Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሁድ ሁድ፡ ተአምረኛው ወፍ!!


ሁድ ሁድ፡ ተአምረኛው ወፍ!!

ነብዩ ሱለይማን ኢብኑ ዳውድ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እጅግ አስደናቂ በሆነ መልኩ አላህ ሁሉን ነገር የገራላቸው ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ከቁርኣን ጥቂት ቀንጨብ እናድርግማ፡-
وَلَقَدْ آتَيْنَا دَاوُودَ وَسُلَيْمَانَ عِلْمًا ۖ وَقَالَا الْحَمْدُ لِلَّهِ الَّذِي فَضَّلَنَا عَلَىٰ كَثِيرٍ مِنْ عِبَادِهِ الْمُؤْمِنِينَ
ለዳውድና ለሱለይማንም እውቀትን በእርግጥ ሰጠናቸው፡፡ አሉም፡- “ምስጋና ለአላህ ይገባው፡፡ ለዚያ ከምእምናን ባሮቹ በብዙዎቹ ላይ ላበለጠን፡፡”
وَوَرِثَ سُلَيْمَانُ دَاوُودَ ۖ وَقَالَ يَا أَيُّهَا النَّاسُ عُلِّمْنَا مَنْطِقَ الطَّيْرِ وَأُوتِينَا مِنْ كُلِّ شَيْءٍ ۖ إِنَّ هَٰذَا لَهُوَ الْفَضْلُ الْمُبِينُ
ሱለይማንም ዳውድን ወረሰ፡፡ አለም “ሰዎች ሆይ! የወፍን ቋንቋን ተስተማርን፡፡ ከነገሩ ሁሉም ተሰጠን፡፡ ይህ እርሱ በእርግጥ ግልጽ የሆነ ችሮታ ነው!!”
وَحُشِرَ لِسُلَيْمَانَ جُنُودُهُ مِنَ الْجِنِّ وَالْإِنْسِ وَالطَّيْرِ فَهُمْ يُوزَعُونَ
ለሱለይማንም ሰራዊቶቹ ከጂን፣ ከሰውም፣ ከወፍም የሆኑት ተሰበሰቡ፡፡ እነሱም በስርኣት ይደራጃሉ፡፡
حَتَّىٰ إِذَا أَتَوْا عَلَىٰ وَادِ النَّمْلِ قَالَتْ نَمْلَةٌ يَا أَيُّهَا النَّمْلُ ادْخُلُوا مَسَاكِنَكُمْ لَا يَحْطِمَنَّكُمْ سُلَيْمَانُ وَجُنُودُهُ وَهُمْ لَا يَشْعُرُونَ
በጉንዳንም ሸለቆ በመጡ ጊዜ አንዲት ጉንዳን “እናንተ ጉንዳኖች ሆይ! ወደ መኖሪያዎቻችሁ ግቡ፡፡ ሱለይማንና ሰራዊቱ እነርሱ የማያውቁ ሲሆኑ እንዳይሰባብሩዋችሁ” አለች፡፡
فَتَبَسَّمَ ضَاحِكًا مِنْ قَوْلِهَا وَقَالَ رَبِّ أَوْزِعْنِي أَنْ أَشْكُرَ نِعْمَتَكَ الَّتِي أَنْعَمْتَ عَلَيَّ وَعَلَىٰ وَالِدَيَّ وَأَنْ أَعْمَلَ صَالِحًا تَرْضَاهُ وَأَدْخِلْنِي بِرَحْمَتِكَ فِي عِبَادِكَ الصَّالِحِينَ
(ሱለይማን) ከንግግርዋም እየሳቀ ፈገግ አለ፡፡ “ጌታዬ ሆይ! ያቺን በእኔና በወላጆቼ ላይ የለገስካትን ጸጋህን እንዳመሰግን፣ የምትወደውንም በጎ ሥራ እንድሰራ ምራኝ፡፡ በችሮታህም በመልካሞቹ ባሮችህ ውስጥ አግባኝ” አለ፡፡
وَتَفَقَّدَ الطَّيْرَ فَقَالَ مَا لِيَ لَا أَرَى الْهُدْهُدَ أَمْ كَانَ مِنَ الْغَائِبِينَ
ወፎቹንም ተመለከተ፤ አለም፡ “ምነው ሁድሁድን አላየውም?! ወይስ (በቦታው) ከሌሉት ሆኗልን?”
لَأُعَذِّبَنَّهُ عَذَابًا شَدِيدًا أَوْ لَأَذْبَحَنَّهُ أَوْ لَيَأْتِيَنِّي بِسُلْطَانٍ مُبِينٍ
“በእርግጥ ብርቱ ቅጣትን እቀጣዋለሁ፡፡ ወይም በእርግጥ አርደዋለሁ!! ወይም (ለመጥፋቱ አሳማኝ የሆነ) ግልፅ የሆነን ማስረጃ ያመጣልኛል” (አለ፡፡)
فَمَكَثَ غَيْرَ بَعِيدٍ فَقَالَ أَحَطْتُ بِمَا لَمْ تُحِطْ بِهِ وَجِئْتُكَ مِنْ سَبَإٍ بِنَبَإٍ يَقِينٍ
(ሁድሁድ ግን) እሩቅ ያልሆነንም ጊዜ ቆዬ፡፡ አለም “ያላወቅከውን ነገር አወቅኩ፡፡ ከሰበእም እርግጠኛን ወሬ አመጣሁልህ፡፡”
إِنِّي وَجَدْتُ امْرَأَةً تَمْلِكُهُمْ وَأُوتِيَتْ مِنْ كُلِّ شَيْءٍ وَلَهَا عَرْشٌ عَظِيمٌ
“እኔ የምትገዛቸው (ሰዎች ያሏት) የሆነችን፣ ከነገሩም ሁሉ የተሰጠችን ሴት አገኘሁ፡፡ ለእርሷም ታላቅ ዙፋን አልላት፡፡
وَجَدْتُهَا وَقَوْمَهَا يَسْجُدُونَ لِلشَّمْسِ مِنْ دُونِ اللَّهِ وَزَيَّنَ لَهُمُ الشَّيْطَانُ أَعْمَالَهُمْ فَصَدَّهُمْ عَنِ السَّبِيلِ فَهُمْ لَا يَهْتَدُونَ
“እርሷንም ሕዝቦችዋንም ከአላህ ሌላ ለፀሐይ ሲሰግዱ አገኘኋቸው፡፡ ሰይጣንም ለእነሱ (መጥፎ) ስራዎቻቸውን ሸልሞላቸዋል፡፡ ከእውነተኛውም መንገድ አግዷቸዋል፡፡ ስለዚህ እነሱ (ወደ እውነት) አይምመሩም፡፡”
أَلَّا يَسْجُدُوا لِلَّهِ الَّذِي يُخْرِجُ الْخَبْءَ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَيَعْلَمُ مَا تُخْفُونَ وَمَا تُعْلِنُونَ
“ለዚያ በሰማያትና በምድር የተደበቀውን ለሚያወጣው፣ የምትሸሽጉትንና የምትገልፁትንም ሁሉ ለሚያውቀው አላህ እንዳይሰግዱ (ሰይጣን አግዷቸዋል)፡፡”
اللَّهُ لَا إِلَٰهَ إِلَّا هُوَ رَبُّ الْعَرْشِ الْعَظِيمِ ۩
“አላህ ከርሱ ሌላ (የእውነት) አምላክ የለም፡፡ የታላቁ ዐርሽ (ዙፋን) ጌታ ነው፡፡”
قَالَ سَنَنْظُرُ أَصَدَقْتَ أَمْ كُنْتَ مِنَ الْكَاذِبِينَ
(ሱለይማንም) አለ፡- “እውነት እንደ ተናገርክ ወይም ከውሸታሞቹ እንደ ሆንክ ወደፊት እናያለን፡፡”
اذْهَبْ بِكِتَابِي هَٰذَا فَأَلْقِهْ إِلَيْهِمْ ثُمَّ تَوَلَّ عَنْهُمْ فَانْظُرْ مَاذَا يَرْجِعُونَ
“ይህንን ደብዳቤዬን ይዘህ ሂድ፡፡ ወደ እነርሱም ጣለው፡፡ ከዚያም ከእነሱ ዘወር በል፡፡ ምን አንደሚመልሱም ተመልከት፡፡”
ሁድሁድ የታዘዘውን ፈፀመ፡፡ ደብዳቤውንም ከሱለይማን ወስዶ የመን ደርሶ የሰበእ (ሳባ) ንግስት ከምትገኝበት ስፍራ ጣለው፡፡ ተልእኮው ግቡን መቷል፡፡ ደብዳቤው ከንግስቲቷ እጅ ገባ፡፡ ይህኔም፡
قَالَتْ يَا أَيُّهَا الْمَلَأُ إِنِّي أُلْقِيَ إِلَيَّ كِتَابٌ كَرِيمٌ
አለች፡ “እናንተ መማክርቶች ሆይ! እኔ የተከበረ ደብዳቤ ወደኔ ተጣለ፡፡”
إِنَّهُ مِنْ سُلَيْمَانَ وَإِنَّهُ بِسْمِ اللَّهِ الرَّحْمَٰنِ الرَّحِيمِ
“እነሆ እርሱ ከሱለይማን ነው፡፡ እርሱም በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው (የሚል መክፈቻ አለው፡፡)
أَلَّا تَعْلُوا عَلَيَّ وَأْتُونِي مُسْلِمِينَ
“በእኔ ላይ አትኩሩ፡፡ ታዛዦችም ሆናችሁ ወደኔ ኑ (የሚል ነው)፡፡ [አንነምል፡ 15- 31]
…………………………
ይህን ልብ አንጠልጣይ ታሪክ መጨረስ የፈለገ ጥሩ የሆነ ተፍሲር ይዞ እስከመጨረሻው መከታተል ይችላል፡፡ እኔ ግን አንድ ጥያቄ ጠይቄ ፅሁፌን ልቋጭ፡፡ ሁድሁድ፡ ንግስተ-ሳባ የታደለችውን ሀብትና ድሎት ከገለፀ በኋላ ፀሀይ አምላኪ የሆኑትን ንግስቲቷን እና ህዝቦቿን ከእውነተኛው የተውሒድ መስመር ያፈነገጡ እንደሆኑ በሚደንቅ ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልፁዋቸዋል፡- “እርሷንም ሕዝቦቿንም ከአላህ ሌላ ለፀሐይ ሲሰግዱ አገኘኋቸው፡፡ ሰይጣንም ለእነሱ (መጥፎ) ስራዎቻቸውን ሸልሞላቸዋል፡፡ ከእውነተኛውም መንገድ አግዷቸዋል፡፡ ስለዚህ እነሱ (ወደ እውነት) አይምመሩም!!”
አላሁ አክበር!! ዛሬም ልክ እንዲሁ ሸይጧን ጥፋታቸውን አስውቦላቸው በአላህ ላይ ማጋራታቸውን እንደ ተውሒድ፣ እንደ ፅድቅ የሚቆጥሩት ስንትና ስንት ናቸው?! ህሊና ያላችሁ አስተውሉ!! ሁድሁድ ቀጠለ፣ የሰዎቹ ምግባር ማስተዋሉን ላልተነፈገ ከህሊና ጋር የሚጋጭ እንደሆነ እንዲህ ገለፀው፡- “ለዚያ በሰማያትና በምድር የተደበቀውን ለሚያወጣው፣ የምትሸሽጉትንና የምትገልፁትንም ሁሉ ለሚያውቀው አላህ እንዳይሰግዱ (ሰይጣን አግዷቸዋል)” አለ፡፡ ዛሬ ግን የተደበቀውን ስውሩን ሁሉ ከዘመናት በፊት የሞቱ ሰዎች ያውቃሉ በሚል በጥፋት ላይ የሚዋልሉት ስንቶች ናቸው?! ከዚያም እንዲህ ሲል ንግግሩን በተውሒድ አሳረገው፡ “አላህ ከርሱ ሌላ (የእውነት) አምላክ የለም፡፡ የታላቁ ዐርሽ ጌታ ነው፡፡” ሱብሓነላህ!!
ጥያቄ፡- በዚህ አስደናቂ ታሪክ ላይ የተወሳው ወፍ ማለትም ሁድሁድ (hoopoe) በአካባቢያችሁ ስሙ ምን ይባላል? ምናልባት በምስሉ የሚያውቀው ካለ ምስሉን ከስር ለጥፌዋለሁ፡፡ (ምስል መጠቀም ከሚፈቀድባቸው ቦታዎች አንዱ ለማስተማር እንደሆነ ዑለማዎች ይጠቅሳሉ፡፡) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ከሚገኘው ናቹራል ቤተመዘክር (ስሙን የዘነጋሁት መሰለኝ የምታውቁት አርሙኝ) የዛሬን ስድስት አመት አካባቢ ገብቼ ነበር፡፡ ሁድሁድን ገድለው አድርቀው አስቀምጠውት አይቼ ስሙን ጠይቄ ነበር፡፡ ሀላፊው ሁለት ስሞችን የነገረኝ ቢሆንም አንዱን ረስቼዋለሁ፡፡ የማስታውሰውን ስም በኮሜንት ስር አሰፍረዋለሁ፡፡ እስኪ ሁድሁድ በአካባቢያችሁ ምን እንደሚባል በኮሜንት ግለፁት፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ ጥቅምት 11/2008)

Post a Comment

0 Comments