም የተፃፈ ዐረብኛ ፅሁፍ ነው፡፡

Post a Comment

0 Comments