Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ሰኔ 30

Jun 26, 2013
 
ሰኔ 30
بسم الله الرحمن الرحيم
الحمد لله رب العالمين، وصلى الله وسلم على رسوله
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
በልጅነታችን ትምህርት ቤት ተማሪ እያለን ብዙ ትውስታዎች ነበሩን፡፡ ከዚህም አንዱ ሰኔ 30 የሚባለው ቀን፤ ለተማሪዎች ሁሉ ታላቅ ቀን ነበር፡፡ አመቱን ሙሉ የለፋ ተማሪ የልፋቱን ውጤት የሚያይበት ቀን ነው፤ ብሎም የተጣሉ ሰዎች ሰኔ 30 እንገናኝ እያሉ አመቱን ሙሉ ሲፎክሩ የነበረበት ቀን ነው፡፡
የመጀመሪያው ሰኔ 30 ሰርተፊኬት የሚሰጥበት ሲሆን፤ ጎበዞች ስማቸው ከነአባቶቻቸው እየተጠራ ያ ሁሉ ሰው እያየ ሂሳባቸው ሲከፈላቸው፤ በጣም ተደስተው፤ ከዛም አልፈው በየዘመድ ቤቱ እና ጎረቤቱ ሁሉ፤ ውጤቲን እዩልኝ ሲባል ነበር ድሮ፡፡ ታድያ ይህን ቀን በልጅነቱ ትዝ ያለው ሰው፤ የሚከተለውን የአላህ አንቀፅ ቢያስታውስ ምን ይለዋል፡፡
فَأَمَّا مَنْ أُوتِىَ كِتَٰبَهُۥ بِيَمِينِهِۦ فَيَقُولُ هَآؤُمُ ٱقْرَءُوا۟ كِتَٰبِيَهْ
መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ (ለጓደኞቹ) «እንኩ፤ መጽሐፌን አንብቡ» ይላል፡፡
إِنِّى ظَنَنتُ أَنِّى مُلَٰقٍ حِسَابِيَهْ
«እኔ ምርመራየን የምገናኝ መኾኔን አረጋገጥኩ፤» (ተዘጋጀሁም ይላል)፡፡
فَهُوَ فِى عِيشَةٍ رَّاضِيَةٍ
እርሱም በተወደደች ኑሮ ውሰጥ ይኾናል፡፡
فِى جَنَّةٍ عَالِيَةٍ
በከፍተኛይቱ ገነት ውስጥ፡፡
قُطُوفُهَا دَانِيَةٌ
ፍሬዎችዋ ቅርቦች የኾኑ፡፡
كُلُوا۟ وَٱشْرَبُوا۟ هَنِيٓـًٔۢا بِمَآ أَسْلَفْتُمْ فِى ٱلْأَيَّامِ ٱلْخَالِيَةِ
በአለፉት ቀናት ውስጥ (በምድረ ዓለም) ባስቀደማችሁት ምክንያት ብሉ፤ ጠጡም፤ (ይባላሉ)፡፡
የአለማቱ ጌታ ሽልማት ይህን ይመስላል፡፡ ዱንያ ላይ ሰርተፊኬቴን እዩልኝ፤ መንጃፍቃድ አለፍኩ፤ ዲቪ ደረሰኝ እንዳልተባለ፤ ደስታውን እንዲካፈሉለት፤ ምንኛ ያማረ ፀጋ ነው፤ ፍጡራን ሁሉ በተሰበሰቡበት ኪታቡ በቀኝ እጁ ተሰጥቶት የሚከተለውን ሲል
فَأَمَّا مَنْ أُوتِىَ كِتَٰبَهُۥ بِيَمِينِهِۦ فَيَقُولُ هَآؤُمُ ٱقْرَءُوا۟ كِتَٰبِيَهْ
መጽሐፉን በቀኙ የተሰጠ ሰውማ (ለጓደኞቹ) «እንኩ፤ መጽሐፌን አንብቡ» ይላል፡፡

ብዙ ሰው አሁንም ድረስ ነጋዴዎች ጋር ሲኬድ ሰኔ 30 የምታስጨንቃቸው ቀን ናት፤ አመቱን ሙሉ የሰራሁበትን ምን እጠየቅ ይሆን፡፡ ታድያ አላህ ነገ ለሰራነው፤ ለተጠቃቀምነው ወቅት ሁሉ እነደሚይቅስ አውቀናል???
ከላይ የጠቀስኩት ሌላ ነገር ነበር፤ ትምህርት ቤት ውስጥ የተጣሉ ሰዎች አመቱን ሙሉ ሰኔ 30 ይድረስ እያሉ ይዝቱ ነበር፡፡ አላህ ደግሞ ስለ እራሱ ሲናገር
مَٰلِكِ يَوْمِ ٱلدِّينِ
የፍርዱ ቀን ባለቤት ለኾነው፡፡
እውነትም ፍርዱ የማይጓደለው ጌታ አደለም በሰዎች መሃል ያለውን፤ በእንስሳት መሃል የነበረውን በደል ፍርድ ይሰጥበታል፡፡ ታድያ ዛሪውን ሰውን ከመበደል መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ የበደሉትን ሰው ይቅርታ መጠየቅ መፍትሄ ነው፤ ነገ ይቅርታ ማለት የማይጠቅምበት ቀን ከመምጣቱ በፊት፡፡
የአላህ ባሪያዎች ሆይ! ሁሉ ነገር ዱንያ ላይ የምናየው ጠፊ ነው፤ አንዳን ምሳሌዎች አኸይራን በግልፅ የሚያስታውሱ ሆኖ እናገኛቸዋለን፤ ታዲያ ለምን ዘንጊዎች እንሆናለን፡፡
አላህ የፍርዱ ቀን ኪታባቸው በቀኝ እጃቸው ከሚሰጣቸው ያድርገን፡፡ ከዚህም በላይ ደስታ የለም፤ አላህ ከሀዘን ጠብቆ፤ የደስታ ባለቤት ያድርገን፡፡
የአላህ ሰላት እና ሰላም በነብያት በደምደሚያ፤ በአበል ቃሲም ላይ ይሁን፡፡ አላሁመ አሚን፡፡