Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

አላህ ያልታመፀበት ቀን ሁሉ ዒድ ነው


“አላህ ያልታመፀበት ቀን ሁሉ ዒድ ነው!!”
ሁሌ በዒድ ኑር፡፡ “ምነውሳ ያለን ዒድ ሁለት ብቻ ሆኖ ሳለ እንዴት ሁሌ በዒድ መኖር ይቻላል” ትል ይሆናል፡፡ እንግዲያውስ ሐሰኑልበስሪ ረሒመሁላህ ይንገሩህ፡- “አላህ ያልታመፀበት ቀን ሁሉ ዒድ ነው!!” (ለጣኢፉልመዓሪፍ፡ 278) እናም የምልህ ከወንጀል ራቅ ነው፡፡ አመቱ በአል ይሆንልህ ዘንድ የአላህን ትእዛዝ አክብር፡፡ እኩይ ምግባርን የምትንቅ፣ በርካሽ ነውሮች የምትሸማቀቅ፣ ሰናይ ምግባርን የምታደንቅ ከሆንክ እንኳን ደስ ያለህ! አንተ ሰላማዊ ህይወት እየመራህ፣ ጣፋጭ ጊዜ እያሳለፍክ ነው! ዒዱን ሰዒድ! ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “መልካም ስራው ያስደሰተው፣ መጥፎ ስራው ያስከፋው፣ እሱ ነው ከናንተ አማኙ!” ይላሉ፡፡ አዎ ወላሂ! በመልካም መደሰት፣ በመጥፎ መከፋት ምንኛ መታደል ነው! ትልቅ ፀጋ! ስንቱ ነው በዝሙቱ፣ በዘፈኑ፣ በመጥፎ ስራ የሚደሰተው? ስንቱስ ነው በሶላቱ በዘካው የሚከፋው ወይም እየከፋው የሚፈፅመው?? ልቦናው በሰኪና ተሞልቶ፣ ህሊናው በኢማን ተረጋግቶ የአላህን ትእዛዝ የሚጠብቀውማ፣ ከክልከላው የሚርቀውማ ሁሌ እርካታ ላይ ነው፣ ሁሌም ዒድ ላይ ነው፡፡ ይሄን ስልህ ግን እንደነንቶኔ “የወሩ ገብረኤል፣ የአመቱ ማርያም፣ …” እያልክ አመቱን በበኣላት እንድታጨናንቅ እየሰበክኩህ እንዳይመስልህ፡፡ እነሱማ ዛሬ እንኳ በመንግስትም በሚዲያም ብዙ ንቃት ተፈጥሮም `ሀይማኖተኛ` የሆኑቱ በአላት ማጨናነቁን አልተዉትም፡፡
ኧረ የነሱ ነገር ተከድኖ ይብሰል! አስታውሳለሁ ልጅ እያለሁ አንዱ አስተማሪ በበአል ሰክሮ ሲጨፍር ቴፑን ይሰብራል፡፡ ስካሩ ሲከዳው ጊዜ አጅሬ አጉል ቁጭትና ብስጭት ጀመረ፡፡ (ግዴላችሁም ለኸይር ነው፡፡) ብስጭቱን በድፍረት መግለፅ ያዘ፡፡ “ዝም ብለው በአል እያበዙ ቴፔን አሰበሩኝ!” “በአመት ሁለት በአል በቂ ነው፡፡ በቃ!!” እያለ ማጉተምተም ያዘ፡፡ ይሄው ሰበብ ይሁነው ሌላ ምክኒያት ይኑር በውል አላስታውስም ብቻ ብዙም ሳይቆይ ሰለመ! አልሐምዱሊላህ፡፡
የማይረሳኝ ገጠመኝ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ መምህራችን ስለ አህመድ ኢብኑ ኢብራሂም ማለትም አህመድ “ግራኝ” ጊዜ የሙስሊሞችና የክርስቲያኖች ጦርነት ያስተምራል፡፡ አንድ ከታች ክፍል ጀምሮ ያለመሰልቸት የሚነሳ የተለመደ ጥያቄ ጠየቀን፡፡ “በዚያን ጊዜ የተከሰተው የሙስሊሞችና የክርስቲያኖች ጦርነት ምን መሰረታዊ ለውጥ አስከትሏል” የሚል፡፡ ተሜ የተለመደ መልሱን መደርደር ተያያዘው፡፡ “ቅርስ ወደመ” ሲሉት “ሌላ” ይላል፡፡ “ብዙ ህዝብ አለቀ” ሲሉት “ሌላ” ይላል፡፡ “ቤተ-ክርስቲያን ተቃጠለ” ሲሉት “ዝም በሉ! ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም መስጊዶች ሲቃጠሉ ነበር፡፡ ይልቅ ሌላ መሰረታዊ ለውጥ ንገሩኝ” አለ፡፡ እና ምን መልስ ይሰጠው? ተማሪ ከታች ጀምሮ ሲጠጣ የኖረው ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደለ ታሪክ ነው፡፡ ከታች ክፍል የመጡት መልሶች ደግሞ አለቁ፡፡ አስተማሪው ግን “ሌላ መሰረታዊ ለውጥ” እያለ አጥብቆ እየጠየቀ ነው፡፡ ለካስ እሱ ከዚያ ከተለመደ ጥያቄ የሚጠብቀው እኛ ሰምተነው የማናውቀው ያልተለመደ መልስ ኖሯል፡፡ እሺ ይሁን፡፡ ተሜ ከየት ያምጣው? እስፖንጅ የያዘውን አይደለ እንዴ የሚተፋው? ከኛ ተስፋ የቆረጠው መምህር ድንገት ወዳላሰብነው አቅጣጫ ወሰደን፡፡ “ዛሬ ቀኑ ማነው?” አለ፡፡ ምን እንደመለሱለት ረሳሁት፡፡ “ቆይማ ከአንድ እንጀምር” አለ፡፡ “በአንድ ምንድን ነው?” ሲል “ልደታ” አሉት፡፡ “በሁለትስ?” ሲል “የሆነ ነገር” አሉት፡፡ እሱ ሲቆጥር እነሱ በአሉን ሲነግሩት እሱ ሲቆጥር እነሱ በአሉን ሲነግሩት 18 ደረሰ፡፡ “በ18 ምንድን ነው?” ሲላቸው “የለም” አሉት፡፡ “አንድ የስራ ቀን አገኘን” አለ፡፡ (አለች ነገር) አሁንም ቆጠራው ቀጥሏል፡፡ 22 ሲደርስ “የለም” አሉት፡፡ “ሁለት የስራ ቀን አገኘን” አለ፡፡ (በቅንፍ ውስጥ 18 እና 22 እራሱ እነሱ እንዳሉት ክፍት የስራ ቀናት እንዳልሆኑ ኋላ አውቄያለሁ፡፡) ቆጠራውን አቆመና “እርግጠኛ ነኝ ደብተራ ቢመጣ ሰላሳውንም ይገጥመዋል!” አለ፡፡ ከዚያም ድንገት ወደሙስሊሞቹ ዞረ፡፡ “እ አንተ ጎበዝ! በኢስላምስ ስራ የማይሰራው መቼ ነው?” አለ፡፡ “የማይሰራበት የለም!” ሲባል ጊዜ “የስ! ኢቭን ጁሙዐ! ሰግደህ ተበተን ነው የሚለው! ኢስላም ለስራ ፍሌክሲብል የሆነ ሃይማኖት ነው!!” አለ፡፡ ሌሎቹ ተንጫጩ፡፡ “እንዴ ቲቸር! የኛም እኮ እነዚህ ሁሉ በአላት መፅሀፍ ቅዱሳዊ አይደሉም” አሉት፡፡ ዝም በል! ለኔ ነው የምትነግረኝ! ከትግራይ ነው የመጣሁት! እንኳን ክርስቲያኑ ሙስሊሙ ሲሰራ እራሱ መቅሰፍት ልታወርዱብን ነው” እያሉ የሚቃወሙ አውቃለሁ፡፡ ይልቅ አዳምጡ፡፡ በዚያን ጊዜ የተካሄደው ጦርነት ይሄ የደገኛው ባህል እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡ ቆለኛው ሙስሊም ወደ ደጋ ሲመጣ እነዚህን ባእላት ስለማያውቅ ቀንን ከቀን ሳይለይ አመቱን መስራት ያዘ፡፡ ህዝቡም በነዚህ በአላት ምክኒያት ከቤቱ ይውል የነበረውን በሂደትም እያላላው ሄደ፡፡ (በነገራችን ላይ ሰውየው ሙስሊም አይደለም!!)
ወይ የኔ ነገር ላወራ የነበረው እኮ ስለዚህ አልነበረም፡፡ በቃ ልመለስ፣ ሙስሊሙ ወገኔ ሆይ ህይወትህን በአል አርገው፤ ደስታ ዝራበት፣ በዒባዳ ርካበት፣ በተቅዋ ሽክ በልበት፡፡ ከልብስ ሁሉ በላጩ የተቅዋ ልብስ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ በአልህንም ህይወት አርገው፡፡ አብዛው፡፡ ዛሬም በአል ነገም በአል፡፡ አስተውል እያወራሁህ ያለሁት ስለ ጋርዶ መቀመጥ አይደለም ወይም ስለሁሌ መቅበጥበጥ አይደለም፡፡ ይህን እማ ታውቃለህ
- በአልህ ሰርክ ቡና እያንቃረርክ ወሬ የምትሰልቅበት አይደለም፡፡
- በዐልህ ደን እየጨፈጨፍክ እያቃጠልክ አገር የምታመክንበት አይደለም፡፡ ግን በአል እየጠበቁ ደን የሚጨፈጭፉት ሙስሊሞች ቢሆኑ ኖሮ እነ እንቶኔ ምን ይሉ ነበር
- በአልህ ሰክረህ እየተንገዳገድክ በየመንገዱ እያደርክ ፀያፍ ቃላትን እየወረወርክ ስብእናህን የምታረክስበት አይደለም
- በአልህ “ጭር ሲል አልወድም” እያቅራራህ ሰፈር የምታብጥበት፣ አላፊ አግዳሚ የምታስቸግርበት አይደለም
- በአልህ ጥንብዝ ብለህ ገብተህ ሚስትና ልጆችህን እያተራመስክ ለጎረቤት አዛ የምትሆንበት፣ ቤተሰብ የምታስመርርበትና የምታሳፍርበት አይደለም፡፡
- በአልህ እስከ ጥንቢራህ በልተህ እንዳትታመም ከወዲሁ በሬዲዮ በቴሌቪዥን አደራ የምትወተወትበት የጤና ተቋማትን የምታጨናንቅበት አይደለም፡፡
- በአልህ ዘመድ ጎረቤትህን ረስተህ የራስህን አለም ብቻህን የምትቀጭበትም አይደለም፡፡
ይልቁንም በአልህ እየሰራህ የምትደሰትበት፣ እየተደሰትክ የምትሰራበት፣ ለጎረቤት፣ ለዘመድ፣ ለምስኪን እየራራህ የምትረካበት፣ እየረካህ የምትራራበት፣ እየተንበሻበሽክ የምታመልክበት፣ እያመለክ የምትንበሻበሽበት… እየሳቅክ፣ እየተደሰትክ፣ እየሰራህ፣ እየበላህ፣ እየጠጣህ ዘና የምትልበት ነገር ግን ከሸሪዐው አጥር የማትዘልበት ሁሉ ነገር ሚዛኑን የሚጠብቅበት ስርኣት ነው፡፡ እንጂ ዒድ ማለት ከእስር እንደተፈታች ጥጃ ያለገደብ የምትፈነጥዝበት፣ ያለስርኣት የምትዘልበት አይደለም፡፡ ይልቅ ዒድ ማለት ባጭሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አላህን የማምለክ ስርኣት ነው፡፡ የዋህ ሰው ውዱእ አርጎ ሶላት ከመቆም፣ ዘካ ቆጥሮ ከመክፈል ያለፈ ዒባዳ ያለ አይመስለውም፡፡ ሊያውም ዝንግት፣ ትክት ብሎ ለሚፈፅመው፣ በእዩኝ ስሙኝ ለሚያጅበው ዒባዳ፡፡ ብልጥ ሰው ግን ፆምና ሶላቱን ብቻ ሳይሆን እንቅልፍና ምግቡን ሳይቀር ኒያውን አሳምሮ የኢኽላስ ማሽን ተጠቅሞ ወደ ዒባዳ ይቀይራል፡፡ እናም ጊዜህን ሁሉ ዒድ አርገው ስልህ ህይወትን የኢባዳ መስክ አድርገህ ትንሽ ትልቅ እንቅስቃሴህን አላህን እያሰብክ ኒያ ጋር እያቆራኘህ ታታሪ እንድትሆን እንጂ ህይወት ለምኔ ስራ ለምኔ ብለህ አለም በቃኝ እንድትመንን አይደለም፡፡
ተቀበለላሁ ሚና ወሚንኩም ሳሊሐልአዕማል!