Header Ads Widget

Ticker

6/recent/ticker-posts

ዒድን በሚመለክት ወሳኝ ነጥቦች

******ዒድ ህግጋትና ስርአቱ******
በኢስላም አመታዊ በአሎቻችን ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ዒደልፊጥርና ዒደልአድሐ፡፡ የመጀመሪያው ረመዳን እንዳለቀ ወርሃ ሸዋል የመጀመሪያ ቀን ላይ ይውላል፡፡ ሁለተኛው - ዒደልአድሐ- ደግሞ ወርሃ ዙልሒጃ በ10ኛው ቀን ላይ ይውላል፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም መዲና ሲገቡ የመዲና ሰዎች የሚጫወቱባቸው ሁለት በአላት ነበሯቸው፡፡ “ምንድን ናቸው እነኚህ ቀናት?” ሲሉ ጠየቁ መልእክተኛው ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም፡፡ እነሱም “ከጃሂሊያህ ዘመን ጀምሮ የምንጫወትባቸው ቀናት ናቸው” ብለው መለሱ፡፡ ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም “አላህ ከነሱ በተሻሉ ቀናት ተክቷችኋል፡- በአድሐ ቀን እና በፊጥር ቀን” አሉ፡፡ (ሶሒሕ አቢዳውድ፡ 1039)
ጥቂት ስለዒድ፡-
1. ቀኑ የደስታ ቀን ነው፡-
1.1. የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መለዋወጥ ከሶሐቦች ተገኝቷል፡፡ (አልፈታዋ፡ 24/253)
1.2. ልጃገረዶች እየዘፈኑ መጫወት ይችላሉ፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
1.3. እለቱ የደስታ የፈንጠዝያ፣ የመብያና የመጠጫ ቀን ነው፡፡ (ሶሒሕ አትቲርሚዚ፡ 777)
1.4. ስለሆነም ቀብር ዚያራና የመሳሰሉ የእለቱን የደስታ ድባብ የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን መፈፀም አይፈቀድም፡፡ (አልኢብዳዕ፡ 263)
1.5. የምንደሰትበት ግን ፈፅሞ በሀራም ነገር መሆን የለበትም፡፡ “የትም ብትሆን አላህን ፍራ!” የሚለው ሐዲሥ አይረሳ፡፡
2. ተክቢራ፡-
2.1. የሚባልበት ጊዜ፡- በዒደልፊጥር የሸዋል ጨረቃ ከታየች ጀምሮ የዒድ ሰላት እስከሚሰገድ ድረስ ሲሆን በዒደልአድሐ ደግሞ ዙልሒጃ 1 ካለ ጀምሮ እስከ አያመትተሸሪቅ መጨረሻ (ዙልሒጃ 13) ድረስ ነው፡፡
2.2. የዒደልአድሐውን በተመለከተ ከዐረፋ ቀን ፈጅር ሰላት አንስቶ እስከ ዙልሒጃ 13 ዐስር ድረስ ከግዴታ ሰላቶች በኋላ ተክቢራ ማድረጉ ከሶሐቦች የተገኘና ኢጅማዕ (ወጥ ስምምነት) የመጣበት ጉዳይ ነው፡፡ (አልኢርዋእ፡ 653) (አልፈታዋ፡ 5/427) በዒደልፊጥር ጊዜ ከግዴታ ሶላቶች በኋላ ተክቢራ ማድረጉ በቂ ማስረጃ የለውም፡፡
2.3. አደራረጉ፡- ሁሉም በየፊናው እንጂ አንዱ እያወጣ ሌሎች በመከተል በህብረት ባንድ ድምፅ አይባልም፡፡ (መጅሙዑፈታዋ ኢብኑ ባዝ፡ 13/21) ባይሆን ይሄ ጉዳይ በዑለማዎች የተለያየ ሀሳብ የተሰነዘረበት ፊቅሃዊ ጉዳይ እንደመሆኑ አላስፈላጊ ንትርክና ልዩነት ውስጥ እስከሚያስገባ መድረስ የለበትም፡፡
2.4. ድምፅን በተክቢራ ከፍ ማድረግ የተወደደ ነው፡፡ (ሶሒሑልጃሚዕ፡ 4934)
2.5. አንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታየው በተክቢራ ሙሉ ሌሊቱን ሳይተኙ ማሳለፍ፣ ሰፈር ጎረቤቱን በከፍተኛ ድምፅ ማወክ ማስረጃ የሌለው ስራ ነው፡፡ “የሁለቱን ዒድ ሌሊቶች ነቅቶ ያደረ ልቦች በሚሞቱበት ቀን ልቡ አይሞትም” የሚለው “ሐዲሥ” በነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ የተቀጠፈ እንጂ ጤነኛ አይደለም፡፡ (አድዶዒፋህ፡ 520)
2.6. ከሶሐቦች የተገኙ የተክቢራ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው
- (አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ ላኢላሀኢለላህ፣ ወላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ ወሊላሂልሐምድ)
- (አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ ላኢላሀኢለላህ፣ ወላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ ወሊላሂል ሐምድድ)
- (አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር ከቢራ፣ አላሁ አክበር ወሊላሂልሐምድ፣ አላሁ አክበር ወአጀል፣ አላሁ አክበር ወሊላሂል ሐምድ)
- (አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር፣ አላሁ አክበር ከቢራ፣ አላሁ አክበር ወሊላሂልሐምድ፣ አላሁ አክበር ወአጀል፣ አላሁ አክበር ዐላ ማ ሀዳና)
- (አላሁ አክበር ከቢራ፣ አላሁ አክበር ከቢራ፣ አላሁ አክበር ወአጀል፣ አላሁ አክበር ወሊላሂልሐምድ)
2.7. እነዚህን ተክቢራዎች ማለት በጀማዐ ለሰገደም ብቻውን ለሰገደም የተወደደ ነው፡፡ ግዴታ ግን አይደለም፡፡ (ሸርሑልሙምቲዕ፡ 5/165)
3. ወደ መስገጃው ቦታ መውጣት፡-
3.1. ወደ መስገጃ ቦታ ሲወጣ መታጠብን፣ ሽቶ መቀባትን የሚመለከት ከሶሐባው ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር ተገኝቷል፡፡ (አልኢርዋእ፡ 104) ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ግን ምንም የለም፡፡
3.2. በእለቱ አቅም በፈቀደ ባማረ ልብስ ሽክ ማለት ተወዳጅ ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
3.3. ለቻለ ሰው ወደ መስገጃው ቦታ በእግር መሄዱ ሱና ነው፡፡ (አልኢርዋእ፡ 636)
3.4. የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች ወደ መስገጃው ሜዳ መውጣታቸው ከሱና ነው፡፡ ከመስገጃው ቦታ ግን ገለል ይላሉ፡፡ (ቡኻሪ) ሴቶች ወደመስገጃው ቦታ ሲወጡ ሽቶ ከመቀባትና ካላስፈላጊ አለባበስ መራቅ አለባቸው፡፡
3.5. ስጋትና እንቅፋት ከሌለ ልጆችም ሊወጡ እንደሚችሉ የሚጠቁም ማስረጃ አለ፡፡ (ቡኻሪ፡ 977) ባይሆን ሰጋጆችን እንዳይበጠብጡ ወላጆች ሊቆጣጠሯቸው ይገባል፡፡
3.6. ከመስገጃው ቦታ ሲመለሱ መንገድ ቀይሮ መመለሱ በላጭ ነው፡፡ (ቡኻሪ)
4. የዒድ ሰላት፡-
4.1. ሶላቱን በተመለከተ ከዑለማዎች ሚዛን የሚደፋው አቋም “ግዴታ ነው” የሚለው ነው፡፡
4.2. ወቅቱ፡- ፀሀይ ወጥታ የጦር ቁመት ያክል ከፍ ካለች ጀምሮ ፀሀዩዋ በአናት ትይዩ እስከምትሆን ድረስ ያለው ነው፡፡ የዒደልፊጥር ሰላት ዘግየት የዒደልአድሐ ሰላት ደግሞ ፈጠን ቢል ተመራጭ ነው፡፡ (አትተልኺስ፡ 144) (ሙስነዱሽሻፊዒይ፡ 74) ምክኒያቱም የዒደልፊጥር ጊዜ ዘግየት ማለቱ ዘካተልፊጥር ለሚሰጡ ሰዎች ጊዜ እንዲኖራቸው ሲያደርግ የዒደልአድሐ ጊዜ መፍጠኑ ደግሞ ከሰላት ቶሎ ተመልሰው ኡዱሒያ የሚያርዱበት ጊዜ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡
4.3. የሚሰገድበት ቦታ፡- ካላስቸገረ ወጣ ያለ ሰፊ ሜዳ ላይ መሆኑ ሱና ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
4.4. ለዒድ ሶላት አዛንም ኢቃማም አይደረግም፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
4.5. የረከዐው ብዛት፡- 2 ረከዐ ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
4.6. የዒድ ሶላት ውስጥ ያሉት ተጨማሪ ተክቢራዎች ሙስተሐብ ናቸው፡፡
4.7. ቁጥራቸውም የመጀመሪያው ረከአ ላይ ከመክፈቻው ተክቢራ ውጭ 7 ጊዜ ሁለተኛው ረከዐ ላይ ደግሞ ከመነሻው ተክቢራ ውጭ 5 ጊዜ ተክቢራ ይደረጋል፡፡ የመጀመሪያውን 7 የሁለተኛውን ስድስትም ተገኝቷል፡፡ የመጀመሪያው 6 የሁለተኛው 5ም ተገኝቷል፡፡ 4፣ 11፣ 12፣ 13 ተክቢራዎችን ማለት እንደሚቻልም ከሰለፎች ተገኝቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ነገሩ ሰፊ እንደሆነና በሶሒሕ ማስረጃ በመጡት ሁሉ መስራት እንደሚቻል ያሳያል ይላሉ ሸይኹልአልባኒ ረሒመሁላህ፡፡ (አልኢርዋእ፡ 639)
4.8. በተጨማሪ የዒድ ተክቢራዎች ላይ እጅን ማንሳትን የሚመለከት ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተላለፈ ሶሒሕ ማስረጃ የለም፡፡ በዚህም ምክኒያት “እጅን ማንሳት አይገባም” ያሉ ዑለማዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከሶሐቦች፣ ከዐጣእ፣ አውዛዒ፣ አቡ ሐኒፋህ፣ ሻፊዒ፣ አሕመድና ሌሎችም ተገኝቷል፡፡ ነብዩም ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ደግሞ ጥቅል በሆነ መልኩ የሶላት ተክቢራዎች ላይ እጃቸውን ያነሱ እንደነበር ሶሒሕ ማስረጃ አለ፡፡ (ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 715) ኢማሙ ማሊም ይህን በተመለከተ አስገዳጅ ሱና ስለሌለ የፈለገ ያድርግ (የፈለገ ይቶወው) ይላሉ፡፡ (ሰዋጢዑልቀመረይን፡ 183)
4.9. በየተክቢራዎቹ መሃል የሚባልን ዚክር በተመለከተ ከነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም የተላለፈ ሶሒሕ ማስረጃ የለም፡፡ (ክፍተቱ ካለ) አላህን ማመስገንና በነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም ላይ ሰለዋት ማውረድ እንደሚቻል ከዐብዱላህ ኢብኑ መስዑድ ተገኝቷል፡፡ (አልኢርዋእ፡ 642)
4.10. የተክቢራዎቹን ቁጥር የተጠራጠረ እርግጠኛ የሆነበትን ዝቅተኛውን ይዞ ቀሪውን ይሞላል፡፡
4.11. ቂራአህ፡- ፋቲሐን መቅራት ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለኢማሙ ሱረቱል አዕላን እና ሱረቱል ጋሺያን ወይም ሱረቱልቃፍና ሱረቱልቀመርን መቅራቱ ከሱና ነው፡፡ (ሙስሊም)
4.12. ለኢማሙ በቂራአህ ድምፅን ከፍ ማድረግ ሱና ነው፡፡
4.13. የዒድ ሰላት ያለፈው ሰው ሳይሰላመት ከደረሰ ያገኘውን አብሮ ሰግዶ ያለፈውን ይሞላል፡፡ ከተሰላመተ በኋላ የደረሰ ደግሞ ካገኘ ከሰዎች ጋር ካልሆነ ብቻውንም ቢሆን ይሰግዳል፡፡ በሆነ ምክኒያት ወደ መስገጃው ቦታ መውጣት ያልቻሉ ከቤታቸውም ቢሆን መስገድ ይችላሉ፡፡ (ሶሒሑልጃሚዕ፡ 369)፣ (ቡኻሪ፣ተዕሊቅ፡ 2/471)
4.14. ከዒድ ሶላት በፊትም በኋላም ከመስገጃው ቦታ የሚሰገድ ሱና የለም፡፡ ቤት ከተመለሱ በኋላ ግን ነብዩ ሰለላሁ ዐለይሂ ወሰለም 2 ረከዐ ይሰግዱ ነበር፡፡ (ቡኻሪ)፣ (አልኢርዋእ፡ 3/100) የዒዱ ሶላት የሚሰገደው መስጂድ ውስጥ ከሆነ ግን መስጂድ እንደገባን የዒድ ሱና ሳይሆን “ተሒየተልመስጂድ” መስገድ አለብን፡፡
4.15. ዒድ መሆኑ ከእኩለ-ቀን በኋላ ከታወቀ በቀጣዩ ቀን ይሰገዳል፡፡ (ሶሒሕ አቢዳውድ፡ 1050)
4.16. ዒድድና ጁሙዐ በአንድ ቀን ከገጠሙ፡- የዒድ ሰላትን የሰገደ ሰው ጁሙዐ ሰላት ላይ የመገኘት ግዴታ የለበትም፡፡ (ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 984)
5. ኹጥባህ፡-
5.1. ኹጥባው የሚደረገው ከሰላት በኋላ ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)
5.2. ለኹጥባው ሚንበር ይዞ መውጣት ከሱና አይደለም፡፡ (ቡኻሪ፡ 956)
5.3. ኹጥባው አንዳንዶች እንደሚሉት አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ነው፡፡ ዝርዝር የፈለገ በዚህ ሊንክ ይግባ፡፡ HTTP://M-NOOR.COM/SHOWTHREAD.PHP?P=12245
5.4. ኹጥባውን ማዳመጡ የሚወደድ ቢሆንም ግዴታ ግን አይደለም፡፡ (ሶሒሑልጃሚዕ፡ 2289)
6. የዒድ ቀን ምግብ፡-
6.1. ዒደልፊጥርን እና ዒደልአድሐን መፆም ፈፅሞ አይፈቀድም!! (ቡኻሪና ሙስሊም) እንዲሁም ከዒደልአድሐ በኋላ ያሉትን ሶስቱን ቀናትም (አያመትተሸሪቅ) ሐጅ ላይ ሆኖ እርድ ያላገኘ ሰው ካልሆነ በስተቀር ለሌሎች መፆም አይፈቀድም፡፡ (ቡኻሪ) (አስሶሒሐህ: 3573)
6.2. በዒደልፊጥር ቀን ወደ ሰላት የሚወጣው ከተመገቡ በኋላ ነው፡፡ የዒደልአድሐ ቀን ግን ሳይመገቡ ወጥቶ ከሰላት በኋላ መመገብ ከሱና ነው፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም) (ሙስነድ አሕመድ፡ 23042)
6.3. በዒደልፊጥር የምንመገበው ተምር ቢሆንና በተናጠል በዊትር ብንበላው የነብዩ ዐለይሂሰላም ሱና ነው፡፡ (ቡኻሪ)
6.4. በዒደል አድሐ ቀን ከሶላት መልስ መጀመሪያ የሚፈፀመው መመገብ ሳይሆን ኡዱሒያን ማረድ ነው፡፡ (ሙስነድ አሕመድ፡ 23042)
*** አላህ መልካም ስራዎቻችንን ይቀበለን፡፡ ኣሚን፡፡ መልካም ዒድ፡፡***
***“ሼር” ማድረግ እንዳይረሱ፡፡***