Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ይህ ሀዲስ የሚያመለክተው እምነት እንደሚጨምርና እንደሚቀንስ ነው።

ይህ ሀዲስ የሚያመለክተው እምነት እንደሚጨምርና እንደሚቀንስ ነው። ይህ የአህሉ ሱና አቋም ከሙርጅዓዎች አቋም ተቃራኒ ነው። ሙርጅዓዎች «እምነት አይጨምርም አይቀንስም። እምነት አንድ ነው፤ ተግባር ከእምነት አይቆጠርም። እምነት ከቀልብ ውስጥ ያለ ነገር ብቻ ነው» ይላሉ። ከመረጃ አንፃር ስናየው፣ ይህ አባባል ያለ ምንም ጥርጥር ስህተት ነው። ከዚህ በተቃራኒው የኸዋሪጅ ቡድን «ከሽርክ ውጭ ያለም ቢሆን፣ ከባድ ወንጀልን የሰራ ሰው ከሀዲ ነው» ይላሉ። ኢማን እንዳለው ሙሉ በሙሉ አይቀበሉም። ሙርጅዓዎች በበኩላቸው «የፈለገውን ወንጀል ቢሰራ ሙሉ እምነት አለው፤ ከኢስላም ጎዳና አይወጣም» ይላሉ። ይህ በነርሱ መካከል ያለ ተቃርኖ ነው። ትክክለኛው የሀቅ ባለቤቶች አቋም ግን «ኢማን ይጨምራል፤ ይቀንሳል» የሚል ነው።
«ሙዕተዚላ» የሚባለው ፊርቃ (ቡድን) በበኩሉ በአዲስ መልክ ከሁለቱም ቡድኖች የተለየ ሀሳብ ይዞ ብቅ ብላል። «ታላላቅ ወንጀሎችን የሚሰሩ ሰዎችን ‘ሙዕሚን’ አንላቸውም፣ ‘ከሀዲም’ አንላቸውም። በሁለቱ መካከል ያለ ነው» ይላሉ። ሙዕተዚላዎችን ከኸዋሪጆች ጋር የሚያስማማቸው ነጥብ «አንድ ሰው በወንጀል ላይ ሆኖ ወደ አላህ በተውበት ሳይመለስ ከሞተ፣በእሳት ውስጥ ዘውታሪ ነው» የሚል አቋም መያዛቸው ነው። «በምድራዊ ህይወት ግን በሙእሚንና በካፊር መካከል ያለ ቦታ ነው ያለው» ይላሉ። ይህ አመለካከት ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው የሚያስበው ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-
«እርሱ ያ የፈጠራችሁ ነው። ከናንተም ከሃዲ አለ፤ ከናንተም አማኝ አለ። አላህም በምትሰሩት ሁሉ ተመልካች ነው።» (ተጋቡን፣ 2)