Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ጥያቄ፦ ሴትን መንካት ወዱእ ያበላሻልን?


Taju Nasir's photo.
ጥያቄ፦ ሴትን መንካት ወዱእ ያበላሻልን?
መልስ፦ ሴትን መንካት ወዱእ አያበላሽም ፈሳሽ ነገር ከብልቱ ካልወጣ በስተቀር። የዚህም ማስረጃ ነቢዩ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ሚስታቸውን ስመው ወዱእ ሳያደርጉ መስገዳቸው ነው። ለማበላሸቱ ግልፅ ማስረጃ እስከሌለ ድረስ በመሰረቱ አያበላሽም። ሰውየው ሸሪዓዊ ማስረጃ በሚያመላክተው መሰረት ወዱእን አደረገ። አንድ በሸሪዓዊ ማስረጃ የፀናን ነገር ደግሞ ያለሸሪዓዊ ማስረጃ ውድቅ ማድረግ አይቻልም።
አላህ በቁርአን ውስጥ <<ሴቶችን ብትነኩ>> ብሏል ከተባለ መልሱ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳሉት በአንቀጹ ውስጥ <<ሴቶችን ብትነኩ>> ማለት ግብረሥጋ ግንኙነት ካደረጋችሁ ማለት ነው። አንቀጹ ያደረገው ክፍፍልም ማስረጃ ይሆነናል። 
አንቀጹ ጠሃራን በመሠረታዊና በአማራጭ መክፈሉ፣ ጠሃራን በትልቁና በትንሹ መክፈሉ እና ለትልቁና ለትንሹ ጠሀራ ሰበብ የሚሆኑትን መክፈሉ ለዚህ በማስረጃነት ይጠቅማል፦ አላህ <<እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሰላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን እስከ ክርኖቻቸውሁ እጠቡ። ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ። እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች (እጠቡ)፤...>>ይላል። (አል-ማዒዳ 5፥6)
ይህ ጠሀራ በውሃ የሚደረግ ሲሆን መሠረታዊና ትንሹ (ወዱእ) ነው። ከዚያም ቀጥሎ << ጀናባ ከሆናችሁ ጠሃራ አድርጉ (ገላችሁን ታጠቡ) ይላል። ይህ ደግሞ በውሃ የሚደረግ ጠሃራ ሲሆን መሠረታዊና ትልቁ (የጀናባ ትጥበት) ነው። ከዚያም በመቀጠል <<... በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትሆኑም ወይም ከናንተ አንዳችሁ ከአይነምድር ቢመጣ ወይም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ ንፁህን የምድር ገፅ አስቡ (ተይሙም አድርጉ)...>> ይላል። <<ተይሙም አድርጉ>> የሚለው አማራጭ ነው (መሠረታዊ አይደለም)። <<ከናንተ አንዳችሁ ከአይነምድር ቢመጣ>> ማለቱ ደግሞ የትንሹን ጠሃራ (የወዱእ) ሰበብ ማብራራቱ ነው። ሴቶችን ከነካካችሁ የሚለውን አንቀፅ በእጅ ብቻ መንካት ነው የሚል ትርጉም ከሰጠነው በአንቀጹ ውስጥ አላህ ለትንሹ ጠሃራ ሁለት ሰበቦችን ጠቅሶ ለትልቁ ጠሀራ ግን አንድም ሰበብ ሳይጠቅስ ተወ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከቁርአን አገላለፅ <<በላጋ>> ጋር ይፃረራል። ስለዚህም << ሴቶችን ከነካካችሁ>> የሚለው ግብረ ስጋ ግንኙነት ካደረጋችሁ ማለት ነው ። እናም አንቀፁ ጠሃራን የሚያስወጅቡ ሁለት ሰበቦችን አካቷል ማለት ነው። ትልቁን ሰበብና ትንሹን ሰበብ። አራቱ የአካል ክፍሎች የሚታጠቡበት ትንሹን ጠሃራና ሁሉም የሰውነት ክፍል የሚታጠብበት ትልቁን ጠሃራ አካቷል። አማራጭ የሆነው ጠሃራ ማለትም ተየሙም ሁለት አካላቶችን (ፊትና እጅን) ብቻ ነው የሚመለከተው። በተይሙም ጊዜ ትልቁ ጠሃራና ትንሹ ጠሃራ እኩል ይሆናሉ።
በዚህም መሠረት ሚዛን የሚደፋው አስተያየት ሴትን መንካት በምንም አይነት ወዱእ አያበላሽም የሚለው ነው። በስሜትም ሆነ ያለ ስሜት ሴትን መንካት ወዱእ አያበላሽም። ፈሳሽ ከወጣ እንጂ። የወጣው ፈሳሽ መኒይ ከሆነ መታጠብ ግዴታ ይሆንበታል። መዚይ ከሆነ ግን መዚዩ የነካውን ክፍል አጥቦ ወዱእ ማድረግ ግዴታ ይሆናል።
(በሸይኽ መሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን ረሒመሁላህ)