Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ቀዳ ያለበት ሰው የሸዋልን ፆም መፆም ይችላልን?



22/07/2015 · 

ቀዳ ያለበት ሰው የሸዋልን ፆም መፆም ይችላልን?

የረመዳን ቀዳ ያለበት ሰው ከሸዋል ፆም በፊት ያለፈውን ግዴታ ፆም ማስቀደም እንዳለበት የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ቀዳው በዝቶ ወይም በሆነ አሳማኝ ምክንያት የሸዋልን ፆም የምንፆምበት ጊዜ ካጣንስ ምን እናድርግ? በተለይ ሴቶች በወር አበባ እና የወሊድ ደም ሳቢያ ረመዳንን ሙሉውን ወይም ብዙውን ሳይፆሙ ይወጣባቸዋል፡፡ በዚህን ጊዜ የሸዋልን ስድስት ቀን ለመፆም ቢጓጉም የግድ ግዴታ የሆነው የረመዳን ፆም መቅደም እንዳለበት ይነገራቸዋል፡፡ በተጨባጭም ይህን የሚጠቁም የዑለማዎች ፈትዋ አለ፡፡ ከሰሞኑም ተተርጉሞ በስፋት ሲሰራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህም የተለየ ፈትዋ ስላለ እሱንም አንባቢ ተመልክቶ የሚችል አመዛዝኖ ቢወስን መልካም ስለመሰለኝ ላቀርበው ወደድኩኝ፡፡
ጥያቄ፡- “የረመዳንን ቀዳ ቀናት ሳያወጣ በፊት የሸዋልን ስድስት መፆም ይቻላልን?”
ሸይኽ ሙቅቢል ኢብኑ ሃዲ ረሒመሁላህ፡- “በረመዳን ያፈጠረባቸውን (ያልፆመባቸውን) ቀናት ቀዳ ካወጣ በኋላ ከዚያም ስድስቱን ከፆመ ይሄ መልካም ነው፡፡ ይህንንም ያንንም ማድረግ የማይችል ከሆነ ግን ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ረመዳንን ፆሞ ከዚያም ከሸዋል ስድስት ያስከተለ ልክ አመቱን ሙሉ እንደፆመ ነው” ያሏትን ስድስቷን (አስቀድሞ) ሊፆም ይችላል፡፡ ለምን ይህን አልን? ምክንያቱም የቀዳው ጊዜ ከስድስቷ ፆም በተለየ (ወቅቱ) ሰፊ ስለሆነ ነው፡፡ (ስድስቷ ግን) ከሸዋል ውጭ ጊዜ የላትም፡፡ የቀዳ ወቅት ግን ከዓኢሻህ ረዲየላሁ ዐንሃ እንደመጣው እንዲህ ብላለች፡ ‘በሸዕባን (ወር) እንጂ ቀዳየን አላወጣም ነበር፡፡’ ምክንያቱም በአላህ መልእክተኛ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ጉዳይ ትጠመድ ስለነበር ነው፡፡” የሸይኹ ንግግር እዚህ ላይ አብቅቷል፡፡ ከዓኢሻህ ንግግር የምንረዳው የረመዳን ቀዳዋን አመቱን ሁሉ አሳልፋ ከረመዳን ቀድሞ ባለው የሸዕባን ወር ነው ማለት ነው ስትፆም የነበረው፡፡
ፈትዋውን በዚህ ሊንክ ማግኘት ይችላሉ፡- -http://olamayemen.com/Dars-9443
ከዚህ በተለየ ሌላ የተቀመጠ አማራጭ አለ፡፡ ቀጣዩን ፈትዋ ይመልከቱ፡
ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ረሒመሁላህ፡- “በአንዲት ሴት ላይ ከረመዳን እዳ ካለባት ስድስቱን (የሸዋል ፆም) ነው ከእዳው የምታስቀድመው? ወይስ እዳውን ነው ከስድስቱ የምታስቀድመው?” ተብለው ሲጠየቁ እንዲህ ነበር የመለሱት፡-
“አንዲት ሴት ከረመዳን ቀዳ ካለባት ቀዳውን ካጠናቀቀች በኋላ እንጂ ስድስቱን ቀናት ልትፆም አይገባትም፡፡ ይህም ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “ረመዳንን ፆሞ ከዚያም ከሸዋል ስድስት ያስከተለ…” ስላሉ ነው፡፡ እናም ከረመዳን ቀዳ ያለባት ረመዳን አልፆመችም ማለት ነው፡፡ እናም ቀዳ ካጠናቀቀች በኋላ እንጂ የስድስቱ ቀናት ሠዋብ (ምንዳ) አይኖራትም፡፡ ቀዳው ሙሉ ሸዋልን የሚያጠቃልል ከሆነ ግን ለምሳሌ የወሊድ ደም ላይ ሆና ከረመዳን የሆነን ቀን የፆመች ካልሆነችና ከዚያም ቀዳውን በሸዋል መፆም ከጀመረች (ቀጣዩ) የዚልቂዕዳህ ወር እስከሚገባ ድረስ ካልጨረሰች የዚህን ጊዜ ስድስቱን ቀናት (ከቀዳዋ በኋላ) ትፆማለች፡፡ በሸዋል (ወር)የፆመ ሰው አጅርም ይኖራታል፡፡ ምክንያቱም ማዘግየቷ ለችግር ነውና፡፡ ማለትም በሸዋል ስድስቱን መፆም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም አጅር ይኖራታል፡፡” [መጅሙዑልፈታዋ፡ 19/20]
“አይ እኔ ከውዝግብ ውስጥ መግባት አልፈልግም” ወይም ደግሞ “ለኔ ሚዛን የሚደፋው “ሸዋል ቢያልፍም ቀዳውን ያጠናቅቅ የሚለው ነው” የሚል አካል ይኖራል፡፡ ሁኔታው ቢመቻችለት ሸዋልን ለመፆም ቁርጠኛ ውሳኔ (ኒያ) ያለው ሰው ካቅሙ በላይ በሆነ ነገር ሳይፈፅም ቢቀር አላህ አጅሩን አያሳጣውም ኢን ሻአላህ፡፡ ይህንን የሚያመላክቱ ጥቅል ሐዲሦችም አሉ፡፡ ለምሳሌም ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዲህ ብለዋል፡፡
1. “መዲና ውስጥ በርግጥም ሰዎች አሉ፤ ጉዞን አትጓዙም፣ ሸለቆንም አታቋርጡም፣ ከናንተ ጋር ቢሆኑ እንጂ፡፡ ህመም ነው ያስቀራቸው፡፡” በሌላ ዘገባም “በአጅር የሚጋሯችሁ ቢሆን እንጂ” ብለዋል፡፡ [ሙስሊም]
2. “ከኋላችን መዲና ውስጥ (የቀሩ) ሰዎች በርግጥም አሉ፡፡ ሸንተረርን ወይም ሸለቆን አልተጓዝንም እነሱ ከኛ ጋር ቢሆኑ እንጂ፤ ችግር ነው ያስቀራቸው፡፡” [ቡኻሪ]
3. “የሆነች መልካም ነገርን ሊሰራ ቁርጠኛ ውሳኔ አድርጎ (በሆነ አሳማኝ ምክንያት) ያልሰራት ሰው የላቀውና ከፍ ያለው አላህ ሙሉ ምንዳን ይመዘግብለታል፡፡” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ወላሁ አዕለም፡፡