Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አንድነት

Mohammed Ibrahim Ali
አንድነት!

እርግጥ ነው! ለአንድ ሙስሊም ስለ አንድነት መንገር “ለቀባሪ ማርዳት” ነው፡፡ ምክንያቱም ከሙስሊሞች የአንድነትን የላቀቦታ እና ዘላቂ ጥቅሙን ያልተረዳ ማግኘት ይከብዳልና፡፡ ቢሆንም የሰው ልጅ መርሳት የተጠናወተው ፍጡር ስለሆነ ይህን ታላቅ ፋይዳያለው አስተምህሮ እንዳይዘነጋ ማስታወሱ የሁላችንም ሀላፊነት ይሆናል፡፡ አላህም …
وَذَكِّرْ فَإِنَّ الذِّكْرَىٰ تَنفَعُالْمُؤْمِنِينَ ﴿الذاريات: ٥٥﴾
“ገሥጽ(አስታውስ) ፤ ግሣጼ ምእመናንን ትጠቅማለችና”አዛሪያት 55
በማለትእንድንተዋወስ አዞናልና፡፡ ታዲያ ከተዋወስን አይቀር ይህን አንገብጋቢ ጉዳይ ሊጠቅመን በሚገባ መልኩ እንነጋገርበት፡፡ እንደሚታወቀውአንድነት አላህ በቁርአኑ እጅግ አበክሮ ያዘዘበት ጉዳይ ነው፤ ተቃራኒ ከሆነው መለያየት ሲከለክልም አጥብቆ በማስፈራራት ነው፡፡አላህ እንዲህ ይላል …
شَرَعَ لَكُم مِّنَ الدِّينِ مَا وَصَّىٰ بِهِ نُوحًاوَالَّذِي أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ وَمَا وَصَّيْنَا بِهِ إِبْرَاهِيمَ وَمُوسَىٰوَعِيسَىٰ ۖ أَنْ أَقِيمُوا الدِّينَ وَلَا تَتَفَرَّقُوافِيهِ [٤٢:١٣]
“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን (ኢስላምን) ደነገገላችሁ፡፡ ያንን ወዳንተ ያወረድነውን ያንን በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ! ማለትን (ደነገግን)” ሹራ 13
{وَاعْتَصِمُوا بِحَبْلِاللَّهِ جَمِيعاً وَلا تَفَرَّقُوا} آل عمران: 103
“የአላህንም (የማመን) ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም!” አሉ ኢምራን103

وَأَطِيعُوا اللَّهَ وَرَسُولَهُ وَلَا تَنَازَعُوافَتَفْشَلُوا وَتَذْهَبَ رِيحُكُمْ ۖ وَاصْبِرُوا ۚ إِنَّ اللَّهَ مَعَ الصَّابِرِينَ [٨:٤٦]
“አላህንና መልክተኛውንም ታዘዙ፡፡ አትጨቃጨቁ፤ ትፈራላችሁ፣ ኃይላችሁም ትኼዳለች፡፡ ታገሱ፤ አላህ ከትዕግስተኞች ጋር ነውና”አል አንፋል-46
وَلَا تَكُونُوا مِنَالْمُشْرِكِينَ [٣١] مِنَ الَّذِينَ فَرَّقُوا دِينَهُمْ وَكَانُوا شِيَعًا ۖ كُلُّ حِزْبٍ بِمَا لَدَيْهِمْ فَرِحُونَ ﴿الروم: 32﴾
“ከአጋሪዎቹም አትሁኑ፡፡ [31] ከእነዚያ ሃይማኖታቸውን ከለያዩትና ክፍልፍሎችም ከሆኑት (አትሁኑ)፡፡ ሕዝቦች ሁሉ እነሱ ዘንድ ባለው ነገር ተደሳቾች ናቸው” አል-ሩም 32

وَلَا تَكُونُوا كَالَّذِينَ تَفَرَّقُوا وَاخْتَلَفُوا مِن بَعْدِ مَا جَاءَهُمُ الْبَيِّنَاتُوَأُولَٰئِكَ لَهُمْ عَذَابٌ عَظِيمٌ ﴿آلعمران: ١٠٥﴾
“እንደነዚያም ግልጽ ተዓምራት ከመጣላቸው በኋላ እንደተለያዩትና እንደ ተጨቃጨቁት አትኹኑ፡፡ እነዚያም ለእነርሱ ታላቅ ቅጣት አላቸው” አሉ-ኢምራን 105
በእነዚህአንቀፆች አላህ አንድ እንድንሆንና በጉልህ አስቀምጦልናል፡፡ መለያየት ምን አይነት ክፋት እንዳለው እና ልንርቀው እንደሚገባበማያወላዳ መልኩ ገልጧል፡፡ በሌላ በኩል ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በብዙ ሐዲሶች ስለ አንድነት ሰብከዋል፣ አነሳስተዋል፣አስተምረዋል ከልዩነት አስጠንቅቀዋል፣ ከልክለዋል፡፡ ከነዚያም መካከል በአንዱ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ …
“አላህሶስት ነገር ይወድላችኋል፡- እርሱን እንድታመልኩትና ማንንም እንዳታጋሩበት፣ በአላህ ገመድ በአንድነት እንድትተሳሰሩናእንዳትለያዩ እንዲሁም በጉዳያችሁ ላይ አላህ የሾመውን (መሪ) እንድትመክሩ!” ሙስሊም አህመድና ማሊክ ዘግበውታል
አንድነትምን ያህል ቦታ በሸሪዓችን እንደተሰጠው ለማወቅ ይህን የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲስ ብቻ ማስተዋል በቂ ነው፡፡ አላህ የራሱ መብት ከሆነው ተውሂድ ቀጥሎ ታላቅ ቦታን ያጎናፀፈው አንድነታችንንነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አላህ በምድር ላይ ጥርት ባለ ተውሂድ ይመለክ ዘንዳ ሙስሊሞች በአንድነት እየተረዳዱ እራሳቸውን ከሽርክመጠበቅ ስላለባቸው ነው፡፡
በሌላ ሀዲስ ደግሞ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ “በአንድነት(በመሰባሰብ)ላይ አደራችሁን፤ መለያየትን ተጠንቀቁ፡፡ ሸይጧን እኮ ከአንዱ ጋር ነው፤ ከሁለት(ሰዎች) የራቀ ነው” አህመድ ዘግበውታል
ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በሌላ ሐዲስ እንዲህ ይላሉ “አንድነት እዝነት ሲሆንመለያየት ግን ቅጣት ነው” አህመድ ዘግበውታል
በተጨማሪም ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “የአላህ እጅ (በድጋፉ) ከጀመዓ(አንድነት) ጋርነው” ብለዋል፡፡ ኢብን አቢ-ዓሲም በሱነኑ ላይ ዘግቦታል
በሌላ ሐዲስ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል “ከአሚሩ ላይ የሚጠላውንየተመለከተ ይታገስ፤ ምክንያቱም ከጀመዓ አንድ ስንዝር የተለየና የሞተ ሞቱ የጃሂሊያ ሞት እንጂ ሌላ አይደለምና” ሰሂህ አል-ቡኻሪ
ሱብሀን አላህ! ስለ አንድነት የሚያወሱ ሐዲሶችን አውስተን ባናበቃም አንድነት በሸሪዓችንምን ያክል ቦታ እንዳለው ለማወቅ ከላይ የጠቀስናቸው ሐዲሶች ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ አላህና መልእክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ትልቅ ቦታ ለሰጡት ነገር እኛም ልዩ ቦታ መስጠት ግዴታችን ከመሆኑምበላይ ይህን አንድነት በተገቢው ሁኔታ መረዳት፣ መጠበቅ እና ለመለያየት የሚያበቁ ነገሮችን በሚገባ አውቆ እራስን ማራቅ ከኛየሚጠበቅ ነው፡፡
እንግዲህ ለዛሬ አንድነት ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ካወሳን በቀጣይ ‹ኢን-ሻአላህ› ቁርዓንናሐዲስ እንዲህ የላቀ ደረጃ የሰጡት አንድነት ለምን ሙስሊሞች መተግበር እንደተሳናቸው እናያለን፡፡
“ይቀጥላል”


ባለፈው ፅሁፍ ላይ አላህ እና መልእክተኛው(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ምን ያክል ስለአንድነትእንደሰበኩ አይተን ነበር፡፡ ለዛሬ ደግሞ …
አንድነት አላህ ከተውሂድ ቀጥሎ የላቀ ደረጃ የተሰጠው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ዛሬ ግን ሙስሊሞች“ላለመስማማት የተስማሙ” ይመስል ከአንድነት እጅጉኑ ርቀዋል፡፡ መጨቃጨቅ፣ መነታረክ፣ መጣላት፣ የከፉ ቃላትን መለዋወጥ፣መተማማትና በሙስሊሞች መካከል በነገር መቆራቆስ የእለት ተግባራት ከሆኑ ዘመናት አልፈዋል፡፡
በእርግጥ ከዚህ ሁሉ ተከልክለን ነበር፡፡ አቢ ሁረይራ(ረ.ዓ) እንዳወሩት ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም)እንዲህ ብለዋል
“አትመቀኛኙ፣ ዋጋ አታሳቅሉ፣ አትጠላሉ፣ ጀርባ አትሰጣጡ፣ ከፊላችሁ በከፊሉገበያ ላይ አይሽጥ፣ ወንድማማች የአላህ ባሮች ሁኑ!!! ሙስሊም የሙስሊም ወንድሙ ነው!፡፡ አይበድለው፣ አያዋርደው፣ አይዋሸው፣አይናቀው፡፡ አላህን መፍራት እዚህ ነው - ሶስቴ ወደ ደረታቸው እያመለከቱ- ለአንድ ሰው ሙስሊም ወንድሙን መናቁ ከክፋት(ከወንጀል) ይበቃዋል፡፡ ሁሉም ሙስሊም በሌላኛው ላይ ደሙ፣ ገንዘቡና ክብሩሐራም ነው፡፡” ሙስሊም ዘግበውታል
የሚገርመው ግን ዛሬ ስራችን ከታዘዝነው የተገላቢጦሽ ሆኖ ጥፋቶቻችን እየገነኑ ወገንተኝነት፣ጭፍን ተከታይነት፣ እራስ ወዳድነት፣ ቡድንተኝነት እየጎመራ ትላልቅ አንጃዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ባስ ሲል ደግሞጎጠኝነት፣ ዘረኝነት፣ ጠርዘኝነት እያየለ መጥቶ ዛሬ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በመጤ አስተሳሰቦች እየተናጠ እጅግ በተራራቁ ጭፍራዎችተወጥሮ ከፊሉ በነገር የተቀረው ደግሞ በጦር እርስ በርስ እየተቀሻመደ ይገኛል፡፡
የአላህ መልእክተኛ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “አላህ ዘንድ የአንድ ሙስሊም ደም ከሚፈስዱኒያ ከነያዘችው ብትወገድ ይሻላል” ቢሉም ዛሬ የሙስሊም ደም ረክሶ በእየአቅጣጫው እየተረጨ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ባለፉትተከታታይ አመታት እንደምናየው በሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ የመን፣ ሱዳን፣ ዒራቅ፣ ግብፅ ሌሎችም ሀገራት ቁጥራቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩሙስሊሞች ደም በገፍ እየፈሰሰ ይገኛል፡፡ ምነው! አላህ እርስ በርስ እንድንጫረስ ነበር እንዴ ያዘዘን? የከሀድያን መሳለቂያእንድንሆን ነበር እንዴ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የመከሩን? አላሁ ሙስተዓን!
በእርግጥ!ነቢያችን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሙስሊሞች ቢድዓን ዲን ውስጥ ሲጨምሩ፣መሪዎቻቸውን አንታዘዝም ሲሉ እንዲሁም ዘረኝነትን ሲንተራሱ እንደሚለያዩ ጠቁመው ነበር፡፡ በተለያዩ ሐዲሶቻቸው ኡማቸውንከእነዚህ አንድነትን አፍራሽ መርዞች እያስጠነቀቁ ሙስሊሞች የነቢዩን እንዲሁም የሶሀቦችን ፈለግ አጥብቀው በመያዝ አንድነታቸውንእንዲጠብቁ አደራ ብለው ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በአንድ ሐዲሳቸው እንዲህ አሉ “ጌታዬን ሶስት ነገር ጠይቄውሁለቱን ሰጥቶ አንዱን ከልክሎኛል፤ ጌታዬን ያለፉትን ህዝቦች እንዳጠፋው እኛንም እንዳያጠፋን ጠየቅኩት ይህን ሰጠኝ፡፡ ጌታዬንበእኛ ላይ ጠላታችንን የበላይ እንዳያደርግብን ጠየቅኩት ይህንንም ሰጠኝ፡፡ ጌታዬን በቡድን እንዳይከፋፍለን ጠየቅኩት ይህን ግንከለከለኝ” ሙስሊም፣ ነሳኢና ቲርሚዚ ዘግበውታል
አላህ ድካ በደረሰው ጥበቡ እርሱ የሚያውቀውን መልካም ነገር ሽቶልን ሁለቱንየነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዱዓ ተቀብሎ ሶስተኛውን ግን መልሶታል፡፡ ይህ የአላህ ቀደር ነው፡፡ ምን እንደፈለገበት እርሱእንጂ ማንም አያውቅም፡፡ መልካም ሁሉ ከአላህ ነው፤ መጥፎ ቢገጠመን እጆቻችን በከሰቡት ነው!
وَمَا أَصَابَكُم مِّن مُّصِيبَةٍ فَبِمَا كَسَبَتْأَيْدِيكُمْ وَيَعْفُو عَن كَثِيرٍ [٤٢:٣٠]
“ከመከራም ማንኛውም ያገኛችሁ ነገር እጆቻችሁ በሠሩት (ኃጢኣት) ምክንያት ነው፡፡ (አላህ) ከብዙው(ኃጢአታችሁ) ይቅር ይላል”ሹራ 30
በአንድ ሐዲሳቸው ነቢዩ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ “አላህንመበመፍራት ላይ አደራ እላችኋለሁ! ባሪያ እንኳ ቢሾምባችሁ እርሱን በመስማትና በመታዘዝ ላይ (አደራ)፡፡ ከናንተ (ረጅም) እድሜንየሚኖር ብዙ መለያየትን ይመለከታል፤ በእኔና በተመሩት ቅን ተተኪዎቼ(ኸሊፋዎች) ሱና ላይ አደራችሁን፣ በቀንጣጤያችሁ አጥብቃችሁያዟት፡፡ መጤ ነገሮችን ተጠንቀቁ፤ ሁሉም ቢድዓ ጥመት ነውና!” አቡዳውድና ቲርሚዚ ዘግበውታል
አዎን! ነቢያችን አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እኛስ አደራውን በላን ወይስተወጣን; በዚህ ሐዲሰ ላይ ሙስሊሞችን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ሁለት ምክንያቶች ተቀምጠው እናገኛለን፡፡ አንደኛው ለሙስሊም መሪ አለመታዘዝሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቢድዓን በዲን ውስጥ መክተት ነው፡፡ እነኝህ ሁለት መርዞች ናቸው በየዘመኑ የአንድነት ጠንቅ ሁነው ለመለያየትበር የሚከፍቱ የነበሩት፡፡ ይሁንና ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) አንድን መርዝ ጠቁመው ማምከኛውን ሳይናገሩ አያልፉምና በዚሁሐዲስ ላይ እነኝህን ሁለት መርዞች ተጠንቅቀን የእሳቸውንና የቅን ኸሊፋዎቻቸውን ጎዳና አጥብቀን እንድንይዝ መክረዋል፡፡
በሌላ ሐዲስ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) "የሁዳ ወደ 71 ተከፋፈለች፣ ክርስትና ወደ 72 ተከፋፈለች፣ ይህችምኡማ ወደ 73 ትከፋፈላለች፤ ሁሉም የእሳት ነው አንዷ ስትቀር" አሉ። ሶሀቦች «የትኛዋ ነች?» ሲሉ ጠየቁ። እሳቸውም"ዛሬ እኔ እና ሶሀቦቼ ባለንበት ምሳሌ ላይ ያለ ነው" አሉ። ቲርሚዚና ሀኪም ዘግበውታል
ይህ ሐዲስ መለያየት ሊከሰት እንደሚችል ከመጠቆም አልፎ ምን ያክል መሰረታዊአንጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ገልፃል፡፡ በሌሎችም ሰሂህ ዘገባዎች አንደመጠው ከሰባ ሶስቱም አንጃዎች ከእሳት የምትድነዋ አንዷ ብቻስትሆን የተቀሩት ግን በወንጀላቸው ልክ በጀሀነም ተቀጥተው ሙስሊም እስከሆኑ ድረስ በአላህ እዝነት ወደ ጀነት የሚመለሱ ናቸው፡፡በዱኒያም ከልዩነት ለመላቀቅ በአኸይራም እጅግ አደገኛ ከሆነው የጀሀነም እሳት ለመዳን ብቸኛው አማራጭ ያችን ነቢዩና ሶሀቦች የሚገኙባትንጎዳና አጥብቆ መያዝ እና በዚህች የሱና መስመር ላይ መሰባሰብ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡
ሙስሊሙ ኡማ መጤ አስተሳሰቦችን ከሌሎች የወረሰ ግዜ ሊከፋፈል እንደሚችል የሚጠቁሙት ሐዲሶች በዚህ አላበቁም፤ ለጥቆማያክል ጥቂቶቹን አሳለፍን እንጂ፡፡ ነቢዩ(ሰለላሁዓለይሂ ወሰለም) ይህ መከፋፈል የሚከሰተው ሙስሊሞች ከከሀዲያን ለተወረሱ መጤ አስተሳሰቦች በር ሲከፍቱና ሙሉ የነበረውንዲናቸውን በአዲስ አመለካከት ሲበርዙት እንደሆነም ባለፉት ሐዲሶች ጠቆም አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂወለሰም) እንዲህ አሉ
“ከእናንተ በስተፊት የነበሩትን(ህዝቦች) ፈለግ ኮቴ በኮቴ ትከታተላላችሁ የወከሌ(አርጃኖ)ጉድጓድ እስኪገቡ ድረስ (እናንተም) ትገቡታላችሁ” ሶሀባዎችም “የየሁዳና የክርስቲያኖችን (ፈለግ) ነውን?” አሉ፡፡ ነቢዩም(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “ታዳያ የማንን ነው?” በማለት አረጋገጡ፡፡ ቡኻሪናሙስሊም ዘግበውታል
ይህ ሆነ ማለት መላው ሙስሊም ከሀዲያንን በመከተል በጥመት ውስጥ ይገባልማለትን እንደማያስይዝ ልንረዳ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የጠመሙ አንጃዎች ሲፈለፈሉ ከላይ የተጠቆመችው “ነጃ” የምትወጣው ጭፍራ እስከቂያማድረስ እንደምትዘልቅ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጠቁመዋልና፡፡
"የአላህ ትዕዛዝ(ቂያማ) አስኪመጣ ከኔ ኡማ በሀቅ ላይ የበላይ የሆነች ጭፍራአትጠፋም፡፡ የሚያዋርድም ሆነ የሚቃረናቸው አይጎዳቸውም" ቡኻሪ ዘግበውታል
ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የተናገሩት አንዱም አልቀረም ከብዙ ሙስሊሞች አላህየጠበቃቸው ሲቀሩ አላህ በሰጣቸው መመሪያ መብቃቃት እየተሳናቸው ጭማሬ በማይሻው ዲናቸው ላይ አዲስ ነገር እየዶሉ ሁሉምበየአቅጣጫው በጨመሩት ቢድዓ ላይ ቡድን መስርተው አንድነትን ወረት አድርገውታል፡፡ ይህ ማንም የማይወቀስበት የኛው ጥፋት መሆኑግልፅ ነው!
ظَهَرَ الْفَسَادُ فِي الْبَرِّ وَالْبَحْرِ بِمَا كَسَبَتْأَيْدِي النَّاسِ لِيُذِيقَهُم بَعْضَ الَّذِي عَمِلُوا لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ[٣٠:٤١]
“የሰዎች እጆች በሠሩት ኃጢኣት ምክንያት የዚያን የሠሩትን ከፊሉን ያቀምሳቸው ዘንድ መከራው በየብስና በባሕር ተገለጠ፤ (ተሰራጨ)፡፡ እነርሱ ሊመለሱ ይከጀላልና”አል-ሩም 41
ወንድሞች! አላህ የሙስሊሙ ኡማ እንደሚከፋፈል መወሰኑ እንዲሁም በኛ ጥፋትይህ መከሰቱ ለአንድነት ከመስራትም አያሳንፈንም፡፡ ምክንያቱም በወንጀላችን ሰበብ ቅጣት ይሆንብን ዘንድ መለያየት በኛ ላይ ሰፈነእንጂ የአንድ መሆን ሀላፊነት ላይመለስ ከኛ ጫንቃ አልወረደም፡፡ እንደውም ከሌላው ወቅት በበለጠ ለዚህ አላህ አበክሮ ላዘዘበትጉዳይ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
ሁሌም ቢሆን እኛ ትክክለኛውን መስመር ይዘን ብንደክም፣ ከጠመሙ አንጃዎችእራሳችንን ብንጠብቅ በአላህ ፈቃድ የምንመኘውን አንድነት ማግኘት አይሳነንም፡፡ ባይሆን አንድነታችን ትክክለኛና ዘላቂ ይሆን ዘንድበምን መሰረት ላይ መመርኮዝ እንዳለበት ጠንቅቀን ማወቅ ለኛ ግድ የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቁርአንና ሐዲስ በግልፅ ሰፍሮ የሚገኝጉዳይ በመሆኑ ሩቅ የምንሄድበት አይደለም፡፡ አላህም እኛ ለመለወጥ ዝግጁ እስከሆን እና በሀቅ ላይ እስከታገልን ድረስ ቀናውን መንገድእንደሚመራን በቁርአኑ ገልጾልናል
وَالَّذِينَ جَاهَدُوا فِينَا لَنَهْدِيَنَّهُمْ سُبُلَنَا ۚ وَإِنَّ اللَّهَ لَمَعَ الْمُحْسِنِينَ[٢٩:٦٩]
“እነዚያም በእኛ መንገድ የታገሉ መንገዳችንን በእርግጥ እንመራቸዋለን፡፡ አላህም በእርግጥ ከበጎ ሠሪዎች ጋር ነው”አል-አንከቡት 69
ለዛሬ ይህን ያክል ካየን በቀጣይ በሙስሊሞች መካከል ለመጀመሪያ ግዜ ኺላፍናመለያየት እንዴ እንደተፈጠረ በጥቂቱ ታካዊ ዳራው እንዳስሳለን ‹ኢን-ሻአላህ›፡፡ ደህና ሁኑ!
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ባሳለፍናቸው ክፍሎች የአንድነትን ትልቅ ደረጃ እና አንደነትን በኡማው መካከልእነዳይኖር እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ከቁርአንና ሐዲስ በማጣቀስ አይተን ነበር፡፡
ዛሬ ደግሞ ነቢያችን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በተውሂድ ላይ አንድ አድርገውትያለፉትን ኡማ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድነቱን ያናጉት እንማን እንደሆኑ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡ አብረን እንቀጥል …
ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ህልፈት በኋላ ተጠናክሮ የቀጠለው የሙስሊሞችሀያል አገዛዝ በአቡበክርና ኡመር(አላህ ስራቸውን ይውደድላቸውና) ዘመነ ኺላፋ እጅግ ተስፋፍቶ የአለምን ታላላቅ ግዛቶች በሙስሊሞችስር አስገብቶ ነበር፡፡ በየአቅጣጫው የኢስላም ዋና አስተምህሮ የሆነው ተውሂድ እየተሰበከ እልፍ አእላፍ ህዝቦች ኢስላምን እየተቀበሉበፍትህ ጥላ ስር እየነጎዱ ነበር፡፡ በወቅቱ የሙስሊሞች እጅግ ሀያል የቆጠቆያቸው ከሀድያን እንደስከዛሬው ሙስሊሞችን በቀላል ግጥሚያማሸነፍ እንደማይቻላቸው ስለተረዱ ሙስሊሞችን ለማዳከም ሌላ ብልሀት ፈጠሩ፡፡ “የሙስሊሞችን አንደነት መናድ!”
ከነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ህልፈት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ የፊትና በርየተከፈተው በኡስማን(ረ.ዓ) ዘመነ ኺላፋ ነበር፡፡ ከኡመር(ረ.ዓ) ሞት በኋላ ይህ እንደሚከሰት የሚጠቁም ሐዲስ ከነቢዩ(ሰለላሁዓለይሂ ወሰለም) ተወርቶ ነበር፡፡
ፊትናው የተከሰተው አብደላህ ኢብኑ ሰበእ አል-የሁዲ(በቅፅል ስሙ ኢብኑ-ሰውዳእ)በተሰኘው ግለሰብ ስውር ሴራ ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ግለሰብ  በኡመር(ረ.ዓ)ዘመነ ኺላፋ ሰለምኩ ብሎ ወደ ሙስሊሞች ሲቀላቀል ከሙስሊሞች ሊዋሀድ አስቦ ሳይሆን ሙስሊሞችን ለመከፋፈልና ለማጋጨት አላማ አንግቦነበር፤ ድሮስ ከየሁዲ ምን ይጠበቃል! ትሉ ይሆናል አዎ “ድሮስ ከዝንብ መች ማር ይጠበቃል!”
ይህ መሰሪ ግለሰብ ሰለምኩ ብሎ ከገባ በኋላ እራሱን ጥሩ ሰው በማስመሰልበሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግነት ሞከረ፡፡ ኋላም በኡስማን(ረ.ዓ) ኸሊፋነት ዘመን አንዳንድ ግልብ ወጣቶችን በኡስማን(ረ.ዓ)አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ ያነሳሳ ጀመር፡፡ እነኝህ ወጣቶች ከነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በቀጥታ አልተገናኙም ወይም በአጭሩ ከእነሱመካከል ሶሀባዎች አልነበሩም፡፡ ይሁንና ወጣቶቹ በተለያዩ ዒባዳዎች እንዲሁም ቁርአንን በማንበብ ላይ የተካኑና ለዲነል ኢስላም ለማገልገልከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ትኩስ ሀይሎች ነበሩ፡፡ አብደላህ ኢብን-ሰበእ አል-የሁዲም እነዚህን ያለበሰሉ ወጣቶች ትኩሳት ተጠቅሞእኩይ አላማውን ለማሳካት ቋመጠ፡፡ በመቀጠልም በዙ-ኑረይን ኡስማን ቢን ዓፋን(ረ.ዓ) ላይ የሀሰት ወሬዎችን በመንዛት የውሸት ክሶችማሰራጨቱን ተያያዘው፡፡ ወጣቶቹም በተነዙት አሉባልታዎች ለመሪያቸው ጥላቻ እንዲያድርባቸው ታገለ፡፡
ይህ መሰሪ ተንኮሉን በማስፋት እነዚህ በአሉባልታ የሰከሩ ወጣቶች ወደ መዲናሂደው በጀነት የተመሰከረለትን ታላቁን ኸሊፋ እንዲገድሉ ቀሰቀሳቸው፡፡ የሀሰት ውንጀላዎችን በመደርደር ወጣቶቹ የሚሰሩትን ፀያፍድርጊት መልካም አስመስሎ ቀረፀላቸው፡፡ ከመሀከላቸው አንድም ዓሊም የማይገኘው እነኝህ ወጣቶች በአብደላህ ኢብኑ ሰበእ ሰበካ ተሸውደውፍትሀዊውን መሪ መዲና ውስጥ በቤቱ እያለ ከበቡት፡፡ ፊትና እንዳይፈጠር የሰጋው ታጋሹ ኸሊፋ ሰራዊቱን በተነ፣ የሙስሊሞች ደም እንዳይፈስሰግቶ ሁሉም ሶሀባ ከቤቱ እነዳይወጣ አገደ፡፡ ሶሀቦችም የመሪያቸውን ትእዛዝ ተቀብለው በቤታቸው ቀሩ፡፡
ኡስማንም(ረ.ዓ) እነኝህን በፖለቲካ ወሬዎች የናወዙ ወጣቶችን ማረጋጋት ያዘ፤እውነታውን ሊያስረዳቸውም ጥረት አደረገ፡፡ እነርሱ ግን አእምሮአቸው በቀላሉ ሊፋቅ በማይችል ጥላቻ ጠልሽቶ ነበርና በኡስማን ላይጨከኑበት፡፡ በቤቱ ውስጥ ቁርአን እየቀራ ሳለ በግፍ ገደሉት፡፡ ያኔ ከሺህ አራ መቶ አመት በፊት በጀነት እጩው ኡስማን(ረ.ዓ)ላይ የተነሳው ሰይፍ ይኸው ዛሬ ድረስ ከሙስሊሞች አንገት አልወረደም፡፡ ዛሬም በአፈ ቀላጤዎች ተሸውደው መሪዎቻቸው ላይ የሚያምፁወጣቶች የትየለሌ ናቸው! የሚፈሰው የሙስሊም ደምም ዋይ ባይ አጥቷል፡፡ አላሁ ሙስተዓን!
በወቅቱ በኡስማን(ረ.ዓ) ላይ ሰይፍ ካነሱት ግልብ ወጣቶች ጥቂት የማይባሉየጀመሩትን ጥፋት “አበጀን” ብለው ቀጠሉበት፡፡ አስከትለውም በዓሊይና በሙዓዊያ(አላህ መልካ ስራቸውን ይውደድላቸውና) መሀል ፊትናለመቀስቀስ የሙናፊቆች ተላላኪ በመሆን አገለገሉ፡፡ በወቅቱ ሁዘይፋ(ረ.ዓ) እንዲህ ብሎ ነበር
“የዛሬ ሙናፊቆች በነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ዘመን ከነበሩት የከፉናቸው፡፡ የዛን ግዜ (ንፍቅናቸውን) ይደብቁ ነበር ዛሬ ግን ግልፅ አውጥተዋል” ቡኻሪ ዘግቦታል
እነኚሁ ኡስማንን(ረ.ዓ) የገደሉ ሰዎች እና መሰሎቻቸው በዚህ ብቻ አልቆሙም፡፡በሸሪዓ መፋረድን ትቶ በሰዎች ሽምግልና ተዳኝቷል በሚል ውሀ የማይቋጥር ክስ ዓሊይን(ረ.ዓ) በመወንጀል ዓሊንም ሆነ ሙአዊያህ እንዲሁምቀሪዎቹን ሶሀባዎች በክህደት ፈረጇቸው፡፡ ከዓሊይ ጦር አፈንግጠው በመውጣትም ከያሉበት ተሰባስበው በኩፋ(ዒራቅ) አቅራቢያ ሐሩርበምትባል ቦታ ሰፈሩ፡፡ በኢስላም ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜም የ“ኸዋሪጅ” (አፈንጋጮች) ፊርቃ ግልጽ ወጣ!
በእርግጥ የኸዋሪጅ ፊርቃ እንደሚፈጠር ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ቀደምብለው ጠቁመው ነበር፡፡ እንደውም ምን አይነት ባህሪ እንዳላቸው ሳይቀር ገልጸው ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ነቢያችን(ሰለላሀ ዓለይሂ ወሰለም) ምርኮ ሲያከፋፍሉ አንድሰው መጣና “አንተ ሙሐመድ ሆይ ፍትህ እየሰራህ አይደለም፤ ፍትሀዊ ሁን!” አላቸው፡፡ ነቢዩም(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “ወየውልህእኔ ፍትሀዊ ካልሆንኩ ማን ፍትሀዊ ሊሆን ነው?” ብለው መለሱለት፡፡ ሰውየው ሲሄድም እንዲህ አሉ “ከዚህ ሰውዬ ዝርያ የሚወጡ ይኖራሉ፤ሶላታችሁን ከነሱ ሶላት ስታስተያዩ ትንቁታላችሁ፣ አምልኮታችሁን ከነሱ አምልኮት አንፃር (ትንቁታላችሁ) ቁርአንን ያነባሉ ነገርግን ከጉሮሮአቸው አያልፍም …” ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ኸዋሪጆች ከዓሊይ(ረ.ዓ) ጦር አፈንግጠው ከወጡ በኋላ በሙስሊሞች ላይ የተሰለጡነቀርሳዎች ሆኑ፡፡ ሙሽሪኮችን ጥለው ሙስሊሞችን መግደል ስራዬ ብለው ተያያዙት፡፡ ለአስተሳሰባቸው ጠላት የሆኑባቸውን ብርቅዬ ሶሀባዎችምየቀስታቸው ኢላማ አደረጉ፡፡ በመጨረሻም በነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲስ እንደመጣው ዓሊይ(ረ.ዓ) እንኝህን በጭካኔ የተሞሉአፈንጋጮችን ተጋደላቸው፤ ብሎም አሸነፋቸው፡፡ ያኔ ከጦር ሜዳው የተራረፉ ኸዋሪጆች ዓሊ(ረ.ዓ) ወደ ነበረበት ኩፋ ከተማ ተደብቀውበመሄድ ለሱብሂ ሶላት ሰዎችን እየቀሰቀሰ ሲወጣ አረመኔ ሰይፋቸውን አሳረፉበት፡፡ የነቢዩን የአጎት ልጅ፣ የፋጢማን ባለቤት፣ በጀነትየተመሰከረለትን ዓሊይ (ረ.ዓ) ኸዋሪጆች ገደሉት፡፡
ሶሀባዎች የበላይ በነበሩበት ዘመን ያቆጠቆጠው የኸዋሪጅ ፊርቃ በየዘመኑ መልኩንእየቀያየር በትንሽ በትልቁ ሙስሊሞችን ማክፈሩን ተያያዘው፡፡ ምንም እንኳ ያን ግዜ ብዙ ተከታይ ባይኖራቸውም ምርጡ የሰለፎች ትውልድእያበቃ ሲመጣ ግን ቀላል የማይባሉ አላዋቂዎችን ማስከተል ችለው ነበር፡፡ ይህ ፊርቃ ከሁሉም የሙስሊም ጠላቶች በባሰ መልኩ ለሙስሊሞችአደጋ ፈጣሪ በመሆን ተቀዳሚ ሆነ፡፡ ይህ ጠማማ አንጃ በየዘመኑ ሲነሳ ተመሳሳይ ከሚያደርጉት መገለጫዎቹ መደበኛ የሆነው በሙስሊምመሪ ላይ በዛም አነሰ ምክንያቶችን ፈጥሮ አምጾ መውጣቱ ሲሆን ይህን አላማውን ያልተጋሩትን ሁሉ እስከማክፈር ብሎም በጦር እስከመጋፈጥይደርሳል፡፡ አላህ ከሸራቸው ይጠብቀን፡፡
ለዛሬ በኢስላም ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የሙስሊሞችን አንድነት የናደውን የኸዋሪጅንፊርቃ አይተናል፡፡ በመቀጠል የሰለፎች ዘመን ሳየጠናቀቅ ብቅ ብቅ ያሉ ሌሎች የሙስሊሞችን አንድነት የተፈታተኑ የቢድዓ አንጃዎችንእናወሳለን፡፡ ሰላም እንገናኝ!

ባለፉት ክፍሎች የአንድነት የላቀ ደረጃ፣ የሙስሊሞች መለያየት መንስኤ እናለመጀመሪያ ግዜ በሙስሊሞች መካከል እንዴት መለያየት እንደተፈጠረ አይተን ነበር፡፡
ለዛሬ በሰለፎች ዘመን ምንም እንኳን ሱና የበላይነቱን እንደተጎናፀፈ ቢቀጥልምእጅግ በተወሰኑ ቦታዎች ብቅ ብቅ እያሉ የሙስሊሞችን አንድነት የተፈታተኑ የቢድዓ አንጃዎችን በጥቂቱ እናያለን፡፡
ባለፈው እንደጠቀስነው ለዑስማን የተገደለበትን ፊትና የቀመረው ዓብደላህ ኢብንሰበእ አል-የሁዲ በፈፀመው ደባ ተብቃቅቶ ስራውን አላቆመም፡፡ ይኸው መሰሪ በዓሊይ ኺላፋ ዘመን ፊቱን ወደ ዒራቅ(ኩፋ) በማዞርአሁንም ለመጤ አስተሳሰብ ማሰራጫነት ምቹ የሆኑ ሰዎችን ይመለምል ጀመር፡፡ ያዘጋጃቸውን አርቆ ማሰብ የማይችሉ ግልብ ጃሂሎችም እንግዳየሆነ መርዝ ይግታቸው ጀመር፡፡ ይኸውም እኛ “የዓሊይ ወዳጆች ነን፤ የእርሱ ቡድን ነን፣ የእርሱ ደጋፊ ነን” የሚሉ “ቅቤ አንጓች”ሰበካዎችን አስሸመደዳቸው፡፡ ቀስ በቀስም ዓሊይን(ረ.ዓ) ከደረጃው ከፍ አድርገው “ዓሊይ አላህ ነው!” እስከማለት እንዲደረሱ ከኋላቸውሆኖ ይገፋ ጀመር፡፡ በመጨረሻም ድንበር በማለፍ ኸሊፋው ዓሊን(ረ.ዓ) የአምላክነት ደረጃ እስከመስጠት ደረሱ፡፡ ይሄኔ በኢስላምታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የ“ሺዓ” አመለካከት አቆጠቆጠ፡፡
ይህንን ክስተት አሚረል ሙእሚኒን ዓሊ(ረ.ዓ) የሰማ ግዜ የዚህን መጤ አመለካከትአራማጆች አይቀጡ ቅጣት ይቀጣቸው ጀመር፡፡ ይህ አይነቱ ማላቅ ለእርሱ እንደማይገባም አበክሮ አስረዳቸው፡፡ ሆኖም አላህ አንዴ ልቡላይ ጥመትን ያተመበት አይመለስምና ከዓሊይ(ረ.ዓ) ቅጣት የተረፉት አንዳንድ ግለሰቦች የሺዓን አመለካከት ይዘው ዘለቁ፡፡
ዛሬም ዓሊይን(ረ.ዓ) እንወዳለን እያሉ “የአዞ እንባ የሚያነቡ” ሺዓዎችዓሊይን ከደረጃው ከፍ በማድረግ “ነቢይ ነው፣ ወደ ሰማይ አርጓል፣ ወደ ፊት ተመልሶ ይመጣል” የሚሉ መሰረተ ቢስ ተረቶችን እምነትአድርገው ይዘዋል፡፡ ከሙስሊሞች ወጣ ባለ መልኩ ብርቅዬ ሶሀባዎችን መጥላት፣ ማነወር፣ ብሎም ማክፈርን ዒባዳ አድርገው ይዘዋል፡፡ዛሬ ለሱና ተከታዮች ከየሁዳና ክርስትያኖች በበረታ መልኩ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው ሺዓዎች እነደነሱ እይታ “ዓሊይን አይወዱም”ብለው የሚፈርጁዋቸውን ሱኒዮች አክፍረው ደማቸውን ሐላል አድርገዋል፡፡ ንብረታቸውን መውረስም ሆነ በክብራቸው መረማመድ እንደሚቻላቸውበመፅሀፍቶቻቸው በግልፅ አስፍረዋል፤ በተግባርም አሳይተዋል!
በየሁዲው አብደላህ ኢብን ሰበእ የተመሰረተው የሺዓ አንጃ ልክ እንደኸዋሪጅሁሉ ብዙ ክፍልፍሎች ያሉት ቢሆንም ሺዓዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ቁርዓንና ሐዲስን ለኛ ያስተላለፉትን ብርቅዬ ሶሀባዎች አምርረውመጥላታቸው ነው፡፡ ከሺዓዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት በመፅሀፍቶቻቸው እንዳሰፈሩት ቁርዓን የተጓደለ(ሙሉ አይደለም) ብለው የሚያምኑሲሆን ከነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) የተወሩትን ሶሂህ ዘገባዎች ሁሉ አሽቀንጥረው ጥለው እምነታቸውን በአፈ-ታሪኮች ላይ ገንብተዋል፡፡አላህ ከጥመታቸው ይጠብቀን!
በሌላ በኩል በሶሀቦች ዘመን ማገባደጃ ላይ በዒራቅ(በስራ) አካባቢ አዲስአስተሳሰብ ብቅ ብቅ ማለት ጀመሮ ነበር፡፡ ሶስተኛ መጤ ፊርቃ በመሆን “ቀደርያ” የጠመመ እሳቤውን በአላዋቂዎች ዘንዳ ማሰራጨትያዘ፡፡ ይህ አይነቱ ፊርቃ እንደሚመጣ ነቢዩም(ሰለለላሁ ዓለይሂ ወለሰም) እንዲህ በማለት ጠቁመው ነበር፡፡
“ቀደሪያ የዚህ ኡማ መጁሳ ነች፤…” አቡዳውድ ዘግቦታል
እነዚህ ደግሞ “አላህ በእኛ ተግባር(ስራ) ላይ ምንም የሚያሳድረው ተፅእኖየለም፡፡ ሁሉንም ነገር ፍጡራን ሲፈፅሙ እነዳሻቸው እንጂ አላህ ምንም መሺአ(ፍላጎት) የለውም” አሉ፡፡ ከእነርሱ መካከል ድንበርያለፉት ደግሞ ጭራሽ “አላህ ምንም እውቀት የለውም” እስከማለት ደረሱ፡፡ ከሌሎች ሀይማኖቶች የቃረሙትን ቅጥፈት በኢስላም ስም ለማሰራጨትጣሩ፡፡ ይሁንና በህይወት የነበሩት በዒልም የበለፀጉ ሶሀባዎች እንዲሁም የእነርሱን ዱካ የተከተሉት ታላላቅ ታቢዒዮች ከእነኝህ ጠማማአንጃዎች ሙስሊሞችን አስጠነቀቁ፡፡ በቁርዓንና ሐዲስ መረጃም ይህን እምነታዊ ቢድዓ አንኮታኮቱ፡፡ የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወለም)ሱናም የበላይነቱን ጠብቆ ቆየ፡፡
እንግዲህ በሶሀባዎች ዘመን ብቅ ያሉት ሶስቱ ፊርቃዎች እነኝህ ነበሩ፡፡ ኸዋሪጅ፣ሺዓ እና ቀደርያ፤ ይሁንና በወቅቱ ሙስሊሞች መመሪያቸውን ቁርዓንና ሐዲስ በማድረጋቸው እንዲሁም አረዳዳቸውን በሶሀቦች ግንዛቤ ላይስለገነቡ በእነዚህ መጤ የቢድዓ አራማጆች በቀላሉ አልተሸነፉም፡፡ የሰለፎች ዘመን አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች ሱናን አጥብቀው በመያዝ የዘለቁበትዘመን ስለነበር አንድነታቸውም ከሌላው ዘመን አንፃራዊ በሆነ መልኩ የተረጋጋ እና ጠንካራ ነበር፡፡
ከሶሀቦች ትውልድ በኋላ በታቢዒዮች(ተከታዮች) እና በታቢዑ ታቢዒዪን ዘመንምያቆጠቆጡ ፊርቃዎች የሙስሊሞችን አንድነት ለመናድ ቢጥሩም አልተሳካላቸውም፡፡ እነደ ጀበሪያ፣ ከራሚያ፣ ሙርጂአ፣ ጃህሚያ፣ ሙዕተዚላናሌሎችም አፈንጋጭ አስተሳሰብን ከተለያዩ የፍልስፍና እና የከሀድያን ሀይማኖቶች የለቃቀሙ አንጃዎች ቢፈለፈሉም በምንም አይነት ተከታያቸውንማበራከት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩ ሙስሊሞች በስልጣንም ሆነ በእውቀት የነቢዩን ሱና የተመረኮዙ ነበሩና፡፡ ማንምአዲስ አስተሳሰብ ይዞ ሲመጣ በቁርዓንና ሐዲስ እንዲመለስ ይደረጋል፤ አልቀበልም ካለ ግን ባመጣው መጤ ቢድዓ ምከንያት ለቅጣት ይዳረጋል፡፡በአጭር አገላለፅ በሰለፎች ግዜ “ሱናው ባላባት ሲሆን ቢድዓው ጢሰኛ ነበር” ስለሆነም የሙስሊሞች አንድነት ከሌላው ወቅት እጅጉኑበተሻለ መልኩ ብርቱ ነበር፡፡
ለዚህም ነበር ነቢያችን በተለያዩ ሐዲሶቻቸው ይህን ዘመን ሲያሞካሹ የነበረው፡፡ከሌላው የኢስላም ትውልድ ተሸለ እንደሆነ እና ምርጥ የሚባለው ዘመን የሰለፎች እንደሆነ የጠቆሙት ይህ ተከታታይ ትውልድ ጥርት ባለውየነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ፈለግ እና በሶሀባዎች ፋና ይጓዝ ስለነበር ነው፡፡
ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለው ነበር "ከሰዎች ሁሉ የተሻለው የኔ ትውልድ ነው፤ ቀጥሎም ተከታዮቻቸው፤ቀጥሎም ተከታዮቻቸው፡፡ ከዚያም የአንዳቸው ምስክርነት መሀላቸውን፣ መሀላቸው ምስክርነታቸውን የምትቀድም ህዝቦች ይመጣሉ!"ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ነዓም! ከሰዎች ሁሉየተሻለው የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ትውልድ የሆነው የሶሀባዎች ዘመን ነበር ቀጥሎም እነርሱን የተከተሉት ታቢዒዮች ቀጥሎምእነርሱን የተከተሉት ታቢዑ-ታቢዒዪን፤ በአንድነት ሰለፍ አ-ሷሊህ ብለን የምንጠራቸው ደጋግ አበው፡፡ ምንኛ ያማረ ትውልድ፤ ምንኛየተመራ ትውልድ!
ከሰለፎች ትውልድ በኋላስ ምን ተከሰተ በቀጣዩ ክፍል የምናወጋው ይሆናል፡፡ሰላም እንገናኝ!
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------- 

ባሳለፍናቸው ክፍሎች ብዙ ትምህርቶችን አግኝተናል፡፡
ዛሬ ደግሞ ከሰለፎች ትውልድ በኋላ በሙስሊሞች አንድነት ዙሪያ ምን እንደተከሰተእንመልከት፡፡
የሰለፎች ዘመን ኢስላም በአለም የገነነበት፣ ሙስሊሞች በትክክለኛ አንድነትየተቆላለፉበት እንዲሁም አብዛኛው ህዝብ የሱናን ፈለግ የያዘበት ቢሆንም ይህ ትውልድ ሲያበቃ ግን ነገሮች መስመራቸውን ጠብቀው መጓዝአልቻሉም፡፡ በዒልም የመጠቀውን ትውልድ የተከተለው ብዙ ሙስሊሞች ከእውቀት ማእድ የተገለሉበትና በጅህልና አረንቋም የተዘፈቁበትውሽልሽል ትውልድ ነበር፡፡ ያንን በዓቂዳው፣ በስነምግባሩ እንዲሁም በአኗኗሩ የመጠቀውን ምርጡን ትውልድ የተካው እዚህ ግባ የማይባል፣ጨርሶ ከሰለፎች ጋር የማይነጻጸር ጥቂቶች ሲቀሩ በሁለመናው የዘቀጠ ነበር፡፡ በእርግጥም ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ይህን ተንብየውነበር
"ከሰዎች ሁሉየተሻለው የኔ ትውልድ ነው፤ ቀጥሎም ተከታዮቻቸው፤ ቀጥሎም ተከታዮቻቸው፡፡ ከዚያም ህዝቦች ይመጣሉ የአንዳቸው ምስክርነት መሀላቸውን፣መሀላቸው ምስክርነታቸውን የምትቀድም!" ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በመጨረሻው የሰለፎች ዘመን የነገሱ አንዳንድ መሪዎችዑለማዎችን ትተው የቢድዓ አራማጆችን ወዳጅ አድርገው መያዛቸው ነበር፡፡ እንዳውም ለሙስሊሞች ውድቀትን እንጂ ሌላ የማይመኙትን ከሀድያንንአማካሪ ሲያደርጉ በል ሚንስትሮቻቸውን ከቢድዓ ጓዶች ሲሾሙ ነበር የሰለፎች ዘመን ማብቂያ ላይ የኢስላምና የሙስሊሞችን ኃያልነትአደጋ ላይ የሚጥል ስህተት የተፈጠረው፡፡
ቢዚህ አጋጣሚ ነበር በእውቀት ላይ ተመርኩዘው የኢስላም ምሁራንን መርታትየተሳናቸው የቢድዓ አንጃዎች የተሳሳቱ መሪዎችን ጡንቻ ተማምነው በዑለማዎች ላይ የዘመቱት፡፡ ይህም የተለያዩ የፍልስፍና መፃህፍትከግሪክና ሌሎች ቋንቋዎች እየተረጎሙ በሙስሊሞች መሀል በማሰራጨት የጥንቱን የነቢዩን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሐዲስ አጥብቆ የያዘውንሙስሊም በመጤ አስታሰሰብ በመበረዝ ሰዉ በቁርዓንና ሐዲስ እነንዳይዳኝ አደረጉት፡፡ በእርግጥ ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም እንዲህብለው ነበር …
“ሁለት ነገሮችን ትቼላችኋለሁ፤ እንሱን እስከያዛችሁ አትጠሙም፡፡ (እነርሱም)የአላህ ኪታብ እና የኔ ሱና ናቸው” ግና በቢድዓ ወጥመድ የተጠለፉ ሰዎች ለሀይማኖት መመሪያነት ምንጭ የነበሩት ቁርአንና ሐዲስወደጎን ገሸሽ አድርገው ለሰዎች ውዝግብ መፍቻነት የነሶቅራጠስና አሪስቶትል ፍልስፍና ፈራጅ አደረጉ፡፡
ፊትናው ተባባሰ፤ ሰዎች የሰለፎችን ፋና ጥለው የፈላስፎችን ዝባዝንኬ መንገድአደረጉ፡፡ ይባስ ብለውም በፍልስፍና መፃህፍት ተንተርሰው ቁርአንና ሐዲስን ለመተንተን ሞከሩ፡፡ ብዙ አንቀጾችን አጣመሙ ሐዲሶችንያለትርጉማቸው ትርጉም ሰጡ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ቀጥተኛውን የሱና ጎዳና ለቀው በዒልመል ከላም(ፍልስፍና) ውስጥ ዋዠቁ፡፡ አእምሮአቸውየሚላቸውን እንጂ መረጃ የሚያመላክታቸውን ላለመቀበል ወሰኑ፡፡ ኺላፉ ተጋጋለ፣ ውዝግቡ ጠና፣ በየአቅጣጫው ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስሰጪዎቹ በፍክስፍና የሰመጡት የቢድዓ አቀንቃኞች ሆኑ፡፡ ከዑለማዎች ይልቅ ጃሂሎች ነገሱ!
ዑለማዎች መጤ ቢድዓዎችን እንዲቀበሉ ተገደዱ፡፡ አሻፈረኝ ያሉትም ታሰሩ፣ተገረፉ ብሎም ተገደሉ፡፡ ምንም ቢመጣ መጤ አካሄዶችን አንቀበልም ያሉና በጥንታዊው የነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ፈለግ የፀኑሙስሊሞች ፍዳቸውን አዩ፡፡ የሙስሊሞች አንድነት ይፈረካከስ ያዘ፡፡ ልቦች ተለያዩ፣ አንደበቶች ተቃረኑ፣ ጥላቻው አየለ፣ መከፋፈልበዛ፡፡ መጤ እሳቤዎች አንደኛው ከሌላኛው ላይስማማ እርስ በእርሳቸውም በንትርክ ተጣመዱ፡፡ በርካታ አንጃዎች ተፈለፈሉ፣ ተበራከቱ፡፡እነ ኸዋሪጅ፣ ሺዓ፣ ቀደርያ፣ ጀህሚያ፣ ሙዕተዚላ ሌሎችም ምንም እንኳ በጅማሮአቸው ብዙ ተከታይ ማፍራት ቢሳናቸውም ኋላ ላይ ግንውዥንብሩን ተጠቅመው ቀላል የማይባል ጀሌ አስከተሉ፡፡
እነ ኩላቢያ፣ አሽዓሪያ፣ ማቱሪዲያና ሌሎችም እንደ አዲስ ተፈለፈሉ፡፡ ሁሉምእንደ ቢድዓው እየተቧደነ፣ ያመጣውን ጉድ በሌላው ላይ መጫን አማረው፡፡ ሁሉም ቡድን ሐይል እያሰባሰበ መሪነትን ለመቆናጠጥ ይታገልያዘ፡፡ ጦር እያነገበ ስልጣን ለመጨበጥ ተፋጀ፤ በሙስሊሞች በጎራ ተቧድነው ይጠዛጠዙ ጀመር፡፡ እነኝህ ፊርቃዎች አንድ የነበረውንጠንካራ የሙስሊሞች ስብስብ በየአቅጣጫው በተኑት፡፡ ማእከላዊው መንግስት ተዳከመ ለራሱም በቢድዓ ተዋጠ፡፡ ይህ ሁሉ ከሰለፎች ዘመንማብቃት በኋላ የተከሰተ ዱብዳ ነበር፡፡
ጊዜ እየረዘመ ዘመንም እየተተካካ የቢድዓ አራማጆች መልካቸውን እየቀያየሩየአንድነት ፀር ሁነው ቀጠሉ፡፡ ምንም እንኳ በየዘመኑ የሚነሱ ዑለማዎች ለእነኝህ መጤ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ፊርቃዎች ወገብ ቆራጭመልሶችን ቢሰጡም እንደሰለፎች ዘመን አብዛኛው ሰው በሱና ላይ መታገስ አልቻለም፡፡ ዓሊሞች በፅሁፎቻቸው፣ ደርሶቻቸው እንዲሁም ኹጥባዎቻቸውከቢድዓ እያስጠነቀቁ ወደ አንድነት ቢጣሩም ከጥቂቶች በስተቀር ሰሚ  ጠፋ፡፡ ይልቁኑ ቀላል የማይባሉ ሰዎች ከሰለፎች መንገድ ይልቅ መጤ ቢድዓ ተሽሏቸውየነቢዩን(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ሱና አሽቀንጥረው መከፋፈልን መረጡ፡፡ ሱና አንድ ያደረገውን ኡማ ቢድዓ በታተነው!
ኢብኑ ተይሚያህ አንድ ያማረ ንግግር አለው “ቢድዓ ከልዩነት ጋር የተቆራኘነው ሱና ደግሞ ከመሰባበሰብ(ሰንድነት) ጋር የተሳሰረ ነው” ሰደቀ ረሂሙላህ!
ከሰለፎች ትውልድ በኋላ እስካሁን ያለው ሁኔታ አጠር ባለ አገላለፅ ሲቀመጥ“ቢድዓው ባላባት፤ ሱናው ጢሰኛ የሆነበት ነበር”፡፡ ይህ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከታሪክ እንደምናገኘው ሙስሊሞች እንዲህ መከፋፈላቸውናመለያየታቸው ከእርስበርስ ንትርክና ግጭት አልፎ ለውጪ ጠላት ሲያሳጣቸው ቆይቷል፡፡ ለጠላት መቀለጃና መጫወቻም አርጓቸዋል፡፡
ከክፍለ ዘመናት በፊት አድብተው የሙስሊሞችን መዳከም ይጠብቁ የነበሩት ሞንጎሎችበዒራቅ የፈፀሙትን ዘግናኝ ድርጊት ማስታወስ ብቻ ለዚህ በቂ ነው፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 500 ዑለሞችን የፈጁት እነኝህ አውሬዎችሙስሊሞችን ለመጨረስ ከመምጣታቸው በፊት ግን አስቀድሞ ሁኔታውን ያመቻቸላቸው በወቅቱ ሱኒይ በነበረው ኸሊፋ እምነት ተጥሎበት ሚንስትርየተደረገው “ሺዓ” ባለመዋል ነበር፡፡ ይህ ለሱኒች የመረረ ጥላቻ ያለው  መሰሪ የመንግስትን ወታደሮች በትኖ ከጨረሰ በኋላ ሙስሊሞች የተዳከሙበትን ወቅትጠብቆ ለሞንጎሊያው መሪ “ሁላጉ” የፈለገውን መጥቶ መፈፀም እደሚችል የሚያበስር ደብዳቤ ፃፈለት፡፡
ሞንጎሎች በሙስሊሞችን መናገሻ ዒራቅ(ባግዳድ) ሲገቡ ሃግ ያላቸው ጠንካራሰራዊት አልነበረም፡፡ ያኔ የፈፀሙትን ግፍ ግን ብእር ሊከትበው የማይቻለው አረመኔነት ነበር፡፡ እርጉዝ እናትን ከሆዷ ፅንስ ቀዶእስከማውጣት የሚዘገንኑ ጭካኔዎችን የፈፀሙት ሞንጎሎች ርህራሄ ቢስነታቸውን ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል፡፡ በኤፍራጠስና ጢግሮስ ወንዞችላይ የፈፀሙትስ … አንደኛው ወንዝ ቀለሙ በደም እስኪለወስ በሙስሊሞች ሬሳ ሲሞላ ሌላኛው ደግሞ እጅግ በርካታ ኪታቦች ተጥለውበትየወንዙ መልክ በኪታቦቹ የብእር ቀለም ተለውጦ ነበር፡፡ አላሁ ሙስተዓን!
በሙስሊሞች መዳከም ምክንያት በየዘመኑ ሙስሊሞች ግዛታቸውን እየተነጠቁ ወደ ኋላ ማፈግፈግ ስራቸው ሆነ፡፡ ሌላው ቀርቶበሶሀባዎች የተከፈተው ኢየሩስሌም(አል-ቁድስ) በአውሮፓውያን መስቀለኞች አደጋ አንዣበበት፡፡ አንዴ ሲነጠቅ ሌላ ጊዜ ሲመለስ ዘመናትነጉደው ዛሬ በኛው ሙስሊሞች መቆራቆስና መዳከም ምክንያት ሶስተኛው ቅዱስ መስጊድ(አል-አቅሷ) የሚገኝባት ኢየሩሳሌም ከእኛ እጅተፈልቅቃ በአረመኔዎቹ የሁዳዎች ስር ወደቃለች፡፡ አሁንም ግን “ዋይ” የሚል ጠፍቷል!
ለ800 አመታት በኢስላማዊ ስርአት የኖረችው “አንደሉስ” ወይም የአሁኗ ስፔን በሙስሊሞች መፈረካከስ ምክንያት በከሀድያንእጅ መግባቷ ሙስሊሞች ብርቅዬውን የሶሀቦች ፋና ለቀው በእንግዳ ተግባራት በመጠመዳቸው ከተሰለጠባቸው ውርደት አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱስፔንን የተቆጣጠሩት ከሀድያን በሙስሊሞች ላይ እጅግ አረመኔነት የተሞላበት የዘር ጭፍጨፋ አከናወኑ፡፡ ብዙዎችን እንዲሰደዱ አድረገውየቀሩትን ግን ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ከነህይወታቸው አቃሉ፡፡ አንድም ኢስላማዊ ፋና በስፔን ላይ እንዳይታይ አድርገው ታሪክን ለማጥፋትምሞክሩ፡፡ ይሁ ሁሉ ሲሆን በመሀከለኛው ምስራቅ የገነነው የኦቶማን ቱርክ መንግስት ምንም አልፈየደም፡፡
ምንም እንኳ በመካከለኛው ዘመን ገናና የነበረው የኦቶማን ቱርክ አስተዳደር እጅግ ሰፊ ግዛትን ቢቆጣጠርም እንደቀደሞዎቹየሰለፎች ዘመን በኡማው መካከል ውስጣዊ አንድነትና የልብ መተሳሰርን ማስረፅ አልተቻለውም ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው አስተዳደርከጊዜ ወደ ጊዜ እራሱን በሱፊያ የቢድዓ አረንቋ ውስጥ በመዝፈቁ ጭራሽ ለሙስሊሞች መለያየት አይተኛ ምክንያት ሆነ፡፡ በዲን ላይአዳዲስ ተግባሮች እንደ አሸን ፈሉ፡፡ ሀግ ባይ ያጡት “ሙብተዲኦች” መዳረሻቸውን በሚስደነግጥ ሁኔታ በአረቢያ ምድር ቀብሮችና ግኡዛንንተመላኪ ማድረግ ሆነ፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታም ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ያስወገዱት ሽርክ የቢድዓን ዱካ ተከትሎ ገባ፡፡ “ውሻበቀደደው ጅብ ይገባል” አይደል የሚባለው፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እራሱን በቅንጦት አለም የሚሽሞነሙነው የኦቶማን መንግስት ብዙ አላዋቂዎች ለሰመጡበት ሀይማኖታዊ ዝቅጠትደንታ ያለው አይመስልም ነበር፡፡ እንዳውም እራሱ የገባበት ልክ የለሽ ቢድዓ ኢስላማዊ ማንነቱን አስረስቶት ሌላ እንዲመኝ አደረገው፡፡በራስ መተማመን የከዳቸው የኦቶማን ሱልጣኖች እራሳቸውን ከምእራባውያን ባህል ጋር ለማቀራረብ የሙስሊሞች መገለጫ የነበሩትን ትውፊቶችበምእራባውያን ባህል ቀየሩ፡፡ የሙስሊሞች ኩራት የነበረው የኦቶማን ሱልጣኔት ኢስላምን አፈረበት፤ እኛ ሙስሊሞችም ታሪክን ባገላበጥንቁጥር በኦቶማን ሱልጣኔቶች ስራ መሸማቀቅ ልምዳችን ሆነ፡፡
ይባስ ብሎም በሀያኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ የአንደኛውን የአለም ጦርነት ተከትሎ ቱርክን የመታት ከባድ ሽንፈት በቢድዓለላቀጡት ሱልጣኖች ግብአተ መሬት መፋጠን አይነተኛ ምክንያ ሆነ፡፡ ኋላ ላይም በቱርክ የገነነው ሙስጠፋ አታቱርክ ለውድቀታችን መንስኤነው ያለውን ኢስላምን አምርሮ በመጥላቱ ቱርክ በኢስላም እንዳልገነነች ከሀገሪቱ ምድር የኢስላምን ስብእና ገፈፈ፡፡ ዛሬ ድረስ ከዘናአምስት በመቶ በላይ ሙስሊሞች በሚኖሩባት ቱርክ ኢስላም ዝቅ እንዲልም ምክንያት ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን በሀገሪቱ የተንሰራፉት ሱፊዮችሁሉን ነገር እንደድራማ ከመከታተል ውጪ የሰሩት የረባ ስራ አልነበረም፡፡ 
የሙስሊሞችን አንድነት ፈረካክሶ ኋላ ላይ አይማሬ የሆነውን ሽርክ ያስገባው ቢድዓ ጉዱ በዚህ አላበቃም በቀጣዩ ክፍልእንገናኝ 
------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ባሳለፍናቸው ክፍሎች ስለአንድነት አስፈላጊነት፣ የአንድነት ፀሮችና የነበረውን ታሪካዊ ዳራ በጥቂቱ ቃኝተናል፡፡ ቀጣዩንክፍል እነሆ …
ጥቂት የማይባሉ ሙስሊሞች ሽቅብ በእድገት እንዳይወጡ የተማማሉ ይመስል ከሰለፎች ዘመን አንስቶ ቁልቁል በውርደት መንደርደሩንመያያዛቸውን እያየን ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በመካከለኛው ዘመን/Dark Age/ በውርደት አዘቅት ውስጥ የከረሙት ምእራባውያንዳግም በኢንዱስትሪ አብዮት አንሰራርተው አለምን በጭብጣቸው ማስገባት ይዳዳቸው ጀመር፡፡ የሙስሊሞችን እርስ በርስ መባላት ያስተዋሉትምእራባውያን ጊዜው አሁን ነው በማለት ልክ አፍሪካን በቅኝ ግዛት እንደተቀራመቱት በንትርክ የደነዘዙትን አረቦችንም ተረባረቡባቸው፡፡በመሆኑም እያንቀላፋ በነበረው የኦቶማን ቱርክ ቁጥጥር ስር የነበሩ ብዙ ግዛቶች ለምእራባውያኑ ሲሳይ ሆኑ፡፡ ገናና የነበሩ ኢስላማዊስልጣኔዎች በነጮች ወረራ ቆሸሹ፡፡ አውሮፓውያን የሙስሊሞችን መሬት ተቀራመቱ፡፡
በወቅቱ ምእራባውያን ያሻቸውን ያክል ጥቅም ሲያጋብሱ ጎን በጎን ፀያፍ የሆነውን ባህላቸውን በአረቦች መሀል እያሰራጩነበር፡፡ ዳግም ሙስሊሞች እንዳያንሰራሩ በሚል እሳቤም ኢስላማዊ ሸሪዓ እንዳይነግስ ያሴሩ ነበር፡፡ ለዚህም የእነርሱን ሶሺያሊዝምአሊያም ካፒታሊዝም ቀድሞም በቢድዓ ሰክሮ ለነበረው ትውልድ በማጠጣት ከኢስላም ይልቅ ከከሀድያን የተወረሱ አፍካሮች በሙስሊሞች አእምሮላይ እንዲገኑ አደረጉ፡፡
ከሀድያኑ አሰራራቸውን ለውጠው ሲለቁም ሙስሊሞችን በሀገራት ከፋፍለው እርስ በርስ አጋጭተው ነጎዱ፡፡ ድሮውንም “አንኳንምዘንቦብሽ…” የነበሩት ሙስሊሞች ጭራሹን ከምእራባውያን ቅኝ ግዛት በኋላ እጅግ ተከፋፈሉ፡፡ በዘር፣ በጎሳ፣ በሀገር አንዲሁም በምእራባውያንመጤ አስተሳሰቦች ተቧድነው ተለያዩ፡፡ ካፒታሊዝም፣ ኮሚውኒዝም፣ ሶሺያሊዝም፣ ባዝ ሌላም ሌላም የንትርክ በሮች ተከፈቱ፡፡ 
የምእራባውያን አመለካከት አፍቃሪዎች ሸሪዓን በመስጂድ የተገደበ በማድረግ ፖለቲካውን በነጮች አስተሳሰብ እንዲቃኝ አደረጉ፡፡ከጥቂት አረብ ሀገራት በስተቀር ሌሎቹ ኢስላማዊ መንግስትን አንቅረው ተፉ፡፡ በመሆኑም መፈንቅለ መንግስት፣ አብዮት፣ አመፅ፤ ሰልፍእና የመሳሰሉት ተግባራት እንደጀብድ ተቆጥረው ደም መፋሰስ አመል ሆነ፡፡
በአረቦችም ሆነ በሌሎች ሙስሊሞች መካከል ምእራባውያን የሚያጃጅሉበትን የሆነውን ዲሞክራሲ ተቀብለው የሚዘምሩ በረከቱ፡፡ጭራሽ የከሀድያን አካሄድ የሆነው ዲሞክራሲ ፍቱን የሰውልጅ መድሀኒት ተደርጎ ቀረበ፡፡ ቀድሞውኑ ከዲናቸው በርግገው የሸሹ አላዋቂዎችምካሉበት ማጥ ለመውጣት ሲሉ አሜን ብለው ተቀበሉት፡፡ ሻል አልን ያሉት ሙስሊሞች ደግሞ ዲሞክራሲን ከኢስላም በመቀየጥ መርዙን በማርለወሱ፡፡ ድሮስ ይህ እንደሚከሰት ነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) ጠቁመውን አልነበር …
“ከእናንተ በስተፊት የነበሩትን(ህዝቦች) ፈለግ ኮቴ በኮቴ ትከታተላላችሁ የወከሌ(አርጃኖ)ጉድጓድ እስኪገቡ ድረስ (እናንተም) ትገቡታላችሁ” ሶሀባዎችም “የየሁዳና የክርስቲያኖችን (ፈለግ) ነውን?” አሉ፡፡ ነቢዩም(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) “ታዳያ የማንን ነው?” በማለት አረጋገጡ፡፡ ቡኻሪናሙስሊም ዘግበውታል
አዎን! የሀያኛው ክፈለ ዘመን ከየትኛውም ግዜ በተለየ መልኩ ሙስሊሞች እጅግ የተከፋፈሉበት ነበር፡፡ በቅኝ-ግዛት አረቦችንይዘው የነበሩት ምእራባውያን የኦቶማን ቱርክን መንግስት ለማዳከም ነጥቀው ያዩዙበትን መሬት በድንበር ሸንሽነው በሀገራት በመከፋፈልአንድ ሆኖ የቆየውን የሙስሊሞች ስብስብ ዛሬ እንደምናየው ለብዙ ሀገራት ከፋፈሉት፡፡ የብዙ ሙስሊሞች በምእራባውያን ባህል መዋጥእንዲሁም ሻል ያሉትና ዲን ይዘዋል የተባሉት ደግሞ በቢድዓ እና መጤ ፍልስፍናዎች ባተሌ መሆን ሙስሊሞች እነዚህን ድንበሮች ሰብረውለአንድነታቸው እንዳይተጉ እግር ከወርች አሰራቸው፡፡
የሚገርመው ለብዙ የተከፋፈሉት እነዚሁ ሙስሊም ሀገራት አሁንም ሰላም ሁነው መቀጠል አለመቻላቸው ነው፡፡ ምክንያቱም በአረቦችአካባቢ የሚገኘው ግዙፍ ተፈጥሮአዊ ሀብት እና የቦታው ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያቋመጣቸው ከሀድያን በእጅ አዙር ፍላጎታቸውን ለማሳካትአረቦችን ማተራመስ መጀመራቸው ነው፡፡ ቀድመው ካበጁት አሻጥራቸው ጋር በሚስማማ መልኩ ሙስሊም ሀገራት በመካከላቸው ሰላም እንዳኖራቸውባስ ሲልም በገዛ ሀገራቸው ውስጥ ሳይቀር እርስ በርስ እዲጣመዱ በማድረግ ሙስሊሞች ሲጠዛጠዙ ከሀድያኑ ያለከልካይ የሙስሊሞችን ንብረትመበዝበዙን ተያያዙት፡፡ ይኸው አልበቃ ሲላቸው ደግሞ ምስኪኑን ሙስሊም እያፋጁ መልሰው እናስማማለን በማለት ራሳቸውን ፈላጭ ቆራጭየአለም ዳኞች አደረጉ፡፡ የዋህ ሙስሊሞችም በከሀድያን ለሚሰራው ድራማ ተዋንያን በመሆን ያለክፍያ ደምና ክብራቸውን ይገብሩ ያዙ፡፡ወይ ነዶ!
ይህን እጅግ የሚያስመርርና የሚያበሽቅ ስራ የተመለከቱና ለዲናችን ተቆረቆርን ያሉ የዋሆች ደግሞ ሌላ ጣጣ አመጡ፡፡
ድሮ በሰለፎች ግዜ ሙስሊሞች ሀያል እንደነበሩት፣ አለምን በተውሂድ እንዳጠመቁት፣ ብዙ ግዛትን በሸሪዓ እንዳስተዳደሩትሁሉ ዛሬም ያንን ምርጥ ዘመን መመለስ የፈለገ ያለጥርጥር እነዛ በነቢዩ(ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) አንደበት ምርጥ የተባሉትን የሰለፎችመንገድ መያዝ ይገባው እንደነበር ያልተረዱ ግልቦች ወደ ሰለፎች አካሄድ መመለስን ኋላ ቀርነት አደረጉና የበላይነትን ለኢስላም እንለግሳለንብለው ዘመን አመጣሽ አዲስ አካሄድ ፈለሰፉ፡፡ ደሞ ሌላ ቢድዓ!
የዛሬ ዘጠና አመት ገደማ ነበር በሰለፎች መንሀጅ መብቃቃት መፍትሄ አልመስል ያላቸው በእውቀት ያልበለፀጉ አፈቀላጤዎችእንደ አመለካከታቸው እየተቧደኑ ደጋፊ

Post a Comment

0 Comments