Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ንጉሰ-ነገስት” ጫት


“ንጉሰ-ነገስት” ጫት
ድሮ ጫት “ንጉስ” ነበር፡፡ የተፈራ የተከበረ፡፡ ሐጃ ማውጫ ጉዳይ ማስፈፀሚያ፡፡ ገራባው እንኳ ካልባሌ ቦታ እንዳይወድቅ የሚጠነቀቁለት ልዩ ቅጠል ነበር፡፡ እንዳውም አንዳንዶች እንደሚተረተሩት አደምና ሐዋ እራሱ እንዳትነኩ ተብለው የነበረው ቅጠል ጫት ነው፡፡ ስለዚህ የጀነት ተክል ነው ማለት ነው- እንደነሱ፡፡ እንዳውም አንዱ ሲያወራ እንደሰማሁት “ጫትና ቡና አላህ ዘንድ ሄደው፣ ቡና ተንቀልቅሎ ሲገባ ጫት በስርኣት ከበር ቆሞ ፈቃድ ጠየቀ፡፡ በዚህ ምክኒያት ቡና እንደተንቀለቀልክ “ይሹህ ይውቀጡህ” ሲባል ጫት ግን “ሐያእ እንዳረግከው ሐያእ ያርጉልህ” ተባለ፡፡ ለዚያም ነው ሰዎች ጫትን በስርኣት እጃቸውን እያሹ የሚቀበሉት”አለኝ፡፡ አዑዙ ቢላህ!!! ዛሬ ግን ያ ቀዳማዊ ወይም ዳግማዊ ጫት የተከበሩበት ዘመን አልፎ እንዲህ የፍንዳታ መጫወቻ ሆኑ፡፡ “ከጫት ሙቀት እንጂ እውቀት አይገኝም” ተብሎም ተተረተባቸው፡፡ አርጅተው ይሆን እንዴ? “አንበሳ ሲያረጅ የዝንብ መጫወቻ ይሆናል” ከሚለው ውስጥ አንድ አባባል ልኮርጅ ነው፡፡ “ጫት ሲያረጅ የፍንዳታ መጫወቻ ይሆናል” የሚል፡፡ ምን ትላላችሁ? እሺ ይቅርብኝ፡፡ (ምነው አርጅቶ ሞቶ በተገላገልነው?! የስንቱን ወኔ አፈሰሰው አይደለም እንዴ?!)
እና በወርቃማ ዘመኑ ጫትን ቃሚዎቹ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ የሆነን ቀን ወይም የሆነን አጋጣሚ አስታከው ለዱዓ ብለው የሚቅሙ፡፡ በእድሜም ሲታይ በአብዛሃኛው የልጆችና የወጣቶች ሳይሆን የሽማግሌዎችና የጎልማሶች ነበር፡፡ አስታውሳለሁ አንዳንድ ልጆች በመቃማቸው አገር ይነጋገር ነበር፡፡ ዛሬ ግን ልጅ አዋቂው፣ ሴት ወንዱ፣ ፍንዳታው ቃልቻውም… ሁሉ እየቃመው ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ጫት ከዙፋናቸው ወረዱ፡፡ የማንም መጫወቻ ሆኑ፡፡ ገራባቸው ለማገዶ ዋለ፡፡ ከሙዚቃውም፣ ከሺሻውም ጋር መጋፋት መታወቂያቸው ሆነ፡፡ ላቅመ-ቂማ ያልደረሰው ሁሉ ይወቅጣቸው ይገባ፡፡ ቃሚዎችን ያስከፋ ይሆናል እንጂ መቃም የሚለው ቃል ምን ያህል እንደሚገልፀው እጠራጠራለሁ፡፡ ምን ላርግ እንግዲህ ጠረጠርኩ፡፡ እስኪ አስቡት አንድ ሰው በጫት ላይ የሚቆየውን ያክል በምግብ ላይ ቢቆይ፣ ከዚያም ሰርክ እንዲህ ቢያደርግ ምን እንለው ይሆን? እስኪ በአላህ ግን አስቡት አንድ ልጅ ይሄን ያህል ጊዜ፣ ሰርክ ቢበላ ቤተሰቦቹ ዝም ይሉታል? እርግጠኛ ነኝ ሀብታም እንኳን ቢሆኑ አያደርጉትም፡፡ ይሄን ያክል ጊዜ ሲቃም ግን አስቡት፡፡ ለመሆኑ ከጫትና ከምግብ ማንኛው ቢጎዳ ነው ውይ ይቅርታ ማንኛው ቢጠቅም ነው? ወይ ጉድ!!
እና ያንን ዋጋቸው ዝቅ ክብራቸው ከፍ ያለበትን ዘመን አሳልፈው ዋጋቸው ከፍ ክብራቸው ዝቅ ያለበት ዘመን ላይ ደረሱ፡፡መደበሪያም፣ መበደሪያም፣ መነገጃም፣ መቀለጃም ሆኑና ይሄው መቀለድ ያዝን፡፡ ባይሆን ጫት ዝናውንና ንግስናውን ቢያጣም ደንበኞቹን ግን ባስገራሚ ሁኔታ አሳድጓል፡፡ “ደንበኛ ንጉስ ነው” አለ ጫት፤ ብለን ሰውኛ ዘይቤ እናናግረው እንዴ ጎበዝ?
እናንተየ ግን ለምንድን ነው ጫት ሲነካ ሰዎች ደርሰው ቱግ የሚሉት? እባካችሁ የምታውቁ ንገሩኝ:: ነገርዮው እንደዚያ ያደርጋል እንዴ? እስኪ አስቡት ዛሬ ስንቶች ናቸው የአላህ ሐቅ ሲደፈር ፍሪጅ የገቡ ይመስል ድርቅ ግግር ብለው ጫት የተነካች ጊዜ ግን አራስ ነብር የሚሆኑት? ስንት ወላጆች አሉ ከቤታቸው ሶላት የማይሰግድ ልጃቸውን ዝም ብለው “ኧረ ይቺ ጫት …” የሚላቸውን ግን የስድብ ናዳ የሚያወርዱበት?!!
አንዳንድ መሀል ሰፋሪ አለ ደግሞ እንዲህ አይነት ርእስ ለምን ታነሳላችሁ ሒክማ ይኑራችሁ ሰፋ በሉ፣ ተንቦርቀቁ፣ ታጠፉ፣ ተዘርጉ፣ ብሮድ ማይንድድ፣… የሚል፡፡ ሺርኩም ሲነካ እንዲሁ ነው፣ ቢድዐውም ሲነካ እንዲሁ ነው፣ ሐራሙም ሲነካ እንዲሁ ነው፡፡ እንደኔ ግን ካጥፊዎቹ የከፉት እነዚህኞቹ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በሁሉም ነገራችን ላይ ሒክማ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ታዲያ ሒክማ ማለት ሊደርስ የሚገባን መልእክት ሊደርስ በሚገባበት ሁኔታ አግባብ ባለው መልኩ ማቅረብ እንጂ ሒክማ የእውነት መቅበሪያ ጉድጓድ አይደለም!! የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ብለው ህዝብ ዘንድ በሰፊው የተንሰራፉ ጥፋቶች በተነኩ ቁጥር “ሒክማ ተበላሸን” የሚያዜሙት ዛሬ ዛሬ በርክተዋል፡፡
ብቻ ለማንም ባይሰወርም እንዲሁ ለማስታወስ ያክል
1. ጫት ጤናን ያቃውሳል፡፡ ይህን እውነታ ምንም እንኳን ሳይንስ ቢያረጋግጠውም ለማንም የሚሰወር አይደለም፡፡ አንዳንዱ ግን ውስጡ እያወቀ ነጩን ጥቁር ካለ አይመለስም፡፡
2. ጫት ከኢባዳ ያዘናጋል፡፡ ከሚቅሙ ሰዎች ሱብሒን የሚሰግዱት እጅግ አናሳ ናቸው፡፡ እስኪ ቃሚ ኢማሞችን ቁጠሩ፡፡ ምን ያህሉ ናቸው አስር ሶላት ላይ መስጂድ የሚገኙት?
3. ጫት ወደሌሎች ደባል ሱሶች የማሸጋገር እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ሲጋራ፣ ሺሻ፣ …:: እንግዲህ የጫት ዘመዶች እነዚህ ናቸው፡፡ “ዘመድ ከዘመዱ፣ አህያ ካመዱ”
4. ጫት በተለይ ዛሬ ዛሬ በተለይም ወጣቶች ጋር ለብልግና የሚገናኙበት መድረክ እየሆነ ነው፡፡ “እሺ በስርኣት ቢቃምስ?” የሚል አይጠፋምና እኔም እንዲህ ማለት ፈለግኩ:: “እሺ ጠላ በስርኣት ቢበጣስ?” ያስኬዳል? ጠላና ጫት አንድ ነው ሁለት ነው ውስጥ አልገባሁም፡፡ ምሳሌ ነው፡፡
5. በምርቃና ጊዜ በርካቶች እራሳቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ከአላህ ሌላ ይለምናሉ፡፡ ይሄ አደገኛ ሺርክ ነው፡፡ “አላህ ይስጥህ” በማለት ፋንታ “እንካ፣ ያዝ፣ ጀባ፣..” የሚሉም ቀላል አይደሉም፡፡ በነሱ ቤት ጫትን ለዱዓ መጠቀማቸው ነው፡፡
6. በጫት ሳቢያ ለከባድ የኢኮኖሚ ድቀት የሚዳረጉ እንዳሉም በየቤታችን በየአካባቢችን የምናየው ነው፡፡
7. የጫት ስርኣቱ በሀሜት፣ በሙዚቃ፣ በሽርክ፣… የተወረረ ነው፡፡
አላህ ገንዘባችንንም፣ አካላችንንም፣ ጊዜያችንንም በመልካም የምናውል ያድርገን፡፡ ቃሚ ወገኖቻችንን አላህ ይገላግላቸው፡፡ የጫት ነጋዴዎችን አላህ የተሻለ የስራ እድል ይክፈትላቸው፡፡ በደረቁ የሚሟገቱን አላህ ልባቸውን ይክፈትላቸው፡፡ ለጫት ቀርቶ ለጠላት የማይረታ፣ የማይልፈሰፈስ ጠንካራ ትውልድ ይስጠን፡፡ ኣሚን፡፡
(ኢብኑ ሙነወር፣ 18/3/2005)