Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

የሶሓቦች ደረጃ በኢስላም

የሶሓቦች ደረጃ በኢስላም
የሶሓባ ትውልድ ከመልእክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ህዝቦች ባጠቃላይ ምርጡ ትውልድ ነው።ይህ ትውልድ ገንዘቡን፤ጊዜውን ፤ቤተሰቡን አልፎ ተርፎም ህይወቱን ጨምር ለኢስላም የሰጠ ትውልድ ነው። ይህ ትውልድ ቁርኣንና ሱናን ማለትም ኢስላምን ከመልእክተኛው (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ተቀብሎ ወደኛ እንዲደርስ ያደረገ ታላቅ ባለውለታችን ነው። ይህ ትውልድ የኢስላምን ብርሃን ለሌሎች ለማድረስ ቤት ንብረቱን ፤ትውልድ ቀየውን ጥሎ በተለያዩ የዐለም ክፍሎች ተበታትኖ ህይወቱን የፈፀመ ባለድንቅ ስብእና ትውልድ ነው። … ስለሆነም ይህ ትውልድ ኢስላምን ለሚወድ ፤ለሚያከብር፤ ለሚከተል ሁሉ ታላቅ ባለ ውለታው ነውና ማንነቱን ሊያውቅ ክብሩን ሊጠብቅ ይገባል።
ሶሐቦች በቁርኣን
1. “ከሙሃጂሮቹና ከአንሷሮቹም ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ ቀዳሚዎች እነዚያም እነሱን በመልካም የተከተሏቸው አላህ ከነሱ ወዷል፤እነሱም ከሱ ወደዋል፤ በስሮቻቸውም ወንዞች የሚፈሱባቸውን ጀነቶች በውስጣቸው ዘለአለም ነዋሪዎች ሲሆኑ ለነርሱ አዘጋጅቶላቸዋል፣ ይህ ታላቅ ስኬት ነው” (አተውባ፡100)
2. “ለነዚያ የአላህን ችሮታና ውዴታውን የሚፈልጉ አላህንና መልእክተኛውንም የሚረዱ ሆነው ከአገሮቻቸውና ከገንዘቦቻቸው ለተባረሩት ሙሃጂሮች ድሆች (ይሰጣል)፤ እነዚያ እነሱ እውነተኞቹ ናቸው፡፡ እነዚያም ከበፊታቸው አገሪቱን መኖሪያ ያደረጉት እምነትንም የለመዱት ወደነርሱ የተሰደዱትን ሰዎች ይወዳሉ፤ (ሙሀጂሮቹ) ከተሰጡትም ነገር በልቦቻቸው ውስጥ ቅሬታን አያገኙም፡፡ በነሱ ላይ ችግር ቢኖርባቸውም በነፍሶቻቸው ላይ ሌላውን ይመርጣሉ፡፡ የነፍሱንም ንፍገት የሚጠበቅ ሰው እነዚያ እነሱ ምኞታቸውን የሚያገኙ ናቸው” (ሐሽር፡8-9)
3. «(የ)ምራቻ (መንገድ) ከተገለጠለት በኋላ መልዕክተኛውን የሚፃረርና ከሙእሚኖች መንገድ ሌላ የሚከተል የመረጠውን (ጥመት) እናሸክመዋለን! (ወደ ዞረበት እናዞረዋለን)፤ ጀሀነምም እናስገባዋለን፤ ከመመለሻነቷ (አንፃር)ም የከፋች ሆነች!» (ኒሳእ፡115)

በመጨረሻው አንቀፅ ውስጥ “ሙእሚኖች” በሚለው ውስጥ ቀዳሚዎቹ ሶሓቦች ናቸው፡፡ ይህም በበርካታ ዐሊሞች ተገልጧል፡፡ መንገዳቸው የግድ መንገዳችን መሆን እንዳለበት እየጠቆመን ነው፡፡
ሶሓቦች በሐዲሥ
ነብዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሓቦችን በተመለከተ ከተናገሩት በጥቂቱ
1. “ከትውልድ ሁሉ በላጩ የኔ ትውልድ ነው ፤ ከዚያም ቀጥሎ የሚመጣው፤ ከዚያም ቀጥሎ የሚመጣው” (ቡኻሪና ሙስሊም)
2. “ሶሃቦቼን የተሳደበ የአላህ፤የመላእክቱና የሰዎች ሁሉ እርግማን በሱ ላይ ይሁን” (ሲልሲለቱሶሒሐ፡5/446)
3. “አንሷሮችን ሙዕሚን እንጂ አይወዳቸውም:: ሙናፊቅ እንጂ አይጠላቸውም:: የወደዳቸውን አላህ ይወደዋል የጠላቸውን አላህ ይጠላዋል” (አልባኒ “ሶሒሕ” ብለውታል)
4. “ሰሃቦቼን አትሳደቡ ነፍሴ በጁ በሆነችው እምላለሁ! ከናንተ አንዳችሁ የኡሁድን ተራራ የሚያክል ወርቅ ቢለግስ ከነሱ በግድፍ(ሁለት እፍኝ) የለገስውን አያክልም፡፡ እረ እፍኙንም!” (ቡኻሪና ሙስሊም)
ሶሓቦችን በሚመለከት ከቀደምቶች አባባል በጥቂቱ
1. የነብዩን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሰሃቦችን አትሳደቡ በርግጠኝነት እነሱ ከነብዩ ጋር ያሳለፏት አንዲት ሰዓት ከናንተ (ታቢዒዮች) የእድሜ ልክ ስራ ይበልጣል።(አብደላህ ኢብኑ ዑመር) ሱብሐነላህ!!! ከኛስ
2. የነቢዩን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሐቦች የሚሳደብ ሰው በኢስላም ውስጥ ምንም ድርሻ የለውም (ኢማሙ ማሊክ)
3. አንድ ሰው ከነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሓቦች የየትኛውንም ክብር ሲያጎድፍ ካየኸው አፈንጋጭ እንደሆነ እወቅ (አቡ ዙርዓ)
4. እራስህን በሱና ላይ አፅና፤ ሰዎቹ(ሶሓቦቹ) ከቆሙበት ቁም፤እነሱ ያሉትን በል፤ እነሱ ከታቀቡት ታቀብ፤ የመልካም ቀደምቶችህን መንገድ ተከተል፤ ለነሱ የበቃቸው ይበቃሃልና! (አውዛዒ)
ስለዚህ ራሱን መካሪ የሆነ ሶሓቦችን ያክብር፡፡ ያለበት ዲናዊ መንገድ ሰላማዊ መሆኑን ማረጋገጥ የፈለገ የሶሓቦችን መንገድ ይምረጥ!! የራሱን ክብር መጠበቅ የፈለገ እራሱን በሶሐቦች መካከል ፈራጅ/ዳኛ አያድርግ፡፡ ጌታችን ሆይ እነዚያን በኢማን የቀደሙንን ማራቸው፣ ከልባችንም ውስጥ በነሱ ላይ ቂም እንዳይኖር አንተ አግዘን፡፡ እነሱንም በመልካም የምንከተል አድርገን፡፡ ኣሚን፡፡