Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የምልካም ስራ እድሎች


بسم الله الرحمن الرحيم

[ የምልካም ስራ እድሎች ]

ምስጋናና ውዳሴ ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ ይሁን ሰላትና ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ ምርጥ በሆኑት በነቢዩ ሙሀመድ ላይ ይሁን

አላህ በእዝነቱ ለባሮቹ የተለያዩ ወደርሱ የሚያቃርቡ ልዩ የመልካም ስራ እድሎችን ፈጥሯል በዚህም ተፎካካሪዎች እንዲፎካከሩ፣ ተሽቀዳዳሚዎችም እንዲሽቀዳደሙ ገፋፍቷል

የስው ልጅ ነፍስ ሁሌ አንድ አይነት ሁኔታ ላይ ስትሆን ትሰለቻለች አዲስ ነገር ስታገኝም ትነቃቃለች ይህንንም ባህሪይ ሽሪዓችን ለነፍሲያ በሚገባ ጠብቆላታል
በሀዲስ
" ነፍስ፥ አንዳንዴ ለመልካም ስራ ትነቃቃለች አንዳንዴም ትታክታለች (ትሰለቻለች) ንቃት ባላት ጊዜ ኸይርን ስራ በሚገባ አሰሯት በታከተች ጊዜም ግዴታ ለሆኑ ነገሮች እንጂ አትጫኗት" ተብሏል
ይህ በጌታው በሚገባ የሚያምንና ስሜቱንም የማይከተልን ሰው ነፍስ ለማለት እንጂ በመሰረቱ ስሜቱን የሚከተልና የጌታውን ህግ የሚጥስን ሰው ነፍስ አይመለከትም!

መንፈስን ለማደስና ነፍስንም መልካም ነገር ላይ ለማነቃቃት አላህ በየጊዜው በመጠነኛ ልፋትና ጥረት ከፍተኛ ምንዳ የሚያስገኙ እድሎችን አስገኝቷል

ይህንንም እድል ፈጥነን እንድንጠቀም ትሩፋቱን ገልጿል
ከነዚህም እድሎች መሀል አንዱ የዙል_ሒጃ የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ናቸው ቡኻሪይና ሌሎችም ባስተላለፉት ሀዲስ ነቢዩ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም የሚከተለውን ብለዋል
[ما من أيام العمل الصالح فيها أحب إلى الله من هذه الأيام يعني أيام العشر .... الحديث]

"ከዙል ሒጃ 10 ቀናት የበለጠ መልካም ስራ ከመቼውም በላይ አሏህ ዘንድ ውድ የሚሆንበት ቀን የለም"

እነሆ አዱኒያ አጭር ናት እድሜያችንም አጭር ነው ከአጭሩም የቀረው በጣም አጭር ነው
ይህም እውነታ ከብዙ ምአተ- ዓመታት በፊት ተነግሮናራል

[قُل متاعُ الحياةِ الدنيا قَليل والآخِرةُ خَيرٌ لِمَن اتَقى....] النساء 77
" ነቢዩ ሙሀመድ ሆይ ንገራቸው፥ የዱኒያ ህይወትና መጠቃቀሚያዋ አጭርና ጥቂት ነው የአኼራ ህይወትም (አሏህን ለሚፈሩ) ከዱኒያ የተሻለ ነው"
ሱረቱንኒሳእ 77

አጭርና ጥቂት ከሆነችዋ የዱኒያ ህይወት የቀረው ጥቂት መሆኑንም ሲነግረን አሏህ እንዲህ ብሏል

(اقتَرَبَت الساعةُ وانشَقَّ القَمَر)
" ቂያማ ደረሰ ጨረቃም ለሁለት ተከፈለች “ ሱረቱልቀመር 1

(اقتَرَبَ للنَّاسِ حِسابُهم)

“ የሰው ልጆች መተሳሰቢያ ወቅታቸው ተቃረበ እነሱ ግን ቸልታና መዘናጋት ላይ ናቸው ” ሱረል አንቢያ 1

አጭሩ እድሜያችን መች እንደሚቋጭ አናውቅም ሁሌም ራስን ለሞት ማዘጋጀት ብልህነት ነው
ለሞት መዘጋጃት፥ መልካምን ስራ ተሽቀዳድሞ በመስራት ከወንጀል በመራቅ አኼራን በመናፈቅ ነው

ጊዜያችንን በአግባቡ እንጠቀም የውርደትም ይሁን የስኬት ሰበቡ የጊዜ አጠቃቀም ነው

በዱኒያ ወይም በአኼራ በማይጠቅም ነገር ጊዜና ገንዘባችንን የምናባክን ሰዎች
በቀጣዩ ምርጥ የዙልሂጃ ቀናት ለመጠቀም ከወዲሁ ነፍሲያችሁን አሸንፉ
ሌት-ተቀን በኔት ጊዜ፣ ገንዘብና አይናችሁን የምታቃጥሉ፥ አሏህን ፍሩ ከማይጠቅም ወሬ ራቁ
ቁርኣን ቅሩ ዘክሩ የኔትን ውዴታ በአላህ ውዴታ ቀይሩ!

= ውድ የአሏህ ባሮች
አላህ ዘንድ ውድ የሆኑ 10 ቀናትን፥
አምስት ወቅት ሰላቶችን በወቅታቸው፣ ከፊትና ከኋላ የሚሰገዱ ሱናችን ከመጠበቅ ጋር፣ ወንዶች በጀማዓ በመስገድ፣

ቁርኣን በመቅራት፣ ዚር፣ ዱዓ እንዲሁም ተክቢራ በማብዛት፣

የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳትና የታመሙን በመጠየቅ፣

ከዙልሂጃ 1 ጀምሮ እስከ 9ኛው ቀን በመጾምና የጾሙ ሰዎችንም በማስፈጠር ወዘተ አሏህ የሚወዳቸው መልካም ስራዎችን በመስራት እናሳልፋቸው

ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጅ እድሜ በጣም አጭር ነው አሏህ ኸይርን የሻለት ሰው ባጭር ጊዜ ብዙ ቁም ነገር መስራት ይችላል::
በነዚህ ውድ ቀናት ለአኼራችን ስንቅ እንሸምት ወላሂ በጣም ድንቅና የተከበሩ ቀናት ናቸው አሏህ በተከበረው ቁርኣኑ በነዚህ ቀናት ምሏል አሏህ ትልቅ ነው በትልቅ ነገር እንጂ አይምልም!
ነቢያችንም በነዚህ ቀናት መልካም ስራ ላይ እንደንበረታ ገፋፍተውናል
እራሳቸውም ቀናቱን በመልካም ስራዎች ያሳልፏቸው እንደነበረ ተዘግቧል

እነሆ ኢማሙ አህመድና ሌሎችም ዘግበውት አልባኒይ ሰሂህ ባሉት ሀዲስ
የምእምናን እናት ሀፍሳ ረዲየላሁ ዐንሃ እንዲህ ብለዋል "ነቢዩ የዓሹራ፣ የዙልሂጃ 10 ቀናትንና በየወሩ 3ቀን መጾምን አይተውም ነበር" ብላለች

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነጥብ ቢኖር እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ " ነቢዩ የዙልሒጃ10 ቀናትን ጾመው አያውቁም" ብላ የተናገረችበት ሀዲስ አለ ይህ ማለት እሷ እስከ ምታውቀው ድረስ ነው

ምክንያቱም ነቢዩ ዘጠኝ ሚስቶች ነበር ያሏቸው እሷ ቤት በሚያድሩበት እለት ጾመው አለማየቷን ነው የሚያሳየው እንጂ በጭራሽ አይጾሙም ነበረ ማለት አይደለም ኡመታቸውን ወደ መልካም ነገር አመላክተው እራሳቸው ወደ ኋላ ይቀራሉ እንዴ? አረ በጭራሽ!

ይህ በንዲህ እንዳለ የኡሱል ትምህርት ዘርፍ ዑለሞች እንደጠቀሱት አንድን ጉዳይ በተመለከተ ነቢዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አድርገዉታል ወይስ አላደረጉትም የሚል ውዝግብ ከተነሳ ማድረጋቸው የተጠቀሰው በትክክለኛ ሰነድ መሆኑ ከተረጋገጠ ቅድሚያ የሚሰጠውና ተቀባይነትም የሚያገኘው እሱ ነው ምክንያቱም አላደረጉም ያለው አካል የማያውቀውን አድርገዋል ያለው አካል በማወቁ ጉዳጋዩ ተሰሚነትና የበላይነት ይኖረዋል

በመሆኑም ከነቢዩ ባለቤቶች መሀል አንደኛዋ ጾመዋል ስትል ሌላኛዋ ደግሞ አልጾሙም ካለች ተቀባይነት የሚያገኘው ጾመዋል ያለችዋ ይሆናል ማለት ነው

== ደጋግ ቀደምቶች ስለነዚህ ቀናት ደረጃ ምን እንዳሉ ያውቃሉ?==

ሰሃቦችና ተከታዮቻቸው እንዲሁም ፈለጋቸውን ይከተሉ የነበሩ ደጋግ ቀደምቶች ትልቁ ጭንቃቸውና የህይወት ዓላማቸው "ዒባዳ" ወይም መልካም ስራ ላይ መሽቀዳደም ነበር

ለዚህም ነው ከነሱ መሀል አንዱ እንዲህ ያሉት
" በዱኒያ ጉዳይ አንድ ሰው ሊቀድምህ ቢፈልግ መንገዱን አስፋለት በአኼራ ጉዳይ ግን ማንም እንዳይቀድምህ "

አሁን አሁን እየዘነጋን ኖሮ እንጂ አሏህም በተከበረው ቃሉ እንዲህ ሲል መክሮን ነበር
(سابقوا إلى مغفرة من ربكم وجنة)
" ተሽቀዳደሙ……..ወደ ጌታህቹ ምህረትና ወደ ጀነት" ሱረቱልሐዲድ 21

ህይወታችን በሙሉ መልካም ስራዎች ላይ መሽቀዳደም ቢያቅተን እንደ ዙልሒጃ 10 ቀናት ያሉ እድሎችን በአግባቡ እንጠቀም ደረጃና ክብራቸውንም እንወቅ
በተከበረው በረመዳን ወር የሚገኙ ትሩፋቶችን በነዚህ ቀናት ማግኘት እንደሚቻል ዑለሞች ጠቅሰዋል (ለይለቱል ቀድር ስትቀር)
የዙልሒጃ 10 ቀናት በጥቅሉ ከረመዳን 10 ቀናት እንደሚበልጡም ገልፀዋል፡፡

- ታላቁ ታቢዒይ ኢብና ሲሪን እና ቀታዳ
" ከዙልሒጃ 10 ቀናት ውስጥ አንደ ቀን መፆም ዓመት እንደፆሙ ይቆጠራል " ሲሉ
ሐሰነል-በስሪ ደግሞ ከአነስ ረዲየላሁ ዐንሁ የሚከተለውን እንደሰሙ ተናግረዋል
"ሰሓቦች፦ የዙልሒጃ 10 ቀናት እያንዳንዱ ቀን በ1000 ቀን (አንድ ሺህ ቀን ) ይባዛል 9ነኛው ቀን ደግሞ በ10,000 (በአስር ሺህ) ይባዛል ይሉ" ነበር
ለጧኢፉል መዓሪፍ፡ ገፅ 459

ይህ ትልቅ የአለህ ስጦታ ነው በሩ ለሁሉም ክፍት ነው አላህ ያግዘን ስንፍናና ቸልተኝነትን ያንሳልን አሏሁመ አሚን

# ማሳሰቢያ #

-1ኛ ኡድሒያ ለማረድ እቅድ ያለው ሰው፦ የዙልሒጃ ጨረቃ መታየቱ ከተረጋገጠበት ቅፅበት ጀምሮ የዒድ ሰላት አስኪጠናቀቅ ደረስ ጥፍሩንና ሰውነቱ ላይ የሚገኘን ማንኛውንም ፀጉር ማንሳት አይቻልም
- 2ኛ የዒድ ቀን ሰላት እስኪጠናቀቅ ድረስ መፆም ሱና ነው ቀኑን ሙሉ መፆም ግን ክልክል ነው
-3ኛ በነዚህ ብርቅዬ ቀናት ቁርኣንን ደጋግሞ ለማክተም መሞከር ይመከራል
ሶስት ጊዜ ቢያከተሙ አላህ ዘንድ ቁጥር ስፍር የሌለውን ምንዳ ያገኛሉ
በያንዳንዱ ፊደል 10 ሐሰናት እንደሚያገኙ አይዘንጉ!

اللهم وفقنا لمرضاتك
وعرضنا لنفحاتك
واجعلنا من عبادك الصالحين

✍አሕመድ ኣደም
ዙል-ቂዕዳ 29/1436 ዓ.ሂ