Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አሕባሾች እነማን ናቸው?



አሕባሾች እነማን ናቸው?
አብዛሃኛው ሙስሊም አሕባሾችን የሚቃወመው መጅሊሱን ተቆናጥጠው በህዝበ-ሙስሊሙ ላይ በሚያደርሱት ግፍ፣ መሳጂድ መንጠቅ፣ ህዝበ ሙስሊሙን ማስጠቃት፣ ማሳደድ፣ ማሳሰር፣ ማስገደል ሳቢያ ነው፡፡ በእርግጥም እነዚህ ነገሮች ብቻቸውን አሕባሾችን ለመቃወም በቂ ምክንያት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አብዛሃኛው ህዝባችን አሕባሾችን ለዚህ ያበቃቸው ከሰፊው ሙስሊም የተለየ የዐቂዳ ብክለት ምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ይሄ እጅግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ መታወቅ ያለበት አሕባሾች በዋናነት ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉት ከመስጂዶቻችን በበለጠ ልቦቻችንን ነው፡፡ ልክ እነሱ እንደጠፉት ልቦቻችንን ሊያጠፉ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም አላማ ሲሉ ከየትኛውም ሃይል ጋር ይተባበራሉ፡፡ በሙስሊሙ ላይ የሚደርሰው የትኛውም ነገር አያሳስባቸውም፡፡ ምክንያቱም የሙስሊሙ ስቃይ ከነሱ ቡድናዊ አላማና ፍላጎት በላይ አይደለምና፡፡ ምክንያቱም የነሱን ጥፉ አስተሳሰብ ያልተከተለ ሁሉ ሙስሊም አይደለምና፡፡ “ግን ለዚህ ያበቃቸው ምንድን ነው?” ስንል ወደ መሰረታዊ ነጥብ ያሸጋግረናል፡፡ አሕባሾች በተለያዩ ዐቂዳ ነክ ርእሶች ጉዳይ ከአህስሱንናህ አስተምህሮት ያፈነገጠ እሳቤዎች አሏቸው፡፡ ለማያውቃቸው መረጃ፣ ለዘነጋቸው ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት
1. አሕባሾች በሙታን እርዳታ መጠየቅን፣ ሙታንን መለመንን፣ ባጭሩ የቀብር አምልኮን እምነታቸው ያደረጉ እጅግ የዘቀጡ ሱፍዮች ናቸው፡፡ ሺርካቸውን በተወሱልና በምልጃ ስም ይሸፋፍኑታል እንጂ ሙታኖችን መለመናቸውን አያስተባብሉም፡፡ ይሄ ደግሞ አይን ያወጣ ሺርክ ነው፡፡ ጌታችን በቁርኣን እንዲህ ይላል፡- (እነዚያም ከርሱ ሌላ የምትጠሯቸው የተምር ፍሬ ሽፋን እንኳን አይኖራቸውም፡፡ ብትጠሯቸው ጥሪያችሁን አይሰሙም፡፡ ቢሰሙም አይመልሱላችሁም፡፡ በቂያማ ቀንም ማጋራታችሁን ይክዳሉ፡፡ እንደ ውስጠ-አዋቂው ማንም አይነግርህም፡፡) [ፋጢር ፡15]
2. አሕባሾች ዘንድ ቁርኣን በሐቂቃ የአላህ ንግግር አይደለም፡፡ የሸይኻቸውን ኪታብ ማየት ትችላላችሁ፡፡ [ኢዝሃሩልዐቂደቲስሱኒያ፡ 58-60] ቁርኣን የአላህ ንግግር ለመሆኑ ግን በአህሉስሱናህ መካከል ምንም አይነት ውዝግብ የለም፡፡
3. በኢማን ጉዳይ አቋማቸው የአፈንጋጮቹ የሙርጂአዎች አቋም ነው፡፡ የአህሉስሱናህ አቋም ኢማን በልብም፣ በምላስም በተግባርም ሲሆን የአሕባሾቹ ቁንጮ አልሀረሪ ግን አቋሙ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ [አድደሊሉልቀዊም፡ 9-10፣ ቡግየቱጣሊብ፡ 51] አሕባሾች በሀሰት የሻፊዒያ መዝሀብ ተከታዮች እንደሆኑ ቢያላዝኑም አልኢማም አሻፊዒ ግን እንዲህ ይላሉ፡- “ከሶሐቦች፣ ከታቢዒዮችና ከነሱም በኋላ ያሉትና ያገኘናቸው ሁሉ የተስማሙበት ኢማን ንግግርም፣ ተግባርም፣ ኒያም (እሳቤም) እንደሆነ ነው፡፡ ከሶስቱ አንዱም በሌላኛው (ከቀሪው ጋር) እንጂ አያብቃቃም፡፡”
4. አሕባሾች የአላህን ከፍጡራን በላይ መሆን ያስተባብላሉ፡፡ በዚህ የሚያምንንም ባደባባይ እንደ ከሃዲ ይቆጥራሉ፡፡ አላህ ከፍጡራኑ በላይ እንደሆነ ከአንድ ሺህ በላይ ማስረጃ የመጣበት ከመሆኑም በላይ ንፁህ ህሊናም የሚያፀድቀው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ህፃናት እንኳን በንፁህ ፊጥራቸው የሚያምኑበት ነው፡፡ ከበርካታ ማስረጃዎች አንዱን ብንጠቅስ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አታምኑኝምን? እኔ በሰማይ ላለው ታማኝ ሆኜ ሳለ?” ይላሉ፡፡ ይሄ የሶሐቦችም፣ የታቢዒችም፣ የአትባዑትታቢዒዮችም፣ የአራቱ መዝሀቦች ኢማሞችም የሚያምኑበት እምነት ሲሆን አሕባሾች ግን ከመቀጣጠል ባለፈ ከዚህ የተለየ ከዚያ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም በምርጥነቱ ከመሰከሩለት ትውልድ አንድም ግልፅ ተቃውሞ ማቅረብ አይችሉም፡፡
5. አሕባሾች በርካታ የአላህ ሲፋዎችን ላለመቀበል ሲሉ ግልፅ መልእክት ያላቸው የቁርኣንና የሐዲሥ ማስረጃዎችን መልእክታቸውን ይጠመዝዛሉ፡፡ ለዚህም ምርኩዛቸው አደገኛው የዒልመልከላም አካሄድ ሲሆን ሸይኻቸው ዐብዱላህ አልሀረሪ ዒልመልካልምን የሚያወግዙ ዑለማዎችን “እብዶች ናቸው” ሲል ገልፁዋቸዋል፡፡ [ኢዝሃሩልዐቂደቲስሱኒያህ፡ 22] ይህ ማለት ደግሞ እነ አልኢማም ማሊክ፣ አሽሻፊዒይ፣ አሕመድ፣ አቡ ዩሱፍ እና ሌሎችም ዒልመልከላምን ያወገዙ በርካታ ዑለማዎች “እብዶች” ናቸው ማለት ነው አሕባሾች ዘንድ፣ ነዑዙ ቢላህ ሚነልኹዝላን፡፡
6. አሕባሾች አንዳንድ የነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ሶሐቦችን በመጥፎ ይወነጅላሉ፡፡ ለዚህም የሸይኻቸው ዐብዱላህ አልሀረሪ የተወሰኑ ሶሐቦችን በመጥፎ ቃላት የወረፈበት ዋቢ መሆን ይችላል፡፡ ሶሐቦችን ማንቋሸሽ የጠማማዎቹ የራፊዷዎች (የሺዐዎች) አቋም ነው፡፡ በዚህ ጥፋት ላይ ኢኽዋኒው ሰይድ ቁጥብም ይጋራቸዋል፡፡ ነገር ግን የሁለቱም ተከታዮች ጭፍንኖች ከመሆናቸው የተነሳ ከሶሐባ ይልቅ ለመሪዎቻቸው ነው የሚሟገቱት፡፡ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን “ሶሐቦቼን የተሳደበ የአላህ፣ የመላእክት እና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁንበት” ይላሉ፡፡
7. አሕባሾች ታላላቅ የሱና ዑለማዎችን ያከፍራሉ፣ ያንቋሽሻሉ፡፡ ከጥንቶቹ ኢብኑ ኹዘይማ፣ ኢብኑ ተይሚያህ፣ አዝዘሀቢ፣ ኢብኑልቀይዪም፣ አለፍ ብሎ ሙሐመድ ኢብኑ ዐብዲልወሃብ፣ ከቅርቦቹም እነ አልባኒን፣ ኢብኑ ባዝን ኢብኑ ዑሠይሚንን እና ሌሎችንም የሱና ዑለማዎች በሚሰቀጥጡ ቃላት ይወርፏቸዋል፡፡ ከፊሎቹን በግልፅ ሲያከፍሩ ከፊሎቹን ደግሞ በሚያስጠሉ ቃላት ይሰድቧቸዋል፡፡
8. አሕባሾች እጅግ አፈንጋጭና አነጋጋሪ በሆኑ ፈትዋዎች የተካኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌም ሸይኻቸው አልሀረሪ ከባንክ ሪባ መብላትን ፈቅዷል፡፡ የሴት ልጅ ከቤተሰቦቿ ጋር ያላት ሀፍረተ ገላ መጠኑ ከእንብርት እስከ ጉልበት ነው ይላል፡፡ [ቡግየቱ ጧሊብ፡290(አዲሱ እትም ላይ ግን አውጥቶታል] ከፍናፍንት ጋር በረመዳን በቀን ግንኙነት መፈፀም ፆም አያበላሽም ይላል፡፡ [ቡግየቱ ጧሊብ፡ 192(አዲሱ እትም፡243)] ዐብደላህ አልሀረሪ፡ ሒጃብ የሰውነትን ቀለምና ፀጉርን ከሸፈነ ይበቃል ብሏል፡፡ [ቡግየቱ ጧሊብ፡ 104(አዲሱ እትም፡137) ]፤ ተማሪው ኒዛር ሐለቢ፡ ሴቶች ወጣቶቻችን በጂንስ ይዋባሉ፤ ምክኒያቱም እኛ ሰውነትን መሸፈንም ፋሺን መከተልም በተመሳሳይ ጊዜ እናስገኛለን ብሏል፡፡ [አልሙስሊሙን ጋዜጣ ቁጥር፡407፣ 1992] የአሕባሽ ሴቶች እንዲህ አይነት ከስሜታቸው ጋር የሚሄዱ አፈንጋጭ ፈትዋዎችን በመከተል ጠባብ ሱሪዎችን በመልበስ ተወጣጥረው አደባባይ መውጣት ከያዙ ሰንበትበት ብለዋል፡፡
9. ዐብደላህ አልሀረሪ፡ ሴት ሽቶ ተቀብታ መውጣቷን ፈቅዷል፡፡ [ቡግየቱ ጧሊብ፡ 351(አዲሱ እትም፡446)]
10. ሸይኻቸው ዐብዱላህ አልሀረሪ፡ “አላህ በአብዛሃኛው ነገር ላይ እንጂ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ አይደለም” ይላል፡፡ [ኢዝሃሩልዐቂደቲስሱኒያ፡ 40]
11. ሸይኻቸው ዐብዱላህ አልሀረሪ ወደ ካፊሮች ሃገር የተሰደደ ሰው ለራሱ ከሰጋ መስቀል ማሰር ይችላል ይላል፡፡ [አድደሊሉልቀዊም፡ 155] የካፊርን ገንዘብ በቁማር ወይም በሌላም መንገድ መውሰድን ይፈቅዳል፡፡ [ሶሪሑልበያን፡ 133]
አሕባሽ ጠማማ አንጃ እንደሆነ በርካታ ታላላቅ ዑለማዎች በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ እራሳቸው አሕባሾቹም ይህን በብልሹ ተግባራቸው አስመስክረዋል፡፡
ወንድም እህቶች፡ ዛሬም ድረስ ብዙ የአሕባሽን ጥመት የማይለይ ወገን ስላለ “ሼር” በማድረግ የበኩላችንን እንወጣ፡፡ አቅማችን በፈቀደም ከራሳችን ጀምሮ ቤተሰባችን ሌላውም ወገናችን ከእውቀት በመነጨ መልኩ የአሕበሽን ብልሹ አቂዳ እንዲረዳ የአቅማችንን እንጣር፡፡
በተጨማሪም ይህን ሊንክ በመክፈት ያድምጡ፡፡ ከሸይኽ ዐብዱልዐዚዝ አርረይዪስ አሕባሾችን በተመለከተ ጥሩ መረጃ ያገኛሉ፡፡
http://islamancient.com/play.php?catsmktba=101836