Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

«ቀደር» ማለት «አላህ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ የሚሆነውን ........

«ቀደር» ማለት «አላህ እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ የሚሆነውን ወይም የሚከሰተውን ነገር በሙሉ ወስኖታል» ማለት ነው። ፍጥረተ አለሙ ከመፈጠሩ በፊት እስከ ትንሳኤ ቀን ድረስ የሚሆነውና የሚከሰተው ሁሉ በለውሀል መህፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። አላህ እንዲህ ይላል፡-
«እኛ ሁሉን ነገር በልክ ፈጠርነው።» (ቀመር፣ 49)
ነገሮች ሁሉ እንዲሁ በአጋጣሚና በዘፈቀደ የሚፈጸሙ አይደሉም፣ በአላህ እቅድና ውሳኔ እንጂ። አላህ በቁርዓኑ እንዲህ ይላል፡-
«በምድርም፣ በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም፤ ሳንፈጥራት በፊት በመፅሀፍ የተመዘገበች ብትሆን እንጂ። ይህ በአላህ ላይ ገር ነው።» (ሀዲድ፣ 22)
በቀደር ማመን አራት ነገሮችን ያካትታል፡-
1ኛ - በአላህ ፍፁማዊ እውቀት ማመን፤
o አላህ በእውቀቱ ሁሉንም ነገር አካቧል።
2ኛ - በለውሀል መህፉዝ (በተጠበቀው ሰሌዳ) ማመን፤
o እስከ ትንሳኤ ድረስ የሚከናወነውን ነገር ሁሉ አላህ በለውሀል መህፉዝ መዝግቦታል።
3ኛ - በአላህ ፍቃድ(መሽአ) እና ኢራዳ ማመን፤
o እርሱ የሻው ይሆናል፤ እርሱ ያልሻው አይሆንም።
4ኛ - አላህ ነገሮችን ሁሉ የፈጠረ መሆኑን ማመን፤
o ከእርሱ ጋር ሌላ ፈጣሪ የለም።
አላህ እንዲህ ይላል፡-
«አላህ የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው።እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ አስተናባሪ ነው»(ዙመር፣62)
በአላህ ውሳኔ ያመነ ሰው ፍፁም የሆነ የህሊና እረፍት ያገኛል። በፀፀት እሳት፣ በቁጭት ረመጥ አይቃጠልም። ባለፈው ነገር እንደማያዝን ሁሉ፣ ባገኘው ነገር ከልክ በላይ አይደሰትም። በተቃራኒው በቀዷና በቀደር ያላመነ ሰው ባጣው ነገር ይበሳጫል፤ ንዴትና ብስጭቱን ገሀድ የሚያወጡ አስቀያሚ ነገሮችን ይናገራል ወይም ይፈጽማል። ሆኖም አንድ ግለሰብ በብስጭት ጦፎ፣ ፊቱን ቢቧጭር፣ ልብሱን ቢቀድና እየዬውን ቢያቀልጥ ያለፈውን ነገር መመለስ አይችልም፤ ትርፉ ንዴትና ኪሳራ ብቻ ነው። ከአላህ ዘንድ ምንዳን አጥቶ ለውርደትና ለኪሳራ የተጋለጠ ይሆናል። በቀዷና በቀደር የማያምን ሰው ስቃይ ባለፈው ነገር መቆጨትና መበሳጨት ብቻ አያበቃም። ወደ ፊት ስለሚመጣው ነገር ልቡ በፍርሀትና በስጋት እየተናወጠ ይፈተናል። ማንኛውንም ነገር ስለሚፈራ ጅሀድ ወጥቶ መታገል አይችልም።
عن أبي العباس عبدالله بن عباس رضي الله عنهما قال كنت خلف النبي صلى الله عليه وسلم يوما فقال لي يا غلام إني أعلمك كلمات احفظ الله يحفظك احفظ الله تجده تجاهك إذا سألت فاسأل الله وإذا استعنت فاستعن بالله واعلم أن الأمة لو اجتمعت على أن ينفعوك بشيء لم ينفعوك إلا بشيء قد كتبه الله لك إن اجتمعوا على أن يضروك بشيء لم يضروك إلا بشيء قد كتبه الله عليك رفعت الأقلام وجفت الصحف رواه الترمذي وقال حديث حسن صحيح
አብዱላህ ብን አባስ ባስተላለፉት ሀዲስ እንዲህ ብለዋል፤ አንድ ቀን ከነብያችን ኋላ ነበርኩኝ ‘አንተ ልጅ ሆይ!’ እኔ ተከታዮቹን ቃላት አስተምርሀለሁ አድምጥ አሉ፤‹‹ከጠየቅክ አላህን ብቻ ጠይቅ፤ መታገዝ ከፈለግህ በአላህ ብቻ ታገዝ፤ ሰዎች ሁሉ ተሰባስበው ‘እንጥቀምህ’ ቢሉ፣ አላህ ለአንተ የጻፈልህን ካልሆነ በስተቀር ምንም ሊጠቅሙህ እንደማይችሉ እወቅ። ሰዎች ሁሉ ተሰባስበው አንተን ‘እንጉዳ’ ቢሉ፣ አላህ እንድትጎዳ የጻፈው ነገር እስከሌለ ድረስ ሊጎዱህ አይችሉም። ብዕሩ ተነስቷል፤ ቀለሙም ደርቋል።›› ቲርሚዚይ ዘግበውታል
በቀዷና በቀደር ማመን ጥንካሬን ያላብሳል፤ የህሊና ሰላምን ያጎናፅፋል። እምነትና ተወኩል (በአላህ መመካት) እንዲኖር ያደርጋል። በቀደር የሚያምን ሙስሊም ባጋጠመው መጥፎ ነገር፣ የቁጭት እርምጃ ሊወስድ ይቅርና አይበሳጭም። ለዚህም ነው ነብያችንه ሙስሊም ከአቡሁረይራ በዘገቡት ሀዲስ እንዲህ ብለዋል፤
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللهِ ه: " الْمُؤْمِنُ الْقَوِيُّ خَيْرٌ وَأَحَبُّ إِلَى اللهِ مِنَ الْمُؤْمِنِ الضَّعِيفِ وَفِي كُلٍّ خَيْرٌ، احْرِصْ عَلَى مَا يَنْفَعُكَ وَاسْتَعِنْ بِاللهِ وَلَا تَعْجَزْ، وَإِنْ أَصَابَكَ شَرٌّ فَلَا تَقُلْ لَوْ أَنِّي فَعَلْتُ كَذَا وَكَذَا قُلْ قَدَّرَ اللهُ وَمَا شَاءَ اللهُ فَعَلَ، فَإِنَّ لَوْ تَفْتَحُ عَمَلَ الشَّيْطَانِ " رَوَاهُ مُسْلِمٌ
«በሚጠቅምህ ነገር ላይ ጉጉት ይኑርህ፤ በአላህ ታገዝ፤ ደካማና ስልቹ አትሁን፤ አንድ ነገር ባጋጠመህ ጊዜ ‘ይህን ነገር እንዲህ ባደርገው ኖሮ…’ አትበል። ነገር ግን ‘አላህ የወሰነው ሆነ፤ አላህ የፈለገውን ይሰራል’ በል። ‘እንዲህ ቢሆን ኖሮ’ የሚለው ንግግር ለሰይጣን ስራ በር ይከፍታል» ሙስሊም ዘግበዉታል
አንተ የአሰብከው ጉዳይ እንዲሳካልህ ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ከተገበርክ በኋላ፣ ባልከው መንገድ ሳይፈጸም ቢቀር፣ አላህ ያልሻው (ያልፈቀደው) ነገር ሊፈጸም እንደማይችል መገንዘብ አለብህ። እንዲፈጸምልህ የፈለከውን ጉዳይ በተመለከተ፣ ለአንተ መልካሙ ነገር ጉዳዩ አለመፈጸሙ ሊሆን ይችላል።
አንድ ሙእሚን ህይወቱን መምራት ያለበት ማንኛውንም ጉዳይ ወደ አላህ በማስጠጋትና በአላህ ብቻ በመመካት መሆን አለበት። ይህ ማለት ግን ከእሱ የሚጠበቅበትን ተግባር መስራት የለበትም ማለት አይደለም። አንድ ነገር ያለምክንያት እንደማይገኝ ማመን አለበት። ለአለመው ነገር መሳካት ምክንያት (ሰበብ) የሆኑ ነገሮችን ለግብር ይውጣ ያህል መስራት ተገቢ አይደለም። በቁርጠኝነት መስራት አለበት። ሆኖም ግን ምክንያት በሆኑ ነገሮች ላይ ብቻ መደገፍና ሙሉ በሙሉ እምነት መጣል ተገቢ አይደለም። ከእሱ የሚጠበቀው ለአለመው ጉዳይ መሳካት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን እያስገኘ በአላህም መመካት ነው።
በአላህ ቀዷና ቀደር እምነት ውስጥ ሌላው የሚካተተው ጉዳይ፣ ባሮች ስራቸውን በፍላጎታቸው መርጠው የሚተገብሩ መሆናቸው ነው። ‪#‎ጀብርያ‬$ የሚባሉ ቡድኖች «የሰው ልጆች ተግባራቸውን የሚፈጽሙት አላህ አሰገድዷቸው ነው» ይላሉ። ይህ በጣም የተሳሳተ አመለካከት ነው። የሰው ልጅ አለማዊ ህይወቱን የሚመራው አስቦና አቅዶ በራሱ ፍላጎት እንደ ሆነ ሁሉ፣ አምልኮታዊ ተግባሩን ማለትም ሶላቱን የሚሰግደው፣ ጾሙን የሚፆመው፣ ዘካውን የሚሰጠውና ሌሎች ኢስላማዊ ተግባራትን የሚፈፅመው በራሱ ፍላጎት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። ከዚህ በተቃራኒ አንድ ሙስሊም ባይሰግድ፣ ባይፆም ወይም የወንጀል ተግባር (ስርቆት፣ ዚና፣ ወዘተ…) ቢፈፅም በራሱ ፍላጎትና ምርጫ ነው የፈፀመው፤ ማንም ያስገደደው አካል የለም።
የሰው ልጅ ራሱ መርጦ የሰራው ተግባር ውጤቱ መልካም ከሆነ ይመነዳል፤ መጥፎ ከሆነም ይቀጣል። «ሁሉም የስራውን ያገኛል» የሚባለውም ለዚህ ነው። ሆኖም ወንጀል የሰራው ሰው በሀይል የተገደደ፣ ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ህፃን፣ አእምሮው ጤነኛ ያልሆነ ወይም በእንቅልፍ ላይ ያለ ሰው ከሆነ በሰራው ሀጢያት ተጠያቂ አይደለም።
‪#‎ሙእተዚላዎች‬$ በበኩላቸው ከጀብርያዎች በተቃራኒ «የአላህ ቀዷና ቀደር የሚባል ነገር የለም፤ የሰው ልጅ ስራውን የሚፈጥረው እራሱ ነው» ይላሉ።
አህሉሱና ያላቸው አቋም መካከለኛ ነው። የሰው ልጆች እቅድንና ምክንያትን መሰረት አድርገው ስራቸውን ይሰራሉ። ነገር ግን ስራው ስኬት ሊኖረው የሚችለው የአላህ ፈቃድ ሲኖር ብቻ ነው።