Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ወዳጅ አያምፅም



ወዳጅ አያምፅም
ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ሰላምና እዝነት በታላቁ ነብይ በሙሀመድ በባልደረቦቻቸው እና በቤተሰቦቻቻው ሁሉ ላይ ይሁን፡፡አላህ የሰው ልጆችን ከማሀይምነት ፅልመት ወደ ኢማን ብርሀን ያመጡ የላካቸውን የነብያት መደምደሚያ ከሰዎች ሁሉ በላጭ የሆኑትን ነብያችንን ከነፍሳችን ከልጆቻችን ከወላጆቻችን እና ከሰዎች ሁሉ አስበልጠን መውደድ እንዳለብን አላህ በሱረቱል ተውባ ቁጥር 24 ነግሮናል፡፡
        በአባቶቻችሁ እና ወንዶች ልጆቻችሁ፣ ወንድሞቻችሁም፣ሚስቶቻችሁም፣ዘመዶቻችሁም የሠበሰባችኋቸው ሀብቶችም፣መክሰሯን የምትፈሯት ንግድም፣የምትወዷቸው መኖሪያዎችም በእናንተ ዘንድ ከአላህ እና ከመልዕክተኛው በእርሱ መንገድም ከመታገል ይበልጥ የተወደዱ እንደሆኑ አላህ ትዕዛዙን እስከሚያመጣ ድረስ ተጠባበቁ በላቸው አላህም አመፀኞች ህዝቦችን አይመራም፡፡ መልዕክተኛውም ይህን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ ‹‹ከወላጁ፣ ከልጁ፣ ከሰው ሁሉ ይበልጥ እርሱ ዘንድ ተወዳጅ እስካልሆንኩ ድረስ አንዳችሁም አላመነም›› ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
እውነተኛ ውዴታ በተግባር ይገለፃል
አላህና መልዕክተኛውን መውደድ የሚገለፀው የነብዩን ፈለግ (ሱንና) በመውደድ እና በመከተል፣ ትዕዛዛቸውን በመተግበር፣ ከከለከሉት በመራቅ ነው፡፡ የነብዩ ወዳጅ ሁልጊዜ ለእሳቸው ታዛዥ ነው አያምፅም፣ መመሪያን አይጥስም፣ ያልታዘዘውን አይሰራም፡፡ አላህ ለእንዲህ ይላል
‹‹ አላህን የምትወዱ እንደሆናችሁ ተከተሉኝ፤ አላህ ይወዳችኋልና፤ ሀጢያቶቻችሁን ለእናንተ ይምራልና አላህም መሀሪ አዛኝ ነው በላቸው›› አል ኢምራን 31
ነብዩን የተከተለ ሰው የሰሩትን ይሰራል የተውትንም ይተዋል አል ኢማም ሙስሊም በዘገቡት ሀዲስ ረሱል  እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ የእርሱን ፈለግ የሚይዙና ትዕዛዙን የሚከተሉ ረዳቶች እና ጓደኞቸ ከህዝቦቹ አድርጎለት እንጂ አላህ ነብይን አልላከም፤ ከዚያም ከእነሱ በኋላ የማይሰሩትን የሚናገሩ ያልታዘዙትን የሚሰሩ ይተካሉ ፡፡ (እነኚህን) በእጁ የታገላቸው ሙዕሚን ነው፤ በምላሱም የታገላቸው ሙዕሚን ነው፤ ከዚህ በኋላ የሰናፍጭ ፍሬ ያህል እንኳ ኢማን የለም፡፡››
ያልታዘዙትን የሚሰሩትን አስመልክቶ (የታገላቸው ሙዕሚን ነው) ማለታቸው የእሳቸው ትዕዛዝ የሌለበትን ነገር ምንም እንኳ ጥሩ መስሎ ቢታየን ልንሰራው እንደማይገባ እንረዳለን፡፡
ቡኻሪና ሙስሊም ከሙዕሚኖች እናት አኢሻ በዘገቡት ሀዲስ ነብዩ እንዲህ ብለዋል
‹‹ትዕዛዛችን የሌለበትን ስራ የሰራ (ስራው) ተመላሽ ነው››
ነብያችን  የተሰጣቸውን መልዕክት በሚገባ አድርሰዋል አማናቸውንም ተወጥተዋል
የተከበሩት የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ ለህዝቦቹ የሚያውቀውን መልካም ነገር መጠቆም እና ከሚያውቅላቸው ክፉ ነገር ማስጠንቀቅ ግዴታ ቢሆንበት እንጂ ከእኔ በፊት (አንድም) ነብይ አልተላከም›› ሙስሊም በቁጥር 1844 ከአብዱላህ ኢብኑ ዓምር ዘግበውታል
ወደ አላህ ውዴታ የሚያቃርቡንን የአምልኮ ተግባራት በሙሉ በጌታቸው መመሪያ መሰረት ቅንጣት ሳያጓድሉ በአግባቡ አስተላልፈዋል፡፡ አማናቸውንም ተወጥተዋል፡፡ ይህንን እውነታ በመሠናበቻ ሀጃቸው ላይ ሠሀቦችን አስመስክረዋቸዋል እኛም ምሉዕ በሆነ መልኩ የአላህን መልዕክት እንዳደረሱ ሀላፊነታቸውንም እንደተወጡ እንመሰክራለን፡፡ የአላህ ሰላምና እዝነት በእርሳቸው ላይ ይሁን፡፡
አላህ ይህንን ዲን ምሉዕ አድርጎታል
ጭማሪን አይቀበልም
እውቁና ታላቁ ዓሊም አል-ኢማም ማሊክ ኢብኑ አነስ የሚከተለውን ተናግረዋል  (አንድ ሠው በኢሳለም ውስጥ አዲስ ፈጠራን አምጥቶ የፈጠረው መልካም መስሎ ከታየው ነብዩ መልዕክታቸውን አጉድለዋል ብሎ ጠርጥሯል ምክንያቱም አላህ እንዲህ ይላል ‹‹ዛሬ ሀይማኖታችሁን ለእናንተ ሞላሁላችሁ ፀጋዬንም በእናንተ ላይ ፈፀምኩ ለእናንተም ኢስላምን በሀይማኖትነት ወደድኩ›› አል ማዒዳህ ቁጥር 5 ያኔ ዲን ያልነበረ ዛሬ ዲን አይሆንም)
       
      ይህ ኢማም ማሊክ የጠቀሱት አንቀፅ የወረደው በ 10ኛው አመተ ሒጅራ በዙልሒጃ ወር በጁምዓ እለት ነብዩ ዓረፋ በቆሙበት ነው፡፡ ይህም የመሠናበቻ ሐጅ (ሐጀቱል ወዳዕ) ነበረ አል ቡኻሪ ቁጥር 45 እንዲሁም ሙስሊም ቁጥር 30/73 ይመልከቱ
        አንዳንድ ሰሀቦች ከዚህ አንቀፅ በኋላ የቁርዓን አንቀፅ አልወረደም ይላሉ፡፡ ቢወርድም በጣም ጥቂት ነው:: የረሱል ምርጥ ባልደረቦች (ሰሀቦች) እና የእነሱ ተተኪዎች (ታቢዕዮች) ዲን ምሉዕ መሆኑን ተረድተው ነብያዊ ፈለግን በመከተላቸው ዲናቸውን ከአዳዲስ ልጣፊዎች ጠብቀው በማስተላለፍ አደራቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ዑማህ ምርጥ አበው ትውልዶች ጊዜ በራቀ ቁጥር ሰዎች ሰወስለዲናቸው ያላቸው ግንዛቤ እየተዳከመ በመምጣቱ ብዙ አዳዲስ የቢድዓ ተግባሮች መፈፀም ጀመሩ፡፡

        አላህ ያላዘዘውን መልዕክተኛው ያልተገበሩትንና መደንገጉን ያልፈቀዱትን ነገር በአምልኮ ተግባርነት መደንገግ ለማንም የምይፈቀድ ግልፅ ጥመት ነው፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ አላህ ከሀይማኖች በእርሱ ያልፈቀደውን ለእነርሱ የደነገጉ (ከአላህ ጋር) ተጋሪች አሏቸውን?! ›› አል ሹራ ቁ 21
        ረሱልም እንዲህ ብለዋል ‹‹በዚህ በጉዳያችን (በዲናችን) ከእርሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ (ስራው) ተመላሽ ነው፡፡››አል ቡኻሪይ 2550 እንዲሁም ሙስሊም በቁጥር 1718 ከአዒሻ ዘግበውታል   
ነብያችን በንግግራቸው መግቢያ ላይ የሚከተለውን ይሉ እንደነበር ተዘግቧል ‹‹ከንግግር ሁሉ የተሻለው የአላህ መፅሀፍ ነው ከመመሪያ ሁሉ በላጩ የሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ)  መመሪያ ነው፡፡ የነገሮች ሁሉ መጥፎ አዳዲስ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁሉም የፈጠራ ተግባር ጥመት ነው›› ሙስሊም በቁጥር 867 ከጃቢ ኢብኑ አብዲሎህ ዘግበውታል
        ይህንኑ ጉዳይ አደራ ብለው ነበር ወደ አኼራ ያለፉት፡፡ እንዲህም አሉ ‹‹ የእኔንና ቅን የተመሩ የሆኑ ምትኮቼን (ኹለፋእ) ፈለግ በመከተል ላይ አደራችሁን (ይህችን ፈለጌን) አጥብቃችሁ ያዟት! አደራችሁን! አዳዲስ ነገሮችን ተጠንቀቁ አዲስ ነገር ሁሉ ፈጠራ ነው ሁሉም ፈጠራ ደግሞ ጥመት ነው›› አህመድ (4/126-127) አቡዳውድ (4607) ቲርሚዚይ (2676) ኢብኑ ማጀህ (44) ከአርባድ ኢብኑ ማሪያህ የዘገቡት ሀዲስ

ሁሉም የቢድዓ ተግባር ጥመት ነው
ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የተላለፉልን ትዕዛዞች በመቀበል እና ሱናቸውን በመተግበር ልንብቃቃ ይገባል፡፡ ኢብኑ መስዑድ እንዳሉት (ተከተሉ! አዲስ ነገር አታምጡ ሱንና በቂያችሁ ነውና) ሁዘይፋ ኢብኑ የማን እንዲህ ይላሉ (ማንኛውም የመልዕክተኛው ሰሀቦች ባልሰሩት የኢባዳ ተግባር አምልኮን አትፈፅሙ! የመጀመሪያዎቹ ለመጨረሻዎቹ ይህንን ክፍተት አልተውም) አቡ ዳውድ እና ሌሎችም ዘግበውታል
አላህ የሚያቃርቡን እና የእርሱን ውዴታ የሚያስገኙልን የመልካም ስራ በሮች ብዙ ከመሆናቸው ጋር አዳዲስ የፅድቅ መንገዶችን ለመቅደድ መሯሯጥ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ እያንዳንዱ ሰው አላህ ከደነገጋቸው እና መልዕክተኛው ከወደዷቸው የመልካም ስራ በሮች ምን ያህሉን አንኳክቻለሁ ብሎ ራሱን ቢጠይቅ ጉድለቱን ያስተውላል፡፡ 
ዐብደላህ ኢብኑ ዑመር እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ሁሉም ቢድዓ ጥመት ነው ሰዎች መልካም አድርገው ቢያዩት እንኳ!›› ኢብኑ በጣህ አለለካኢይና ሌሎችም በትክክለኛ ሰነድ ዘግበውታል
የአላህ ዲን ሞልቷል ነብዩም መልዕክታቸውን አድርሰዋል ብሎ ያመነ ሰው በፍፁም ቢድዓ የሆነን ነገር ፈጥሮ ጥሩ ነው አይልም! ፈጠራ እስከሆነ ጥሩ ሊሆን አይችልም፡፡ እስቲ ይህንን ክስተት እናስተዉል፡፡
አንድ ቀን አቡ ሙሳአል-አሽዓሪ ወደ ዓብዱላህ ኢብኑ መስኡድ ቤት ይመጡና እንዲህ ይለዋቸዋል፡- ‹አሁን መስጂድ ውስጥ የሚነቀፍ ነገር ተመለከትኩ።› ‹ምንድነው›? አሉ ኢብኑ መስዑድ።‹በሕይወት ካለህታየዋለህ! ሰዎች መስጊድ ውስጥ ሆነው ክብ ሰርተው ተቀምጠው ሶላትን ይጠባበቃሉ፤ ከተሰበሰቡት አንዱ በእጁ ጠጠር ይዞ፡-አንድ መቶ ጊዜ ተክቢራ አድርጉ፣ አንድ መቶ ተስቢህ፣ አንድ መቶ ታህሊል እያለ ያዝዛቸዋል።እነሱም መቶ፣ መቶ ጊዜ ይላሉ።› ኢብኑ መስዑድም ‹ምን አልካቸው ታዲያ?› ብለዉ ይጠይቋቸዋል።‹ምንም አላልኩም፣ የአንተን አስተያየት በመጠበቅ!› ኢብኑ ‹ታዲያ ለምን ወንጀላቸውን እንዲቆጥሩ በመንገር፣ በጎ ተግባራቸውን መስዑድም ግን አላህ ዘንድ እንደማያጡት ዋስ አትሆናቸውም?› ከዚያም ወደ መስጊድ ‹ምንድነው መሥራት የያዛችሁት? ገቡ። ወደተሰበሰቡት ሰዎች በመምጣትም ወንጀላችሁን ቁጠሩ፣ ጥሩ ሥራችሁን ግን አላህ ዘንድ እንደማታጡት ቃል እገባላችኋለሁ።የሙሀመድ (ሠ.ዐ.ወ) ኡመቶች! ለመጥፋት ምን አስቸኮላችሁ።የነቢዩ (ሠ.ዐ.ወ) ሰሀቦች ሞልተዋል፤ የነቢዩም (ሠ.ዐ.ወ) ልብስ (ገና) አላለቀም፤ ዕቃቸው እነኳ አልተሰበረም።ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ! እናንተ ከነቢዩ (ሠ.ዐ.ወ) መንገድ የበለጠ የተመራችሁ ናችሁ ወይም የጥመት በር ከፋች ናችሁ?!› ‹አቡ አብዱራህማን እኛ እኮ ጥሩ አስበን እንጂ ሌላ አሏቸው። ሰዎቹም አይደለም›‹ጥሩ እያሰቡ ግብ የማይመቱ ስንቶች አሉ?! ነቢዩ (ሠ.ዐ.ወ) አሉ። እንደነገሩን፡- (ሰዎች ይመጣሉ፣ ቁርዓን ይቀራሉ፤ ግን ከጉሮሯቸው አይወርድም!) ምናልባት ብዙዎቹ ከእናንተ ሳይሆኑ አይቀሩም።…› ከዚያ ጥለዋቸው ሄዱ። (
አድዳሪሚይና ሌሎች ዘግበውታል)

መውሊድን ማክበር በቁርዓንና በሐዲስ ሚዛን ሲለካ
1.   የመውሊድ በዓል በቁርዓንና በሐዲስ መሠረት አለው ብሎ መድከም ከንቱ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡መውሊድ በነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ የሕይወት ዘመን ፈፅሞ እንዳልነበረ ዑላማዎች ሁሉ ይስማሙበታል፡፡ እንዲያውም መውሊድን የሚያከብሩት ሳይቀሩ ይህንን እውነታ አያስተባብሎም፡፡ ይህ አይነቱ የመልእክተኛዉ ፈለግ የሌለበት ተግባር ደግሞ ወደ አላህ መቃረቢያ መንገድ መሆን እንደማይችል በዚህ ፅሁፍ መግቢያ ላይ በበርካታ ቁርአናዊና ሀዲሳዊ አስረጆች ተብራርቷል፡፡ በዓሉ መከበር የጀመረዉ ከአራተኛዉ የሒጅራ ክፍለ ዘመን በኋላ ራሳቸዉን “ፋጢሚዬች” ብለው ይጠሩ በነበሩ የኡበይድ አልቀዳህ ዘሮች ነው በግብፅ ነው፡፡ መዉሊድ እንደማይፈቀድ ለማስረዳት ከዚህ የተሻለ ግልጽ አስረጅ የለም። መልካም ተግባር ቢሆን የነብዩ ባልደረቦች ቀድመዉን በተገበሩት ነበር። የአላህ መልዕክተኛ እንዲህ ብለዋል ‹‹በዚህ በጉዳያችን (በዲናችን) ከእርሱ ያልሆነን ነገር የፈጠረ (ስራው) ተመላሽ ነው፡፡›› አል ቡኻሪይ 2550 እንዲሁም ሙስሊም በቁጥር 1718 ከአዒሻ ዘግበውታል
2.    ዲናዊ በዓሎች ውስን ናቸው። አምልኮ እንደመሆንቸው ድንጋጌያቸውንም የምናገኘው ከዲናዊ የመረጃ ምንጮች ብቻ ነው። ከተደነገጉልን ዒዶች ውጭ ሌላ ዒዶችን መፈብረክ በፍፁም አያስፈገንም፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ ባወሩት ሀዲስ ነቡዩ /ሰ.ዐ.ወ/ እንዲህ ብለዋል፡፡ ወደ መዲና በመዲና በመጣሁ ጊዜ የመዲና ሰዎች በጃሂሊያ ዘመን የሚዝናኑባቸው ሁለት በዓላት ነበሯቸው። አላህም እነሱን በተሻሉ ሁለት ዒዶች ቀየረላቸው፡፡ የፊጥር በዓል /ዒደልፊጥር/ እንዲሁም የዕርድ እለት /ዒደልዓድሀ/” አቡዳውድ ዘግበውታል አል-ኢማም አል-አልባኒም ሰሂህ ብለውታል፡፡
የሁለቱ ዒዶች አከባበር በረሱል ሱና ዉስጥ የዒድ ሰላት እና ተክቢራ እንዲሁም ሌሎች ዒባዳዎች አፈፃፀም በዝርዝር ተብራርቶ እናገኛለን። ስለ መዉሊድ አከባበር ግን ከነአካቴው ምንም አልተገለፀም።
3.   የነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ትክክለኛ የልደት ቀን በውል አይታወቅም በሐዲስ የተገለፀው ሰኞ እለት መወለዳቸው ብቻ ነው፡፡ በታሪክ ‹‹የዝሆኑ ዓመት›› ተብሎ በተሰየመው ዓመት መወለዳቸውን የሚጠቁም መረጃም አለ። የታሪክ ምሁራን በረቢዕ አል-አወል እንደሆነ ቢናገሩም የትኛው ቀን እንደሆነ ግን በመካከላቸው ከባድ ውዝግብ አለ፡ 
ለምሣሌ፡- አቡ ማዕሸረ ሲንዲ በረቢዕ 2 እንደተወለዱ ይናገራሉ ኢብኑ ኢስሃቅ በረቢዕ 12 ዋቂዲ በረቢዕ 10 ሱለይማን አል መንሱርሪ በረቢዕ 9 መወለዳቸውን ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ግን ያረፉት በረቢዕ 12 መሆኑን በርካታ የታሪክ ዘጋቢዎች ተስማምተውበታል፡፡ ከዚህም በመነሳት በእርግጥ ሰዎች እያከበሩ ያሉት የተወለዱበትን ቀን ላይሆን ይችላል ቀኑ ግን ያረፉበት /የሞቱበት/ እለት ነው፡፡
4.   በዙዎች መዉሊድ የሚያከብርበትን ሰበብ ሲንገሩ “ክርስቲያንች የነብዩ ዒሳን የዉልደት ቀን ያከበራሉ እኛስ ከእነርሱ በምን እናንሳለን?” ይላሉ። የአላህ መልዕክተኛ /ሰ.ዐ.ወ/ ከ1400 ዓመታት በፊት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ከእናንተ በፊት የነበሩትን /ሕዝቦች/ ፈለግ ስንዝር በስንዝር ክንድ በክንድ ትከተላለችሁ የፍልፈል /ወከሎ/ ጉድጓድ ቢገቡ እንኳን /ተከትላችሁ/ ትገባላችሁ” ሰሀቦችም እንዲህ አሉ፡- “ይሁዶችንና ክርስቲያኖችን? ረሱልም ”ታዲያ/ ማንን?” አሉ፡፡ አል ቡኽሪ /3269/ ሙስሊም /6852/ ዘግበውታል
በሌላም ሀዲስ እንዲህ ብለዋል፡፡ “ከህዝቦች ጋር የተመሳሰለ ከእነሱ ነው”  አህመድ /5114/ - አቡዳውድ / 4033/ ከኢብኑ ዑመር ዘግበውታል የክርስቲያኖች የቀን አቆጣጠር ከኢሳ/ዐ.ሰ/ ልደት ይጀምራል ልደታቸውንም ያከብራሉ። የራሱል /ሰ.ዐ.ወ/ እውነተኛ ወዳጅ የሆኑት ቅን ሰሃቦች ግን በታላቁ ኸሊፋ በዑመ ኢብኑል መሪነት የቀን አቆጣጠራቸውን የጀመሩት በሂጅራ ክስተት ላይ እንጂ በነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ውልደት ያልነበረው ላለመመሳሰል ነው። ልብ በሉ!!


መውሊድን የጀመሩት ዑበይዲዮች እና ማንነታቸው
 ምንም እንኳን ራሳቸውን ወደ ፋጢማ ቢያስጠጉም፤ የአላህን ትዕዛዛት በመጣስ፣ በአመፀኛነት፣ ድንበር በማለፍ፣ ዲንን በማዋረድ፣ ዑለማዎችን በመጨፍጨፍ፣ መጤዉን የባጢኒያን አመለካከት በማስፋፋት፣ አንዲሁም የዲነል ኢስላም ፋና እንዲጠፋ የቻሉትን ሁሉ እኩይ ምግባር በመፈፀም የተወቁ ነበሩ፡፡ የኩፍር ንግግሮችን በመናገራቸው፣ አላህንና ነቢያቶችን በግልፅ በመሳደባቸው፣ ክልክሎችን ሀላል በማድረጋቸው፣ ወዘተ…  በዘመናቸው የኖሩ  ታላላቅ የኢስላም ሊቃውንት ከኢስላም ምንም ድርሻ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡አላህ ይዘንለትና ሰላሀዲን አል-አዩቢይ ከመስቀላዊያን እጅ ቁድስን ካስለቀቀ በኋላ እነዚህ ዑበይዲዮች ላይ በመዝመት አሸንፏቸው ሙስሊሙን ህብረተሰብ እፎይ አሰኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ነቢዩ /ሰ.ዐ.ወ/ እና ኹለፋዎቻቸው እንዲሁም ታላላቅ የነብዩ ባልደረቦችና ታብዕዮች እንዳልፈፀሙት የታወቀ ነው። መውሊድ በነዚህ ዑበይዲዮች በ­­­ ----------- ዓመተ ሂጅራ እንደተጀመረ የታሪክ ሊቃውንት እና ዑለማዎች አረጋግጠዋል፡፡ ለመዉሊድ የሚከራከሩ ሰዎች አልመሊክ ሙዘፈር የተባለ ደግ ሰዉ ነው የጀመረው በማለት የሚያቀርቡት ሙግትም መሰረት የለዉም። ስለአጀማመሩ ይህን ያልነው ታሪክን በታሪክነቱ ከማስፈር አንፃር እንጂ ይህን ቢድዓ የፈጠሩት እነሱም ሆኑ ሌሎች፣ ደጎችም ሆኑ ክፉዎች ፍርዱ አንድ ነው፡፡ ዒባዳ በቁርአንና በመልእክተኛው አስተምህሮት ወይም በሰሀቦች ስምመነት ካልፀደረ ውግዝ ይሆናል፡፡ ሰዎችን በሀቅ ሚዛን እንመዝናለን እንጂ የእነርሱን ስራ መረጃ በማድረግ ሀቅን በሰዎች ልንለካ አይገባም።

መውሊድ የቢድዓ በዓል ብቻ ነውን?
        የመውሊድ አከባበር ሥርዓትን በተመለከተ በርካታ እንከኖችና የተወገዙ ተግባራት ሲፈፀሙበት ይስተዋላል። የተፈቀደ በዓል ቢሆን እንኳ ወንድና ሴት በመቀላቀል በድቤ በጭብጨባና ጭፈራ ማክበር በኢስላም አይታወቅም፡፡ እንዲያውም ከቀድሞዎቹ የመካ ሙሽሪኮች አምልኮ ጋር የሚያመሳስል ውግዝ ተግባር ነው፡፡ ይህም በቁርዓን ተወስቷል “በቤቱ ዘንድም /በካዕባ/ ስግደታቸው ማፏጨትና ማጨብጨብ እንጂ ሌላ አልነበረም” ቅዱስ ቁርዓን 8-35 በመውሊድ በዓል በአብዛኛው የተለያዩ የሽርክ ተግባራት ይፈፀማሉ፡፡ እንዲሁም ይዘቱ እየሰፋና ከቀብር አምልኮ ጋርም እየተሳሰረ መጥቷል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የቀብር አምልኮዎች “መዉሊድ” በሚል ስያሜ የሚተገበሩ ናቸው።በሀገራችንም “የእነ ሸይኽ እገሌ መውሊድ” እየተባለ ወደተለያዩ ሩቅ ሥፍራዎች ጉዞዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ስለት፣ ዱዓዕ፣ እርድና የመሳሰሉ የኢባዳ ዘርፎች ሁሉ ለፍጡራን። በሱረቱልኑር ቁጥር 63 እንደተገለጸው የረሱልን ትዕዛዝ መጣስ ለከፋ ችግር ያጋልጣል። ለመሆኑ በእንዲህ ያሉ መዓቶች የተሞላ መድረክ በየትኛው ሚዛን ሲለካ ነው “ጥሩ ፈጠራ” የሚባለው?
        ብዙውን ጊዜ መውሊድ ሲከበር በሀሰት የተሞሉ ትምህርቶች፣ ተቀባይነት የሌላቸው መውዱዕ ሃዲሶች፣ ድንበር ማለፍ /ጉለው/ ያለባቸው ውዳሴዎች ይነበባሉ፡፡ “በችግራችን ጊዜ ከአንተ ሌላ ወደ ማን እንዞራለን?” የሚለውን የቡስይሪ ግጥም ዓይነት ድንበር ማለፍ /ጉሉውን/ በየመንዙማቸው ውስጥ ያካትታሉ ይህንን ነቡዩ /ሰ.ዐ.ወ/ ከተናገሩት ጋር ማነፃፀር ብቻ በቂ ነው “ነሳራዎች የመርየምን ልጅ ኢሳን ከልክ በላይ ከፍ እንዳደረጉት እኔንም ድንበር አልፋችሁ ከፍ እንዳታደርጉኝ። እኔ (የአላህ) ባርያው ነኝ ‹ባሪያዉና መልእክተኛው በሉ፡፡”

Post a Comment

0 Comments