Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

“ተነቃብሽ ምስር በለጠችሽ ቀይስር”


“ተነቃብሽ ምስር በለጠችሽ ቀይስር”
ጌታዬ እሱ ከዐርሹ በላይ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ “መካሪዎች” “ዟሂሩን እንዳትወስድ መልእክቱ ሌላ ነው” አሉኝ፡፡ እኔ ግን “ከናንተ ይልቅ ግልፅ በሆነ ዐረብኛ የነገረኝን ጌታዬን አምናለሁ፣ እንዳለኝም እርሱ ከዐርሹ በላይ ነው” አልኩኝ፡፡ “አንተ ወሃቢ” ተባልኩኝ፡፡ ይሁን ብዬ ተቀበልኩኝ፡፡
“ከአላህ ጋር ማንንም አትጣሩ” የሚል ቁርኣናዊ ጥሪ ሰማሁኝ፡፡ ተከትየም አስተጋባሁኝ፡- “ነብዮችም ሷሊሖችም አክብሮት እንጂ አምልኮት አይገባቸውም” አልኩኝ፡፡ “አንተ የነቢ ጠላት ወሃቢ!” ተባልኩኝ፡፡ የነቢዩን ዐለይሂሠላም ትእዛዝ ስላከበርኩኝ፡፡ ይሁን ምን አደርጋለሁኝ፡፡
“ቢድዐ ሁሉ ጥመት ነው” የሚል ሐዲሥ አገኘሁኝ፡፡ ነብዩን ዐለይሂሠላም አምኜ እውነት ብየ ተቀበልኩኝ፡፡ ከማንም ፍጡር በላይ ነብዬን አስቀደምኩኝ፡፡ “ሁሉም ቢድዐ ጥመት ነው” አልኩኝ፡፡ ነብዩን ዐለይሂሠላም እንወዳለን በሚሉ ሰዎች ቅፅል ስም ተወጣልኝ፡፡ “ወሃቢው” ተብየ ተጠራሁኝ፡፡ ትእዛዝ ስላከበርኩኝ፡፡
ለወንዶች ልብስ “ማስረዘምን ተጠንቀቁ፣ ማስረዘም በራሱ ኩራት ነውና” የሚል ሐዲሥ ሰማሁኝ፡፡ ትእዛዙን አክብሬ ልብሴን አሳጠርኩኝ፡፡ ይህን በሚቃወሙት “ምልክቱ ታይቶብሃል አንተ ወሃቢ” ተባልኩኝ፡፡ የነብዩን ዐለይሂሠላም ትእዛዝ ስለፈፀምኩኝ፡፡
“ፂማችሁን አሳድጉ” የሚል ሐዲሥ አገኘሁኝ፡፡ የምወደውን ነብይ ትእዛዝ አከበርኩኝ፡፡ ፂሜንም አሳደግኩኝ፡፡ ስላሳደግኩ “ከኛ ወዲያ ነብዩን ወዳጅ ላሳር” በሚሉ ጀሌዎች ተወነጀልኩኝ፡፡ “ወሃቢ” ተባልኩኝ፡፡ ትእዛዝ ስለፈፀምኩኝ፡፡
.
.
.
ቆምኩኝ አሰላሰልኩኝ፡፡ ሂሳብ አወራረድኩኝ፡፡ ሰዎቹ ዘንድ “ወሃቢ” ማለት እንዲህ ሆኖ አገኘሁኝ፡፡ ወደተውሒድና ሱና የሚጣራ፤ ከሺርክና ከቢድዐ የሚጠነቀቅና የሚያስጠነቅቅ፤ ሱናን በላዩ ላይ ለማንፀባረቅ የሚታትር፤ ለእኛንዳንዱ እምነታዊ ጉዳይ መረጃ የሚጠይቅ፡፡ በቃ ይሄው ነው “ወሃቢ” ያስባለው፡፡ “አይ..” የሚል ካለ I am ዝግጁ for any የተረጋጋ ውይይት፡፡
ለመሆኑ “ወሃቢያ” የሚለው ስያሜ ከየት መጣ
ጠላቶቹ እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ፡ “ስያሜው የተወሰደው ከመስራቹ ነው”
ማነው መስራቹ “ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ” አሉ፡፡
ታዲያ “ወሃብያ” ብላችሁ ለምትጠሯቸው አካላት እንደመነሻ የተጠቀማችሁት “ወሃብ” የሚለው ቃል መስራች ነው የምትሉት ሰውየ ስም ነው በጭራሽ!!!
እሺ የአባቱስ ስም ነው በፍፁም!!!
እና የማን ስም ነው የአላህ!!!
አላሁ አክበር!!! ለማውገዝ ወደ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ ያስጠጋችሁት ስያሜ እንዳሰባችሁት ሳይሆን ወደ አላህ ነው የተጠጋው፡፡ ለመሆኑ ዐረብኛ የማይችል ነው እንዴ ስሙን ያወጣላችሁ አይ የናንተ ነገር፡፡ ኢማሙሻፊዒን አላህ ይማራቸውና “አንድ ሰው ጧት ሱፊ ከሆነ ከሰዐት ሞኝ ሆኖ እንጂ አይመለስም” ያሉት ትዝ አለኝ፡፡ ማስታወስ መብቴ ነው፡፡ አንዳንድ “ሰፋ” “ቦርቀቅ” ያሉ ሰዎች ይችን ጥቅስ ሲሰሙ ሲቆጡ ስላየሁ ነው፡፡ ብቻ እኔ “ኢማሙሻፍዒ አሉ” ነው ያልኩት፡፡ በቃ፡፡
ለማንኛውም ሁሉም ይወቅ፡፡ “ወሃቢ” የሚለው ቃል የተወሰደው “አልወሃብ” ከሚለው የአላህ ስም እንጂ ከሙሐመድ ኢብኑ ዐብዱልወሃብ ስም አይደለም፡፡ ሰዎችን ከትክክለኛው ቁርኣናዊና ሐዲሳዊ አስተምሮ ለማስበርገግ ያወጡት ስያሜ ሳያውቁት ለሚጠሉት አካል ሙገሳ ሆኖባቸዋል፡፡ ምን እንደሚሻላቸው አላውቅም፡፡ ማናቸው “ተነቃብሽ ምስር በለጠችሽ ቀይ ስር!!!” ያሉትብቻ ተነቅቶባችኋል፡፡
ግን ለእነኚህ የሱና ጠላቶች “የወሃቢ” መገለጫ ምንድን ነው
- “ወሃቢዮች ነብዮችንና ሷሊሆችን ይጠላሉ” አሉ፡፡ “ይቺ ጠጋ ጠጋ እቃ ለማንሳት ነው፡፡” እንዴት ነው ነብዮችንና ሷሊሆችን የምንጠላው
“በዱዓ ላይ እነሱን አማላጅ ማድረግን ትቃወማላችሁ” አሉ፡፡ አዎ እንቃወማለን!! የገብሬ “ድንግል ማሪያም ሆኝ አማልጂኝ” ስህተት ነው እንደምንል ሁሉ፣ የኑርሁሴን “ጀይላኒ ሆይ አማልዱኝ፣ ድረሱልኝ” ማለት ስህተት ነው እንላልን፡፡ እንዴ የጥፋት ቡላና ዳለቻ አለውንዴ በቃ ከማንም ይምጣ ከማን ጥፋት ጥፋት ነው፡፡ ሺርክ ጀለብያ ስለለበሰ ተውሒድ አይሆንም!!! አይሆንማ! ለምን አይሆንም ስለማይሆን አይሆንም!!! ያለበለዚያማ የመካ ሙሽሪኮችም የሚያመልኳቸውን አካላት “አማላጆቻችን ናቸው” አላሉም እንዴ ይሄው ቁርኣን ይመስክር፡፡ ለምሳሌ ሱረቱ ዩኑስ ቁጥር፡18 እንዲህ ይላል፡- ((ከአላህም ሌላ የማይጎዳቸውን የማይጠቅማቸውንም ያመልካሉ፤ እነዚህም አላህ ዘንድ አማላጆቻችን ናቸው ይላሉ፤ አላህን በሰማያትና በምድር ውስጥ የማያውቀው ነገር ኖሮ ትነግሩታላችሁን በላቸው፤ ከሚያጋሩት ሁሉ አላህ ጠራ ፤ ላቀም))
ባይሆን ከአላህ ብቻ ይጠየቅ አልን እንጂ ምልጃ የሚባል ነገር ጭራሽ የለም አልወጣንም፡፡ እንግዲህ ተመልከቱ፡፡ ሺርክን መቃወም ነው “ወሃቢ፣ የነቢዮች ጠላት፣ የሷሊሆች ጠላት” ያስባለን፡፡ ይሄ ከሆነ “ወሃቢዮች” ያስባለን በሉን ምንም አይደንቀንም፡፡ እንዳውም ስያሜው ከአላህ ስም ጋር እንደሚያያዝ እናውቃለን፡፡
- “ወሃቢዮች ነብዩን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም አይወዱም” አሉ፡፡ እንዴት ሲባሉ “መውሊድ ይቃወማሉ” አሉ፡፡ ነብዩ ዐለይሂሠላም “የኔ ትእዛዝ የሌለበትን ስራ የሰራ ስራው ውድቅ ነው” አሉ፡፡ አላሉም በሉን ደግሞ!! እሺ “መውሊድ አክብሩ” የሚል ቀጥተኛ ነብያዊ ትእዛዝ አምጡ ሲባሉ ቤሳቤስቲን የላቸውም፡፡ “እንግዲያውስ ውድቅ ነው” አልን፡፡ አሁን ማነው እውነተኛው የነቢዩ ዐለይሂሠላም ወዳጅ ትእዛዝ የሚያከብረው ወይስ ያለትእዛዝ የሚያነፍረው ለማንኛውም ይሄ ከሆነ “ወሃቢዮች” ያስባለን ይሁንላችሁ ያሻችሁን በሉን፡፡ ባይሆን አስታውሱ፡፡ ይሄን ባመት አንዴ የምትሰባሰቡበትን መውሊድ ሶሐቦቹም ፣ ታቢኦቹም፣ አትባኡታቢኦቹም፣ አራቱም የመዝሀብ መሪዎች አላከበሩትምና ከወሃቢያ መዝገባችሁ ውስጥ እንዳትረሷቸው፡፡ in your blacklist ማለቴ ነው! ኧረ ወይኔ! እናንተ አኮ አታደርጉትም አይባልም!!! ለነገሩ ብታደርጉት ባታደርጉት…:: ሲመስለኝ እዚያ ስትደርሱ ወይ ሚዛናችሁን ወይ ግራማችሁን ትቀይራላችሁ፡፡
- “ወሃቢዮች ሙስሊሞችን ያከፍራሉ” አሉ፡፡ እኛም እንዲህ እንላለን፡፡ ይሄ የሚያንፀባርቅ ነጭ ውሸት ነው!! አንዳንድ ተክፊሮችን አይታችሁ ሺርክና ቢድዐን ያወገዘን ሁሉ ይህን ካባ ለማልበስ የምትቧጭሩት ጥረት የተበላበት ንግድ ነው!! እኛን በሚያከፍሩ ሰዎች ጠቅልላችሁ “ተክፊሮች” ካላችሁን ተመሳሳይ ሂሳብ እንድንጠቀም እየጋበዛችሁን ነው፡፡ ስለሆነም ከናንተም ውስጥ “አላህ ከዐርሹ በላይ ነው” ያለን ሁሉ የሚያከፍሩ አሉና ሁላችሁንም “ተክፊሮች” እንበላችሁ ይሄ ሂሳብ ያዋጣል ለነገሩ ለማስታወስ ያክል አነሳሁት እንጂ የናንተን ሂሳብ እንጠቀማለን እያልኩ አይደለም፡፡
.
.
.
ቢሆንም
“ወሃብያ” የሚሉት እውነተኛውን የነብዩን ዐለይሂሠላም አስተምሮ ነው ብንልም፣ “ወሃብያ” የሚሉት የፀረ-ሺርክና ፀረ-ቢድዐ እንቅስቃሴን እንደሆነ ብናውቅም፣ “ወሃብያ” የሚሉት ተውሒድና ሱና ተኮር አካሄድን ነው ብንልም፣ “ወሃብያ” ማለታቸው የሚጠሉትን ደዕዋ ጭራቅ አድርጎ በመሳል ሰዎችን ከሐቅ ለማስበርገግ ነው ብንልም፣ … ይህም ከመሆኑ ጋር “ወሃብያ” ሲሉ ሳያውቁት እያሞገሱ እንደሆነ ብናውቅም በጭብጡ ውስጡ ስህተትም ነውርም እንደሌለ ለመጠቆም እንጂ ስያሜውን ተቀብለን መጠሪያችን እናደርጋለን እያልኩ አይደለም፡፡ ከሌሎችም የአላህ ስሞች እንዲሁ እየቆነጠርን ለራሳችን ስያሜ ወደማውጣት አይዳዳንም፡፡ ለምን ቢባል መልካም ቀደምቶቻችንን የበቃቸው ይበቃናል፡፡ አላህ እውነትን አውነትነቱን አይተው ከሚከተሉት ሀሰትን ሀሰትነቱን አይተው ከሚርቁት ያድርገን፡፡ ኣሚን፡፡