Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ትዝታ ህይወት አይሆንም ቁጭት እንጂ! ካ.. ም.. ፓ.. ስ




ትዝታ ህይወት አይሆንም ቁጭት እንጂ!
#ካ.. #ም.. #ፓ.. #ስ

ያላችሁበትን ፀጋ እወቁት፡፡ ቁጭት ውስጣችሁን ሳያብከነክነው፣ ብሽቀት ሆዳችሁን ሳይሞላው አላህ በሰጣችሁ ኒዕማ ተጠቀሙበት! የዩኒቨርሲቲ እድል ደርሷችሁ የተቀላቀላችሁና አሁንም በመማር ላይ የምትገኙ እህት ወንድሞቼ ሁላችሁም አላህ በትልቅ ፀጋ ውስጥ እዳስቀመጣችሁ አትዘንጉ፡፡ የያዛችሁትን ወርቅ ከመዳብ አትቁጠሩት፡፡ ወላሂ! የግቢ ህይወትን የመሰለ ዳግም አታገኙትም፤ የትም ብትፈልጉት አይመለስም፡፡ ያላችሁ እድል አንድ ብቻ ነውና በምትቆዩባቸው አመታት መጠቀም ከቻላችሁ ተጣደፉ፤ ለከርሞ የምታስቀምጡት ነገር አይኑር፡፡

እንዳይመስላችሁ! ስትወጡ አንዱንም አታገኙትምና፡፡

ወንድም እህቶቼ ሁሉም ነገር ያለው ግቢ ነው፡፡ ቂርዓቱ፣ ዳእዋው፣ መጣጥፉ፣ ምክሮቹ፣ የእርስበርስ መረዳዳቱ፣ መደጋገፉ፣ መዋደዱ፣ አንድነቱ ስንቱን ቆጥሬ ልጨርሰው? ያሁሉ ያለው እናንተ ጋር ነው፡፡ አሁን በእጃችሁ ነው፤ ያው መዳፋችሁ ውስጥ፡፡ አያያዛችሁን አሳምሩ፡፡ አጠቃቀማችሁን ቀምሩ፡፡ አንዱም ሳይቀርባችሁ ውሰዱ፡፡ ከግቢ ስትወጡ የቱንም አታገኙትም፡፡ የለም! አታስቡት፡፡ ያሁሉ ነሻጣ የሚያበቃው እዛው ካምፓስ ነው፤ አላህ የሻለት ሲቀር፡፡ አላህ የሻለት ሲቀር! እወቁበት! ፊታችሁ ከተደቀነው የኸይር ማእድ ተቋደሱ፡፡ ሳትሰስቱ ዝገኑ፣ ሳትራሩ ቁረሱ እየመጠናችሁ ጉረሱ … ሁሉም የናንተ ነው፡፡

ቁርአን ያልቀራን እንቅራ፣ የቀራነው እንሀፍዝ፣ የቀራነውን እናስቀራ፡፡ ዲናችን ያለእውቀት አያራምደንምና በቂርአት እንበርታ፡፡ ኢኽዋኒ ኪታብ ይዘን ጎንበስ ብለን እንማር፡፡ የተማርነውን እንሞጥል፣ እንድገመው፣ እንደጋግመው፣ እንከርረው! ጊዜውም ጓድኛም ዳግም አይገኝም፣ ብትናፍቀው አይመጣም! በፍፁም! ወንድም እህቶቼ በአላዋቂነታችን ማንም ወደ ግራና ቀኝ የሚያውለበልበን ወላዋዮች እንዳንሆን ዛሬ እንጠንክር፡፡ እንማር እህቶቼ፡፡ እንቅራ ወንድሞቼ፤ ጥልቅ እውቀት የሚገኘው በቂርዓት ነው፡፡ አስተውሉ፤ ቂርዓትን የመሰለ ስር-ነቀል ለውጥ የምታመጡበት፣ ዘላቂ እውቀት የምትሸምቱበት፣ የህይወት ስንቃችሁን የምትቋጥሩበት፣ የአኸይራ መኖሪያችሁን የምትደለድሉበት ነገር የለም፡፡
ቅ… ሩ! አዎን ! የጌታችሁን ተውሂድ የነቢያችሁን ሱና የሶሀቦችን ጎዳና ከየትም አታገኙትም ከቂርአት ነው! ግድየላችሁም ጎንበስ በሉና ቅሩ፡፡ አቀርቅራችሁ ተማሩ፣ ቁጢጥ ብላችሁ ውሰዱ፤ ቀጥ ብላችሁ ትኖሩበታላችሁ፡፡
አብሽሩ! ዛሬ ሰአታችሁን መስዋእት አድርጉና በቂርአት ተሳተፉ፡፡ ጧት ማታ ውረዱበት፡፡ በመስጂድ፣ በዶርም፣ በስፔስ ዝመቱበት፡፡ የእውቀት አቁማዳችሁን ደህና አርጋችሁ ጠቅጥቁ፣ የዒልም ዳውላችሁን አሳምራችሁ ቀርቅቡ፡፡ ዛሬ የጫናችሁት ነገ በአኸይራ ትርፋማ ያረጋችኋል! በርቱ ተበራቱ! ወላሂ ይህን እድል ዳግም አታገኙትም! አሊያ እንደኛው ቀሪ ህይወታችሁን በመሸማቀቅ ታሳልፋላችሁ፡፡

ወንድም እህቶቼ ትዝታ ህይወት አይሆንም ቁጭት እንጂ፡፡
በዋለፈሰስ ያባከነው የግቢ ህይወታችን የእግር እሳት እንጂ አላወረሰንም፡፡ እናንተ ግን ግዜ አላችሁ ተጠቀሙበት፣ ጥቀሙበት! በእርግጥ ፀጋ ሲወገድ እንጂ አይታወቅም፡፡ እኛም አምልጦን እንጂ አልተረዳነውም፡፡ በኛ ይብቃ፤ እናነተ ግን ንቁ! አይናችሁን ግለጡ፡፡ እናንተ ናችሁ ትውልድ ተረካቢ፤ እናንተ ናችሁ የኡማው ጌጦች፤ እናንተ ናችሁ ተስፋዎቻችን፤ እናንተ ናችሁ የዲኑ ሞተር፤ ታዲያ የት ናችሁ? ይቅር ላውንች፣ ተዉት ኳሱን ይቅር ሱሱ፣ ጣለው እሱን! ትቅር ቺኳ አትፈይድም ጥቂት አንኳ! በወንጀል ውስጥ ከምንኖር እንቶብት እንያዝ ፈር! ይጠቅመናል ለአኸይራ ለሩቅ አገር ሁሉም ሟች ነው፤ አፈር ገቢ ጠባብ ቀብር! ያ አኺ! ተመለስ ወደ ዲንህ፤ ና ወደ ኢስላም! መጀመሪያ ኢስላምን እወቀው፣ በምን እንደሚያዝህ ተረዳ፣ ከምን እንደሚከለክልህ ተማር፡፡ ያወቅከውን ተግብር፡፡ ሸይጧን አከበደብን እንጂ ይህ ዲን እኮ ገር ነው፤ እጅግ ቀላል! አልሀምዱሊላህ ያ ሸባብ! አንተ እኮ ነህ ጌጣችን፡፡ አንተ እኮ ነህ የኃይላችን መዘውሩ፣ አንተ እኮ ነህ ኩራታችን፣ አንተ እኮ ነህ ብሌናችን! ታዲያ አንተ ካልተማርክ ማን ይማር? አንተ ካልቀራህ ማን ይቅራ? እንዴት ያላወቅከውን ዲን መርዳት ይቻልሀል? ወይስ ልትረሳው አስበሀል? አታደርገውም! ወሬው ይቅር እርሳው እሱን እንደ ጉም ነው አይጨበጥ አይያዘን በርታ ቅራ፣ ተማር ፍጠን! ሄዷል ግዜው አትሳነፍ፣ አትዛነፍ ሸምት ዒልሙን ውሰድ ሸክፍ አትግደርደር አትንከርፈፍ!

እህትዬ! ታወቆሻል ግን አንቺ እኮነሽ የትውልድ መሰረት፣ አንቺ አኮ ነሽ የነገዋ እናት፣ አንቺ እኮነሽ የመጀመሪያዋ ት/ርት ቤት፣ አንቺ እኮነሽ የኡማው ምንጭ፣ አንቺ እኮ ነሽ ንግስቲቷ፣ አንቁ አልማዝ ወርቅ ፈርጣችን!! ታዲያ የት ነሽ እቱ? አንቺ ካልሰመርሽ ማን ሊሰምር? አንቺ ካልተቃናሽ ማን ሊመራ? አንቺ ካልበረታሽ ማን ሊቆም ለዲኑ? የት ትተሸን ትሄጀለሽ? ሁላችንም እኮ ያንቺ ውጤት ነን! ንቂ እንጂ! ቆፍጠን በይ ቆራጥ ሁኚ ከእህቶችሽ ጓድ ምረጭ አትሞኚ ቅሪ በደንብ እወቂበት ፁሚ በርቺ ስገጅ ሶላት እርግፍ አርጊው መኳኳሉ መሽሞንሞንሽን አይጠቅምሽም እህቴዋ! ቢጋፋ እንጂ ዲን ክብርሽን ከፈተና መጠበቂያ ያዥ ሂጃብሽን መሰተሪያ ይሆንሻል ልበሽ እህት ጅልባብሽን! አይንሽን ግለጭ እህቴ! አይንህን ግለጥ ወንድሜ! ከጊዜያችሁ ሳትጠየቁ ከአላህ ፊት ንቅንቅ አትሉም፡፡ ጊዜያችሁን ተጠቀሙበት፡፡ ታገሉበት፣ ልፉበት፣ ድከሙበት፣ ለአኸይራችሁ ስሩበት፡፡ በኢኽላስ ኑሩ፣ ስራ አሳምሩ፤ ምንዳ ሰብስቡ፣ አጅር አጋብሱ ሳያልቅባችሁ ተሸቀዳደሙ፣

ሂዱ ሩጡበት፤

ያው ሜዳው

ያው ፈረሱ!
.
.
.
.
.
.
ሙስተዒድ?!