Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

እንዳያልፈዎ! ከሸይኽ አልባኒ ድንቅ ምክሮች

እንዳያልፈዎ!
ከሸይኽ አልባኒ ድንቅ ምክሮች
- ጠያቂ፡- አንድን ሰው ለአላህ ብሎ የወደደ “ለአላህ ብየ እወድሃለሁ” ብሎ ማሳወቅ አለበት?
• ሸይኽ አልባኒ፡- አዎ፡፡ ግን ለአላህ ብሎ መውደድ ዋጋው ከባድ በመሆኑ የሚከፍለው ጥቂት ነው፡፡ ለአላህ ብሎ የመውደድ ዋጋ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? እስኪ ማነው የሚያውቅ መልሱን የሚሰጠን?
- ከታዳሚዎች አንዱ፡- ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡ ((ሰባት አይነት ሰዎች አላህ ከሱ ጥላ ውጪ ጥላ በሌለበት (በቂያማ) ቀን ከጥላው ስር ያስጠልላቸዋል…) ከነዚህም ውስጥ ((ለአላህ ብለው ተዋደው በዚያም ላይ ተገናኝተው በዚያው ላይ የተለያዩ ናቸው)) ሲል መለሰ፡፡
• ሸይኽ አልባኒ፡- እሱ በራሱ ትክክኛ ንግግር ነው፡፡ ግን የጥያቄው መልስ አይደለም፡፡ አንተ የጠቀስከው ነገር ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን ቀረብ ባለ መልኩ ለአላህ ብሎ መውደድ ምን እንደሆነ የሚገልፅ ነው፡፡ የኔ ጥያቄ ግን “ሁለት ለአላህ ብለው የተዋደዱ ሰዎች አንዱ ለሌላው ሊከፍለው የሚገባው ዋጋ ምንድን ነው?” የሚል ነው፡፡ እንጂ የአኺራ ሽልማቱን (አጅሩን) ማለቴ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማለት የፈለግኩት ሁለት ሰዎች እውነት መዋደዳቸው ለአላህ እንደሆነ በተግባር የሚያመላክተው ምንድን ነው የሚል ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ሊዋደዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ውዴታቸው እውነተኛ ያልሆነ ዝም ብሎ ቅርፃዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነተኛ እንደሆነ የሚያመላክተው ምንድነው?
- ከታዳሚዎች አንዱ፡- “ለራሱ የሚወደውን ለወንድሙ መውደዱ”
• ሸይኽ አልባኒ፡- ይሄ የመውደድ ነፀብራቅ ነው ወይም ከመውደድ ነፀብራቆች አንዱ ነው፡፡
- ከታዳሚዎች አንዱ፡- የላቀው ጌታችን እንዲህ ብሏል፡ ((አላህን የምትወዱ ከሆናችሁ መልእክተኛውን ተከተሉ፡፡ አላህ ይወዳችኋል- በላቸው)) (3፡32)
• ሸይኽ አልባኒ፡- ይሄ ትክክለኛ መልስ ነው- ግን ለዚህ ሳይሆን ለሌላ ጥያቄ!
- ከታዳሚዎች አንዱ፡- ምናልባት መልሱ በዚህ ሶሒሕ ሐዲስ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡ ((ሶስት ነገሮች በውስጡ ያሉበት የኢማን ጣእም/ጥፍጥና አግኝቷል…)) ከነዚህ ውስጥ ((ለአላህ ብለው የተዋደዱ ናቸው)) አለ፡፡
• ሸይኽ አልባኒ፡- ይሄ ለአላህ ብሎ መውደድ የሚያስከትለው ውጤት ነው- በልቡ የሚያገኘው ጥፍጥና!
- ከታዳሚዎች አንዱ፡- የላቀው ጌታችን እንዲህ ብሏል፡ ((በጊዜ እምላለሁ! የሰው ልጅ በክስረት ውስጥ ነው ያለው!!! እነዚያ አምነው መልካም የሰሩት፣ በሀቅም የተመካከሩት፣ በትእግስትም የተመካከሩት ሲቀሩ))
• ሸይኽ አልባኒ፡- በጣም ጥሩ ብለሃል! ይህ ነው ትክክለኛው መልስ!! ይህም ሲብራራ እኔ አንተን እውነት ለአላህ ብየ የምወድህ ከሆነ በምክር ልከተልህ ይገባል፡፡ አንተም እንደዚያው፡፡ ለዚህም ነው “ለአላህ ብለን እንዋደዳለን” በሚሉ ሰዎች ዘንድ ይሄ አንዱ ሌላውን በምክር መከተል በጣም ውስን ነው፡፡ ምናልባት መዋደዳቸው ከፊል እውነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ግን ሙሉእ አይደልም፡፡ ለምን ቢባል እያንዳንዳችን የሌላውን ስሜት ይጠብቃል፡፡ “እውነቱን ስነግረው ቢቆጣስ፣ ቢሸሽስ፣… ወዘተ” እያለ ሀቅን ሳያስተላልፍ ይቀራል፡፡ ስለዚህ ለአላህ ብሎ መውደድ ዋጋው አንዳችን ለሌላው በምክር ኢኽላስ ሊኖረው ነው- እውነተኛ መካሪ ሊሆን፡፡ ሁሌም በመልካም ሊያዘው ከመጥፎም ሊከለክለው ይገባል፡፡ ወዳጅ ለሚወደው ከጥላው የበለጠ በምክር የሚከተለው ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡ ሶሐቦች ተገናኝተው ሲለያዩ አንዱ ለሌላው ይችን ምእራፍ (ወልዐስር…) ይቀሩ እንደነበር የሚያመላክተው ሶሒሕ ማስረጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ማሳሰቢያ፡- የተጠቀምኩት ነፃ ትርጉም እንጂ የቃል በቃል ትርጉም አይደለም፡፡
አላህ የሐቅ ለአላህ ብለን የምንዋደድ ያድርገን፡፡ ኣሚን፡፡
https://www.facebook.com/IbnuMunewor