Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እህቴ ሆይ የምር የኢማን ጥፍጥና ከልብሽ ሰርፇልን



🌺 ተንቢሃት የዋትሳፕ ግሩፕ

እህቴ ሆይ የምር የኢማን ጥፍጥና
ከልብሽ ሰርፇልን ??

ለዚህስ የአምላካችን ማስጠንቀቂያ ራስሽን አስገዝተሻልን ?
" ﻭَﻣَﺎ ﻛَﺎﻥَ ﻟِﻤُﺆْﻣِﻦٍ ﻭَﻟَﺎ ﻣُﺆْﻣِﻨَﺔٍ ﺇِﺫَﺍ ﻗَﻀَﻰ ﺍﻟﻠَّﻪُ
ﻭَﺭَﺳُﻮﻟُﻪُ ﺃَﻣْﺮًﺍ ﺃَﻥ ﻳَﻜُﻮﻥَ ﻟَﻬُﻢُ ﺍﻟْﺨِﻴَﺮَﺓُ ﻣِﻦْ ﺃَﻣْﺮِﻫِﻢْ
ﻭَﻣَﻦ ﻳَﻌْﺺِ ﺍﻟﻠَّﻪَ ﻭَﺭَﺳُﻮﻟَﻪُ ﻓَﻘَﺪْ ﺿَﻞَّ ﺿَﻠَﺎﻟًﺎ ﻣُّﺒِﻴﻨًﺎ "
‹‹ አላህ እና መልእክተኛው አንድን ነገር በፈረዱ ጊዜ (በአንድ ጉዳይ ላይ ውሳኔን ካስተላለፉ) ለምእምናን እና ለምእምናት በጉዳያቸው ላይ ለእነርሱ ሌላ ምርጫ ሊኖራቸውአይገባም። !

የአላህንና የመልእክተኛውንም ትዕዛዝ የጣሰ ሰው ግልፅ የሆነን መሳሳትበእርግጥ ተሳሳተ።››ይላልና

እህቴ ሆይ እስኪ የእነዚያን ምርጥ ትውልዶች ታሪክ የኋሊት ተጉዘን እንቃኛቸው።

አንድን አስገራሚ ክስተትም እነግርሻለሁና ተከታተዪኝ።

ጉዳዩ እንዲህ ነው ☞
መዲነቱል ሙነወራህ ከነበሩት አንሷሮች መካከል የመጨረሻው ድሃ የነበረ፣ በመልኩም መልካም ያልነበረ፣ ቤተሰብም ማደርያ ቤትም ያልነበረው እናበሰዎች ዘንድም ቦታ የማይሰጠው የተገለለና ሴቶችም ለጋብቻ የማይሹት ሰው ነበር።

ከዚህም ጋር ግን በአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ዘንድ ተወዳጅና ቦታ ያለው ሰው ነው፡፡ስሙም ጁለይቢብ ይባላል (ረዲየላሁ አንሁ)

አቡ በርዛህ አል-አስለሚ ረዲየላሁ አንሁ ስለሱ እንዲህ ብለው ነበር:-

« ጁለይቢብ ማለት
(ረድየላሁ አንሁ) ሴቶች ዘንድ የሚገባና ከነሱም ጋር የሚያወራ ነበርና እኔምለባለቤቴ እንዲህ አልኳት "ጁለይቢብ እናንተ ያላችሁበት እንዳይገባ። ! እናንተዘንድ ከገባ ግን እንዲህ እንዲህ አደርገዋለሁ ።" አልኳት ፡፡ ይላሉ

ጁለይቢብ ጎልቶ የታወቀበትን ታሪክ ስናወሳም☞
በዘመኑ አንሷሮች አንዲት ሴት ባሏ የሞተባት እንደሆን ሊያገባት የጠየቃቸው ሰው ካለ የመልእክተኛውን ፍላጎት ሳያውቁ አይድሩም ነበር።

የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ከአንሷሮች መካከል አንዱን ሰው "ልጅህን ዳረኝ" ሲሉት ፤ 'የአላህ መልእክተኛ ሆይ (ለኛ ክብር ነው። እሷን ድረንልህም አክብሮታችንን እንገልፅልሃለን) አላቸው '

ከዚያም መልእክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) "እኔኮ ለራሴ ፈልጌያት አይደለም"። ሲሉት… 'የአላህ መልእክተኛ ሆይ ለማን ነው ታዲያ' ? አላቸው
እሳቸውም "ለጁለይቢብ ነው"። ኣሉት… እሱም 'የአላህ መልእክተኛ ሆይ እንግዲያውስ እናቷን ላማክራት' ኣላቸው።

ከዚያም ወደ እናቷ መጥቶ 'የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ልጅሽን ስጡኝ ይሉናል' ኣላት። እሷም “ነዐም'መ ወኑዕመቱ ዐይኒ” ኣለች (ለኛ ክብር ነው። እሷን ድረንለትም አክብሮታችንን እንገልፃለን) እንደማለት ነው።

'ለራሳቸው አይደለም እኮ፤ ለጁለይቢብ ሊድሯት ነው' ሲላት… 'ጁለይቢብን… እንዴት ተደርጎ ?
ጁለይቢብን… እንዴት ተደርጎ ?
ጁለይቢብን… እንዴት ተደርጎ ?
አይሆንም ! በአላህ ይሁንብን አንድርለትም'። ኣለችው።

በዚህን ግዜ ባለቤቱ ያለችውን ለአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሄዶ ሊነግር ሲነሳ ልጅቱ "ማነው እሱ ሊያገባኝ የጠየቃችሁ? " ስትል ጠየቀቻቸው።

እናቷም ነገረቻት። ከዚያም ልጅቱ "የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ያላችሁን ነገር ትመልሱበታላችሁ ?! ለመልእክተኛው (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ተዉኝ፤ እሱ በሚጎዳኝ ነገር ላይ አይጥለኝምና።" ኣለቻቸው።

አባቷም ወደ አላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሄደና"ያሻህን አድርጋት" አላቸው። እሳቸውም ለጁለይቢብ ዳሯት።

ትረካውን የሚያወጉን አክለው ስለ ቀጣዩ የጁለይቢብ ህይወት እንዲህ ይላሉ ☞

የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) በሆነ ወቅት ለዘመቻ ወጡ። በዘመቻው ድልን ተጎናፅፈው እንዳበቃም ለሶሃቦቹ "ከመሃላችሁ ያጣችሁት ሰው ኣለን ?" ሲሏቸው … 'አገሌን አጥተናል፣ እገሌን አጥተናል'። ኣሉ።

"ተመልከቱ! አንድም ያጣችሁት ሰው ኣለ" ? ሲሉዋቸው 'ኧረ የለም' ኣሉ። "እኔ ግን ጁለይቢብን ኣጥቼዋለሁ። የተገደሉት መካከልም ፈልጉት" አሏቸው። ከዚያም ፈለጉትና ሰባቱን ጠላቶች ገድሏቸው ከዚያም ገድለውት በመሃላቸው አገኙት።

'የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሆይ ይኸው እሱ ነው። ሰባት ሰዎችን ከገደላቸው በኋላ ገደሉትና ከነሱ ዘንድ አገኘነው።' ኣሉ

የአላህ መልእክተኛም (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) መጥተው ቆመው እያዩት "ሰባቱን ገደለና ከዚያም ገደሉት፤ ይኸ ከኔ ነው፣ እኔም ከሱ ነኝ" ሲሉ ሁለቴ ወይም ሶስቴ ደጋገሙ። (ስጋዬ ነው። ወዳጄ ነው። እንደምንለው አገላለፅ ነው።)

ከዚያም ቀብር ተቆፈረለት። ከአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ትከሻ ውጭ አልጋ የሚባል የለውምና የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ትከሻቸው ላይ አስደገፉት። ከዚያም ከቀብሩ አስገቡት። ኣጥበውታል የሚል ነገርም አልተጠቀሰም።

ሚስቱን በተመለከተም ባል ከሞተባቸው የአንሷር እንስቶች መሃል የሷን ያህል (ገቢ ኖሯት በአላህ መንገድ ላይ) ወጪ የምታወጣ ባልቴት አልነበረችም።

ኢስሃቅ ቢን ዐብደላህ ቢን አቢ ጦልሃ ከሳቢት ጋር እንደተነጋገሩት 'ለመሆኑ የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ምን ብለው ዱዓእ እንዳደረጉላት ታውቃለህን' ? ሲሏቸው

"አምላኬ ሆይ መልካም ፍሰትን ወደሷ አፍስስላት። ኑሮዋንም ከበድ ከበድ አታድርግባት"። ብለዋል። ባል ከሞተባቸው የአንሷር ሴቶች መሃልም ከሷ ይበልጥ የምታወጣ (በቂ ገቢ ኖሯት ለሚያስፈልጋት ጉዳይ ወጪ የምታወጣ ሴት) የለችም። ብለዋል።

ምንጭ⇣
በኢማሙ አህመድ ሙስነድ (33/28) እንደተዘገው
عفان بن مسلم ، كما في " مسند الإمام أحمد " (33/28)

ከዚህ ታሪክ የምንቀስመው ቁምነገር በርካታ ሲሆን በጥቂቱ

~የሰው ልጆች ክብርና በላጭነት በኢማን የሚገኝ መሆኑን፣ ሰዎች በተለምዷቸው ለድሃ ሰው ያውም ለማያምርና ዘመድ አዝማድ ለሌለው ሰው ብዙም ቦታ እንደማይሰጡ፤

~የጁለይቢብ ከሴቶች ጋር ቀርቦ ማውራት ወይም መቀለድ ከልካይ የሆነው የሒጃብ አንቀፅ ከመውረዱ በፊት እንደሆነና በአንፃሩም ሴቶች በጣም ተራ ሞኛሞኝ ለመሰላቸው ወንድ ያለ ስጋት እንደሚያቀርቡት

~ጥሩ ባል በሚስቱ ላይ ቀናተኛ እንደሆነና የሚያሰጋ ነገር ሲገጥመው ራሷን እንድትጠብቅና እንዳታቀርበው እንደሚያስጠነቅቃት

~አንሷሮች ማለትም መልእክተኛውን [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] በስደታቸው ወቅት የተቀበሏቸው የመዲና ሰዎች ለሳቸው ያላቸው ፍቅርና ክብር የላቀ መሆኑን

~ሴትን ልጅ ለማግባት ሲፈለግ ቅድሚያ የሚጠየቀው ሃላፊዎቿ ወላጆቿ እንደሆኑ

~ወላጆች ለልጆቻቸው ምርጥ የሚሉትን ሰው እንደሚፈልጉና የዚያ ተቃራኒ የመሰላቸው ሰው ሲገጥማቸው ተማክረው በክብርና በስርዓት ለምላሽ መዘጋጀት እንዳለባቸው

~ባልና ሚስት በህይወታቸው ውስጥ ለሚገጥማቸው ጉዳይ እንደሚማከሩ፣ በዚህን ግዜ ሚስት ክርር እንኳ ባል ሃሳቧን ተረድቶ ነገርን እንደሚያበርድ

~ ሴቶች ስለሚያገባቸው ሰው ከሚድራቸው ሰው የመጠየቅ፣ ሙሉ ኢንፎርሜሽን የማግኘትና እምቢም እሺም የማለት መብት እንዳላቸው

~ከመልእክተኛው [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] የመጣን ውሳኔ ኣለመቀበል አግባብነት እንደሌለውና ላይላዩን የሚጎዳ የሚመስል ነገር ቢገጥም እንኳ በትእግስት ውሳኔያቸውን በተግባር ማዋሉ ለዱንያም ለኣኪራም ስኬት ሰበብ መሆኑን

~ሴት አይፈልግም ወይም ሴቶች አይፈልጉትም የሚሉ ተረቶችን ወደጎን ትተን ያላገቡ ወንዶችን ደግፈን ባል የሚያስፈልጋቸውንም ፈልገን ማጋባት እንዳለብን

~አንዳንድ ሰዎች ብቃታቸው ድብቅ መሆኑንና የሚገልፁበት መድረክ ሲመቻችላቸው ማንነታቸውን ከማንም በተሻለ ሊያሳዩ እንደሚችሉ… ሰባት ገደለ ከዚያም ተገደለ !

~የመልእክተኛው ልዩ ስብእና

~ለጁለይቢብ የተዳረቿ እንስት የአላህን ውሳኔ ተቀብላ ሰዎች ቦታ ያልሰጡትን ወንድ አግብታው ሳለ የጀመረችው ህይወት ዳግም በአላህ ውሳኔ ሲቋረጥ በቀጣይ ህይወቷ ደጋፊ አጥታ እንዳትቸገር መልእክተኛው [ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም] ከጌታቸው የለመኑላት ምቾት ከየትኛዋም ባል የሞተባት እንስት በተሻለ እንድትኖር ማስቻሉ ተጠቃሽ የሆነ ጉዳይ ነው።

ባጠቃላይ እነዚህንና መሰል ቁምነገሮችን ከታሪኩ እንገነዘባለን።

ወላሁ አእለም ወሰለላሁም'መ አላ ሙሃመዲን ወአላ ኣሊሂ ወሳህቢሂ ወሰለም።
------------------
www.fb.com/tenbihat
ሙሀረም (01/01/1437)
October (14/10/2015)

Post a Comment

0 Comments