ተውሒድ የሌለው ልብ ካለ አይቆጠርም። ልብህን በተውሂድ አለስልስ፣ በተውሒድ አርጥብ። ጠቢቡ ኢብኑልቀይዪም ረሒመሁላህ " ቀልብ ከአላህ ተውሂድ ከተራቆተ ይደርቃል ይላሉ። [አስራሩስሶላት፡ 1/3] አዎ! የሺርክ አረም ተውሒድን አኮስሶ፣ አመንምኖ ህልውናውን ያጠፋል። እናም ተውሒዳችንን በሚገባ እንረዳ፣ እንከባከብ፣ እንከታተል። ያለበለዚያ ወዴት እየቀረብን እንደሆነ እናስተውል! " ከተውሒድና ከሱናህ የራቀ ሁሉ ለሺርክ፣ ለቢድዐና ለቅጥፈት የቀረበ ነውና፡።" " ሃይማኖት የልብ ምግብ ነው።" [ አልኢቅቲዳእ፡ 291፣ 281] የዚህ ምግብ ዋናው ክፍል ደግሞ ተውሒድ ነው። ይህን የሚያውቀው ግን ያጣጣመው ነው። " የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም " ነገር። አዎ ወደው አይደለም ቀደምቶቻችን " ንጉሶችና የንጉሳን ልጆች ያለንበትን ፀጋና ተድላ ቢያውቁ ኖሮ ሊነጥቁን ጦር ይሰብቁብን ነበር" ያሉት። [አልዋቢሉስሶይዪብ፡ 110] አምልኮትን ለአላህ የሚያጠራው ሙእሚን ምቹ ኑሮን ከሚኖሩት ነው። ከነዚያ ህሊናቸው ከተረጋጋው፣ ደረታቸው ፈታ ካለው፣ ልባቸው ከሚደሰተው። ይቺ ነች ጀነት! ከዋናው ጀነት በፊት ያለች ዱንያዊ ጀነት።
[አልጀዋቡልካፊ፡465]
( ከኢብኑ ሙነወር ተውሒድ የሁለት ሀገር የስኬት ቁልፍ
ከሚለው መፀሀፉ መግቢያ ላይ ከፃፈው የተወሰደ)
Taju Nasir