ከረመዳን በተሻለ መልኩ ለመጠቀም
ሁሌም ቢሆን ስለ ዲናችን ወቅቱን የጠበቀ ትኩረት ሊኖረን ይገባል። ዒድ ሲመጣ ስለዒድ፣ በሐጅ ወቅት ስለሐጅ፣ ሰርግ ስናስብ ስለ ሰርግ፣ ልጅ ሊወለድ ሲል ስለ ዐቂቃና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ወዘተ ብናተኩርና ብንማማር በዚያ ጉዳይ የበለጠ እንድንጠቀም ያደርገናል።
ይሄው ረመዳን ከፊታችን ነው። ስለ ረመዳን ምን አነበብን? ምን አደመጥን? በምን ተዘጋጀን? ምን አስተማርን? ምንስ ሀሳብ ተለዋወጥን? የዘንድሮውን ረመዳን ከእስከዛሬው በተለየ ለመጠቀም ወይም ለመጥቀም አስበናል? ለዚህስ ምን ቀይሰናል? እስካሁን ካላሰብንበት ባስቸኳይ እንነሳ!! ምን እናድርግ ከተባለ በኔ በኩል እነዚህን ጠቅሻለሁ። ሀሳቦቹ እንደመጣልኝ የተከተቡ እንጂ በስርኣት የተሰደሩ አይደሉም። እናንተም የምታስቡትን በመጨመር እንተዋወስ★ አቅሙ ካለን ስለ ረመዳን ሰዎችን ለማስተማር እናቅድ። በረመዳን ብዙ አዳዲስ ሰዎች ወደ መስጂድ እንደሚመጡ በማሰብ መሰረታዊ ትምህርቶችንም የእቅዳችን አካል እናድርግ። ከቻልን አስተማሪ የሌላቸው ዘንድ ሄዶ ማስተማር። ወይም ማስተማር የሚችሉ ሰዎችን በማገዝ እናንቀሳቅስ። ሶላት የማይሰግዱ ወገኖቻችን ማንቃት። ሰዎች በቁርኣን፣ በዒባዳ እንጂ በዘፈን፣ በመንዙማና ነሺዳ እንዳይዘናጉ ማሳሰብ።
★ ወንጀል ላይ ካለን ከወዲሁ በሚገባ መመለስ። መዳከም ካለ በተሻለ መንፈስ መነሳሳት።
★ ደካሞችን በፆሙ የሚያግዝ ነገር አቅማችን የፈቀደውን ከወዲሁ እናድርግ ወይም ለማድረግ እንዘጋጅ። በተለይ ቤተሰቦቻችንና ጎረቤቶቻችን ምን እንደሚጎድላቸው አይቶ የተቻለውን ማገዝ።
★ ቁርኣን ለማያገኙ መስጂዶች – በተለይም በገጠር ላሉ – ገዝቶ መስጠት። አስቡት በረመዳን ያ ሁሉ ሰው ሲቀራበት የሚገኘውን አጅር። እንዲሁም ለገጠር መስጂዶች በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ መብራት፣ የድምፅ ማጉያዎችን፣ ጥሩ የኹጥባና ሌሎችም ኪታቦችን፣ ማፍጠሪያ የሚሆን ተምር፣ … ማበርከት።
★ ረመዳንን በሰላማዊ ልቦና እንፆመው ዘንድ ውስጣችንን ከቂም ማፅዳት። ሰዎችን ከልብ ይቅር ማለት። ለትዳር አጋር፣ ለጎረቤት፣ ለጓደኞች ባጠቃላይ ለሰዎች ይበልጥ መልካም፣ ፊተ በሻሻና ቸር መሆን።
★ በረመዳን ልንሰራቸው የምናስባቸውን መልካም ነገሮች ከወዲሁ ማሰብ። ሰዎችን ማስፈጠር (በተለይም ችግረኞችን፣ እስረኞችን)፣ ሰዎች ላይ ብድር ካለንና ከቻልን ይቅር ማለት፣ ወይም እንዲከፍሉ ማገዝ፣ በሽተኞችን መጠየቅ፣ ቤተሰብ፣ ጎረቤትና ወዳጆችን መዘየር፣ …
★ መኪና ካለን የተቸገሩን ሊፍት በመስጠት መተባበር።
★ ለረመዳን ጊዜያችንን የሚሻሙ ነገሮችን ቀድሞ ማጠናቀቅ፣ መቀነስ ወይም ለቀጣይ ወር ማሻገር። አመታዊ ፈቃድ ማመቻቸት የሚችል ሰራተኛ ማመቻቸት።
★ ለራሳችን፣ ለሞቱ፣ በመከራ ለሚማቅቁ፣ ከዲን ለራቁ ወገኖች ከወትሮው በተለየ አጥብቆ ዱዓ ማድረግ፣
★ ረመዳንን በሚገባ እንዳንጠቀም ሊያደርጉን ይችላሉ ብለን የምንሰጋቸውን ነገሮች ለመቆጣጠር መወሰን።
★ ኢኽላሳችን ላይ ይበልጥ ማተኮር። ለሰዎች ምሳሌ ሆኖ ያነሳሳል የሚል ግምት ካላሳደርን በስተቀር ኸይር ስራዎቻችንን በምስጢር ማድረግ።
★ ቁርኣንን በብዛት ለመቅራት መዘጋጀት፣ የማይችል ካለ ማድመጥ፣ አልፎም ለመማር ቁርጠኛ ሆኖ መነሳት።
★ ፆምን በተሻለ መልኩ እንዲያፈጥሩ የምትደክሙ ሴቶች በሚያፈጥረው ሰው አጅር ለማግኘት ኒያ ማድረግ። ሆኖም ግን የተጋነነ የምግብ ዝግጅት ውስጥ አለመጠመድ።
★ መስጂድ ማፅዳት፣ የተበላሹ መገልገያዎቹን መጠገን ወይም ማስጠገን፣
★ ባጭሩ ረመዳን የስልጠና ወር ነው። ከረመዳን በሁዋላም የሚዘልቅ የተሻለ ስብእና ለመጎናፀፍ ስልጠናውን በሚገባ መካፈል።
0 Comments